>

‹አይደገምም››  ያሉንን በከፋ መልኩ ሲደጋግሙት...!?! (አሳዬ ደርቤ)

‹አይደገምም››  ያሉንን በከፋ መልኩ ሲደጋግሙት…!?!

አሳዬ ደርቤ


*….. ከመከላከያ ጋር ለመሞት የተዘጋጁ ፋኖዎችን ባፈኑበት መዳፍ ሰሜን እዝን ከወጉ አሸባሪዎች ጋር መተቃቀፍ ቢቻልም ይህ አይነቱ የኃይል አሰላለፍ ግን የኋላ ኋላ ውድቀትን እንጂ የዙፋን መርጋትን አያመጣም!!!

*….. ጥጋባችሁን የሚናገሩ አንደበቶችን ወደ እስር ቤት በመወርወርም መራባቸውን እና እጦታቸውን መናገር የጀመሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፎች ዝም መሰኘት አይቻልም!!!

➔ህውሓት የተባለው የቀድሞ ድርጅታችሁ ድክመቱን የሚነግሩትን የተቃውሞ ድምጾችን እያፈነ እንደ ዋልታ፣ ኢቲቪና፣ ፋና ያሉ የገደል ማሚቶዎችን ከፍቶ የእራሱን ድምጽ እያዳመጠ ‹‹ጠንካራ ነኝ›› ይል ነበር፡፡

➔ከዘጠና ሰባቱ ምርጫ ጋር አብረው የመጡ ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን ከሕትመት ውጭ ካደረገ በኋላ የሞደሊስቶችን እና የአርቲስቶችን የምግብ ምርጫ ለሕዝብ የሚያሳዉቁ መናኛ መጽሔቶችን ስፖንሰር ያደርግ ነበር፡፡

➔የሚተቹትን ጸሐፊዎች እና ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት አስገብቶ በብዕር ሥም እየጻፈ እራሱን በእራሱ ያንቆለጳጵሰው ነበረ፡፡

➔ከዚህ ባለፈም የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ እልፍ አእላፍ ወጣቶችን አፍሶ ወደ አዋሽ አርባ የማጎሪያ ካምፕ ካስገባ በኋላ ‹‹መለስ አልሞተም፣ ሕገ-መንግሥቱ አይደፈርም›› የሚል ሥልጠና ሲግታቸውና ‹‹አይደገምም›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ቲሸርት አልብሶ ሲያስመርቃቸው ነበረ፡፡

ያ ሁሉ የመብት አፈና ግን እንቢተኛ ወጣትን እና አፈንጋጭ ቡድኖችን ከማፍራት ባለፈ አልጠቀመውም፡፡

በመሆኑም ከእለታት ባንዱ ቀን ወጣቶችን የሚያፍንበትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግብሮ፣ እንደ ኢሳት ያሉ ሚዲያዎችን የሚያስተላልፉ ዲሾችን የሚነቅል ኮማንድ ፖስት አዋቅሮ እንዲሁም እነ ኢቲቪን የሚከታተል ትውልድ እፈጥራለሁ ብሎ ጣሪያ ላይ ሲንደፈደፍ ከከረመ በኋላ ወደ ምድር ሲወርድ አራት ኪሎ አካባቢ ያስቀመጠው ወንበር ጠፋው፡፡

ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ከቦሌ ወደ መቀሌ ተሸኝቶ በአየር መንገድ ፈንታ በጋሪ ሲሄድ እራሱን አገኘው፡፡

የሚገርመው ነገር ታዲያ ታሪክ እራሱን ይደግማል›› እንደሚባለው የብልጽግና መንግሥትም ህውሓት በወደቀበት የአፈና መንገድ ሕያው ሆኖ ሊኖርበት አስቦ እየዳከረ መሆኑ ነው፡፡ በህውሓት ጊዜ በባሕር ዳር ወጣቶች ላይ የተፈጸመው እልቂት በብልጽግና ዘመን ሲፈጸም ትክክል ሆኖ የሚገኝ ይመስል በረከት ስምዖንን ለእስራት የዳረገውን ጥፋት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንትና ባለሥልጣናት እየደገሙት ነው፡፡

ሆኖም ግን ከመከላከያ ጋር ለመሞት የተዘጋጁ ፋኖዎችን ባፈኑበት መዳፍ ሰሜን እዝን ከወጉ አሸባሪዎች ጋር መተቃቀፍ ቢቻልም ይህ አይነቱ የኃይል አሰላለፍ ግን የኋላ ኋላ ውድቀትን እንጂ የዙፋን መርጋትን አያመጣም፡፡

ጥጋባችሁን የሚናገሩ አንደበቶችን ወደ እስር ቤት በመወርወርም መራባቸውን እና እጦታቸውን መናገር የጀመሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፎች ዝም መሰኘት አይቻልም፡፡

ችግር ፈጣሪን ታቅፎ ‹‹ሕግ ማስከበር›› በሚል ሥም ‹‹ሕግ ይከበር›› የሚሉ ዜጎችን በማፈን ብሎም ‹‹ሕልውናችን ይጠበቅ›› የሚሉ ፋኖዎችን በማሳደድም ሕገ ወጦችን ማስፋፋት እንጂ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚቻል አይሆንም፡፡

ብልጽግና ሆይ እናም እልኻለሁ…

ወንጀለኛ ወይም ደግሞ ጽንፈኛ ብለህ ያፈንካቸው አማራዎች የሰነዘሩብህን ትችት እንደ ጥፋት ቆጥረህ ማንንም የማያሳምን ተራ የፈጠራ ክስ ስትደርት እራስህን ለትዝብት ከምትዳርግ እንዲህ አድርግ፡፡

አንድም ህውሓቶችን ወደ አዲስ አበባ አስመጥተህ ‹‹ከሳሾች›› አድርጋቸው፡፡ ወይንም ደግሞ ያፈንካቸውን ዜጎች በኢንተርፖል በኩል ለመቀሌው መንግሥት አሳልፈህ ስጣቸው፡፡

ያን ጊዜ ‹‹ለሕዝባችን እና ለአገራችን ቀጣይነት ስንል ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ለመሞት መዘገጃታችን ወንጀል አይደለም›› በማለት የሚሞግቱህ ፋኖዎች ‹‹ከመንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈን ስንወጋችሁ መክረማችን የሚካድ ስላልሆነ የትኛውንም ቅጣት ለመቀበል ዝግጁ ነን›› ብለው ጥፋታቸውን ያምናሉ፡፡

‹‹በመንግሥት ላይ የፈጸምነው ጥፋት የለም›› ያሉህ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞችም ከህውሓት እጅ በገቡ ቅጽበት ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ እንጦሮጦስ ድረስ›› ከሚለው የእናንተ ዛቻ ይልቅ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› የሚለውን ዘመቻ ተቀላቅለን በተለያዩ ሚዲያዎች ስንዘምትባችሁ ነበር›› በማለት ጥፋታቸውን ያምናሉ፡፡

ወይም ደግሞ ‹‹እያደር ከመጠንከር ይልቅ መልፈስፈስ የሚወድ መንግሥት አገር እንዳያፈርስ በማሰብ ሦስት ዓመት ሙሉ እሱን ተሸክመን እያንዘፋዘፍን እናንተን ስናሳድድ ነበር›› በሚል ንግግር ጥፋታቸውን ቀርቶ ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡

እናም እልኻለሁ…

‹‹የተለመደ ድጋፋቸውን ነፈጉኝ›› በሚል ቅሬታ ያፈንካቸው ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እንዲሁም ፋኖዎች ላይ ለችሎት የማይመጥን ክስ ከምትጽፍ ያሰርካቸውን ወገኖች ወደ መቀሌ ሸኛቸውና አምሥት ሺህ ምርኮኛ መልቀቁን ለነገረህ አካል ‹‹አምሥት ሺህ እሥረኛ ልኬልኻለሁ›› በለው፡፡

Filed in: Amharic