>

ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ከእስር ሳይለቀቁ ቀሩ...!!! (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ከእስር ሳይለቀቁ ቀሩ…!!!

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

*…. ፖሊስ ይግባኝ ተጠየቀባቸው!!!

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ዋስትና በተፈቀደላቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ላይ ይግባኝ ጠየቀ። የይግባኝ አቤቱታው የቀረበለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት “ዳኛ የለም” በመባሉ ጉዳዩ ለነገ ረቡዕ ሰኔ 1፤ 2014 ተቀጥሯል።

መርማሪ ፖሊስ ይግባኝ የጠየቀው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ነው። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለጋዜጠኞቹ ዋስትናውን የሰጠው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 30 ረፋድ በነበረው የችሎት ውሎ ነው።

ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ከሰጠ በኋላ የሶስቱም ጋዜጠኞች ቤተሰቦች የተጠየቁትን የዋስትና ገንዘብ መክፈላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የፍርድ ቤት መፈቻ ትዕዛዙን ይዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኙት የሰለሞን ሹምዬ ቤተሰቦች “ይግባኝ ጠይቀናል አንፈታውም” መባላቸውን እህቱ ትግስት ሹምዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩት ሶስቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዛሬ ከሰዓት በፖሊስ ታጅበው በፍርድ ቤት ቅጽር ግቢ ቢገኙም ችሎት ፊት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሰራተኞች “የይግባኝ ጉዳይ የሚመለከት ዳኛ የለም” በማለታቸው  የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ታስረው ወደሚገኙበት ፖሊስ ጣቢያ ተመልሰዋል።

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲፈታ የተወሰነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስካሁን ፖሊስ አልፈታውም

ታሪኩ ደሳለኝ

***

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ዛሬ ግንቦት 30/2014 በዋለው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት፣  በ10,000 ብር ዋስ ከእስር ቤት እንዲወጣ መወሰኑን ተከትሎ፣ በአሰራርና ደንቡ መሰረት ረፋድ ላይ በሞዴል 85 በደረሰኝ ቁጥር 987306 ለዋስትና የተጠየቀውን ገንዘብ ማስያዛችን ተረጋግጦ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር እንዲለቀቅ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በፅሁፍ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እስከዚህ ሰዓት ድረስ አልተፈፀመም።

Filed in: Amharic