የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ ስንታየሁ ቸኮል ዶሴ ላይ ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
ጌጥዬ ያለው

አቶ ስንታየሁ ቸኮል “ፖሊሶች እኛን ሲይዙና ሲፈትሹን በእጃችን ውዳሴ ማርያም እንጂ ቦምብ አላገኙም። የፓርቲያችንን ጠቅላላ ጉባኤ ለማደናቀፍ ነው ያሰሩኝ። አሁንም ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብተን ነው የምንጠይቀው” ብለዋል። ችሎቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ በወለጋ ለተጨፈጨፉ አማሮች የኅሊና ፀሎት እንዲደረግም ጠይቀዋል። ሆኖም ዳኞች ሀዘኑ የእነርሱም ጭምር መሆኑን ገልፀው ይህንን ለማድረግ የችሎቱ ስነ ስርዓት እንደማይፈቅድ አስረድተዋል።
“በሙያየ ለብዙ አመታት ሰርቻለሁ። ከቤንሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅዬ አገሬ ብየ ብመጣ ለግፉዓን ድምፅ በመሆኔ ታሰርኩ። ቤተሰቦቸ የህልውና አደጋ ላይ ናቸው። እኔም ታምሜያለሁ። ፍርድ ቤቱ ቢቻል በነፃ ካልሆነ ግን በዋስትና ያሰናብተኝ” በማለት ጋዜጠኛ ያለለት ተናግሯል።
ደምስ አያሌው በበኩሉ በማህበራዊ ሚዲያ ሁከት ቀስቃሽ መረጃ በማሰራጨት መወንጀሉን ጠቅሶ፤ እርሱ ግን ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ከመጠቀም አንፃር ጥሩ አስተዋፅኦ ያላቸውን ሰዎች የሚሸልም አደረጃጀት በመፍጠር ሲሰራ እንደቆየ አስረድቷል።