>

ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን፣ ከቅድስት፣ ድንግል ማርያም መወለዱ/ሰው የመኾኑ ሃያ አንዱ/21ዱ ምስጢራት፤ (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን፣ ከቅድስት፣ ድንግል ማርያም መወለዱ/ሰው የመኾኑ ሃያ አንዱ/21ምስጢራት፤

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


  • የእግዚአብሔርን ፍቅር ለሰው/ለዓለም ለመግለጽ፡-

(የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 3)

16፤ ‘‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። 17፤ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።’’

‘‘… ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ፣ እግዚአብሔር ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና፡፡ አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና፤ ልዑል ክንዱን ሰደደልን፡፡’’

(የሰኞ ውዳሴ ማርያም፣ በቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ) 

‘‘ፍቅር ስሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት/ፍቅር ኃያል ወልድን ከመንበሩ ሳበው፣ ከዙፋኑም አወረደው፣ እስከሞትም አደረሰው፤’’

(የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴ፣ አባ ሕርያቆስ ዘሀገረ ብህንሳ) 

  • ፍጹም የኾነ የራሱን ሰላምን ሊሰጠን፡-

(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 9)

6፤ ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። 7፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። 

ሉቃስ ወንጌል ምዕ. 1፣ 13-15)

‘‘… መላእክቱና እረኞቹ በአንድነት ሆነው እንዲህ እያሉ ዘመሩ፤ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ሥምረቱ ለሰብእ ሃሌ ሉያ! ክብር ለእግዚአብሔር በአርዓያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ!” 

‘‘ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም፡፡’’

(የዮሐንስ ወንጌል 14፣27)

ኤፌ. 2፣15 ‘‘… እርሱ ሰላማችን ነውና፤’’ 

‘‘ከዳዊት ዘር ሰው ኹኖ በሰው አካል የመጣ ወልድን እንሰብካለን፤ ከጌትነቱ ዙፉን ሳይለይ ሳለ በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ዐደረ፤ ሥጋ ኾነ ተወለደም፤ ትጉኀን መላእክት ልደቱን ያምናሉ፤ ሱራፌልም በዙሪያው ይቆማሉ፤ ይቤዠን ሰላምን ይሰጠን ዘንድ መጣ (ሰው ኾነ)፤ ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ቊርባንን ለእርሱ ያስገባሉ)’’ (ድጓ ዘጌና-ቅዱስ ያሬድ) 

  • መድኃኒት ሊኾነን፡-

‘‘ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ [ተወለደ] የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤”

(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፣15)

‘‘ዳግመኛ ወገኖቹን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ኢየሱስ ይባላል፤ በችሎታው /በኃይሉ/ ያድነን ዘንድ ኃጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ፤’’

(የኀሙስ ውዳሴ ማርያም፣ አቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ) 

“ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና፡፡ ጌታ በነቢዩ (በኢሳያስ) እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈፀም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤” (የማቴዎስ ወንጌል 1፣ 21-23)

  • ብርሃን እና ሕይወት ሊሆነን፡-

‘‘በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች፤’’ (ዮሐ. ምዕ. 1፣4)

‘‘በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤’’

(የዮሐንስ ወንጌል 12፣46)

‘‘በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ [ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው የኾንክ] ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፣ አዳምን ከስሕትት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኻታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን፤’’

(የእለተ ሰኞ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)

‘‘በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ [ተወልጃለኹ] 

(የዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 12፣46)

‘‘… ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው፤’’

(ስምዖን አረጋዊ/ሉቃ. 2፣32))

‘‘የእግዚአብሔር ሀገር/ከተማ [ማርያም ሆይ] ነቢያት ድንቅ ድንቅ ነገርን የተናገሩልሽ፤ ደስ የተሰኙ የጻድቃን ማደሪያ ሆነሻልና የምድር ነገሥታት ሁሉ በብርሃንሽ [በልጅሽ በጌታችን፣ በአምላከችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ] ይሔዳሉ፣ ማርያም ሆይ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑሻል ከአንቺ ለተወለደውም ይሰግዱለታል፣ ያገኑታልም፡፡ ቅድስት ሆይ ለምኝልን፤’’

የረቡዕ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በእመቤታችን የምስጋና ድርሰቱ/በአርጋኖን፤

“ሥርዐተ ሰማይ ከማሁ ተሠርዐ በዲበ ምድር፤ ቤተልሔም ተመሰለት ከመ ሰማይ ህየንተ ፀሓይ ዘየዐርብ ሠረቀ በውስቴታ ፀሓየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኢየዐርብ ወዘዘልፈ ያበርህ ዲበ ቅዱሳን …” (የሰማይ ሥርዐት በምድር ላይ ተሠራ፤ ቤተልሔምም እንደ ሰማይ ተመሰለች፤ በሚጠልቅ ፀሓይም ፈንታ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ኅልፈት ጥልቀት የሌለበት አማናዊ ፀሓይ ኢየሱስ ክርስቶስ በውስጧ ወጣ (ሚልክ ፬፥፪)፤

ከብርሃኑ ጒድለት መምላትን የማያፈራርቅ በጨረቃ ፈንታ የድንግልናዋ ምስጋና ዘወትር የማይጐድል በኹሉ የመላ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባለች የተመረጠች ድንግል ማርያም ተገለጠች (መሓ ፮፥፲)፤ በክዋክብት ፈንታም የብርሃን መላእክት ታዩ፤ (ሉቃ ፪፥፲፫)፤ በዚኽ ማኅበር እኖር ዘንድ ከጥበብ ሰዎች ጋራ እጅ እነሣ ዘንድ (ማቴ ፪፥፲፩)፤ ከእረኖችም ጋራ አገለግል ዘንድ፡፡ (ሉቃ ፪፥፲፮-፲፰)፤

  • ‘‘አማኑኤል’’ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን፡-

‘‘እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም ‘አማኑኤል’ ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው፤’’

(የማቴዎስ ወንጌል 1፣23)

አማኑኤል ‘አማነ’ እና ‘ኤል’ ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመመሠረተ ስም ነው፡፡ ትርጓሜውም የአምላክ ሰላም፣ የእግዚአብሔር ዕርቅ፣ የጌታ አንድነት ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃም ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክት ዘር አይደለም፤’’

(ወደ ዕብራውያን ምዕ. 2፣15-16)

‘‘አስተርአየ ገሃደ፣ በለቢሰ ሥጋ ኮነነ ዘመደ/እግዚአብሔር በግልፅ ታየ የእኛን ሥጋን በመልበሱም ዘመድ ሆነን፤’’

የሀገራችን ባለቅኔም በዘለሰኛ ዜማው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን፣ ከቅድስት፣ ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆኑ የሥጋ ዘመድ እንደኾነን ሲያመሰጥሩ እንዲህ ተቀኝተዋል፤

አብን ተወውና ንገረው ለወልድ፣

ጥሎ አይጥልምና የሥጋ ዘመድ፡፡

  • ትሕትናውን ሊያሳየንና ዝቅ ብሎ ለማገልገል

‘‘… የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገልግሉት አልመጣም፡፡” (ማቴ. 20፣28)

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በማሕፀነ ማርያም ከተከናወነው አንሥቶ በልደት እስከኾነው ታላቅና አስደናቂ ምስጢርን በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ሲገልጸው “ወሶበ ይቤላ መልአክ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ተቀደሰት በርደተ መንፈስ ቅዱስ ለከዊነ እመ አምላክ …”

(መልአክ መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል ባላት ጊዜ የአምላክ እናት ለመኾን በመንፈስ ቅዱስ ተለየች ይኽም ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ነው የልዑል ልጅ ይባላል ሲላት ያን ጊዜ ከርሷ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ አስተዋለች (ሉቃ ፩፥፴፭)፤ ኅሊናዋን ወልድ ከአባቱ ጋር ወዳለበት ወደ ጽርሐ አርያም አሳረገች፤ ርሱም ዝቅ ብሎ ከሰማያት ወረደ ራሱንም በማሕፀኗ ውስጥ አሳደረ (ዮሐ ፩፥፲፬)፤

“እናንተ ደካሞች ወደ እኔ ኑ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ …. ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ. 11፣28-29)፡፡

“ዮም እግዚአ ሰማያት ወምድር በጎል ሰከበ፤ እሳት በአጽርቅት ተጠብለለ፤ ሐሊበ ጠበወ ዮም ዘይጸውርዎ ሱራፌል በክነፊሆሙ በከርሥ ተጸውረ፤ እግዚእ በሠረገላ ተሐቅፎ ድንግል ዮም፤ ዘያሌዕሎ ለማዕበለ ባሕር ሐሊበ ጠበወ፤ ኢንክል ከቢቶቶ በአርምሞ ናአኲቶ ዘእንበለ ሐቲት ንስግድ ሎቱ ለክርስቶስ”

(ዛሬ የሰማይና የምድር ጌታ በግርግም ተኛ፤ እሳት በጨርቅ ተጠቀለለ ዛሬ ወተትን ጠባ፤ ሱራፌል በክንፎቻቸው የሚሸከሙት በማኅፀን ተቻለ፤ ኪሩቤል በሚሸከሙት ሠረገላ ጌታ የኾነ ርሱን ድንግል ዛሬ ታቅፈዋለች፤ የባሕርን ማዕበል ከፍ የሚያደርገው ወተትን ጠባ፤ ይኽነን በዝምታ ልንሸሽገው አንችልም፤ ያለምርምር እናመሰግነዋለን (እናመስግነው)፤ ለርሱ ለክርስቶስ እንሰግዳለን)፤ (ድጓ ዘልደት/ቅዱስ ያሬድ)

“ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ በጎል ሰከበ፤ ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ በአጽርቅት ተጠብለለ፤ በከርሥ ተጸውረ፤ እሳተ መለኮት ውስተ ማሕፀነ ድንግል ኀደረ፤ ሐሊበ ጠበወ፤ ሰብአ ሰገል ሰገዱ አምኃሆሙ ወርቀ ወሰዱ ረኪቦሙ ሕፃነ ዘተወልደ ለነ”

(ሰማይና ምድር የማይችለው በበረት ተኛ፤ ሰማይና ምድር የማይችለው በጨርቅ ተጠቀለለ፤ በኾድ ተቻለ፤ እሳተ መለኮት በድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ ዐደረ፤ ወተትን ጠባ፤ የጥበብ ሰዎች የተወለደልንን ሕፃን አግኝተው እጅ መንሻቸው ወርቅን ወሰዱለት) እንዲል (ድጓ ዘክብረ ቅዱሳን)፤

‘‘… የማይደፈር ግሩም ነው በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፤ የማይገኝ ልዑል ነው በእኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብርን ነሣ/የባርያን መልክ ይዞ ታየ ተገለጠ/፡፡ የማይዳሰስ እሳት ነው እኛ ግን አየነው ዳሰስነውም ከእርሱ ጋራ በላን ጠጣን፡፡’’

(የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴ፣ አባ ሕርያቆስ ዘሀገረ ብህነሳ)

  • የዘላለምን ሕይወት ሊሰጠን/ሊያድለን፡-

የዮሐንስ ወንጌል 17፥3 ‘‘እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።’’ 

‘‘ሌባው [ጥንተ ጠላት ሰይጣን] ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው፣ እንዲበዛላቸውም መጣሁ [ወርድኩ፣ ተወልደኹ]፤’’

(የዮሐንስ ወንጌል 10፣10)

‘‘… ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፣ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ [ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ኾኖ] ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው፤’’  

‘‘የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥20)፡፡

ከሰማይ የወረደ [ከድንግል ቅድስት ማርያም የተወለድኩት] ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፣ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔ ስለ ለዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡’’ (ዮሐ. 6፣51)፡፡

 ‘‘… ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፣ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ [ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ኾኖ] ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው፤’’

ለክርስትና እምነትት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችኹ፤ አደረሰን!!  

Filed in: Amharic