>
7:16 pm - Tuesday January 31, 2023

የማለዳ ወግ ... ህግ አስከባሪው ማነው ? የህግ የበላይነትስ የት ነው ያለው ? [ነብዩ ሲራክ]

* የሳውዲዋ ግፉዕና የጋዜጠኛ ተመስገን ወንድም ድብደባ አንድምታ !

Nebiyu Sirak (2006 -2007 )በዛሬ ማለዳ ወጌ ሶስት አራት ወጎች ነበሩኝ ፣ በማለዳው ተነስቸ ፣ አንዱን አንስቸ አንዱን መጣል ያዝኩ … በሳውዲና በከባቢው ሃገራት የከረመብን የሚለባለበው የበርሃው ሞቃታማ አየር አሁን በረድ ብሏል ፣ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎችማ ብርዱ አይጣል ነው! ጅዳ ከቀይ ባይር ዳርቻ በደቂቃዎች ልዩነት ርቀት የተከተመች ውብ የወደብ ከተማ ነች ፣ የሰሞኑ እኩለ ቀንና ማምሻ ላይ ያለው የጅዳ ነፋሻ አየር ደግሞ ነፍስን በሃሴት ይሞላል ፣ ቅዳሜ ለእሁድ ምሽቱ ላይ ከቤተሰብ ጋር ሰብሰብ ብየ በቅንጦት የተነሳሁትን የፎቶ ማስታዎሻ ከጥምቀቱ የከተራ በአል በዓል ጋር አዋህጀ ለማቅረብና ፎቶውንም ለመለጣጠፍ ስጀምር በደረሰኝ የስልክ ጥሪ ተደናቀፍኩ …! አንድ ወዳጀ ስልክ ደውሎ ” ያንተ ፖስፖርት ጉዳይ አሳስቦኝ ፣ የምሰማውን አላምን በወየ ቢገርመኝ ፣ ብበሽቅ ደወልኩልህ ” የሚል መልዕክት ነው ፣ የአሳቢ ተቆርቋሪ ወዳጀ መልዕክት ቢገባኝም የእኔ የግል መብት ገፈፋ እውን ከሆነ የራሴ ብቻ በመሆኑ ላነሳውም አልፈለግኩም ፣ አናም ከምሰማው ከማየው የማያስጨንቀኝ ጉዳይ በላይ አልሆነምና ለተቆርቋሪነቱ አመስግኘው ስልኩንም ፋይሉንም ዘጋሁት … ከዚያ በኃላ የቀጠለው ሌላ መረጃ ግን የጀመርኩትን የቅንጦት መረጃ ቅበላ ከእርምጃ ገታው ! ….

በመኪና ግጭት የተጎዳችው እህት አበሳ!

እዚህ ጅዳ የመኪና ግጭት አደጋ ደርሶባት ሆስፒታል በአልጋ ላይ ስላለችው እህት ተደረሰኝ መረጃ ደስ አይልም ” አንተ ነቢዩ ባለፈው ሳምንት ያየሃት እና አጭር መረጃ የሰጠህን እህት እኮ ወደ ሌላ ክፍል አዛወሯት? አሰሪዎቿም መንግስታችሁ ጉዳዩን ይከታተል ብለው ትተዋታል ፣ ምን ይሻላል ? እባክህ ደግኘህ ለጅዳ ኢንባሲ ሰዎች ንገርልን? ወዳንተ የምንደውለው አንቆን እኮነው! እርዳን ?” ይላል ፣ የሚያም ደረቅ እውነት … የእህታችን ግጭት አስመልክቶ ባቀረብኳት አጠር ያለች መረጃ የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች በተለይም ተጠባባቂ ሃላፊው ቆንስል ሸሪፍና ቆንስል ሙንትሃ ጉዳዩ ያደረስኳቸው ሲሆን ያን ሰሞን ቆንስል ሙንትሃ ተጎጅዋን እንደ ጎበኟት ፣ የፎቶ መረጃ ሳይቀር እንደወሰዱ አውቃለሁ ፣ ከጉብኝታቸው ወዲህ ግን ያደረጉት ነገር ስለመኖሩ የማውቀው ነገር ቢኖር ሃላፊዋ ደግመው መጠየቁ ቀርቶ የዜጋቸውን ጉዳይ እስካሁን በውል አለመያዛቸውንና ፣ ጉዳዩ ባለቤት አልባ መሆኑን ነው ! ለዚህ ጉልህ መረጃ አለኝ … ተጎጅዋ እህት ባለፉት ሳምንታት በቂ ህክምና ይሰጣት ከነበረችበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውራለች ፣ ህመሙ ጸንቶባታል … ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ሚመለከታቸው ደዋውየ በቂ መረጃ እስካገኝ ግን ይህን ለዛሬ ላልፈው ተገድጃለሁ ! የህግ አስከባሪ የት ነው ያለው ? እያልኩ ሙሉ መረጃውን በፎቶ አስደግፊ አስካሳያቸሁ ወደ ሌላው ህመም ልሻገር … ! በህግ የበላይነት ዙሪያ የታየኝ ሌለው ህመም …

ጋዜጠኞቹ …

ወጌ እንዳይደርቅ ላዋዛው መሰል … ? የኢራቁ የቀድሞው መሪ ፕሬዚደንት ሳዳም ሁሴን እና የባህረ ሰላጤው ጦርነት ሲወሳ የዘመኑ ትንታግ ጋዜጠኞች ትውስ ይሉኛል ፣ ጋዜጠኛ አለምንህ ዋሴ ፣ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሃመድ እና ጋዜጠኛ ንግስት ( የአባቷ ስም ሰይፉ መሰለኝ ) … ዛሬ የጋዜጠኛ ንግስት የት አንዳለች ባላውቅም ጋዜጠኛ ነጋሽ መሃመድና አለምነህ ያሉበትን አውቃለሁ ።

ጋዜጠኛ ነጋሽ መሃመድ ያለው ሀገረ ጀርመን ቦን ሲሆን እንደኔው በትርፍ ሰዓት ሳይሆን በቋሚነት ለአንጋፋው የጀርመን ራዲዮ የአማርኛ ክፍል እየሰራ ነው ። ጋዜጠኛ ነጋሽ ዘወትር ሰኞ በጀርመን ራዲዮ የማህደረ ዜና ሳምንታዊ ቅንብር በማቅረብ በተወዳጅ ተስጎድጓጅ ድምጹ አልፎ አልፎ በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ የፖለቲካ ዙሪያ ወቅታዊ ትንታኔን እየቀረበልን ይገኛል ።

ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ እውቅናን ከዛቀ ካተረፈበት የኢትዮጵያ ራዲዮ ለአመታት በመራቅ ወደ ሀገረ እስራኤል ከትሞ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ሀገር ቤት ነው። ጋዜጠኛ አለምነህን በአለም አቀፍ መድረኮች ብዙ ብቅ ባይልም በሀገር ውስጥ በሚገኙ ጣቢያዎች ሁለገብ መረጃዎችን በሚያናልልና ቀልብን በሚስብ ድምጹ መረጃዎች እንደሚያቀርብ ለመረዳት ችያለሁ … የጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴን ተጨማሪ መረጃዎች ማግኘት የቻልኩት ደግሞ ከቅርብ ወረት ወዲህ በፊስ ቡክ Facebook ገጹን መከታተል ከጀመርኩ ወዲህ ነው።

የጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ አወዜ ዜናና ድብደባው !

ጋዜጠኛ አለምነህ “አዋዜ ” እያለ የሚያቀርባቸው መረጃዎች ደግሞ ቀልቤን ከሚስቡት የመረጃ ምንጮች እየሆነ መጥቷል …በመረጃው ቁልጭ ያለጭብጥና እውነት የወለደው ድፍረት ከርቱዕ አንደበት ጋር ተቀባጅተው በአዋዜ አስተውያለሁ ! … ጫዎታን ጫወታን አንስቶት የባህረ ሰላጤውን ጦርነትና በተዛማጅ የሚወሱትን ጋዜጠኞች ጠቃቀስኩ እንጅ የማለዳ ቅኝቴ መድረሻ ተጎጅዋ እህት በሳውዲና ቀጣዩ በህግ ጥበቃ የሚገኘው ሌላ ብርቱና ትንታግ ጋዜጠኛ ቤተሰብ አባል ላይ የተፈጸመ ግፍ ነው …

እርግጥ ነው ሰብአዊ ሀሳቡን በነጻነት በገለጸ ወህኒ የተወረወረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም ታሳሪ ወንድሙን ለመጠየቅ ቂሊንጦ ወህኒ ባቀናበት አጋጣሚ በመንግስት ታጣቂዎች ተደብድቧል … ጋዜጠኛ አለምነህ አፍታቶና ቀሽሮ ያብራራዋል ! ከዚያ በፊት ግን እኔ የሚሰማኝን ላስቀምጠው …

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሰብአዊ፣ ተፈጥሯዊና ህገ መንግስታዊ ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቱን የተጠቀመና በሰላማዊ መንገድ ባቀረበው ሀሳብ ክስ ተነስርቶበት ወህኒ የወረደ ብቸኛ ታዳጊ ጋዜጠኛ ነው ። ጋዜጠኛ ተመስገን በሚያቀርባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች የማህበረሰቡን እሴቶች ፣ ባህል ወጉንና ግለሰባዊ የመብት ዳራን ሳይጋፋ ” ህግ ይከበር ፣ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ይከበር !” ብሎ መንግስትንና ፒለቲከኞችን በሰላማዊ መንገድ የሞገተና ብትቱና ትንታግ ለውጥ ናፋቂ ወጣት ነው ። ለውጥ ናፋቂው ወዳጀ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አልተፈለገምና ቀለብ እየተሰፈረለት በአጥር ተከልሎ አመታትን ከሚገፋበት የግፉአን መናህሪያ ተወርውሯል ፣ ተመስገን ስለሆነው ሁሉ የሚጨነቅ ሰው አለመሆኑን በወህኒ ላይ ሆኖ ያቀረባቸው የታሳሪው ህይዎትና የህግ የበላይነትን መጣስ ያሳየባቸው መጣጥፎቹ የወጣቱን ብርታት ያሳያችሁ እንደሁ እንጃ … እኔ ግን የወጣቱን ጋዜጠኛ የተመስገንን ብርታት ደጋግሜ አይቸባቸዋለሁ ።

ጋዜጠኛ ተመስገን እነሱና እኛ “ነጻ ” ከምንለው አየር ተወግዷል ፣ በአደባባይ አይዘናከትም ፣ እንዳሻው አይነሳም አይንቀሳቀስም እንጅ ተመስገን ያመነበትን እንዳሻው አይጽፍ አይናገርም ማለት ዘበት ነው … ቀለምና ብራናው ሊያርቁበት ቢችሉም በውስጡ የባህር መዝገብ ይመዘግበዋል ፣ ያለለት ቀን ደግሞ ሞነጫጭሮ መረጃውን ይካፍለናል ! እሳትን መጨበጥ ፣ ጽኑ ፍላጎትና እምነት ያላትን ነፍስ በማሰቀየት ፣ እስከ ቤተሰብ በደረሰ ድብደባ ፣ በማግለል እና ህግን እየጣሱና መብትን እየደፈጠጡ በሚፈጸም በዚህ ስልጡን የመረጃ ዘመን ከበቀል የማይተናነስ ህገ ወጥ ድትጊት መፈጸም አራዊነት ነው ፣ ይህ ህግን የማያከብሩ እኩያብ ድትጊት ለሚያምኑበት የቆሙትን ወገኖች ድምጽ ማፈን የሚያስችል ብልሃትም አይሆንም ! በዚህና በዚያ የታሳሪውን የጋዜጠኛ ተመስገንን ሞራል ማድቀቅ አለያም የቤተሰብ አፍቃሪና አድናቂዎቹን ቀልብ ከመግፈፍ እስከ ማስፈራሪያነት መጠቀሚያነትም የማይበጅ ከብቱ ሙከራ ይመስለኛል ። ህግ በመጣስ ህግን ማስከበር አይቻልምና !

እኛ ” ነጻ” በምብለው አለም ነጻነታችን ሸብበን ፈራ ተባ እያልን ኑሮን ስንኖረው ፣ ተመስገን ” ነጻ ” በማይባለው ወህኒ በደስታ የመኖሩ ሚስጥር ለሚወዳት ሀገሩ ራሱን አሳልፎ በመስጠቱ የሚሰጠው እርካታ እንጅ የከተመው ተማርጦ በሚበላ በሚጠጣበት ጣራ ስር አለመሆኑ እሙን ነው ። ጋዜጠኛ ተመስገን ላመነበት ግንባሩን ሰጥቶ ፣ በነጻነት እየኖረ ያለ ግፉዕ እንጅ ወንጀለኛ ታሳሪ አይደለም ! ተመስገን ላሻው ጉዳይ ከወህኒ ሲወጣ ሲገባ እግሮቹና እጆቹ ሰንሰለት አይለያቸውም ፣ ዳሩ ግና ልቡና መንፈሱ የማያስሩት ጀግና ልብ ያለው ጽኑ ጋዜጠኛ ነው …

ጋዜጠኛ ተመስገን ፍርደኛ የህግ ታሳሪ ነው ፣ የህግ ታሳሪ ደግሞ ከሰብአዊ አያያዝ ጀምሮ በቤተሰብ የመጎብኘት በህገ መንግስት የተደነገገ መብት አለው ። ድንግግ መብቱን የሚያስከብሩ ህግ አስከባሪዎችም አሉ ። ዳሩ ግና የተደነገገው መብትም ሆነ ህግ አስከባሪዎች በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ግፍ ሲፈጸም መከታ ሲሆኑ አልታየም ። በጠራራ ጸሃይ የፍርደኛ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መብት ከቀን ቀን እየተሸራረፈ ማየቱ ቢያምም ካለበት ወህኒ ስንቅ ይዞ ሊጠይቅ የሄደ ወንድሙን መደብደብ ግን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ወንጀል ነው! ታሪኩ በፊስ ቡክ ባሰራጨው ዘልቆ የሚያም መልዕክቱ እንዲህ አለ ” ወንድምየ አንተን ያለማየት ሸክሙን እንዴት ልቻለው? ” …
አዎ ያማል ለእኔ ተመስገን ተወንጅሎ ከታሰረበት ወንጀል ይልቅ ጠያቂ ቤተሰብን መደብደብ የከፋ ወንጀል ነው ባይ ነኝ ! …የህግ የበላይነት የት ነው ?

በታሪኩ ደሳለኝ ላይ ስለደረሰው ድብደባ የጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴን ቀጣዩ መረጃ ነው …

“አለ” የሚለው ህግ ይከበር !

ነቢዩ ሲራክ
ጥር 10 ቀን 2007 ዓም
( ሁሉንም ስለ እውነት በተሰበረ ልብ ጻፍኩት)

Filed in: Amharic