>

አትሰቀል ይቅር! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

አትሰቀል ይቅር!

አሥራደው ከፈረንሳይ

በገባለት ቃሉ – አባትህ ለ’ኛ አባት፤

አንተ ለኛ ሞተህ – ልንድን ከሃጢያት፤

እኛን አድናለሁ – ብለህ ከመከራ፤

መስቀል ተሸክመህ አትውጣ ተራራ::

በጨካኞች ጅራፍ – አይገረፍ ጀርባህ፤ 

ምስማር አይቸንከር – በጅና በግሮችህ፤

በጦር አይወጋ – አይበሳ ጎንህ፤

አትጠጣ ፍጹም – የሃሞት መራራ፤

አድናለሁ ብለህ – እኛን ከመከራ፤

መከራህ አይብዛ መከራችን ላይቀር፤

ተንገላተህ አትሙት አትሰቀል! ይቅር::

ተከባብሮ መኖር – አብሮ መብላት ቀርቶ፤

ጥላቻ፤ ጭካኔ – መከራ በርክቶ፤

ወንድማማችነት – ፍቅር መተባበር፤

አንድነት፤ ነፃነት – ፍጹም ጠፍተው ካገር፤

መቻቻል፤ ደግነት – ከሃገር ተሰደው፤

ግፍ በደል በርክቶ – ሞልቶ ፈሶ ጽዋው፤

ሰው ሆነን ሰው ካልሆን – ተፈጥረን ባምሳልህ፤  

ከሰማየ ሰማይ – ወርደህ ከዙፋንህ ፤

አፈር ለባሽ ገላ : ከንቱ ሥጋ ለብሰህ፤  

አትሰቀል በቃ! እኛን ላድን ብለህ ::

ይልቅስ ከሰሙህ እንዲህ ምከራቸው………!

እንደዚህ በላቸው – ስልጣን ላዋስካቸው……!

ስልጣን ተገን አርጎ – ቀምቶ የበላ፤ 

ለሥጋው አድልቶ – ወገኑን ያጉላላ፤

ዘረኝነት አርሶ – ቂም በቀል የዘራ፤  

የሚያበዛ ት’ቢት – ሰው የሚያስፈራራ፤

ውሸት ያመረተ – በደል የከመረ፤ 

በግፍ የገደለ – ወህኒ ቤት ያጎረ፤

ጥላቻን አንግሶ – ፍቅርን ያኮሰሰ፤

ወንድሙን የገፋ – በደል ያነገሰ፤

ቁጣዬን አብዝቶ: መከራውን ያጭዳል፤ 

ሕዝቤን አታጉላሉ: ከንግዲህ ይበቃል !

ብለህ ንገራቸው………!

ልቦና ቢገዙ…. ድንገት ቢመለሱ.… ወደ ሕሊናቸው ::

ግን፤

የሕዝብህን ጩኸት – እየሰማ ጆሮህ፤

ስቃይ መከራውን – እያየኸው ባ’ይንህ

ሲካድ ሰብዕናው – ፈጥረኸው ባምሳልህ፤

ዝምታህ ከበዛ – ከዘገየ ፍርድህ፤

ኤሎሄ ! ኤሎሄ ! ላማ ሰበቅታኒ: ላ’ባትህ ልናገር፤

ቁም ስቅልህ ይብቃ! እኛ አልዳንምና: አትሰቀል ይቅር!!

አንድ ቀን 

በፍትህ እጦት በወህኒ ቤት፤ በኑሮ ውድነት፤ በሥራ አጥነት፤ በስደት ለሚጉላው፤ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ማስታወሻ ትሁንልኝ::

Filed in: Amharic