>

ኢትዮጵያን ማዳን የፈለገ ሁሉ፤ አማራን ለማዳን መነሳት አለበት (አንዱ ዓለም ተፈራ)

ኢትዮጵያን ማዳን የፈለገ ሁሉ፤ አማራን ለማዳን መነሳት አለበት

አንዱ ዓለም ተፈራ 

አማራ በኢትዮጵያ ብቻውን ኖሮ አያውቅም። አማራ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ጎሳዎች ሁሉ፤ ኢትዮጵያን ባለ በሌለ እውቀቱና ጉልበቱ ታድጓታል። አማራ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ፤ በኢትዮጵያዊነትና በአማራነት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳይኖር፤ በፖለቲካው ሂደት፤ አማራነቱን ለኢትዮጵያዊነቱ አስረክቦ፤ ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ ተቀብሏል። ሌሎችም ጎሳዎች፤ እስከ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ወደ ሥልጣን መምጣት ድረስ፤ በፖለቲካው ሂደት የየጎሳቸውን ማንነት ለኢትዮጵያዊነት አስረክበው ኢትዮጵያዊነትን ተቀብለው ይኖሩ ነበር። አማራ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጎሳዎች ጋር በመሆን፤ ኢትዮጵያን ከውጪ ወራሪም ሆነ ከውጪ ከሃዲዎች ከፍተኛውን መስዋዕትነት ከፍሎ ጠብቋል። አማራ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካል ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ሀቁ፤ አሁን ያለው መንግሥት፤ አማራን ለማጥፋት በሰፊው ዘምቷል። ይህን ዝም ብሎ ማየት አይቻልም። በዚህ ጽሑፍ፤ የደቡብ አፍሪካው የፕሪቶሪያ ስምምነትና ክንውኑ፣ ለምን በመጀመሪያ የአማራውን ልዩ ኃይል ማፍረስ እንደተፈለገ፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምንነትና ተግባሩ፣ በመጨረሻም ለዚህ ሁሉ ትክክለኛ መፍትሔው ምንድን ነው? የሚለውን አስፍሬያለሁ።

እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊ ነን። ኢትዮጵያ መስተዳደር ያለባት፤ በኢትዮጵያዊያን ነው። ኢትዮጵያዊነቱን አምኖና ተቀብሎ በኢትዮጵያዊነቱ የማያስተዳድር አካል፤ በሥልጣኑ ላይ መቀመጥ የለበትም። መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን፤ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር አባልነቱ ገዛ። እናም አይቀሬዎቹ ሙስናና አድልዖ፣ ያልተመጣጠነ የየክልሉ ልማትና የአስተዳደር ሂደት ባገሪቱ ሰፈነ። ያንን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃኝ ብሎ አስወገደው። ነገር ግን፤ የሕዝቡ ልጆች ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ኮትኩቶ ያሳደጋቸውና በፖለቲካ ስርዓቱ ያጠመቃቸው ግለሰቦች፤ ኢሕአዴግን እንዳለ ይዘው፤ ስሙን ብቻ ለውጠው፤ በቦታው ተተኩ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ ብሎ ሲነሳ፤ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ቦታ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተተክቶ፤ ያንኑ የተወገደ የፖለቲካ ስርዓት፤ ከነሰንደቅ ዓላማው፣ ከነሕገ-መንግሥቱ፣ ከነ “ክልል” አስተዳደር መምሪያው፤ ከነምልምል ካድሬዎቹ ቀጠለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ የጉልቻ መቀያየር መሆኑን ተረድቶ፤ አልገዛም አለ። የአማራው አልጠፋም ብሎ ተከላካይነት፤ የዚሁ አልገዛም ባይነት አካል ነው። ዝርዝሩን ቀጥዬ አቀርባለሁ። በመጀመሪያ በቅርብ የተጠቃለለውን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የወረራ ጦርነትን እንመለከት።

“እኔ በምፈልገው መንገድ አልሄደም!” ብሎ ጠቅልሎ መቀለ የገባው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ጎሰኛ ቡድን፤ ተመልሼ የፈልግሁትን አደርጋለሁ ብሎ፤ በ “አማራ ክልል” እና በ “አፋር ክልል” የወረራ ዘመቻ አካሄደ። ለዚህ ተባባሪ የሆነው የአሜሪካን መንግሥት፤ ከጎኑ ተሰለፈ። አውሮፓዊያንም ከጎኑ ተሰለፉ። ከቪየትናም ያልተማረችው አሜሪካ፤ ሕዝብን አቸነፋለሁ በማለት፤ ያለ የሌለ ኃይሏን ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ጎን መደበች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፤ በመከላከያ ሠራዊቱ፤ በልዩ ኃይሎቹና በቆራጥ ፋኖዎቹ በታተናቸው። ከፍተኛ ጉዳት በ”አማራ ክልል” እና በ”አፋር ክልል” ደረሰ። ስፍር ቁጥር የሌለው የሰው ሕይወት ጠፋ። በቀላሉ የማይገመትና ሊተካ የሚያዳግት ንብረት ወደመ። በአማራውና በአፋሩ ኅብረተሰብ ውስጥ ከፍተኛ የስነ ልቡና ጥቃት ተፈጸመ። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መደምሰሻው ጫፍ ላይ ሲደርስ፤ ይሄ ነው የሚባል ክን በሌለው መንገድ፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት፤ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርና በ”መንግሥት” መካከል ተደረገ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እስካሁኗ ሰዓት፤ ስምምነቱ ለምን እንደተደረገ ብቻ ሳይሆን፤ በስምምነቱ ውስጥ ምን እንደተካተተ አያውቅም። ለምን? በኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ የተደረገ ስምምነት ምን ይዟል? ግምት አግቡ!

የፕሪቶሪያው ስምምነት የተደረገው፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ቡድን ያሰማራው ሠራዊት ሊደመሰስ ትንሽ ሲቀረው ነው። በዚህ ወቅት፤ የአቅም ማነስ ወይንም የሕዝቡ ፍልጎት ጠፍቶ አይደለም፤ ወደ ስምምነቱ የተኬደው። አሜሪካ ጣልቃ ገብታ፤ አገልጋ የሆናትንና ኢትዮጵያን ያዳከመላትን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሠራዊት እንዳይደመሰስ ስለፈለገች፤ በትዕዛዝ አስቁማው ነው። “ከኔ ብር ማግኘት ከፈለግህ፤ ጦርነቱን አሁኑኑ አቁም!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ነበር። ጦርነቱ ሲቆም፤ ያለው መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት በዝርዝር ተቀምጧል። ያ ለሕዝብ አልተገለጠም። አሁን የምናየው በአማራው ላይ የሚካሄደው ዘመቻ፤ የዚያ ስምምነት ውጤት ነው። በተለያዩ ድረገጾች እንደተገለጠው፤ በስምምነቱ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር ቡድን ምን እንደሚያገኝ ሰፍሯል። የሚገርመው፤ ለሕዝብ በተነገረው መሰረት፤ የታጠቀው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ትጥቁን መፍታት ነበረበት። የፌዴራል ወታደሮች ትግራይን እንደሚቆጣጠሩና መሳሪያዎችን እንዲረከቡ ነበር የተነገረው። ያ አልሆነም። ለምን? ከዚያ አልፎ ተርፎ፤ በሱዳን ያሉትን የዚሁ የፀረ-ኢትዮጵያ ቡድን ታጣቂዎች፤ የበለጠ በማዘጋጀት፤ ወልቃይትን ለመውረር እየጠበቁ ነው። 

በሌላ በኩል፤ የኦሮሞ ልዩ ኃይል፤ ከፌዴራሉ ሠራዊት አመራሮችን ወስዶ፤ በቁጥርና በጥራት የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ተጠናክሯል። ለምን? አሉ የሚባሉት የሌሎች “ክልሎች” ልዩ ኃይሎች፤ በቀላሉ በኦሮሞው ልዩ ኃይል ሊጠቁ የሚችሉ ናቸው። እንግዲህ በኢትዮጵያ የጉልበት አስላለፍ፤ የኦሮሞው ልዩ ኃይል የበላይነት ሲይዝ፤ የትግራይ ሕዝባዊ ነጻ አውጪ ግንባር ታጣቂ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። በርግጥ በፕሪቶሪያው ስምምነት ይሄ ዋናውን ማዕከል ይዞ ነበር። በአደባባይ ወጥቶ ያልሰማነው፤ በስምምነቱ መሓከል፤ አማራውን ማዳከምና ማጥፋት! የሚለው ጉዳይ ነው። በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ዘመን፤ በአማራው ላይ የደረሰውን የማያውቅ የለም። ጉዳዩ አሁን አማራው በሌላ ገዢ ሥር በከፋ ሁኔታ ያው ድርጊት እየተካሄደበት መሆኑ ነው። ለዚህ ነው አማራው በቃኝ ያለ! “እኛ አዛዦችህ ነን! እኛ የምንልህን ስማ!” “የፈለግነውን ባንተ ላይ ማድረግ እንችላለን!” ስለሆነበት ነው፤ አማራው ራሴን ባርያ አላደርግም! ብሎ መከላከል የያዘው። 

ወደኋላ ልመለስና የአማራነት ፖለቲካን ሂደት ላቅርብ። አማራ የፖለቲካ ማንነት አልነበረውም፣ የለውምም። አማራ፤ የአማራ መርኀ-ግብር አስቀምጦ፣ የአማራ ፓርቲ መሥርቶ፣ ይሄ ነው የኔ መሬት ብሎ ካርታ ቀርጾ፤ በአደባባይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ አልወጣም። አማራነት ይሄን፣ ይሄን ይዟል የሚባል ትርክት የለውም። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በያዘው ፍልስፍናና ፀረ-ኢትዮጵያ ፖለቲካው፤ ትግራይነት፣ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ሶማሌነት፣ አፋርነት፣ ደቡብነት፣ ጋምቤላነት፣ አዲስ አበቤነት፤ የፖለቲካ ምንነት ያዙ። ያስተሳሰብ አንድነት ገደል ገብቶ፤ ኦሮም ከሆንክ የኦሮሞ ፓርቲ፣ ትግሬ ከሆንክ የትግሬ ፓርቲ፣ አማራ ከሆንክ የአማራ ፕርቲ እንጂ፤ የራስህ ምርጫና የአስተሳሰብ ነፃነት የልህም! ተባለ የኢትዮጵያ ሕዝብ። አማራው ያን ጊዜም ሆነ አሁን፤ ያንን ከኢትዮጵያዊነት የሚያርቀውን የጎሳ ፖለቲካ ማንነት አልተቀበለም። በኢትዮጵያዊነቱ ቆመ። በዚህ ሂደት፤ ድሮም ሲነሳ በአማር መቃብር ላይ የትግራይን የበላይነት አኖራለሁ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ አማራነትን ወንጀል አድርጎ አቀረበውና፤ አማራ ባለበት ቦታ ሁሉ ዒላማ ተደርጎ፤ ያለ ኢትዮጵያዊነት ርኅራሄ፤ በየተገኘበት ታረደ፣ ሬሳው ተከተፈ፣ ንብረቱ ወደመ፣ መንደሩ ተቃጠለ፣ . . . ተዘርዝሮ ያማያልቅ ፍዳ ደረሰበት። እንግዲህ ይህ አማራ ለአማራነቱ የሚቆምና ተከላካይ አጣ! እያንዳንዳችን አማራው ሲጠቃ፤ በኢትዮጵያዊነታችን የኔ ወገን ተጠቃ ብለን መነሳት ካልቻልን፤ አማራ የራሱ የሆኑ ጠበቃዎች ማበጀቱ፤ በአማራነቱ ለመኖር ሲል መታገሉ፤ የተፈጥሮ ግዴታ ሆነበት። አሁን አማራው ራሱን ለመከላከል መነሳቱ ከዚህ ይመነጫል። ይህ ግን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው! ነበር አልልም። ምክንያቱም፤ አሁንም አማራ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ፤ የአማራ መጠቃት፤ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መጠቃት ነው! ብለን እንነሳለን የሚል እምነት አለኝ። በአማራነት መጠቃት ምን ማለት እንደሆነ፤ አንድ ምሳሌ ላቅርብ። ያቺ ሁላችን የተረዳነው አንዲት ትንሽ ልጅ፤ “ወላሂ ካሁን በኋላ አማራ አልሆንም!” ያለች ልጅ፤ በአረመኔዎች እጅ ሕይወቷ ሲቀጠፍ፤ ጥፋቷ አማራ መሆኗ ብቻ እንደሆነ፤ ግልጥ ነው። ከዚህ ወዲያ ምሳሌ፤ ላሳር ነው። አሁን የተያዘው ዘመቻ፤ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት፣ የአማራ ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት ይባልለት እንጂ፤ ተልዕኮው አማራን ለማንበርከክና በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ነው።

እንመርምረው! ለምንድን ነው ይሄ ጉዳይ አሁን ቅድሚያ የያዘበት? በመጀመሪያ አማራው የራሱ ወኪሎች እያስተዳደሩት አይደለም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ቅልቦች ናቸው በቦታው የተቀመጡት። ለአማራው ተቆርቋሪ አማራው ብቻ እንዳልሆነ ከላይ እንዳሰፈርኩት፤ የአማራውንም ጥቃት የሚፈልጉት አማራ ያልሆኑት ብቻ አይደሉም። ከአማራውም ሆድ አደሮች አሉ። ከሌሎች ጎሳዎችም ለአማራው የቆሙ አሉ። በሁለተኛ ደረጃ፤ አደጋ በተጋረጠበት ቦታ ካለው የአማራ ልዩ ኃይልና ምንም ችግር ከሌለበት የኦሮሞ ልዩ ኃይል፤ የትኛው ነው ቀድሞ ትጥቅ መፍታት ያለበት? በስምምነቱ መሠረት ትጥቅ ፍታ የተባለው፤ ወራሪው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ኃይል ነው፤ ወይንስ ይሄ ኃይል በጎረቤት አገር ተጠናክሮና በኦነግ ሸኔ እየተጠቃ ያለው አማራ ነው ፋኖውን እና ልዩ ኃይሉን መበተን ያለበት?

ነገሩን ባጠቃላይና በፍልስፍና ደረጃ ወስዶ ማየት አንድ ነገር ነው። ተጨባጩን ሀቅ ተገንዝቦ ትክክለኛ መንገድ መከተል፤ እውነተኛው መንገድ ነው። እንዲያው፤ “አንድ አገር ውስጥ አንድ ሠራዊት ነው መኖር ያለበት! ልዩ ኃይሎች መፍረስ አለባቸው!” የሚለው መርኅ፤ አንድ አገር ውስጥ አንድ መንግሥትና አንድ ሰንደቅ ዓለማ ነው መኖር ያለበት! አንድ አገር ውስጥ፤ የተለያዩ ክልሎች መሥርቶ፤ አንዱ ወደሌላው ቦታ እንዳይሄድ ኬላ ማቆም የለባቸውም! የሚለውን የት ረሱት!!! በኢትዮጵያ ያሉት “ክልሎች!” እኮ መንግሥታት ናቸው!!!

ወደ ጀመርኩት ሃሳብ ልመለስ። አሁን በዚች ሰዓት፤ የፌዴራል ልብስ ያጠለቁ ወታደሮች፤ በተለያዩ “የአማራ ክልል” ከተሞችና ገጠሮች ዘምተው፤ በሕዝቡ ላይ ያለ ርህራሄ እየተኮሱ፣ ምንም ዓይነት የሕግ ወይንም የአስተዳደር ተጠያቂነት በሌለው መልክ፤ ከፍተኛ ጉዳይ እያደረሱ ነው። ይህን ድርጊት በ “አማራው ክልል” ብቻ ዘመቻውን ያነጣጠረው ይሄ መንግሥት፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስና የራሱ አገር ለመመሥረት ያሰበው የአክራሪው የኦሮሙማ ፍልስፍና አራማጅ በመሆኑ ነው። በርግጥም አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሙማ መንግሥት ነው። ይሄን ስል ግን፤ ይህን መንግሥትና አድራጎቱን ሁሉም ኦሮሞዎች ይደግፉታል ማለት አይደለም። ይህ ግን የዚህ መንግሥት መገለጫ ነው። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የትግራይን ሕዝብ ወክያለሁ ብሎ በዘመኑ እንደገዛ ሁሉ፤ አሁን በማርሻል ብርሃኑ ጁላ አነጋገር፤ ታዲያ ምናለ የኛ ተረ ነውና ብንገዛችሁ! እንዳሉን ተረኛው ኦሮም እየገዛ ነው። የኦሮሞ ገዥነት በዘመቻው ብቻ አልተወሰነም። አዲስ አበባ ውስጥ እየተደረገ ያለውን ማጤን ያስፈልጋል። አዲስ አበባ የኛ ናት! ከሚለው አንስቶ፤ ወደ ከተማዋ የሚገባውን እና የሚወጣውን እኛ እንወስናለን! በማለትና ከባቢ ከተማ በመመሥረት የተኬደበት መንገድ፤ ገዥዎች እኛ ነን! ማለታቸውን እያሳወቁን ነው። የደቡብ አፍሪካው የፕሪቶሪያ ስምምነት፤ በኦሮሞ መንግሥትና በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መካከል የተካሄደ ስምምነት ነው። ለዚህም ነው ዝርዝሩ ለአባሎቻቸው ብቻ የተገለጠውና ቀሪዎቻችን እንዳናውቀው የተደረገው። አሁን የዚህ መንግሥት ወታደሮች የስምምነቱን ጉዳይ ማስፈጸም ላይ ናቸው።

አገራችንን ፈጥርቆ የያዛትን የፖለቲካ ምስቅልቅል ሊመልስ ወደ ሚችለው መፍትሔ ልመለስ። ትጥቅ የማስፈታቱ ጉዳይ፤ የመርኅ ጉዳይ አይደለም። የፖለቲካን ግብ ማስፈጸሚያ መንገድ ነው። ልዩ ኃይሉ የ “ክልሎች” የታጠቀ ሠራዊት ነው። ይህ ልዩ ኃይል ብቻ ሳይሆን፤ “ክልሎች” ራሳቸው መፍረስ እንዳለባቸው ነው የሚነግረን። እውነተኛ መፍትሔ ከተፈለገ፤ “ክልሎች” ፈርሰው፤ ማዕከላዊው መንግሥት የሚያስተዳድረው አንድ አገር እንድትኖረን፤ ላስተዳደር የሚመች ክፍፍሎች ብቻ ነው በአገራችን መኖር ያለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያባረረው፤ “አትከፋፍለን!” “እኛ አንድ ነን!” “የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ የነጻ አውጪ ግንባር መንግሥት አንፈልግም!” ብሎ ነው። ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፤ ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት አጽድቆ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ፤ አንድ የጦር ሠራዊት ኖሮት፣ አገራችንን ወደፊት የሚወስዳት። ልማት፣ ሰላም፣ ዕድገት የሚመጣው በዚህ ከሄድን ብቻ ነው። ያሉት ክልሎች ለአድልዖ፣ ለሙስና፣ ለየኔን አትንኩብኝ፣ እኔ ትልቅ ነኝና ብዙ ይሠጠኝ በሚል የተበሻቀጠ ሂደት መጓዣ ናቸው። ያ ደግሞ ለጥፋት እንጂ ለዕድገት አይሆንም። በነካ እጅዎ! ብዬ ነበር። አሁን ደግሞ ለራስዎ የወደፊት ሕልውና ሲሉ! እልዎታለሁ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ።

Filed in: Amharic