>

በደብረ ኤልያስ በፋኖ ሳቢያ መንግሥት የመኪና መንገዶችን ዘጋ (ጌጥዬ ያለው)

በደብረ ኤልያስ በፋኖ ሳቢያ መንግሥት የመኪና መንገዶችን ዘጋ 

ጌጥዬ ያለው

በምስራቅ ጎጃም ዞን፤ ደብረ ኤልያስ ወረዳ የመንግሥት ታጣቂዎች መንገድ በመዝጋት ሕዝቡን እያጉላሉ እና አጥረው እየከበቡ ናቸው። ከደብረ ኤልያስ ከተማ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ገነቴ ከተማ በአባይ በረሃ በኩል እስከ ወለጋ የሚወስደው መንገድ ከሚያዚያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በታጠቁ የመንግሥት ሃይሎች ተዘግቷል። መንገዱ የተዘጋው ‘በበረሃው ፋኖ አለ’ በሚል ሰበብ ሲሆን የሞተር ብስክሌቶችን ጨምሮ ማንኛውም ተሽከርካሪ ወደ በረሃው ማለፍም ሆነ ከበረሃው ወደ ከተማ መግባት አይችልም። 
በዚህም በበረሃማው የደብረ ኤልያስ አካባቢ በእርሻ  ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ማቅረብ አልቻሉም። ከምርቶቹ መካከል ከፊሎቹ አትክልትና ፍራፍሬዎች በመሆናቸው በደረሱበት ፍጥነት ለገበያ ፍጆታ ካልዋሉ የሚበላሹ ናቸው። በመሆኑም አምራቾች በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ። ለእርሻ ሥራ ወደ አካባቢው የገቡ የጉልበት ሠራተኞችም ለሥራ አጥነት ችግር እንደሚጋለጡ ስጋት አለ። 
በተመሳሳይ ከደብረ ኤልያስ ከተማ በብሄረ ብፁአን መልክዓ ሥላሤ አንድነት ገዳም በኩል ወደ አባይ በረሃ ብሎም ወደ ወለጋ የሚወስደው መንገድ በመንግሥት የታጠቁ ሃይላት ከተዘጋ ወራት ተቆጥረዋል። ለዚህም ሰበብ የተደረገው ገዳሙ ፋኖን ያግዛል የሚል ነው። በዚህ አቅጣጫ ከመንገዱ መዘጋት በዘለለ የመንግሥት ታጣቂዎች ከእነጫማቸው በምግባረ ቢስነት የገዳሙን በር ረግጠው በመግባት 11 ጸበልተኞችንና ካህናትን በግፍ ገድለው 17ቱን ክፉኛ ማቁሰላቸውን ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢ.ሰ.መ.ጉ.) ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እስከ ዛሬም ቁስለኞች ህክምና ተከልክለው፥ ወደ ገዳሙ መግባትም ሆነ መውጣት ብሎም ወደ አባይ በረሃ ማለፍ በታጣቂዎች ታግዷል። 
በአጠቃላይ የደብረ ኤልያስ ወረዳ ኗሪ በሁለቱም መንገዶች መዘጋት እርስ በእርሱ እንዳይገናኝ ተደርጎ በመንግሥት ታጣቂዎች ተከቧል። ድባቡም ወረዳዋን የጦርነት ቀጣና ውስጥ ያለች አስመስሏታል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በወረዳዋ ዋና ከተማ ደብረ ኤልያስ በርካታ ታጣቂዎች እየተተረማመሱ ይገኛሉ።

Filed in: Amharic