>

ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ ልትመለስ ትንሽ ወራቶች ሲቀሯት እነሆ መዳረሻዋን ለማወክ ሁለት ዓይነት ቡድኖች "እሪ" እያሉ ነው!

ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ ልትመለስ ትንሽ ወራቶች ሲቀሯት እነሆ መዳረሻዋን ለማወክ ሁለት ዓይነት ቡድኖች “እሪ” እያሉ ነው!

ብርሃኑ ድንቁ፣ ኦስሎ ኖርዌይ

እድሜ ለአምሓራ ህዝብና ለፋኖ ጀግኖች ይሁንና ኢትዮጵያ ዳግም ለኢትዮጵያኖች ልትመለስ ትንሽ ውጥን ነው የቀረው። ፋኖ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ፣ በአለም ታሪክ ውስጥ ባልታየ ስልትና ልዩ በሆነ የደፈጣ ውጊያ የአብይን ጦር ከጥቅም ውጭ እያደረገው ነው። ጠንቋይ አትበሉኝ እንጂ – በደርግ የመጨረሻ ዘመን እንደታየው አሁንም የአገዛዙ ወታደሮች ጠመንጃቸውን ትከሻቸው ላይ አርገው የውጊያ ቀጠናውን እየለቀቁ ወደ አዲስ አበባ ይጎርፋሉ የሚል ግምት አለኝ። በግራም በቀኝም ሳስተውል ይህ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም።

ታድያ ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ሳለ ሁለት ቡድኖች ሁኔታውን ለማዛባት ወይንም አቅጣጫ ለማስቀየር ሲዳከሩ ይታያል። አንደኛው ቡድን ከአብይ ጋ ሲያጨበጭብ የነበረው የከንቱዎች ስብስብ ሲሆን ሌላኛው “ኢትዮጵያን በአምሓራ ልክ እንሰፋታለን የሚለው አምሓራ ሊያጠፋህ መጣ” እያለ የሚንቦጇወጀው ተስፋ ቆራጩ ቡድን ነው። እነዚህ ሁለት ቡድኖች አገዛዙን ለመደርመስ የሚደረገውን ትግልና ታላቂቱ ኢትዮጵያ ወደነበረችበት ቦታዋ ለመመለስ የሚደረገው የመላ ኢትዮጵያውያንን እርብርቦሽ ለማጨናገፍ የቆሙ የሃገር ኅልውና ፀሮች ናቸው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ግንዛቤ ወስዶ እነዚህን ሁለት ቡድኖች ገለል ሊያደርጋቸው ይጋባል።

እስኪ በተናጥል እንያቸው፤

1/ የመጀመሪያው ቡድን የኮሎኔል አብይን እጅና እግር ሲስም የነበረው አብይን እንደ ልዩ ፍጡር ሲያመልከው የነበረ ነው። ይሄ ቡድን ከእንቅልፉ ሲነቃ አብይ የአይምሮ በሽተኛ መሆኑ ገባው። ታዲያ አምስት አመት እንቅልፍ ተኝቶ የነበረ ሰው ሲነቃ ድምፁን አጥፍቶ በዛው ጭልጥ ብሎ መደበቅ ሲገባው – “ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች፣ አብይ ኢትዮጵያን ሊያጠፋት ነው፣ አብይን መታገል አለብን” እያለ ድንገት ነቅቶ ያዛኝ ቅቤ አንጓች መሆኑ ግራሞትን ፈጥሯል። በዚህ ቡድን ውስጥ የተካቱት ሰዎች አሁንም አንዳች የልብ ስብራት አይታይባቸውም። ሲጀመር ገና “አብይን ያልተቀበላችሁ ችግር አለባችሁ” ይሉ ነበር። እነኚህ ሰዎች “ተዉ” እየተባሉ ከአብይ ጋር ወግነው ኢትዮጵያንና የአምሓራን ህዝብ ታላቅ መከራ ውስጥ የዘፈቁ ናቸው። ታዲያ እነዚህን የመከራ ባለቤቶች እንዴት ብለን “እንኳን ደህና መጣችሁ” እንበላቸው?

ይልቁንም ለዚህ ቡድን አንድና አንድ ምክር አለኝ። እባካችሁ ስለ እግዚአብሄር ብላችሁ ዝም በሉ አለያም ወደ ገዳም ገብታችሁ እጆቻችሁን ወደ እግዚአብሄር ዘርግታችሁ ይቅር በለን በሉ!

እንደው ድካም ይሆንባችኋል እንጂ ከዚህ በኋላ የፈለጋችሁን ብትለፈልፉ ማንም ከቁብ የሚቆጥራችሁ የለም። ስለዚህ እባካችሁ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ራሳችሁን አግልሉ።

2/ ሁለተኛው ቡድን ዘር ላይ ተመስርቶ ጥላቻን ሲሰብክ የቆየው ቡድን ነው። ይሄ ቡድን በሁለት ስብስቦች የተከፈለ ነው።

የመጀመሪያው ስብስብ በአምሓራ ሕዝብ ጥላቻ በእጅጉ የታወረ ነው። በዚህ ስብስብ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ትርክት ከበታችነት ስሜት የመነጨ የአዕምሮ ብክለት ነው። ከመነሻቸው “አምሓራ የሚባል ዘር እስካለ ድረስ ኢትዮጵያን መግዛት ስለማይቻል – በአምሓራ ላይ ጥላቻ እየሰበክን አንገታቸውን ማስደፋት አልያም ገለን መጨረስ አለብን” ብለው ክፉ ሃሳብ አንግበው የተነሱ ናቸው። እነኝህ ዓይነቶቹ የእርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ሰዎች ከስልሳዎቹ ዘመን ጀምሮ ይሄን የከረፋ ትርክታቸውን በየቀኑ ከመደስኳር አልቦዘኑም። ዳሩ ግን አሁን የአምሓራው ህዝብ ቆርጦ በመነሳቱና ሌላውም ኢትዮጵያዊ “የብሄር ብሄረሰብ ትርክት” ሃሰት መሆኑን በሃምሳ ዓመቶቹ የፖለቲካ ተሞክሮ ስላረጋገጠ ጩኸታቸው ሁሉ የቀበሮ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ውሻዎች ይጮሃሉ ግመሎቹ ግን ጉዞአቸውን ቀጥለዋል።

ሌላኛው የዚህ ቡድን ስብስብ “ኢትዮጵያን በአምሓራ ልክ እንሰፋታለን፣ አምሓራ ከአለም አንደኛ ነው፣ የዚህን ወይም የዚያን ዘር እናጠፋለን” እያለ በአምሓራ ስም የሚደነፋው ተንኮለኛ ቡድን ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች – አምሓራ ነን እያሉ የአምሓራን ስም ለማጠልሸት የተነሱ፣ የአምሓራን ህዝብ ማንነትና ባህላዊ ትውፊት የማያውቁ፣ ምናልባትም አማርኛ ስለተናገሩ አምሓራ የሆኑ የመሰላቸው አልያም የአምሓራን ህዝብ ለማስጠላት ከሌላ ቦታ የቤት ስራ የተሰጣቸው ናቸው። እነኝህ ሰዎች – ፋኖ የጀመረው ትግል ልክ አዲስ እንደፈነዳ እሳተ ገሞራ አካባቢውን እያጥለቀለቀው ስለመጣ በዚህ ደካማ ትርክት እሳቱን ማስቆም እንችላለን አለያም ሌላውን ጎሳ በአምሓራ ላይ አስነስተን የእሳቱን ወንዝ እንገድባለን ብለው የሞኝ ሃሳብ ይዘው ብቅ ያሉ ናቸው። ለነዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦችም ምክር አለኝ። “እባካችሁ ይብቃችሁ! ህዝብን በህዝብ ላይ አታነሳሱ፣ ይህ እኩይ ሥራ ለማንም ወገን አይጠቅምም። ክፉ ፖለቲካ ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን አልታየም።

በዚህም በዚያም ብንቃኘው የአምሓራ ህዝብ ነፃነቱን ሳያገኝና ህልውናውን እስከወዲያኛው ሳያረጋግጥ መሬት ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢል ወደ ኋላ አይመለስም።

ወጣም ወረደም – የፋኖ ትግል በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። አሁን ኃይላችንን እና እውቀታችንን መጠቀም ካለብን “የሽግግር መንግስት ወይም የጊዜያዊ መንግስት ይቋቋም” እሚለው ሳይንስ ላይ መሆን አለበት።

ከፋኖ ጋ ወደፊት!

Filed in: Amharic