>

ኮንጎ፣ የኮሪያ ዘማቾች እና የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሰራዊት ሁሌም በክብር ሊዘከሩ፣ ሊታወሱ  ይገባቸዋል!!

የኮንጎ፣ የኮሪያ ዘማቾች እና የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሰራዊት ሁሌም በክብር ሊዘከሩ፣ ሊታወሱ  ይገባቸዋል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

 

‹‹…አገርህን ጠላት እንዳይደፍራት ወታደር ሆነህ ጠብቃት፣ እንደ አባቶችህ ጀግና ሆነህ አሳያት፣ በጀግንነት ታሪክ ሥራላት። ታሪክ ያለው ከወታደርነት ነው፣ ጀግንነት ያለው ከወታደርነት ነው። ጀብዱ ያለው ከወታደርነት ነው፣ ታላቅ ስም ያለው ከወታደርነት ነው…፡፡›› የሚል የአባቶቻችን የጀግንነት የአደራ ቃል ውርስ አለን እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡

በርግጥም ደግሞ ታሪካችንን ስንፈትሽም- ታላቁ የዓድዋ ድል የአርበኝነት፣ የወታደርነት ውጤት ነው፡፡ የአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራና የኢትዮጵያዊያን ድል የወታደርነት ውጤት ነው፡፡ ካራማራ የወታደርነት ውጤት ነው፣ የኢትዮጵያ የተከበረ ታሪክ የወታደር ታሪክ ነው፡፡ ለምን ሲባል ኢትዮጵያ የተከበረችው በጀግኖች ልጆቿ፤ በወታደሮች ብርቱ ክንድ ነውና፡፡

ዛሬ እኔም፣ አንተም ሁላችንም የቆምንባት የኢትዮጵያ ምድር በቀደሙ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት መሠረትነት የተገነባ ነው፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉም አርበኛ፣ ሁሉም ጦረኛ ነው፡፡ ሁሉም ሰንደቁን አስቀድሞ ይገሰግሳል፡፡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ጀብዱ እየሠሩ ዛሬ ላይ ኮርተን የምንኖርባት አገር፣ ኮርተን የምንናገረው፣ በአሸናፊነት የምንመሰክረው ታሪክ አኑረውልናል፡፡

ከጉንደት እስከ ጉራዕ፣ ከዓድዋ እስከ ማይጨው፣ ከኦጋዴን እስከ ካራማራ… ያበበ የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና እምቢ ለነፃነቴ ባይነት፣ የኢትዮጵያ ድንበር ሳይገድበው አውሮፓ ምድር ሮም/ጣሊያን ድረስ ተሻግሮ ዓለምን ያስደመመ፣ በኮሪያ ልሣነ-ምድር፤ በአፍሪካ (በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳንና በሶማሊያ ምድር የኢትዮጵያ ሰራዊት በተጋድሎ ድልና በሰላም አስከባሪነት ትልቅ ስምና ዝናን ያተረፈ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ለመጥቀስም፤ የተባበሩት መንግሥታት ከጥቂት ዓመታት በፊት ባወጣው መረጃ መሠረት፤ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካና በመላው ዓለም ባደረገችውና እየደረገችው ባለው የሰላም አስከባሪነት የጎላ ተሣትፎዋ ምክንያት- በአፍሪካ የአንደኝነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃነት እንደሚያስቀምጣት እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፤

Besides being a seat to various International Nongovernment Organizations (NGOs) and Diplomatic Seats, Ethiopia is the Political Capital City of African. This ancient state has been wholeheartedly and constructively contributing to world peace and stability in line with the principles and missions of UN so that the world could enjoy peaceful coexistence. Evidently, it is number one in Africa and Second largest Peace Keeping Force producer in the world.

እነዚያ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ታሪክ ሠርተው፣ ስማቸውን ከመቃብር በላይ ትተው ‹አገሩን ያስደፈረ ታሪክ ይውቀሰው፣ አፅማችንም እሾህ ሆኖ ይውጋው› ብለው ቃል ኪዳን አስረው፣ አደራ ሰጥተው በክብር አልፈዋል፡፡

ትናንትና በመስቀል አደባባይ ለ116ኛ ጊዜ በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በኮንጎና በኮሪያ ዘምተው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በጀግንነትና በድል ከፍ ያደረጉና በክብር ያስጠሩ አባቶቻች ተዘክረው ነበር። በወታደራዊ ሰልፍ ትርዒትም /Military Parade/ ዐይተናቸዋልና ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ክብር ተሰምቶናል።

ታሪካችን ምልዑና የተከበረ ማድረግ የምንችለው ትናንትናን ጥለን ዛሬን አንጠልጥለን አይደለምና የኢትዮጵያን በነጻነትና በሉዓላዊነቷ አስከብረው ያቆዩልንን የትናንትና ጀግኖቻችንን ሁሌም በክብር ልንዘክራቸው ይገባል፡፡

በዚህ የጀግንነት ገድል ታሪክ ውስጥ ደማቅ ታሪክን አሻራ ከተዉ ኢትዮጵያውያን መካከል- ከበርካታ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ታላቅ አኩሪ ታሪክን ለሀገሩ ያስመዘገበውን አርበኛውንና በተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ በመሆን ኮንጎ ድረስ የዘመተውን የወላጅ አባቴን አኩሪ የታሪክ ቅርስ ፎቶዎች ላጋራችሁ ወድድኹ፡፡

ምስሉ የኢትዮጵያዊው ጀግና አርበኛ እና በኮንጎ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ሆነው ያገለገሉትና እስከ በሕይወታቸው እልፈት ድረስም በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር በጸሐፊነት ያገለገሉት ወታደራዊ መኮንን፣ አርበኛው፣ የመ/አ ወርቁ ደስታ ምስሎች ናቸው፡፡

ሜዳሊያዎቹንና ኒሻኖቹን በተመለከተም፤

  1. በ5ቱ የፀረ ፋሽስት አርበኝነት ዘመን አርበኛው ወርቁ ደስታ በጎንደርና በዙሪያው ላበረከቱት የአርበኝነት ተጋድሎ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተበረከተ ኒሻን፤
  2. በተባበሩት መንግሥታ በኮንጎ የሰላም ማስከበር የጀግንነት ተጋድሎ ከተባበሩት መንግሥትና ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተበረከተ ኒሻንና ሜዳላይ፤
  3. ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ለመደምሰስ ላደረጉት የጀግንነት ተጋድሎ ከኅብረተሰባዊት አብዮታዊ መንግሥት የተበረከተ ዘንባባ ናቸው፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ሰላም ለሀገራችን!!

Filed in: Amharic