>

ሚናወቻቸውን የተለዋወጡት አቡነ ኤርምያስና አቶ ታየ ደንድአ

ሚናወቻቸውን የተለዋወጡት አቡነ ኤርምያስና አቶ ታየ ደንድአ

 

የሐይማኖት አባት ሚና ግፈኞችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ፍርድ ጠፋ፣ ግፍ ተንሰራፋ፣ ፍትሕ ጎደለ፣ ሕዝብ ተበደለ እያለ በመጮህ ለእውነትና ለእውነት ብቻ በመቆም እመሸበት ማደር ነው።  የፖለቲከኛ ሚና ደግሞ አማላይ ንግግር በመናገር ሕዝብን አደንዝዞ ተወዳጅነት ማትረፍና የግልን ወይም የቡድንን ጥቅም ማሳካት ነው።  

የሐይማኖት አባት የሚባሉት አቡነ ኤርምያስ ደግሞ የአማራን ሕዝብ በንቦቴ (drone) እየነቦተ ያለርህራሄ ከሚጨፈጭፍ የጭራቅ አሕመድ አረመኔ ወታደር ጎን ተኩራርተው ተቀመጠው በቅርቡ ላሊበላ ላይ ያደረጉት ንግግር በግልጽ የሚመሰክርባቸው የሐይማኖት አባትነት ሳይሆን የፖለቲከኛነት ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ነው።

አቶ ታየ ደንድአ ከፖለቲከኛ መንገድ ሙሉ በሙሉ አፈንግጠው፣ ግላዊ ጥቅም ባፍንጫየ ይውጣ ብለው፣ አምባገነኑን ጭራቅ አሕመድን ፊት ለፊት ተጋፍጠው፣ ውሸት በልቶ ውሸት የሚያራ ቀጣፊ ብቻ ሳይሆን፣ በሰው ደም የሚጫወት አረመኔ መሆኑን በግልጽ ተናግረው፣ ለእስር ተዳርገው በተመስገን ጡሩነህ ገራፊወች እየተገረፉ ይገኛሉ።  በጭራቅ የመጣ ሥጋ አልበላም ይቅርብኝ ብለው ሥቃይ መብላት ጀምረዋል።     

ስለዚህም አቡነ ኤርምያስ ሆይ፣ ተግባርወ ሁሉ የመንፈሳዊ አባት ሳይሆን የፖለቲካኛ መሆኑ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ስለሆነና በሐይማኖት ካባ የፖለቲካ ደባ ለመፈጸም ከማይችሉበት ደረጃ ስለደረሱ፣ ፖለቲካውን በግልጽ ይያዙት።  ሳይመሽ ገሸሽ ብለው ብልጽግናን ይቀላቅሉና፣ ጭራቅ አሕመድ ባቶ ታየ ደንድአ ምትክ የሰላሚ ሚኒስቴር እንዲያደርግወት እግሩ ላይ ወድቀው ይማፀኑት።  አቡን እየተባሉ የነ አቡነ ጴጥሮስን ስም አያጉድፉ።    

መስፍን አረጋ 

mesfin.arega@gmail.com 

Filed in: Amharic