>
5:21 pm - Monday July 20, 7536

ፋሺስታዊው አገዛዝ ሳይወገድ በተናጥል የሚፈታ ችግር የለም!

ፋሺስታዊው አገዛዝ ሳይወገድ በተናጥል የሚፈታ ችግር የለም

ከይኄይስ እውነቱ

በዚህ ጽሑፍ ኹለት ቁም ነገሮችን በስሱ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ 1ኛ/ ፋሺስታዊው አገዛዝ የጥፋት ርኲሰትን በኢትዮጵያችን በይፋ ለማንገሥ የሔደበትን ርቀት፤ እና/ ሰሞኑን ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በሚመለከት ለአንባብያን ያካፈልሁትን መልእክት በሚመለከት ከተጠቀሰው የነውሮች ነውር አኳያ ያለኝን ተጨማሪ አስተያየት ይመለከታል፡፡

1ኛ/ የርጉም ዐቢይ ፋሺስታዊ አገዛዝ በይፋ ሰይጣናዊ መሆኑ አሁን ላይ የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ አገዛዙ የሕይወት ክሩ ኢትዮጵያንና የቆሙባትን ዓይነተኛ ተቋማዊ ዓምዶች ለማፈራረስ የሚረዱ ወቅታዊ አጀንዳዎችን በመስጠት ላይ የተንጠላጠለ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ እነዚህን አጀንዳዎች ለጥንቃቄ ሲባል የሚመለከተው በሙሉ በተገቢው መስመር ርምጃ የመውሰድ ተገቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አብዛኛውን ጊዜ መነጋገሪያ ማድረግና ማስጮኽ በርጉማኑ ወጥመድ ውስጥ መግባት ከመሆኑም በላይ ጊዜያዊውን እና ዘላቂውን፣ ዐበይቱን እና ንኡሳኑን ለይቶ በማወቅ የክፋቱን ሥር/ምንጭ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም በተናጥል ለሚነሡ ወቅታዊ አጀንዳዎች ‹ማገዶ› ማባከን አይገባም፡፡ 

ከአገዛዙ ሰይጣናዊነት መገለጫ አጀንዳዎች አንዱ አገርን በዲን እሳት የሚያጠፋው ግብረ ሰዶማዊነት የተባለ ዐቢይ ርኵሰት እና የአእምሮና አካል ጽኑ ደዌ ውስጥ ውስጡን ሲንተከተክ ከርሞ አሁን በተቀደሰችው ምድር በኢትዮጵያ በይፋ ለመናኘት ፋሺስታዊው አገዛዝ ከምዕራባውያኑ ጋር ውል መፈጣጠሙ ተሰምቷል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ዘግይቶም ቢሆን ርጕም ዐቢይንና አገዛዙን ባወገዙበት ቃላቸው በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን በማስጠንቀቂያ መልክ አንሥተውታል፡፡ አገዛዙ አገርና ነባር የእምነት ተቋማትን ከማፍረሱ ጋር አቋም የሌለው ‹ለዘብተኛ› ትውልድ መፍጠሩም በ‹አሳዳሪዎቹ› ከተሰጠው ተልእኮ አንዱ ይመስለኛል፡፡ ከነባር ኢትዮጵያዊ እሤቶች ጋር እንዲፋታ አጥብቀው የሚሠሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አገዛዙ ይህ ርኵሰት አጀንዳ ሆኖ እንዲራገብለት ይፈልጋል? አዎ! ይህንን አይነኬ ጉዳይ ሕዝባችን እንዲለማመድለት ስለሚፈልግ፡፡ በእምነት ጉዳይ ‹ምን አለበት› የሚል ትውልድ ተነሥቶ ተሐድሶ ፕሮቴስታንት የተባለ የመናፍቃንን ጥርቅም እንደፈጠረ ማለት ነው፡፡

ሰይጣናዊውን ዓለም የተቆጣጠሩት ምዕራባውያን ራሳቸው አብደው ቀሪውንም ዓለም ለማሳበድ ኢትዮጵያን ዒላማቸው ካደረጉ ዘመናትን ያስቆጠሩ ሲሆን ለዚህም ዲያቢሎሳዊ ተግባር ዋነኛ ቅጥረኛና ተባባሪአቸው ወያኔ ሕወሓት ነበር፡፡ በሰብአዊ መብት ሽፋን በዚህ ደዌ የተጠቁ ግለሰቦች ከተለያየ የዓለም ክፍል መጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ስብሰባ እንዲያደርጉ እስከመፍቀድ የደረሰበት ጊዜም ነበር፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበረው ቢል ክሊንተን በተለይም በኦባማ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረችው ባለቤቱ ሂላሪ ክሊንተን በፆታ ትምህርት ሽፋን ይህንን ነውር በአገራችን ለማስፋፋት ፕሮጀክት አዘጋጅተው ይንቀሳቀሱ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በተለያየ ጊዜም ዕርጥባንና ብድር ለመስጠት አሜሪካኖቹም ሆኑ ሌሎች በነሱ የሚመሩ ምዕራባውያን ተቋማት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጡት እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያችን የበቀለው ‹የጥፋት ልጅ› ርጉም ዐቢይ አንድ ሐሙስ በቀረው አገዛዙ ይህንን የነውሮች ሁሉ ቁንጮ ሊተክልብን እየተሯሯጠ ይገኛል፡፡ በቀደመው ጊዜም ሆነ አሁን የተሽመደመዱትና ራሳቸውም በጽኑ ደዌ ተይዘው የሚገኙት ቤተ ክህነቱም ሆነ መጅሊሱ ዝምታን መርጠዋል፡፡ 

ሰሞኑን ርጉም ዐቢይ ለራሱ ዓላማ ያቋቋመውና ኢትዮጵያዊነት የሌለው ‹የሃይማኖት ተቋማት› የተባለ አንድ ተቋም በርጉሙ ፈቃድ ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ ዓይነት ‹የውግዘት› መግለጫ አውጥቷል፡፡ ከማይወክሉትና ለዓመታት በአገዛዙ በጅምላ እየተጨፈጨፈ ከሚገኘውና እልቂቱን በዝምታቸው ካፀደቁለት ሕዝብ ቁጣ የሚያመልጡ መስሎአቸው፡፡ የሚያሳዝነው ምእመናኑን እና ሊቃውንቱን ለመስማት የማይፈልገውና በተግባር አያገባችሁም ያለው ቤተ ክህነትና የጐሣ ሸንጎ የሆነው ሲኖዶስ በኢኦተቤክ. ስም በዚህ በፍጹም አላስፈላጊ በሆነ ተቋም ውስጥ ዲያቢሎሳዊ ኅብረት ፈጥረው ሀገር የሆነችውን የኢትዮጵያ ቤክ አዋርደዋል፡፡ አንድ ዮናታን የተባለ ጋጠ ወጥ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያነውር የዚህ ‹ባዕድ› ተቋምን አቋም የምናስታውሰው ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አገርና ቤተ ክርስቲያንን ለማዳን ተሰልበዋል፡፡ አገር ማቅ ለብሳ÷ ሕዝብ በጦርነትና በቀጠና እያለቀ እየዞረ የሚጨፍረውን አውደልዳይ አድር ባይ ቡድን  ‹የተሰለበው ጃንደረባው ትውልድ› እንዳለ ‹የምሥራቁ ዘመዳችን›፡፡ እውነተኛ ሲኖዶስ እና መጅሊስ ቢኖረን ክርስቲያኑን እና ሙስሊም ኢትዮጵያዊውን በማስተባበር ሕዝቡ ለአገዛዙ እንዳይገዛ ማድረግና ውድቀቱን ማፋጠን በተቻለ ነበር፡፡ ስለሆነም ፋሺስታዊው አገዛዝ በየጊዜው ከነባር የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርሶች፣ በምልክትነት ይታዩ የነበሩ ብሔራዊ ተቋማትን አገርን ለማፍረስ ተግባር በማዋል፣ ከብሔራዊ በዓላት፣ ከሃይማኖታዊ በዓላት፣ በዘረፋና በቃጠሎ እንዲሁም ማባሪያ በሌለው የሐሰት/ፈጠራ ወሬዎች ማሸበር፣  ወዘተ. ጋር ተያይዞ የሚፈጽማቸውን ግዙፍ ጥፋቶችና  በትንኮሳ መልክ የሚያነሣቸውን ጉዳዮች ወይም የሕማም ምልክቶች የምንፋለማቸው እያንዳንዱን ጉዳይ በተናጥል በማየትና ጊዜያዊ ርምጃ በመውሰድ ሳይሆን በጦር ሜዳ እየተፋለሙ እንዳሉት የዐምሐራ ፋኖ ወገኖቻችን ቊርጥ ኅሊና በማድረግ አገዛዙን ለማስወገድ ሁላችንም በኅብረት ስንነሣ ብቻ ነው፡፡ ጥግ ይዞ ወይም ዳር ቆሞ በኹለት ልብ እያነከሱ የሚደረግ ትግል የለም፡፡ በየአጀንዳው የሚደረግ የተናጥል እንቅስቃሴ የተናጥል እልቂትን እንዳያስከትል ሥጋት አለኝ፡፡

2ኛ/ በቅርቡ ኢትዮጵያዊ ዜግነት በዓለማዊ ሕይወት እና በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥልጣን ደረጃ እንዴት እንደሚታይ አንድ መጣጥፍ ለአንባብያን አቅርቤ ነበር፡፡ ጽሑፉ በዝርወት ለሚገኘው አንዳንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ስስ ጉዳይ በመሆኑ በበጎ የማይመለከቱት ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ እኔ ግን የማምንበትን ጽፌአለሁ፡፡ እንደውም አለዘቤው እንጂ ‹ኢትዮጵያዊ ዜግነትን› ከአገር ባለቤትነት ባለፈ ‹በምሥጢር/ሃይማኖት› ደረጃ የተቀደሰ አቋም አድርጌ የማይ ሰው ነኝ፡፡ አዎ! የቤተ ክርስቲያናችን ዋና ጉዳይ ፓስፖርት እንዳልሆነ በሚገባ ዐውቃለሁ፡፡ ለፋሺስታዊው አገዛዙ ደግሞ የተለመደ ወቅታዊ አጀንዳው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሆኖም የጽሑፉ ዋና ዓላማ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል የዜግነት ሕጉን አቋም በሚመለከት ብዥታና አለዕውቀትም የተደረጉ ንግግሮች ስላደመጥሁ ያንን ለማጥራት በማሰብ የቀረበ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዜግነት ጉዳይ በፖለቲካ ካልሆነ በሃይማኖት (ተመሳሳይ ተቋማትና የጥቅም ግጭት በሌለበት) ቦታ የለውም የሚል አንድምታ ያለው አመለካከት ስሕተት ነው፡፡ የጻፍሑት ለክርክር ስላልሆነ ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ ከዋናው ጉዳይ ስለሚያናጥበን፡፡ ዛሬ በምዕራቡ ዓለም በስደት የሚኖሩ ወገኖቻችን (ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ቊጥር) ሥጋዊ ሕይወታቸውን ለማቅለል ሲሉ በፈቃዳቸው የሚኖሩበትን አገር ዜግነት ይይዛሉ፡፡ ተራውን የሚጠባበቅም ይገኛል፡፡ ያ የየግለሰቡ ውሳኔ፣ፈቃድና ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ያንን አከብራለሁ፡፡ የሃይማኖት አባት ጉዳይ ግን ይለያል፡፡ ጥያቄው ቋሚ መኖሪያውን በውጭ አድርጓል/አላደረገም የሚለውም አይደለም፡፡ ሹመቱ ሥልጣኑ የአገሩ ባለቤት ባለርስት (ዜጋ በሆነ) በሕዝብ/ምእመናን ላይ ነውና፡፡ አንዳንድ በውጭ የምትገኙ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያናችን ላለፉት 50 ዓመታት በአጠቃላይ፣ ላለፉት ዐምስት ዓመታት በተለይ የምትገኝበትን የተሟላ ሥዕል ሳይኖራችሁ ለግለሰቦች ምስክርነት መስጠት ትክክል አይመስለኝም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ቀኖና የጣሱ ‹አባቶች› ምእመናንን በነፍስ ሊያድኑ የሚችሉበት መንፈሳዊ ብቃት የላቸውም፡፡ አገርና ቤተ ክርስቲያንን እያፈረሰ ያለን ዲያቢሎሳዊ አገዛዝ በጥብዐት ማውገዝ ያልቻሉና ሥጋ ከለበሱ አጋንንት ጋር ለንግግር የሚቀመጡ ሰዎችን ብፅዕናው ቀርቶ እንዴት ‹አባት› ማለት ይቻላል? ገዳማውያን በጅምላ ሲጨፈጨፉ ሞታቸውን ከባዕዳን ስንሰማ ለመናገር ያልደፈሩ፣ እነሱው ጥሪ አድርገው ሰማዕትነትን ለተቀበሉ የሻሸመኔ ምእመናን እና ካህናት ጸሎተ ፍትሐት ያላደረጉ፣ በሐዘን የደቀቁ ቤተሰቦቻቸውን ያላጽናኑና ያልረዱ (የትግራይን አህጉረ ስብከት አስገንጥለው የጐሣ ‹ቤተ ክህነት› እንዲቋቋም – በነፍስም በሥጋም ለሚገሉት በሽተኞች – ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ከባንክ ወጭ አድርገው የምእመኑን ገንዘብ ሲልኩ፤ ለሻሸመኔዎቹ በሚያሳፍር መልኩ ምእመኑን ሲለምኑ ተስተውሏል)፡፡ ይልቁንም ያሳረዱአቸውን ካህናተ ጣዖት በላያቸው ላይ የሾሙባቸው የሲኖዶስ ሰዎችን እንዴት በአባትነት ነፍሳችንን ለእነሱ አደራ እንሰጣለን? ማቅ በመልበሳቸው ቤተሰባቸውን በትነው ከሥራ ገበታ የተባረሩት ምእመናንሰ? አገራችንን ከቅኝ ገዢዎች የታደገው የሊቀ ሰማዕታት ታቦተ ሕግ የሚገኝበትን የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤክ በታላቁ ብሔራዊ የድል በዓላችን (ዓድዋ) ዓላውያኑ ሲደፍሩና ሕዝብ በጭስ አፍነው ሲገድሉ፣ አሁንም በዓመቱ ከጥቂት ቀናት በፊት የደብሩን ዕቃ ቤት በማን አለብኝነት ገብተው ዘርፈው ሲወጡ በሚያስደነግጥ ዝምታ ላለፉ ሰዎች ምክንያት እየፈለገ የሚያስታምም ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ሊሆን አይችልም፡፡ የመርዓዊውስ ጭፍጨፋ ቤተ ክህነቱ አይመለከተውም፣ መጅሊሱ አያገባውም፣ በቀሩት ክፍለ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ነግ በኔን አያውቁም? ክርስትና እንደ ዴማስ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብሎ ከመንገድ መቅረት ሳይሆን፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሩጫን በሰማዕትነት ጭምር መጨረስን ይጠይቃል፡፡ እንኳን መንጋውን ሊጠብቁ ለራሳቸው የማይሆኑ የእኛዎቹ ጉዶች መንጋውን ለማይራሩ ጨካኞች ተኵላዎች አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ በጅምር ከመንገድ ለቀሩ ‹አባት› ተብዬዎች ምስክርነት/ጥብቅና መቆም ክርስትናውን ያለመረዳት ወይም ሰማዕተ ሐሰት መሆን ነው፡፡ 

ወደ ቀዳሚ ነገሬ ልመለስና የዜግነቱን ጉዳይ ምዕራባውያኑ መንግሥታት በየአገራቸው ካነገሡትና በቀረውም ዓለም እያስፋፉ ካሉት ግብረ ሰዶም/ግብረ ገሞራ ከተባለ ርኲሰት ጋር አያይዘን እንየው፡፡ ርኲሰቱን እና ደዌውን እንደ አንድ ሰብአዊ መብት ቆጥረውና ሽፋን ሰጥተው ጥብቅና የቆሙለት ሰይጣናዊ መንግሥታት እና ይህንን በለዘብተኝነት ትክክል ነው ብሎ በተቀበለ ኅብረተሰብ ሰንደቅ ዓለማ ሥር ተንበርክኮ፣ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሰይጣናዊ ሥርዓት የታማኝነትና ታዛዥነት መሐላ በመፈጸም የሚገኝ ዜግነት እንዴት ይታያል? መልሱን ለእያንዳንዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ዜጋ ኅሊና እተወዋለሁ፡፡ ለኑሮ ለቤተሰቤ የተሻለ ዕድል ይሰጠኛል ብሎ የሚደረገው ውሳኔ አንድ ነገር ሆኖ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ አድጎና ጣዕሟን ቀምሶ በአሜሪካዊ ዜግነቴ በጣም እኮራለሁ የሚል ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲገኝ ግን ያምማል፡፡ ሳይገባው ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር እጁ ላይ ወድቃ እየገዛ ካለውና የሱ ቢጤ የአእምሮ ድኩማኖችና መሸጦዎች በተሰባሰቡበት ሸንጎ ፊት  ለአሜሪካ እሞታለሁ ካለው በሽተኛ ሰው ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ይህን አሳፋሪ ‹ኩራት› በአደባባይ የተናገረው ደግሞ በወያኔ ዘመን የኦሕዴድ ካድሬ የነበረ፣ ‹ከኢሕአዴጋዊ› በሽታ የተሻለው መስሎ መልሶ ያገረሸበት፣ ዋና የትግል ሚዲያ በሆነው ኢትዮ-360 አባል ሆኖ ከቆየ በኋላ በወሳኝ ሰዓት ‹ዐምሐራ ዐምሐራ አትበሉ› ብሎ በመርህ ሳይሆን በቤተሰቦቹ ምክር ተለይቶ የወጣው ግለሰብ ነው፡፡ ‹መለየትን የሚወድ ምኞቱን ይከተላል፡፡› እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የውጭ አገር ዜጋ ትውልድ አገሩን ኢትዮጵያን በ‹ልቡ› እንደሚወድ ይነገራል፡፡ አዎ! የአብዛኞቹ እውነታ ይሄ ሊሆን ይችላል፡፡ ላገሩ ዐቅሙ በፈቀደ መጠን አስተዋጽኦ የሚያደርገውም በዛ መንፈስ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ባለገርነቱን ባለ ርስት መሆኑን ባለቤትነቱን ወይም ዜግነቱን ባዕድ አገር በፈጸመው የታማኝነትና የታዛዥነት ሥርዓት የተቀማ ይመስላል፡፡ ይሄ ደግሞ ‹በልብ አምኖ በአፍ መመስከሩን› እንዳጎደለበት ይሰማኛል፡፡ የተጠቀሰው ርኵሰት ኢትዮጵያውያኑ በሚኖሩባቸው ምዕራባውያን አገራት ሥርዓት አካልና ዓይነተኛ መገለጫ በመሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ይነካል፡፡ ይረብሻልም፡፡ በተለይም (ተገፍተው ከወጡት በስተቀር) በፈቃዳቸው፣ በዘመድ አዝማድ ወይም ለቤተ ክህነቱ ጉቦ ጭምር ሰጥተው ወደነዚህ ዓለማት የሔዱና ለዓለም ምውት ነን ያሉ ‹መነኮሳትን› ለጽድቅ ተሰደው ነው እንበል? ዛሬም ‹ሱባኤ ለመያዝ› በጾም ወራት ወደ ምዕራቡ ዓለም በተለይም ወደ ሀገረ አሜሪካ ለመሔደ ያኮበኮቡ ‹መነኮሳት› በርካታ ናቸው፡፡ አንገርምም!? ከገዳማት ሀገር ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ ምድረ ለሱባኤ፡፡ ‹መልካም ሱባኤ›፡፡

Filed in: Amharic