>
5:21 pm - Monday July 21, 1952

ከኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የተሰጠ መግለጫ!

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች

– በአውሮፓ ኅብረት እና በአፍሪካ፣ በካሪቢያንና በፓስፊክ ሀገራት መካከል የተፈረመውንና የሳሞአ ስምምነት በመባል የሚታወቀውን የንግድና የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነት አስመልክቶ የተሠጠ መግለጫ

የተወደዳችሁ በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ልጆቻችን ከሁሉ በማስቀደም መንፈሳዊ ሰላምታችንን እናቀርባለን፡፡

ባሳለፍነው የህዳር ወር በ5ኛው ቀን 2016 ዓም የተወሰኑ የአፍሪካ የካሪቢያንና የፓሲፊክ ሀገራት ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ጸንቶ የሚቆይ የንግድና ኢኮኖሚ አሳሪ የአጋርነት ስምምነትን ከአውሮፓ ኅብረት ጋራ ሳሞአ በምትባል ሀገር በተከናወነው የስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያም ይህንኑ ስምምነት መፈረሟን በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 

ይህ በአውሮፓ ኅብረት እና በአፍሪካ፣ በካሪቢያንና በፓስፊክ ሀገራት መካከል ለ20 ዓመታት እንዲዘልቅ ታሳቢ ተደርጎ የተከናወነው የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር የአጋርነት ስምምነት በዋናነት የሰብኣዊ መብቶች፣ የዲሞክራሲና የአስተዳደር፣ የሰላምና ደኅንነት፣ የሰብኣዊና ማኅበራዊ ልማት፣ አካታች የሆነ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ፣ እና የሰዎች ፍልሠትና የመዘዋወር ጉዳዮች ላይ በጋራ መርኅና የየሀገራቱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ተፈፃሚ እንደሚሆን የሰምምነት ሰነዱ ያትታል፡፡ 

በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ በትብብርና በአጋርነት ለመስራት የሚያስችል ሕጋዊ የስምምነት ማዕቀፍ መኖሩ መልካም ቢሆንም የስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮችና ነጥቦች ሲፈተሹ ግን ከየሃይማኖታችን ሕግጋትና አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የሚቃረኑ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች የያዘ ሰነድ በመሆኑና በዚህም ምክንያት በህዝባችን ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤን፣ መረበሽንና ስጋትን እንደፈጠረ በማጤን እና ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስፈላጊውን ማጣራት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ 

በዚህም መሠረት የትብብርና የአጋርነት ስምምነቱ በውስጡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሃይማኖትና የባህል እሴቶች ጋር የሚፃረሩ ጽንስ ሀሳቦችና ትርጉሞች ያላቸውን ይዘቶች ያካተተ ስለመሆኑና ይህም በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መድረኮችም ጭምር የሚታወቁ ሐረጎችንና አንቀፆችን እንደያዘ ጉባኤው ካገኘው መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል:: ለአብነት ያህል፡- 

ሀ) በስምምነቱ አንቀፅ 36.2 ላይ የተጠቀሰው “የወሲብና የተዋልዶ ጤናና መብቶች” (“Sexual and Reproductive Health and Rights”) የሚለው ሐረግ በቀጥታ ከግብረሰዶም መብቶች፣ ከፆታ መቀየር፣ ከውርጃ፣ ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርትና ግልሙትናን ሕጋዊ ከማድረግ ጋራ በቀጥታ የተያያዘ መሆኑ በአውሮፓ ፓርላማና በዓለም የጤና ድርጅት የመረጃ ምንጮች ላይ በግልፅ መቀመጡ ፣

ለ) በስምምነቱ የአፍሪካ ፕሮቶኮል አንቀፅ 40.6 ላይ በአህጉሪቱ ለሚገኙ ልጆችና ታዳጊዎች ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርት (Comprehensive Sexuality Education) የተባለ እጅግ አደገኛ ኢግብረገባዊና ልቅ የወሲብ ትምህርት እንዲማሩ አስገዳጅ መሆኑ ለዚህም በዩኔስኮ የተዘጋጀውና እጅግ አደገኛ ይዘት እንዳለው የተረጋገጠው መተግበርያ “International Technical Guidance on Sexuality Education” በስም ተጠቅሶ መቀመጡ ፣

ሐ) ይህም “ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርት” በሚል የሚታወቀውና በዚህ ስምምነት ውስጥ “Comprehensive Sexual and Reproductive Health Information and Education” የሚል ስያሜን ይዞ የሚገኘው  ዕድሜንና ባህልና ያማከለ እንደሆነ  የሚነገርለት ኢግብረገባዊ የትምህርት ዓይነት  በዓለማችን በበርካታ ሃገራት ተተግብሮ በታዳጊዎችና በወጣቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሞራል ውድቀትንና ወሲባዊ ልቅነትን ማስከተሉ በብዙ ሳይንሳዊ ምርምሮች የተረጋገጠና በተለይም በአፍሪካ ካሁን በፊት በተተገበረባቸው ሃገራት 84% ጊዜ ውድቀት ያስከተለ መሆኑ መረጋገጡ 

መ) በዚህ ደረጃ ያለ ዓለም አቀፋዊ ስምምነትን የያዘው ዶኩመንት በውስጡ የቃላት መፍቻ (Glossary) አለመካተቱ, እንዲሁም ሃገራት ያለተስማሙባቸውን አንቀፆች የሚቃወሙባቸው ዕድሎች (reservation clause or interpretive declaration) ሆን ተብለው እንዲወጡ ወይም እንዳይኖሩ መደረጋቸው፤

ሠ) በስምምነቱ አንቀፅ 40. 6 ውስጥ እንደተመለከተው ሀገራችንን ካሁን በፊት ተካሂደው በነበሩና ገና ወደፊት በሚካሄዱ ውጤታቸውም በማይታወቅ ዓለም አቀፍ ሰብሰባዎች የሚወጡ አደገኛ ይዘት ያላቸው የጋራ መግለጫዎችን    እንዲህ በሚሉ አንቀጾች (“The Parties shall commit to the full and effective implementation of the Beijing Declaration and Platform for Action and the Programme of Action of the International Conference on Population and Development and the outcome documents of their review conferences.”) ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ ውስጥ የሚያስገባት መሆኑ እየታወቀ መፈረሙ፣

ረ) እንዲሁም ኢትዮጵያ ፈራሚ ባልሆነችባቸው አካባቢያዊና አህጉራዊ ስምምነቶች አካል የሚያደርጋት መሆኑና የሀገር ሉዓላዊነትን በግልፅ ተቀምጦ እያለ የተፈረመ መሆኑ፣

ሰ) የፆታ ትንኮሳን (gender based violence) ማስቀረት በሚል በጣም አሻሚ የሆኑ ግብረሰዶማዊ አስተሳሰቦችን ለማስረፅ እንዲረዳው በሰነዱ በበርካታ ክፍሎች ውስጥ “አካታች” (“inclusive”) በሚሉ ቃላት ተሸፍኖ እንዲገባ የተደረገ መሆኑ፣

ሸ) በተጨማሪም በበርካታ ሥፍራዎች የተጠቀሰው “Gender” የሚለው ቃል ወንድና ሴት ተብሎ እንደሚተረጎም በስምምነቱ በግልጽ ባለመቀመጡ ይልቁንም በርካታ ጾታዎች እንዳሉ በማስመሰል ሀገራትን የሚያደናግሩባቸው እንደ (sexual orientation አና gender identity)ን የመሳስሉ ግብረሰዶማዊ አስተሳሰቦችን የያዙ ዶክመንቶች በስም ተጠቅሰው በስምምነቱ ውስጥ መካተታቸው፣

ቀ) ስምምነቱ የወላጆችን መብት የሚጥስና የኢትዮጵያዊ ቤተሰብ እሴቶችን አደጋ ላይ የሚጥሉ አንቀፆችን የያዘ ስለመሆኑ በሰነዱ ላይ ከተደረገ የኤክስፐርቶች ጥልቅ ጥናት ተረድተናል፡፡

በአጠቃላይ ይህ አዲስ የአጋርነት ስምምነት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡና ትውልድንና ብሎም ሀገርን እጅግ የሚጎዱ በርካታ አንቀጾች የተካተቱበት በመሆኑ ለሀገራችን ህዝብ ዕድገትን ሳይሆን ውድቀትንና ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠትን የሚያስከትል የሀገራችንንም ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በሚገባ ተረድተናል፡፡ ስለሆነም እኛ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የአጋርነት ስምምነቱ አስገዳጅና አሳሪ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ከመሆኑ አንፃር መንግስት ከዚህ በታች ያቀረብናቸውን ምክሮችና ተግሳፆችን በመቀበል የሀገርን ሉዓላዊነትና ትውልድን የመጠበቅ ሕጋዊ፣ ሞራላዊና ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ከታላቅ አባታዊ አደራ ጋር በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡

1. መንግስት የአዲሱን የሳሞአ የንግድና የኢኮኖሚ የአጋርነት ስምምነትን በርካታ ጎጂ ጎኖች እንዳሉት በማመን ከዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ ራሷን እንድታገልል በማድረግ መንግስታዊ ኃላፊነቱንና አደራውን በተግባር እንዲወጣ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

2. የሀገሪቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካል የሆነው የተከበረው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በሥሩ ያሉ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የስምምነት ሰነዱ ውስጥ በዝርዝር የቀረቡትን በተለይም ከሰብኣዊ መብቶች፣ ከወሲባዊና የተዋልዶ ጤናና መብቶች፣ ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርት፣ አካታችነት እና መሰል በሰነዱ የተካተቱ አንቀጾች ወይም ይዘቶች ከግብረሰዶማዊነትና ጾታን ከመቀየር እንዲሁም ከልቅ ወሲብና ከውርጃ ጋራ በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው ጽንሰ ሃሳቦች መሆናቸውን በመረዳት ይህንን እጅግ አደገኛ ስምምነት ባለማጽደቅ ህዝባዊና ታሪካዊ አደራውን እንዲወጣ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

3. መንግስታችን ከህዝብ አደራን ተቀብሎ ሀገርን የሚያስተዳድር እንደመሆኑ ከዚህ በኋላ በሚያደርጋቸው ተመሳሳይ የትብብር ስምምነቶች ከላይ የዘረዘርናቸውን ዓይነት የሀገራችንን ኃይማኖት፣ባሕልና ነባር እሴቶችን የሚንዱ ጽንሰሃሳቦችን ያዘሉ አሳሳች ሀረጎች ያሉባቸውን ስምምነቶች ፈጽሞ እንዳይፈርም እያሳሰብን፣ ስምምነቶችንም ለመፈራረም በሚደረጉ ድርድሮች ወቅትም የሚፈርማቸው ዶክመንቶች ውስጥ የምንወዳት ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደሀገር የማትስማማባቸውን ወይም የማትቀበላቸውን አንቀጾች የምትቃወምበት (reservation clause or interpretive declaration) ዕድልና መብት  እንዲኖራት ሊሠራ እንደሚገባ በአጽንኦት እንመክራለን፡፡

በመጨረሻም የአጋርነት ስምምነቱ ማዕቀፍ ውስጥ በሰብኣዊ መብት፣ በንግድና የኢኮኖሚ ትብብር ሽፋን ከሃይማኖታችን መሠረታዊ አስተምህሮ የወጡና የሀገራችንን ባሕልና ነባር እሴቶችን የሚንዱ ጸያፍ ልምምዶች ቀጥተኛ ባልሆነ አግባብ በሰነዱ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን ተገንዝበናል፡፡ ስለሆነም በየትኛውም ሁኔታና አግባብ የሰነዱ ዋናና ዝርዝር አንቀጾች ወይም ይዘቶች ትርጓሜ ከሃይማኖቶቻችን መሠረታዊ አስተምህሮ፣ ከዶግማዊና ቀኖናዊ ጉዳዮች ጋር የሚቃረኑና  የማይስማሙ ወይም ተቀባይነት የሌላቸው አንቀጾች ወይም ይዘቶች/ሀሳቦች በሀገራችን ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታና ደረጃ በምንም መልኩ ፍፁም ተፈፃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ ከወዲሁ በአጽንኦት እያስገነዘብን 98% የሚሆነውን ህዝባችንን እንደመወከላችን ይህን ቁርጠኝነታችንን የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ምዕራባውያኑ ሀገራት እና የአፍሪካ ኅብረት ከወዲሁ እንዲገነዘቡ በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡

ኢኦተቤክ

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

 

 

 

Filed in: Amharic