ሰቀሉት
ኢየሱስ በቍሰለ ትከሻው መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ አድካሚ ጉዞ ጀመረ። ከእርሱ ጋር የሚሰቀሉ ሁለት ክፉ አድራጊዎች ነበሩ። የቤተ መቅደስ ካህናት የተረገመ ሆኖ ስላገኙት ከኢየሩሳሌም አወጡት። የኃጢአት መስዋዕት በግ ከከተማ መውጣት ነበረበት። ዘሌ.16:27
የኃጢአት መስዋዕት የሆነው ክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወጣ። ከዚያ ጀምሮ ከተማዋ ክብሯን አጥታለች በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ተተካች። ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.13:12
በጣም ደክሞ ስለነበር በመንገድ ይሞታል ብለው ስለፈሩ ጠላቶቻቸው የቀሬና (ሊቢያ) ሰው ስምዖንን በማስገደድ መስቀል አሸከሙት። መታደል እንዲህ ነው። ለአይሁድ ፋሲካ በዓል የሄደ ስምዖን ብቸኛ መስቀል ተሸካሚ የክርስቶስ ስቃይ ተካፋይ ሆነ። አንደኛ ክብር አገኘ። ማር.15:21
ስምዖን በጉዞው መስቀልን ተሸክሞ ሲሄድ ጌታ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል ነው ያለውን ተረዳ። የዚኽ ሰው ስምዖን ሁለት ልጆች የቤተ ክርስቲያን ዐምዶች እንደ ነበሩ ቅዱስ ጳውሎስ ጠቅሷል።
ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ብዙ ሴቶች ተከትለውታል። በመስቀል አጠገብ አራት ሴቶች ከሐዋርያት አንድ ብቻ ይገኛሉ። ከስቅለቱ ሳምንት ቀድሞ “ሆሳዕና” ብለው የጮኹ ሰዎች “ስቀለው” እያሉ ጮዂ። ዮሐ.16:43 ሴቶች ግን አለቀሱለት ። ጌታ ግን ለእርሱ ሳይሆን ለኢየሩሳሌም ጥፋት እንዲያለቅሱ አሳሰባቸው። ጌታችንን በዚኽ ቀን የሕማማትን ስብከት ጀመረ። የራሱን መከራ ረስቶ ስለ ሰዎች አሰበ። የሌሎችን እንባ የሚጠርግ እርሱ የሌሎችን እንባ አያስፈልገውም።
ሴቶች ያለቀሱለት ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን መስዋዕት የሚሆን ካህን ነው። እርሱን ለሚያምኑ ሰዎች በእርሱ ቁስል ይፈወሳሉ። እንባ ለእርሱ አያስፈልገውም።
ወደ ስቅለት ቦታ ሲደርሱ የኢየሱስ ክርስቶስን ልብስ ገፈፉት። የአዳምን በኃጢአት የተገፈፈ ጸጋውን ይመልስ ዘንድ። ልብሱ ተጣብቆበት የነበረ አካሉ እንደገና ቆሰለ። የክሱ ጽሑፍ በሦስት ቋንቋ ተዘጋጅቶ በመስቀሉ አናት አኖሩት። የጌታችን ንጉሥነት በጊዜው በታወቁ በሦስት ቋንቋዎች ታወጀ። እብራይስጥ የኢየሩሳሌም አይሁዶች ይናገሩታል፣ ሮማይስጥ የገዢዎቻቸው ሮማውያን ቋንቋ ሲሆን የሥራ ቋንቋ ነበር። ግሪክኛ የወቅቱ የአሕዛብ ቋንቋ በገሊላ በስፋት ይነገር ነበር። ዮሐ.19:20
ጲላጦስ የጻፈውን እንዲለውጥ ተጠየቀ። “የጻፍኩትን ጻፍኩ” አለ። ተገዶ እውነትን ጻፈ። ለጊዜው ዙፋኑ መስቀሉ ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥነት አዋጅ ሆኖ ቀረ። ልብሱ ተገፎ በራቁትነት የሁሉም ሆነ። የጠፋውን የአዳም ልጅ የፈለጉ እግሮቹ በምስማር ታሰሩ። ትንቢቱ ሁሉ ፍጻሜ እያገኘ መጣ። ቅዱስ ዳዊት “እጆቼና እግሮቼን ቸነከሩኝ” ያለው ተፈጸመ። ቅዱስ ዳዊት ምስማርና መዶሻ በጌታ ሕይወት ያላቸውን ድርሻ አንስቶ ነበር። መዝ.22:12
ስቅለት በጣም ስቃይ ያለበት በመሆኑ በስሜት የሚያደነዝዝ መጠጥ ልማድ ነበርና ጌታ ግን አልተቀበለውም አስታራቂነቱን የሚፈጽመው ሥቃዩን በሙሉ በመቀበል ነውና። ማር.15:23
በተወለደ ጊዜ እናቱ ድንግል ማርያም የሞቱን ምልክት ከርቤ ከጥበብ ሰዎች ተቀብላ ነበር። በሞቱ ጊዜ ግን የሚያደነዝዘውን ሐሞት አልተቀበለም። ጎርጎጭ አድርጎ ተወው። ከዚያ ይልቅ አባቱ የሰጠውን ጽዋ እንደሚጠጣ ለጴጥሮስ አስረድቶት ነበር። ዮሐ.18:11
በመስቀል ላይ ወጣ። ፈሪዎች በሩቅ ቆመዋል። እርሱን የሰቀሉት በልብሱ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። በዚኽም ሌላ ትንቢት ተፈጸመ። በመስቀል አጠገብ ዮሐንስ ተገኘ። መግደላዊት ማርያምና እናቱ ቅድስት ማርያም ቆመዋል። ዮሐ.19:25
ሆምጣጣ ሐሞት አጠጡት
ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ አለ። አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ጌታችን ሆምጣጤ መጠጣቱን መዝግበዋል (ማቴ 27፥48 ማር 15፥36 ሉቃ 23፥36
ነቢዩ ዳዊት ለጌታችን ሆምጣጤ እንደሚሰጡት “ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ” መዝ 68፥21 ብሎ ተንብዮ ነበር። በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት። ማቴ 27፥34
ሐሞት፡- መራራ ነው። ጌታን ግምት ያጠጡት ሕመም ማስታገሻ እንዲሆን ነው። የሐሞት ምረት እንደ እሬት ስለሆነ ከእሬት ጋር ይነገራል “ሐሞትና እሬት የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ።ዘዳ 29፥18፣ ፍሬያቸው ሐሞት ነው ዘለላውም መራራ ነው። ዘዳ 32፥32 “መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ። ሰቆ.ኤር. 3፥19 “ፍርድን ወደ ሐሞት የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት የለወጣችሁ” አሞ 6፥12-13 እንዲል።
እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በኃጢአታቸው ሊቀጣቸው ስለ ፈለገ “እነሆ” ይህን ሕዝብ እሬትን አበለዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ። ኤር 9፥15፡23፥15 ብሎ ተናግሮ ነበር።
ሆምጣጤ- ሰሎሞን ሆምጣጤ ጥርስን እንደሚጎዳ ይናገራል። ምሳ 10፥26 ጌታችን የሐሞትን ውኃና ሆምጣጤውን ከተቀበለና ከጠጣ በኋላ ተፈጸመ የሚል ቃል ተናግሮአል። በነቢይ የተነገረው ትንቢታዊ ቃል ተፈጸመ ማለቱ ነው።
“ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ”አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱን፣ ነፍሱን ከሥጋው መለየቱን መዝግበዋል። ማቴ 27፥50 ማር 15፥37 ሉቃስም ከሦስቱ ለየት ባለ ሁኔታ “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ማለቱን መዝግቦአል ሉቃ 23፥46
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላካዊ ሥልጣኑ ነፍሱን ከሥጋው እንደሚለያት “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና” እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም” ዮሐ 10፥17:18 ብሎ ነበር። አሁንም በሥልጣኑ ነፍሱን ከሥጋው ለያት እንጂ ማንም አልወሰዳትም። “አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ማለቱ፡- የእኛ ነፍስ ከሥጋችን ስትለይ በእግዚአብሔር እጅ የምትያዝ መሆንዋን ለመግለጽ ነው። ሥጋችን ወደ መቃብር ሲወርድ ነፍሳችን ወደ እግዚአብሔር እንደምትሄድ ሲነግረን ነው።
@ትርጓሜ ዮሐንስ
@ መምህር ንዋይ ካሳሁን