>

‹‹የዛን ዕለት ማታ የሚገድሉኝ መስሎኝ ነበር›› ኦሞት አጉዋ

Amot Aguwo Ethiopia Human Rights project

መጋቢት 6/2007 ዓ.ም ከቀኑ 7፡10 ላይ ወደ ኬንያ ለመብረር ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሼ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ሌሎች ለተመሳሳይ ጉዞ አብረውኝ ነበሩ፡፡ ትኬቴን እና ሌሎች ‹ፕሮሰሶችን› እያስጨረስኩ እያለሁ ወደ ሰባት የሚሆኑ የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች ድንገት አጠገቤ ደርሰው እንደሚፈልጉኝ ነገሩኝ፡፡ ደንገጥ ብዬ ‹‹ምነው በሰላም ነው?›› ስላቸው ‹‹ሁላችሁንም ለጥያቄ ስለምንፈልጋችሁ አንዴ ወደ ውጭ መውጣት አለብን፣ አሁንኑ!›› አለ ከመካከላቸው አንዱ፡፡

አንድ ወዳጄ ወደውጭ ልሄድ መሆኑን ያውቅ ነበርና እሱ ጋር ደውየ እየሆነ ያለውን ነገር ለማሳወቅ ስልክ ስነካካ ከእጄ ላይ መንጭቀው ቀሙኝ፡፡ አስከትለው ኪሴ ውስጥ ያለውን ብር ሁሉ ሳይቀር ፈትሸው ወሰዱ፤ የምወስደው መድሃኒት ነበር፣ እሱንም ወሰዱብኝ፡፡ ፓስፖርቴንም ቀሙኝ፡፡ ምን እያደረጉ እንደሆነ አልገባኝም፤ ብጠይቅም ከግልምጫና ግፍተራ በቀር መልስ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ግቢ ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ሰብስበው አግተውን ቆዩ፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ የደም ግፊት በሽታ እንዳለብኝ በመጥቀስ መድሃኒት እንድወስድ ጠየቅሁ፡፡ ግን የሚሰማኝ አላገኘሁም፡፡

ጥቂት እንደቆየን የፌደራል ፖሊስ መኪኖች እኛ ወዳለንበት መጡ፡፡ ወዲያው ‹‹ዳይ ቀጥሉ! ግቡ መኪና ውስጥ!›› እያሉ አጣደፉን፡፡ ሲገፈታትሩኝ ጊዜ ‹‹እኔ ግፊት አለብኝ፤ አትንኩኝ፣ ያመኛል!›› አልኳቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ተሳለቁብኝ፤ ‹‹ለመሆኑ አንተ በእውነት ኢትዮጵያዊ ነህ?›› ሲለኝ አንደኛው ከመካከላቸው፣ በጣም ተሰማኝ፤ አንቀጠቀጠኝ፡፡ ከእሱ ብሶ የእኔን ዜግነት ጥያቄ ውስጥ ሲያስገባው በጣም ከነከነኝ፡፡ በአማርኛ እያወራሁት፣ ከሀገሬ ልጆች ጋር በተገኘሁበት ‹‹በእውነት አንተ ኢትዮጵያዊ ነህ›› ብሎ ሲጠይቅ እኔ ለእሱ አፈርኩ፡፡
እየገፈታተሩ መኪና ውስጥ ካስገቡን በኋላ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ነበር የወሰዱን፡፡ ማዕከላዊ እንደደረስን ትንሽ ግቢው ውስጥ አቆይተው እኔን ተከራይቼ እኖርበት ወደነበረው ቤት ወሰዱኝ፡፡ ቤቴን ፈተሹ፤ ያገኙትን ላፕቶፖች ወሰዱ፡፡ ስድባቸው ይገርማል፤ ብዙዎችን በእድሜ እበልጣቸዋለሁ፡፡ ግን እኔን ለመስደብ አያመነቱም፣ ሰው በሰውነቱ እንኳ መከበር ነበረበት፡፡ ቤቴ ተፈትሾ ሲያበቃ ወረቀቶች ላይ እንድፈርም አድርገውኝ ወደ ማዕከላዊ መለሱኝ፡፡

ማዕከላዊ የገባሁ እለት ሳይቤሪያ የሚባል ቤት ነበር ያስገቡኝ፡፡ ቤት ውስጥ እንዳስገቡኝ እዚያ ቀድመው ገብተው የነበሩ ሰዎች ‹‹አይዞህ! አይዞህ!›› እያሉ አበረታቱኝ፡፡ ፍቅራቸው ደስ አለኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ ምግብ አልበላሁም፡፡ በዚያ ላይ በሽተኛ ነኝ፡፡ መድሃኒቴን ስጡኝ ብላቸውም እምቢ ብለውኛል፡፡ የዛን ዕለት ማታ የሚገድሉኝ መስሎኝ ነበር፡፡ በቀጥታ ባይገድሉኝ እንኳ መድሃኒቱን የከለከሉኝ እኔን ለመግደል እንደሆነ ነበር የገባኝ፡፡ በጣም ፈታኝ ጊዜ ነበር፤ ለተከታታይ ቀናት እንቅልፍ አልወሰደኝም፡፡

ከወርልድ ባንክ፣ ከኤምባሲዎች እና ከሌሎችም ህጋዊ አካላት ጋር በጋንቤላ የማስተርጎም ስራ እሰራ ነበር፡፡ ይሄን ስራየን መንግስት እንደማይወድልኝ ብገነዘብም እታሰራለሁ ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ታስሬም አላውቅም፡፡ አሁን በሽብር ሲከሱኝ ለእኔም በጣም ይገርመኛል፡፡

(ማስታወሻ፡- ኦሞት አጉዋ አክቲቪስት (በተለይ በጋንቤላ ስላለው የመሬት ንጥቂያ እና የመንደር ማሰባሰብ ላይ በማተኮር እየሰሩ ነበር) ሲሆኑ እስከተያዙበት ጊዜ ድረስ በ Development Studies ትምህርት መስክ የማስተርስ ዲግሪያቸውን እየሰሩ ነበር፡፡ ኦሞት የፕሮቴስታን ቄስም ናቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስንም በአኙዋክኛ እየተረጎሙ እንደነበር ነግረውናል፡፡ አሁን የቀረበባቸው ክስ ሽብር እንደሆነ እናስታውሳለን፡፡)

ምንጭ:-  Ethiopia Human Rights Project

Filed in: Amharic