በዘ–ህወሀት የተወገዘችው ኢትጵጵያ
ባለፈው ሳምንት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተባለ የሚጠራው አዲስ ስምምነት የተፈረመበት የብዕር ቀለም ሳይደርቅ የግብጽ ፕሬዚዳንት ጀኔራል አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ በአንድ ብሄራዊ የእርሻ ፕሮጀክት የምረቃ ስነስርዓት በዓል ላይ በመገኘት ለግብጽ ህዝብ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፣ “ውኃ የህይወት ወይም የሞት ጉዳይ መሆኑን እና ይህም የግብጽ ህዝብ ጭንቀት መሆኑን ሙሉ በሙሉ እገነዘባለሁ፡፡ እነርሱም መኖር እንደሚፈልጉ ሁሉ እኛም መኖር እንደምንፈልግ ከወንድሞቻችን ከኢትዮጵያውያን ጋር ስምምነት አድርገናል፡፡ ከዚህ ቀደምም በተሳሳተው መንገድ አልመራኋችሁም፣ አሁንም በተሳሳተው መንገድ አልመራችሁም፡፡“
ይኸ ነገር የጦርነት ወይስ የሰላም ንግግር ነው?
“ውኃ የህወይት እና የሞት ጉዳይ ነው?“ “እኛ ለመኖር እንደምንፈልግ ሁሉ እነርሱም ለመኖር ይፈልጋሉን? “አሁንም በተሳሳተው መንገድ አልመራችሁም?“
ጀኔራሎች (የሲቪል ልብስ ለብሰውም እንኳ ቢሆን) ስለህይወት እና ሞት እንዲሁም ስለመኖር እና በተሳሳተው መንገድ አልመራችሁም የሚል ንግግር ሲያደርጉ መስማት በእርግጠኝነት እኔን ያሳስበኛል፡፡ የወገናዊነት ስሜት አጥቅቶኝ ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ግን ጀኔራሎች ህዝቦቻቸውን በተሳሳተው መንገድ አንመራም ሲሉ ምክንያቱም አንድ መንገድ ብቻ ስለሚያውቁ ነው፡፡ የጦርነት መንገድ! ከጀኔራሎች የሚመጣ እንደዚህ አይነቱ ንግግር በእርግጠኝነት እጅግ በጣም እንድጨነቅ ያደርገኛል፡፡ በጣም ስሜታዊ ሆኘ ነውን?
ጀኔራሎች አብዛኛውን ጊዜ በመንታ ምላሳቸው ነው ንግግር የሚያደርጉት፡፡ ግልጽ በሆነ መልኩ ወደ አደባባይ በመውጣት “ይህንን ወይም ደግሞ ያንን በቦምብ እናጋያለን“ የሚል መልዕክት አያስተላልፉም፡፡ ስለአየር ጥቃት ዘመቻ ኢላማዎቻቸው ነው ንግግር የሚያደርጉት፡፡ ጀኔራሎች ሰዎችን በመያዝ ስለሚያደርጉት ማሰቃየት አይናገሩም፡፡ ስለአስገዳጅ ቃለ መጠይቆቻቸው ነው የሚናገሩት፡፡ በወገን ላይ ስለደረሰ ጉዳት ወይም ደግሞ ከጠላት ስለተተኮሰ ጥይት ይናገራሉ፣ ገድለናል ብለው በፍጹም አይናገሩም፡፡ ጀኔራሎች ስለፈጣን ወታደራዊ ጥቃት ይናገራሉ፣ ሆኖም ግን ስለእልቂት እና ሽብር አይናገሩም፡፡
ኤል ሲሲ ግለጽ የሆኑ እና ቀላል ቃላትን የተናገሩ አይመስልም፡፡ ለእኔ በጣም ጥልቅ የሆነ ንግግር ያደረጉ እንደሆኑ ነው የተሰማኝ፡፡ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት ምን ማለታቸው ነው?
እርግጠኛ ለመሆን ኤል ሲሲ ለግብጽ ህዝብ በእርግጠኝነት ያስተላለፉት መልዕክት ምንድን ነው?
ኤል ሲሲ ለግብጽ ህዝብ የዓባይ ውኃ የሞት እና የህይወት ጉዳይ ነው ብለው ሲናገሩ አሁን በስልጣን እርካብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለሚገኘው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) በእርግጠኝነት ምን ዓይነት መልዕክት እያስተላለፉ ነው?
ኤል ሲሲ “እነርሱም ለመኖር እንደሚፈልጉ ሁሉ እኛም ለመኖር እንፈልጋለን፣” ሲሉ እኛ የማንኖር ከሆነ እነርሱም አይኖሩም ለማለት ነው?
“ለኢትዮጵያውያን ወንድሞች” መልዕክት ሲያስተላልፉ በእርግጠኝነት ምን እየተናገሩ ነው?!
ለቀጣናው ጎረቤቶች ምን መልዕክት እያስተላለፉ ነው? ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ ኃያላን ምን እየተናገሩ ነው?
ኤል ሲሲ በአሁኑ ጊዜ እና ወደፊትም ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደሚያውቁ እና የግብጽ ህዝብ መጨነቅ እንደሌለበት መልዕክት እያስተላለፉ ነውን? ጭንቀቱስ ምንድን ነው?
የኤል ሲሲ አደጋን ያረገዙት ወታደራዊ ትችቶች ለእኔ አስጊዎች እና በቀጣይነት በሀገራችን ላይ አደጋን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በማሰብ የጄኔራሉን ስትራቴጂያዊ ዓላማ እና ብቃት ጥልቅ በሆነ መንገድ እንድመረምር አስገድዶኛል፡፡
ኤል ሲሲ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተባለ የሚጠራው ግድብ ሊገነባ የሚችለው ዓባይ ወደ በረዶ ክምርነት ሲቀየር እና ሰይጣን በበረዶው ክምር ላይ የሸርተቴ ጨዋታ መጫወት በሚጀምርበት ጊዜ ነው እያሉ የሚናገሩትን እሰማለሁ፡፡
ለመንደርደርያ ያህል አንዳንድ ነገሮችን ግልጥ ላድርግ፡፡
በመጀመሪያ በተለያየ መልኩ ከሰብአዊ መብት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሁኔታ ከፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ጋር አልስማማም፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በግብጽ ተከስቶ በነበረው ህዝባዊ አመጽ ምክንያት ተገኝቶ የነበረው የሰብአዊ መብት አጠባበቅ እንደገና እየተቀለበሰ ነው ከሚለው የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ከሂዩማን ራይትስ ዎች ግምገማ ጋር እስማማለሁ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኤል ሲሲ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 እራሱን የኢራቅ እና የሌባነን እስላማዊ መንግስት/Islamic State of Iran and Levant (ISIL) እና ከዚህም በተጨማሪ የኢራቅ እና የሶርያ እስላማዊ መንግስት እያለ በሚጠራው አረመኔ እና አሸባሪ ወሮበላ ድርጅት የ30 ወጣት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በመሆናቸው ምክንያት አንገት በተቀላ ጊዜ ኤል ሲሲ ፈጣን በሆነ መልኩ ወደ አደባባይ በመውጣት በግብጽ ህዝብ ስም በሊቢያ አሰቃቂ በሆነ መልኩ አንገታቸውን በተቀሉት ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ነበር፡፡
ኤል ሲሲ ከዚያ እልቂት የተረፉትን ኢትዮጵያውያን አንገት ከመቀላት ለመታደግ እና በሰላማዊ መንገድ በቻርተርድ አውሮፕላን ወደ ግብጽ ለማምጣት የግብጽ ወታደሮችን ወደ ሊቢያ የላኩ ሰው ነበሩ፡፡
የዘ-ህወሀት መሪዎች ኢትዮጵያውያን በሊቢያ ውስጥ አንገታቸውን መቀላታቸውን በሰሙ ጊዜ ያንን የመሰለ ኢሰብአዊ ድርጊት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ኢትዮጵያውያውን እንዲያውቁት እንኳ ይፋ አላደረጉም፣ ለድርጊቱም እውቅና አልሰጡም ነበር፡፡
በወቅቱ የዘ-ህወሀት አፈቀላጤ የነበረው ሬድዋን ሁሴን እንዲህ ብሎ ነበር፣ “አይሲስ የኢትዮጵያውያንን አንገት እየቀላ ገድሏል እየተባለ በስፋት ሲዘገብ ይደመጣል፡፡ የጥቃት ሰለባዎቹ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው መንግስት የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ጉዳዩን በማጣራት ላይ ይገኛል“ ነበር ያለው፡፡
ዘ-ህወሀት ለዚያ አሰቃቂ እልቂት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በኃይል የለሾች እና በረዳት አልባዎች ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን እልቂት ጣቶቹን እያጣመረ እና እራሱን እያከከ ከዳር ቆሞ ሲመለከት በነበረበት ጊዜ ኤል ሲሲ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ታድገዋል፡፡
ኤል ሲሲ ከሞት አደጋ በመዳን ወደ ካይሮ ለመጡ ኢትዮጵያውያን በካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው በክብር በመቀበል አንድ በአንድ እጆቻቸውን እየጨበጡ ሰላምታ በመስጠት የማጠናከሪያ ቃላት ተናግረዋል፡፡ በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ አንድም የዘ-ህወሀት ተወካይ አልታየም፡፡
ጥቂት ሰዎች ኤል ሲሲ የህዝብ ግንኙነት ስራ ጥቅም ዕድሎችን ከሚፈለገው በላይ ተጠቅመውበታል በማለት ሀሳብ ሊሰነዝሩ ይችላሉ፡፡
የእኔ መልስ ግን ቀላል እና እንዲህ የሚል ነው፡ “እየሰመጠ ያለ ሰው ማን ገመድ እንዳቀበለው ደንታው አይደለም! እንደዚሁም ሁሉ አንገቱን የመቀላት መጥፎ አጋጣሚ ባጋጠመው ጊዜ ህይወቱን ማን እንዳዳነው ወይም ደግሞ ህይወቱ በምን ምክንያት ከአደጋው እንደተረፈ ጉዳዩ አይደለም!“
ቀላሉ እውነታ ግን ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ወጣት ኢትዮጵያውያንን ከሞት አደጋ ለማዳን ትዕዛዝ ሰጥተዋል ምክንያቱም እርሳቸው ይህንን ፈልገዋል፣ ምክንያቱም ያንን ማድረግ ችለዋልና፣ ምክንያቱም ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ነው የሚል እምነት ነበራቸውና፣ ምክንያቱም ይኸ ጉዳይ በኢትዮጵያውያን እና በግብጻውያን መካከል መልካም ወንዳማማችነትን እና እህትማማችነትን ይመሰርታል ብለው ያምኑ ነበርና፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እንደ ክርስቲያን እና እንደ ሰብአዊ ፍጡር ፍትሀዊ በሆነ መልክ እና ክብራቸው ተጠብቆ መስተናገድ አለባቸው የሚል እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ድፍረት በተመላበት እና ፈጣን በሆነ መልኩ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ በሊቢያ ውስጥ ታፍነው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት በመታደግ በሁለቱ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ሀገሮች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን ወዳጅነት እና እህትማማችነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ አድርገዋል፡፡
ይህን ከዚህ በላይ ያልኩት የምቀጠለዉን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ኤል ሲሲ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ ይመኛሉ ብዬ አላስብም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ለማካሄድ ይፈልጋሉ ብዬ አላስብም፡፡ ኤል ሲሲ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እየተባለ ከሚጠራው የግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰቱትን በርካታ ችግሮች ዴፕሎማሲያዊ በሆነ መልኩ እና ብቃት ባለው ቴክኒካዊ አካሄድ ይፈቱታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኤል ሲሲ ለችግሮቹ ሁሉ ከዘ-ህወሀት ጋር ምክንያታዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በመወያየት ፍትሀዊ መፍትሄ ለመስጠት ይሞክራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኤል ሲሲ ከዘ-ህወሀት ጋር የሚያደርጓቸው ዴፕሎማሲያዊ ጥረቶች በእብሪተኞቹ በዘ-ህወሀት መሪዎች ሰንካላ እና የድንቁርና አካሄድ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ይከሽፋል ብዬ አምናለሁ ፡፡
ችግሩ የፈለገውን ያህል ገፍቶ ቢመጣ እና በዓባይ የውኃ ፍሰት ላይ በሚመጣ የውኃ እጥረት ምክንያት በግብጽ ላይ ችግር ቢከሰት ኤል ሲሲ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተባለ የሚጠራው ግድብ ጉዳት እንዳያደርስባቸው ወይም ደግሞ የግብጻውያንን የእርሻ መሬቶች፣ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ምርቶችን እና በየጊዜው እያደገ የመጣውን የግብጽን ህዝብ ለመመገብ የሚያስችሉትን የወደፊት የእርሻ መሬቶች ተግባራት በድርቀት የሚያስፈራራቸው ከሆነ የወታደራዊ አማራጭ እንጅ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው አምናሁ፡፡
የእኔ አስተያየት ከአዲሱ ስምምነት በኋላ ኤል ሲሲ ያሉት ነገር ከስልታዊ ዓላማ እና ብቃት እኳያ እና ከታሪካዊ ትስስር አንጻር ሲባል እንደገና ጥልቅ በሆነ መልኩ መመርመር አለበት፡፡
በሌላ አገላለጽ ወደፊት ለመጓዝ ግልጽ በሆነ እና በማያሻማ መልኩ መመለስ ያለባቸው ሁለት ጥያቄዎች ብቻ አሉ፡፡ እነርሱም፡
1ኛ) ውኃን በተመለከተ 97 በመቶ የሚሆነው የግብጽ ህዝብ የውኃ ምንጭ የሚገኘው ከዓባይ ወንዝ ስለሆነ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ እጥረት እና ችግር ቢፈጠር ኤል ሲሲ ጦርነትን በማስወገድ ወይም ደግሞ ከማናቸውም ወታደራዊ እርምጃ በመከላከል ጎልተው የወጡትን ችግሮች እና ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ በዴፕሎማሲያዊ መንገድ ላይ ብቻ በመመስረት ሊፈቱት ይችላሉን?
2ኛ) ኤል ሲሲ በአሁኑ ጊዜ ወይም ደግሞ ወደፊት በመካከለኛ ጊዜ የውኃው ፍሰት ቀድሞ በነበረው ሁኔታ ያለምንም ችግር ወደ ግብጽ በእርግጠኝነት መፍሰስ እንዲችል ሊያደርግ የሚያስችል ወታደራዊ ብቃት አላቸውን?
በእኔ ትንታኔ ኤል ሲሲ እና የጦር አበጋዞቻቸው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እየተባለ የሚጠራው ግድብ በግብጽ ህዝብ ላይ የህይወት አደጋ ደቅኖ እንደሚገኝ እና የዚህ ታላቅ አደጋ ብቸኛ መፍትሄውም ወታደራዊ እርምጃ እንደሆነ ሊቀለበስ በማይችል መልኩ ከድምዳሜ ላይ የደረሱ ለመሆናቸው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡
ይህ ዓይነት አቋም ኤል ሲሲ እንዲሁ በባዶ አየር ላይ የፈጠሩት አይደለም፡፡ የወታደራዊ አማራጭ ሁልጊዜ በግብጽ ላይ የተፈራረቁት አገዛዞች ሁሉ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም የግድብ ግንባታ በግብጽ ህዝብ ህይወት ላይ የማይቀር አደጋን የሚጋርጥ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩት ስለሆነ በማናቸውም መንገድ እና አስፈላጊ ነው ተብሎ በሚታመንበት መንገድ ሁሉ መወገድ ያለበት ስልታዊ አማራጫቸው ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ቂጥ ለቂጥ እየተያያዙ እያካሄዱት ያለው የዴፕሎማሲ ቸበርቻቻ አስረሽ ምችው ዳንስ ወደፊት የማይቀረውን ነገር ለማዘግየት ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት የሚፈይደው ነገር በፍጹም የለም፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የመጀመሪያዎቹ ወራት የአረብ የጸደይ አብዮት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዘ-ህወሀት የግብጽ ፖለቲካ እንዳይረጋጋ፣ በቋፍ ላይ እንዲቆይ እና የአገዛዝ ለውጥ እንዲኖር ሲፈልግ ቆይቷል፡፡ የዘ-ህወሀት መሪዎች በግብጽ ውስጣዊ ችግር ሳቢያ የግድብ ስራውን ማፋጠን እና የዓባይን ወንዝ የውኃ ፍሰት አቅጣጫ ማስቀየስ ከግብጻውያን የሚመጣ ጠንካራ ተቃውሞ የለም በሚል ጥቅም የሚያገኙ መስሎ ይታያቸዋል፡፡
ኤል ሲሲ እና የእርሳቸው ጀኔራሎች ያሉባቸውን ፖለቲካዊ አደጋዎች ተገንዝበዋል፣ እናም ላለፉት ሶስት ዓመታት ዴፕሎማሲያዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡
ኤል ሲሲ እና ጄኔራሎቻቸው ጊዜዎቻቸውን ለዴፕሎማሲያዊ ስራ ሲያውሉ ቆይተዋል፡፡ በአንድ ወቅት ሮጀርስ እዳሉት፣ “ዴፕሎማሲ ማለት አንድ ጥሩ አለት እስከምታገኝ ደረስ ተናካሽ ዉሻዉን ማባበል ሙከራ ማለት ነው“ እንዳሉት ነው፡፡
ከእኔ የሁኔታዎች ትንታኔ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ኤል ሲሲ ከሁለት ዓመታት በፊት ከነበሩበት የበለጠ ጠንካራ አቋም አላቸው፡፡ እ.ኤ.አ ጥር 2011 እና ሰኔ 2013 በግብጽ ላይ ታይተው የነበሩት የፖለታካ አለመረጋጋት እና ህዝባዊ አመጽ በአሁኑ ጊዜ ምክንያት ሆኖ ሊነሳ አይችልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኤል ሲሲን መንግስት በህዝባዊ አመጽ ለማስወገድ የሚደረግ ህዝባዊ ተቃውሞ የለም፡፡ ኤል ሲሲ በአሁኑ ጊዜ ኃይላቸውን ከማጠናከራቸውም በላይ ወታደራዊ አገዛዛቸው ውስጣዊ አንድነትን ፈጥሯል፡፡ በሙስሊም ወንድማማቾች ላይ ሲወሰድ የነበረው የኃይል እርምጃ በምሁራን፣ በወታደሩ፣ በቢሮክራሲው እና በሌሎች የሲቪል ተቋማት ሰፊ የድጋፍ መሰረት አለው ብዬ እጠርጥራለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ኤል ሲሲ ግብጽ ወደ እርስ በእርስ ጥላቻ እና የኃይማኖት ግጭት ውስጥ እንዳትገባ የተሻሉ ሰው ናቸው የሚል ሰፊ መግባባት አለ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኤልሲሲ ስለግድቡ ምንም ዓይነት ጭንቀት እንዳይኖርባቸው ለግብጻውያን ለመናገር በእራስ የመተማመን ስሜት አላቸው፡፡ ከመስመር በወጣ መንገድ ላይ አይመሯቸውም፡፡ ነገሮች ገፍተው ከመጡ በየትኛው መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ህዝቦቻቸውን ወደ ውድቀት አይወስዱም፡፡ ኢትዮጵያውያን ወንድሞች የዓባይን ወንዝ በመገደብ በግብጻውያን ላይ አደጋን የሚጋብዙ ደደቦች አይደሉም፣ ምክንያቱም ግብጻውያን መኖር እንደሚፈልጉ ሁሉ እነርሱም መኖር ይፈልጋሉ፡፡
በሌላ አገላለጽ ኤል ሲሲ በአሁኑ ጊዜ የሮጀርን አለት አግኝተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ለ–ዘህወሀት ተናካሽ ዉሾችአያባብሉም ፡፡ ብቸኛ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ግን ኤል ሲሲ አለቱን በሰራ ላይ የሚያዉሉት መቼ ነው የሚለውነው!
ስለኤል ሲሲ እና ስለወታደራዊ ዕቅድ አውጭዎቻቸው ያለኝ ትንታኔ ለማይቀረው ነገር ዘረፈ ብዙ እና የተሰላ የእርምጃ ደረጃ ያለው ታላቅ መሻሻሎችን አዘጋጅተው ተቀምጠዋል፡፡
የግብጾች ስልታዊ ዓላማዎች ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተባለ በሚጠራው ግድብ ላይ ጦርነትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ይዘው የተቀመጡ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ ብቃት እንዳላቸው ወይም ደግሞ በግድቡ ከሚሰነዘርባቸው ማንኛውም አደጋ ለመከላከል እና ለወደፊትም ማንኛውንም ነገር ለመቆጣጠር እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አምካኝ የሆነ ወታደራዊ ኃይልን የመጠቀሙ አስፈላጊነት አልታያቸውም፡፡
የግብጾች ስልት በዚህ በሚቀርበው ቅደም ተከተል ባይሆንም የሚከተሉትን ነገሮች ለመከተል እቅድ አላቸው ብየ አምናለሁ፡
አንደኛ፡ ግብጻውያን ዓለም አቀፍ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶችን ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለዘ-ህወሀት እንዳይሰጡ በማግባባት ላይ እንደሚገኙ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ግብጽ በሁለት መንገድ ዘመቻዋን ጀምራለች፡ 1ኛ) የግብጽን የውኃ እና የውጭ ግንኙነት ሚኒስትሮችን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ስብሰባ እንዲቀመጡ በማድረግ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ማድረግ፣ 2ኛ) የግብጽ አምባሳደሮች ከእነዚህ ሀገሮች ለግንባታው የሚውል ገንዘብ እንዳይገኝ የማግባባት ስራ መስራት የሚሉት ናቸው፡፡ ይህ ስልት ዘ-ህወሀት ለግድቡ ግንባታ የሚውል ብድር ወይም ደግሞ ሌላ የገንዘብ እርዳታ እንዳያገኝ በማድረግ ስኬታማ ሆነዋል፡፡
ሁለተኛ፡ ኤል ሲሲ ማቋረጫ የሌላቸው የቴክኒካዊ እና የትንታኔ ጥናቶች መጠናት አስፈላጊ ነው በማለት የግድቡን የግንባታ ስራ የማዘግየት ተግባራትን ይሰራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ባለፈው ሳምንት በተደረገው አዲስ ስምምነት መሰረት እ.ኤ.አ ከየካቲት 2016 ጀምሮ ለቀጣዮቹ 15 ወራት ግድቡ ስለሚያስከትለው ተጽዕኖ የቴክኒክ ጥናት ተጠንቶ ይቅረብ የሚለው ለዚህ ዓይነቱ ስልታዊ አካሄዳቸው የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው፡፡ ያለምንም ጥርጥር ወደፊት ብዙ ጥናቶች ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ቴክኒካዊ ጥናቶች በአሁኑ ጊዜ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የግድቡ ግንባታ በግብጽ ላይ በበርካታ መንገዶች አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚሉ የጥናት ግኝቶች ይቀርባሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በመጨረሻ በኤል ሲሲ እና ጀኔራሎቻቸው እነዚህን ቴክኒካዊ እና የምህንድስና ጥናቶች የጦርነት መንስዔ (ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ አሳማኝ ድርጊት) አድርገው ሊወስዱ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡
ሶስተኛ፡ ጊዜውን በማራዘም እና በሌሎችም አማራጮች ኤል ሲሲ በግድቡ ግንባታ ላይ የስራ ማስኬጃ ወጪዎች እጅግ በጣም እንዲንሩ የማድረግ አላማን በማራመድ በመጨረሻም ግድቡን ለመግንባት እና ለመጠገን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የገንዘብ አቅም እንዳይኖር ያደርጋሉ፡፡
በተለመደው አሰራር መሰረት ታላላቅ ግድቦች በሚገነቡበት ጊዜ የስራ ማስኬጃ ወጪዎች መናር የተለመደ ነው፡፡ እጅግ በጣም ግዙፍ በሆኑ እና የገንዘብ አዋጭነታቸው ላይ አጠቃላይ በሆነ መልኩ እስከ አሁን ድረስ ዝርዝር የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት በተሰራላቸው ግድቦች ላይ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች አቲፍ አንሳር፣ ቤንት ፍላይብጀርግ፣ አሌክሳንደር ቡዚየር እና ዳንኤል ሉን እ.ኤ.አ. በ1934 እና በ2007 መካከል በተገነቡ አስተማማኝ ወጭ እና የጊዜ ሰሌዳ ባላቸው ግድቦች ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት አካሂደዋል፡፡ የዚያ የጥናት ውጤት በግልጽ እንዳመላከተው ታላላቅ ግድቦች በሀገሩ ቋሚ የገንዘብ መለኪያ መሰረት 96 በመቶ የሚደርስ ከፍተኛ የሆነ የስራ ማስኬጃ ወጭ የሚጠይቁ መሆናቸውን ደምድመዋል፡፡ የፕሮክቱ ተግባራዊነት በአማካይ 44 በመቶ የመዘግት ችግር ይገጥመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የግድብ ግንባታ ወጭዎች የስራ ማስኬጃ ወጭዎች ከዚህ የተለዩ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል በሰሜን ኢትዮጵያ የዓባይ ገባር በሆነው በተከዜ ወንዝ ላይ የተካሄደው የተከዜ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታ ጠቅላላ ወጭ በመጀመሪያ ደረጃ 224 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይፈጃል ተብሎ ነበር የተገመተው፡፡ ሆኖም ግን ከተጀመረ ከስምንት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ2008 ሲጠናቀቅ ዋጋው ወደ ሰማይ እንደሮኬት ተተኩሶ 360 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሊሆን ችሏል፡፡ በምህንድስና ብቃት ማነስ ምክንያት ጥራት የሌላቸውን የግብዓት ቅሳቁሶች በመጠቀም እንደዚሁ የግንባታ ችግሮች/Structural problems የተለመዱ ችግሮች ናቸው፡፡ በኦሞ ወንዝ ላይ እ.ኤ.አ የካቲት 2010 በግልገል ጊቤ ሁለት ግድብ ላይ የተካሄደው ግንባታ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ሁሉ የበለጠ ትልቅ የተባለው የግድብ ግንባታ የግድብ ስራው ተጠናቅቆ በተመረቀ 10 ቀናትን ሳያስቆጥር ተደረመሰ፡፡
አራተኛ፡ ኤል ሲሲ ግድቡ የሚጠናቀቅ ቢሆንም እንኳ ኃይል ማመንጨት እንዳይችል የስራ ማስኬጃ ወጭውን በዘ-ህወሀት ላይ በማናር የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቡ እንዳይሞላ ረዥም ጊዜ በመውሰድ እንዲጓተት ያደርጋሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአንድ በኖርዌ ባለሙያዎች የተካሄደ የምህንድስና ጥናት እንደሚያመለክተው ሁሉም ነገር እንደታሰበው ይከናወናል ብለን ብናስብ እንኳ 67 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለመሙላት ሰባት ዓመታትን ይፈጃል፡፡ ጥቂት ነገሮች ብቻ ናቸው በታቀደው መሰረት ከፍጻሜ የሚደርሱት፡፡
እጅግ ሲበዛ ድብቅ የሆነው ዘ-ህወሀት የኤሌክትሪክ ኃይል ምርቱን ግብ ለማሳካት እንዲቻል የውኃ ማጠራቀሚያው ግድብ በምን ያህል ጊዜ በውኃ እንደሚሞላ ግልጽ ያደረገው ነገር የለም፡፡ ያም ሆነ ይህ የመጀመሪያው የግድቡ የውኃ መሙላት ስራ እና ከዚህም ጋር ተያያዞ የሚከሰተው የውኃ ትነት ወደ ግብጽ በሚፈስሰው የውኃ መጠን ላይ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ቅናሽ ያሳያል፡፡
ግድቡን በውኃ የመሙላት የስራ ሂደት ልዩ በሆነ ጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት ከባለሙያዎች ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ ግድቡን በውኃ የመሙላት ስራ በበርካታ ነገሮች ማለትም የመሙላት መጣኔን በመወሰን፣ በውኃው ወቅታዊ የመጠን ለውጦች፣ የግድቡን የመውጣት መጠን የመቆጣጠር ሁኔታ፣ በመጀመሪያው የግድብ ሙሌት ጊዜ ሊከሰቱ በሚችሉ ችግሮች ላይ በሚሰጥ መፍትሄ፣ በግድቡ የውኃ ሙሌት ሂደት ጊዜ ችግሮችን ለመለየት በሚደረጉ ዝርዝር የቴክኖሎጂ መመርመሪያዎች፣ ግድቡን ለመቆጣጠር በሚደረግ ዕቅድ እና በሸለቆው የታችኛው አካባዎች ላይ ግድቡ እየተሞላ ባለበት ሁኔታ በሚደርሱ ተለዋዋጭ ነገሮች እና በመሳሰሉት ተጽእኖ ፈጣሪ ነገሮች ላይ ይወሰናል፡፡ የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቡ መሙያ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለ ዋና የፍልምያ ጊዜ ሂደት ነው፡፡
አምስተኛ፡ ግድቡ የሚጠናቀቅ ቢሆን እንኳ ኤል ሲሲ የኤሌክትሪክ ምርቱ ገበያ እንዳይኖረው ጠንክረው በመስራት የገንዘብ ማነቆ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ እንደ ዘ-ህወሀት ዕቅድ ከሆነ የግንባታ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት ለሱዳን፣ ለግብጽ እና ለአረብ ፔንሱላ ሀገሮች ይሸጣል የሚል ነው፡፡
እ.ኤ.አ ጥቅምት 2015 በወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ አዜብ አስናቀ እንዲህ ብለዋል፣ “የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን አንድ ኪሎ ዋት (kwh) የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዘጠኝ የአሜሪካ ሳንቲሞች ወጭ ይደረጋሉ፡፡ ሆኖም ግን የሚሸጡት በስድስት የአሜሪካ ሳንቲሞች ነው፡፡“
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአሁኑ ጊዜ 33 በመቶ ኪሳራ እየደረሰበት ሽያጩን ያካሂዳል፡፡ በዚህ መጣኔ ስሌት መሰረት ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተባለ የሚጠራው የኤሌክትሪክ ኃይል ተምኔታዊ የምጣኔ ሀብት ቀያሽ በነበረው እና በአሁኑ ጊዜ በህይወት በሌለው የአለቆች ሁሉ አለቃ በነበረው በመለስ ዜናዊ የዘ-ህወሀት ፕላኔት (ዓለም) ውስጥ ብቻ ነው ትርፋማ ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው፡፡
በአፍሪካ በኃይል ምርት አቅርቦት ላይ በቀጣናው ሀገሮች መካከል መልካም ትብብር የሚደረግ ከሆነ እና አህጉር አቋራጭ ጥረትም ከታከለበት በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ዋጋ ዝቅ ሊል እንደሚችል በርካታ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ዋናው ቸግር እነዚህ ትብብሮች በአፍሪካ ሀገሮች መካከል ወጭን በመጋራት ባለ አለመተማመን ብቻ ሁኔታውን የሚያሳንሰው አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን ለረዥም ጊዜ ዘላቂ የጋራ ጥቅም ሲባል በግድቦች ላይ ስለሚደረገው ቁጥጥር እና አስተዳደር ጭምር እንጅ፡፡
አስገራሚው ነገር ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሀት እና በግብጽ መካከል ባለው የግድቡ ውዝግብ ምንም ዓይነት መተማመን የሚባል ነገር የለም፡፡ ሶስቱ ጎረቤት ሀገሮች አስተማማኝ የኃይል ዘርፍ መገንባት እንዲቻል እንደ ልማት አጋርነት ሊተባበሩ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል ማስረጃ የለም፡፡ ይኸ የማይካድ እውነታ ነው!
ስድስተኛ፡ የግድብ ስራው ከተጠናቀቀ እና ስራውን የሚጀምር ከሆነ ኤል ሲሲ የኃይል ግሪዶችን፣ የስርጭት እና የማከፋፈያ መስመሮችን፣ ቅርንጫፍ ጣቢያዎችን እና የመሳሰሉትን ከስራ ውጭ ለማድረግ የተለያዩ የአጭር ጊዜ ስልቶችን በመንደፍ ለማደናቀፍ ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ለብዙ ጊዜ ለሚቆይ እና አስቸጋሪ ለሆነ የኃይል ችግር ብቻ የሚዳርጉ አይደሉም፡፡ ሆኖም ግን እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች በግደቡ የመሰረተ ልማት እና በምርታማነት አቅሙ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግርን ያስከትላሉ፡፡
ሰባተኛ፡ ኤል ሲሲ የመጨረሻ የሆነውን ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ማንኛውንም ዴፕሎማሲያዊ እና ህጋዊ ማዕቀፎች በሽምግልና፣ በእርቅ፣ በፍርድ ቤት ሂደት እና በተባበሩት መንግስታት ጣልቃ ገብነት አማካይነት በግብጽ ላይ የተደቀነ አደጋ ነው ብሎ የሚያስበውን ነገር ለማስወገድ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ስምንተኛ፡ የግድብ ስራው ከተጠናቀቀ እና ስራውን የሚጀምር ከሆነ ኤል ሲሲ በግብጽ ላይ ምጣኔ ሀብታዊ የሆነ ጉዳት እስኪያመጣ ድረስ ዝም ብለው ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወስዱ ተቀምጠው ይቆያሉ ብዬ አላምንም፡፡ ግድቡ እንደተጠናቀቀ በቀናት ጊዜ ውስጥ ፈጣን የሆነ ጥቃት ይሰነዝራሉ ብየ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም!
ዘጠነኛ፡ ሁሉም ሊቀበለው የሚችል እንዲህ የሚል አንድ እውነታ አለ፡ “ምንም ይሁን ምን ታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተባለ የሚጠራው ግድብ ወደ ግብጽ ሀገር በሚፈስሰው የውኃ መጠን ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግብጽ እያደገ በመጣው የህዝብ ብዛቷ የውኃ እጥረት ችግር እየተከሰተ ነው፡፡ ብዙ ውኃ ትፈልጋለች፡፡ ግድቡ ወደ ግብጽ ሀገር የሚፈስሰው የውኃ መጠን ላይ ከፍተኛ እጥረትን ያስከትላል፡፡“
እንደተባበሩት መንግስታት ዘገባ “ግብጽ ከተባበሩት መንግስታት የውኃ የድህነት መለያ መስመር በታች ናት፣ እናም እ.ኤ.አ በ2025 የተባበሩት መንግስታት ወደ “ፍጹም የውኃ እጥረት ቀውስ” ውስጥ እንደምትገባ ትንበያ ሰጥቷል፡፡ በሌላ አገላለጽ እ.ኤ.አ በ2025 ግብጽ በውኃ እጥረት ቸግር እጅ ከወርች ትያዛለች! በዓባይ ወንዝ የውኃ ፍሰት ላይ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የውኃ ቅነሳ በግብጽ ላይ እልቂትን ይፈጥራል” ይላል፡፡
ባለፈው ሳምንት ግሎባል ኢንተሊጀንስ እንዲህ በማለት ደምድሟል፣ “ከዓባይ ወንዝ የውኃ መጠን በመቀነስ ወደ ማጠራቀሚያ ግድቡ የማስገባት ስራው ስድስት ዓመታትን የሚወስድ በመሆኑ የግብጽን የውኃ አቅርቦት በእጅጉይቀንሰዋል፡፡ በመጨረሻም በግድቡ ውስጥ የሚኖረው የማይንቀሳቀስ ውኃ በውኃ ትነት ምክንያት የውኃ መጠን መቀነስ ያስከትላል፣ ይህም በበኩሉ የውኃውን ጥራት ያበላሸዋል“ ብሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 በኖርዌዎች በተጠና ጥናት መሰረት በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቡን ለመሙላት 67 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ውኃ መሞላት ያለበት ሲሆን ይህም ወደ ግብጽ ሀገር የሚፈስሰውን የውኃመጠን በ25 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል፡፡ እንደዚህ ያለው የውኃ ቅነሳ ለግብጽ ታላቅ መቅሰፍት ነው፡፡ የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቡ አንድ ጊዜ ከሞላ ወደ ግብጽ ሀገር የሚፈስሰውን የውኃ መጠን በ50 በመቶ ይቀንሰዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም በወጣ ዘገባ መሰረት በግድቡ ላይ ሊከሰቱ በሚችሉ በርካታ ችግሮች ላይ አጋሮቹ የሚሸጧቸው መፍትሄዎች እውነታን ያላገናዘቡ ናቸው በማለት እንዲህ በማለት ደምድሟል፡
“ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአሁኑ ጊዜ የገጠሟቸውን ችግሮች ለማስወገድ ዓለም አቀፍ አማካሪዎችን በመቅጠር ፈጣን የሆነ መፍትሄ ለማግኘት የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ከእኛ እይታ አንጻር ይህ ጉዳይ ዝም ብሎ ባዶ ምኞት ብቻ ነው፡፡ ወደፊት የሚመጡት ጠንካራዎቹ ስምምነቶች ከእያንዳንዳቸው ሶስት ሀገሮች የውጭ ፖሊሲ እና የውኃ ባለሙያዎችን በማዋቀር በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር እና ለስምምነት ፈቃደኝነቱ እንዲኖር የሚያግዙ ሲሆን ስለግድቡ አሰራር ዝርዝር አፈጻጸም ስምምነት፣ ስለኃይል ንግድ ስምምነት፣ ስለግድቡ ደህንነት እና ስለጨዋማነት አያያዝ ቁጥጥሩ የሚመለከቱ ስምምነቶች ወደ ፊት የሚመጡ ከባድ ጉዳዮች ናቸው“ ብሏል፡፡
ጉዳዩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓባይ ወንዝ ላይ እያስተጋባ ያለው የጦርነት ወሬ ነገ በዓባይ ወንዝ ላይ እውነተኛ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ዘ-ህወሀት ለግብጽ መጠነ ሰፊ የሆነ የውኃ መጠን በመከልከል በተጻራሪው ተቃውሞውን እያሰማ መሄዱን ብቻ እንደ ስልት የሚወስደው ከሆነ ጦርነቱ አይቀሬ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
ግብጻውያን ውኃ ለእነርሱ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው በማለት ለብዙ ጊዜ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አበ2025 በእርግጠኝነት ለእነርሱ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ይሆናል!
እ.ኤ.አ በ1979 የግብጽ ፕሬዚዳንት የነበሩት አንዋር ሳዳት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ግብጽን እንደገና ወደ ጦርነት እንድትማገድ ሊያደርጋት የሚችል ብቸኛ ነገር ቢኖር ውኃ ነው፡፡“ የግብጽን ውኃ በ25 በመቶ ቀንስ እናም ጦርነት ይነሳል፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፋሲሊቲዎች ጋር በተያያዘ ሊነሱ ለሚችሉ ውዝግቦች ማስተንፈሻ አገልግሎት ሊውል የሚችል ወታደራዊ አደጋ ለመጣል እገዛ የሚያደርግ ትንሽ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ከኦማር አልባሽር ጋር ስምምነት አድርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በግብጽ ላይ የዓባይን ውኃ በ25 በመቶ መቀነስ በግብጽ ደቡባዊ የሀገሪቱ ጫፍ ላይ ግዙፍ የአየር ማረፊያ ግንባታን ያስከትላል፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 በዚያን ጊዜ የነበሩት ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ እንዲህ ብለው ነበር፣ “የግብጽ የውኃ ደህንነት በምንም ዓይነት መልኩ ሊሻር አይችልም፡፡ እንደ መንግስት ኃላፊነቴ ሁሉም ዓይነት አማራጮች ክፍት እንደሆኑ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ የጦርነት ጥሪ እያሰማን አይደለም፣ ሆኖም ግን በውኃ ደህንነታችን ላይ አደጋ እንዲደቀን በፍጹም አንፈቅድም፡፡ አንዲት የውኃ ጠብታ ብናጣ ደማችን ተለዋጩን ይይዛል፡፡“ የግብጽን ውኃ በ25 በመቶ (ወይም ደግሞ በአንድ አንድ የውኃ ጠብታ) መቀነስ ጦርነትን ያስከትላል፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2014 የግብጽ ሜጀር ጀኔራል የሆኑት ታላት ሞሳላም እንዲህ ብለው ነበር፣ “አሁን ያሉን አማራጮች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ዴፕሎማሲ የመጀመሪያው ነው፣ ሆኖም ግን የግብጽ የማድረግ ብቃት ከዝቅተኛው ደረጃ ላይ ነው ያለው፣ እናም ሰላማዊ ንግግር ፍሬ የማያፈራ ከሆነ የግብጽ ወታደራዊ አዛዦች በውኃ ጥም ከመሞት ይልቅ በጦርነት መሞት ይሻላል የሚል ውሳኔ ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡“ የግብጽን የውኃ መጠን በ25 ከመቶ ቀንሱት እናም የግብጽ ወታደራዊ አዛዦች በውኃ ጥም ከመሞት ይልቅ በጦርነት መሞት ይሻላል የሚል ውሳኔ ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡
ጥቂት የግብጽ ምርጥ የፖለቲካ መሪዎች ግድቡን ለማፍረስ የተለያዩ መንገዶችን ማለትም ጸረ ዘ-ህወሀት የሆኑ ተቃዋሚዎችን መርዳት ጭምር የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
እንደ አንድ የታመነ የስለላ ድርጅት ምንጭ ከሆነ ግብጽ ሁሉም ዴፕሎማሲያዊ አማራጮች ካለቁ እና ከከሸፉ በኋላ በዓባይ ወንዝ ላይ በሚገደብ ማንኛውም ግድብ ላይ ጦርነት የማካሄድ እንዲህ የሚል ዕቅድ አላት፡
“ቀውስ የሚመጣ ከሆነ ግድቡን የሚያፈርስ አንድ ጀት በመላክ በአንድ ቀን ውስጥ ግድቡን አፍርሶ እንዲመለስ እናደርጋለን፡፡ የዚያን ያህል ቀላል ነገር ነው፡፡ ወይም ደግሞ በግድቡ ላይ ሻጥር እንዲሰሩ የእኛን ልዩ ኃይሎች እንልካለን፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ አማራጭን እንደ ብቸኛ መፍትሄ አንወስድም፡፡ ይኸ የመጠባበቂያ ዕቅድ ነው፡፡ እስቲ ግብጽ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ያደረገችውን ወታደራዊ ግዳጅ ወደ ኋላ መለስ ብለን እናስተውል፡፡ እ.ኤ.አ በ1976 ኢትዮጵያ ታላቅ ግድብ ለመገንባት ሙከራ ያደረገችበት ጊዜ እንደነበረ አስባለሁ፡፡ መሳሪያው በባህር ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ዶግ አመድ አደረግነው፡፡ ጠቃሚ የሆነ ልዩ ጥናት ነው“ ነበር ያሉት፡፡
የግብጽን ውኃ በ25 በመቶ ቀንሱ እና ኤል ሲሲ ግድቡን በቦምብ የሚያጋይ ጀት ይልካሉ፣ ወይም ደግሞ ልዩ ኃይላቸውን በመላክ በግድባችን ላይ አሻጥር ይፈጽማሉ፡፡
አስረኛ፡ በእኔ አስተያየት የግድቡ ግንባታ ለግብጻውያን በምንም ዓይነት መልኩ የስምምነት፣ የውይይት፣ የሽምግልና፣ የእርቀ ሰላም ወዘተ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በጥሞና አስቡበት፡፡ ግብጽ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው በህይወት እና በሞት መካከል ስምምነት ልታደርግ የምትችለው?
አሁን በህይወት የሌለው እና የዘ-ህወሀት ቆንጮ አድርጊ ፈጣሪ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ግብጻውያን በኢትዮጵያውያን ላይ በድንገት ወረራ ይፈጽማሉ የሚል ስጋት የለኝም፡፡ ያንን የሚሞክር ካለ ታሪኩ ሊነገረው ይገባል፡፡“
መለስ ብዙ ይናገራቸው ከነበሩት ጥቂት ጊዜዎች ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል የተጠቀመ መሆኑን አምናለሁ፡፡ እርሱ ሁልጊዜ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ብቻ ነው የሚጠቅሳት፡፡ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል መጥራት የሚያሳፍረው መስሎ ይሰማኛል፡፡ መለስ እራሱን ኢትዮጵያዊ አድርጎ የጠራበትን ጊዜ ፍጹም የሰማሁበት ጊዜ የለም፡፡ በፍጹም! ማንም ቢሆን መለስ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የተናገረበት ጊዜ ቢኖር በመረጃ አስደግፎ የሚያቀርብልኝ ሰው ካለ ከስህተቴ እታረማለሁ፡፡
መለስ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ብቃት ላይ ታላቅ ኩራት በማሳደሩ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በእርግጥ መለስ በታሪካዊ ምልከታው ትክክል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ወራሪ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣች በማባረር ከሶስት ሺ ዘመናት በላይ ሉዓላዊነቷን እና ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የአውሮፓ ኃያላን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ በመቀራመት በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ የሚያስችላቸውን የበርሊን ኮንፈረንስ/ጉባኤ ካጠናቀቁ ከሁለት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ1896 አደዋ ላይ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድባቅ በመምታት አሳፋሪ ሽንፈቱን ተከናንቦ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጻረረ መልኩ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ከምንም በላይ በሚጠላቸው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ በዚህ ጀግንነታቸው ለምን ኩራት እንደማይሰማው የሚገርም ነገር ነው፡፡
ኢጣሊያ እ.ኤ.አ በ1935 ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ በዱር በገደሉ ተሰማርተው አመራር ይሰጡ በነበሩ እና በአልሞ ተኳሽ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አርበኞች ብርቱ ተጋድሎ ተሸንፋ ለመውጣት ተገድዳለች፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን ተባበሩ በምንም ዓይነት መልኩ ለውጭም ሆነ ለውስጥ ጠላት እንዳተንበረከኩ የምለው፡፡
መለስ ይገምተው እንደነበረው ግብጽ ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የመፈጸም ዕቅድ የላትም በሚለው አባባል ላይ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ኤል ሲሲ ለጦር ኃይሉ ልዩ ትዕዛዝ በመስጠት በኢትዮጵያ ላይ የአውሮፕላን ጥቃት ወታደራዊ ግዳጅ ሊፈጽሙ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡
ግብጽ ወታደራዊ ብቃት ስለሌላት በግድቡ ላይ ወታደራዊ ግዳጅ በመፈጸም ችግር ልትፈጥር አትችልም የሚል አስተያየት የሚሰጡ የፖለቲካ ትንታኔ የሚሰጡ ሰዎች አሉ (ለምሳሌ ያህልም በአየር ላይ ነዳጅ የሚሞላ ጀት)፡፡ በዚህም መሰረት ረዥም ርቀትን በመጓዝ ጥቃት ለማድረስ የሚያስችል አቅም የላቸውም ብለው ያስባሉ፡፡ ግብጻውያን ለእንደዚህ ዓይነቱ ዕቀድ የመጠባበቂያ ዕቀድ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 2015 ኤል ሲሲ ሁለት የጦር አሮፕላን ተሸካሚ መርከቦችና እስከ 1850 ኪ/ሜ ርቀት በመብረር እና እስከ 50 ሺ ጫማ የመጨረሻ ከፍታ በመውጣት ጥቃት ሊሰነዝሩ የሚችሉ 24 ኦምኒሮል ተዋጊ ጀቶችን መግዛታቸዉን ማስተዋል ጠቃሚ ነገር ነው፡፡
“በገንዘብ እጦት የተገደበ ግድብ?” በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት ትችት ላይ የእራሴን አመለካከት በማንጸባረቅ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡
በመርህ ደረጃ የግድቦችን መገንባት አልቃወምም፡፡ ሆኖም ግን “ዛፍ ተንከባካቢ” የሚል የማስታወቂያ ልብስ መልበስ ያኮራኛል፡፡ ባለም ላይ ሁሉ በአካባቢ ጥበቃ እና አያያዝ ላይ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ: አካባቢ ጥበቃ ድረጅቶችንም ረዳለሁ፡፡ አካባቢ ጥበቃ ለወደፊት ተውልድ ተጠብቆ መቆየት አለበት:: ትናንሽ ግድቦች ከትላልቆቹ የተሻሉ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ የእኔ አመለካከት በብዙ ሳይንሳዊ ጥናቶች የተደገፈ ነው፡፡
ኃይል ለአፍሪካ በሚለው ለፖለቲካ እና ለኤሌክትሪክ በሚለው አጠቃላይ ጥያቄ ላይ የተለየ አመለካከት አለኝ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ አፍሪካውያንን በቤታቸው እና በንግዳቸው ከማሻሻል በፊት በተሻሻለ አስተዳደር እና ተጠያቂነት ማጠናከር ጠቃሚ ነገር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ የግድብ ግንባታ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ በውድድር ላይ የተመሰረተ የጨረታ ኮንትራት በማይሰጥበት ሁኔታ በግድቡ ውስጥ የሚሰራው ብቸኛው ነገር ሙስና፣ ሙስና እና የበለጠ ሙስና ብቻ ነው፡፡
አሁን በቅርቡ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባ እጅግ በጣም ማራኪ የሆነ ግድብን የመጎብኘት ዕድል አግኝቸ ነበር፡፡ ለእኔ ይኸ ነገር በጣም ትምህርታዊ የሆነ ልምድ ነው፡፡ እጅግ በጣም ግዙፍ የሆነ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ መገንባት እና ማስተዳደር ብዙ አደጋዎች ያሉበት አስቸጋሪ ነገር እንደሆነ አምናለሁ፡፡
የግልገል ጊቤ ሶስትን ግድብ ማስተዳደር ያልቻሉ ሰዎች ከአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቅ ግደብ ማስተዳደር ስለመቻላቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዚያ በ2014 “የቅንጦት ግድብ ወጭ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሌለው የቅንጦት ግድብ ነው በማለት ተችቼ ነበር፡፡ ዴቨሎፕመንት ቱደይ/Development Today የሚባለው የእርዳታ ነጻ መጽሔት እና በኖርዲክ እና በዘርፈ ብዙ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እየታገዘ በፖለቲካ፣ በቢዝነስ እና ከአካባቢ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚዘጋጀው መጽሔት የህዳሴውን ግድብ “ፖለቲካዊ እንደምታን የተላበሰ አሁን በህይወት የሌለው የመለስ ዜናዊ የቅንጦት ፕሮጀክት“ በማለት ጠርቶታል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አየተባለ አሁን የሚጠራው እና ቀደም ሲል የሚሊኒየሙ ግድብ እየተባለ ይጠራ የነበረው ግድብ እንደሌሎቹ ቀደምቶቹ የታላቅነት ስሜት ይሰማቸው እንደነበሩት የአፍሪካ አምባገነኖች ሁሉ የአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የአዕምሮ ልጅ ነበር፡፡ በግብጽ ውስጥ ያለው የአስዋን ከፍተኛ ግድብ እንደ ጋማል አብደል ናስር ሀውልት ሆኖ ይቆጠራል፡፡ መለስ የማይሞት የኮንክሪት ስሚንቶ ማስታወሻ በመገንባት እራሱን ዝነኛ በማድረግ ትንሹ የአፍሪካ ታላቅ ለመባል ይፈልግ ነበር፡፡
ግድቡ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የውኃ ጦርነት መንስዔ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁልጊዜ ትችት በምጽፍበት ጊዜ የዘ-ህወሀት አነብናቢዎች፣ ሎሌዎች እና በጥላቻ የተሞሉ ግብዞች ብሄራዊ ስሜት የሌለው የዘ-ህወሀት ጠላት፣ ወዘተ በማለት ይጠሩኛል፡፡ ስለዘ-ህወሀት፣ ስለስኬቱ፣ እና በሀገሪት ውስጥ ልማት ለማምጣት በሚታገለው ድርጀት ላይ አሉታዊ ነገር ለመናገር ምንም ዓይነት አጋጣሚ የማያመልጠኝ አድርገው በመቁጠር ጥላሸት የመቀባት ሱሳቸውን ይወጡብኛል፡፡
የዘ-ህወሀት ሎሌዎች እና በጥላቻ የተሞሉ የዕኩይ ምግባር አራማጆች ሁል ጊዜ ሰኞ እያዘጋጀሁ የማወጣቸውን የትንታኔ ትችቶች አንበቦ መረዳት ይችላሉ ብዬ አላምንም፡፡ ቢችሉ በእውነታዎቹ እና በአመክንዮዎቹ ላይ በመመስረት እኔን በማፋጠጥ መሞገት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን በፍጹም አያደርጉትም!
ሆኖም ግን ማንም እውነታውን መሞገት ለሚፈልግ አድሉን አሰጣለሁ፡፡ ስለ “ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ” የተለያዩ ጦርነት አያስከትልም የሚል ትንታኔ ቢሰጥ በጣም ጠቃሚ ነው ፡፡
የእራሴን አመለካከት አቅርቤአለሁ፡፡ ሌሎችም አስተያየታቸዉን አንድያካፈሉ አጋብዛለሁ!
በጉዳዮቹ ላይ ክርክር እናድርግ፡፡ እውነታዎችን እንመርምር፡፡ ህዝቡ መረጃ እንዲኖረው እናድርግ፡፡ በግድቡ ሊመጣ የሚችለው መዘዝ ምን ሊሆን እንደሚችል እናስጠንቅቃቸው፡፡ ህዝቡ ስለግድቡ ያለውን እውነት በሚገባ እንዲገነዘብ እናድርግ!
በበኩሌ ምንም ዓይነት የውኃ ጦርነት ወይም ደግሞ ሌላ ግጭት አለመኝም፡፡ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል አህጉራዊ ትብብር እና ከዚያም ባለፈ መልኩ ጠቅላላ አህጉራዊ ትብብር ቢኖር ከምንም በላይ ደስታ የሚሰጠኝ ነገር የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ትብብር በምኞት አላሚዎች ዓለም ውስጥ ብቻ እንጅ በሰሜን ምስራቅ የአፍሪካ አህጉር ሀገሮች ውስጥ ባሁን ጊዜ ሊሰራ አይችልም፡፡ እንደ ወርቅ የጠራው እውነታ ይኸው ነው፡፡
በእኔ ትንታኔ ላይ ስምምነት የሌላችሁ ሰዎች ባለፈው ሳምንት በግሎባል ኢንቴሊጀንስ የተዘጋጀውን እና ይፋ የሆነውን እንዲህ የሚለውን ዘገባ ተመልከቱ፡
“…አህጉሩ ስለግድቡ የተለያየ አቋም በመያዝ ተለያይቶ እስከቀጠለ ድረስ እርግጠኛ የግንባታ ስራው በማንኛውም ጊዜ ሊሰናከል እና ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ግድቡ በአሁኑ ጊዜ 50 በመቶው ተጠናቅቋል የሚል ዘገባ ቀርቧል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የውኃ አቅጣጫ ማስቀየስ ስራ በግንባታ ቦታው አካባቢ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግንባታው እየተካሄደ ቢሆንም ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውል የውጭ መዋዕለ ንዋይ ማግኘት አልቻለችም፡፡ የግድቡን ስራ ለማጠናቀቅ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ ገንዘብ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ሊገኝ የቻለው ገንዘብ ከ30 በመቶ በታች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቀሪውን ገንዘብ ለማግኘት ካልቻለች ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ለበርካታ ዓመታት ሊዘገይ ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ስምምነቶች አስፈላጊዎች ሊሆኑ የሚችሉት፡፡ የተሻሉ ስምምነቶች ከተካሄዱ ኢትዮጵያ ገንዘብ የማግኘት ዕድሏ የተሻለ ይሆናል፡፡“
ግድቡ ምን መሆን እንዳለበት ዕድሉ ያለው በኤል ሲሲ እጅ አይደለም፡፡
የዓባይ ወንዝ አስከፊ ዕድል ያለው በዘ-ህወሀት እጅ ላይ ነው፡፡
ይገርማል! ወይ ዳመና መዝገን!
ብር የለም ግድብ የለም!
አይገርምም! ግድብ በጦርነት ሳይሆን በገንዘብ ሲገደብ!
የሰኞ ትችቶቼን ለአስር ዓመታት ገደማ ያህል ስትከታተሉ ለቆያችሉ ለሁሉም ታማኝ አንባቢዎቼ (ወይም ደግሞጥቂቶች ፍቅርን የተላበሱ የኃይማኖት ሰዎች እያሉ ለሚጠሯቸው) እንኳን ለፈረንጆች አዲስ ዓመት በሰላምአደረሳችሁ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ታህሳስ 26 ቀን 2008 ዓ.ም