>
10:31 pm - Wednesday February 1, 2023

የትዊተር አራማጅነት መሬት ይረግጣል? [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

ግርማ ጉተማ የተባለ ሰው ታኅሣሥ 29/2008 የፌስቡክ ገጹ ላይ የጻፈውን ቀንጭቤ በማስነበብ ልጀምር፤ እንዲህ ይላል፣

twitter“ባለፈው ክረምት ‹ለሆነ የፖሊሲ ትምህርት› ኔዘርላንድ በነበርኩ ጊዜ አንድ በመስኩ የአውሮጳ ኅብረት ሰዎችን የማማከር ሥራ የሚሠራ አንጋፋ ፕሮፌሰሬን የማናገር ዕድል አግኝቼ ነበር። ያ መልካም ሽማግሌ ፕሮፌሰር በአውሮጳ ኅብረት የፓርላማ አባላት ሁኔታ ተደናግጧል። እንደአባባሉ፣ ‹እዚያ ያሉ ፖለቲከኞች ደደቦች ናቸው፤… በፖሊሲ ጉዳይ እንድናማክራቸው ባዘጋጁልን ስብሰባ ላይ የምንናገረውን በጥሞና አያዳምጡንም። በየስብሰባው ሁሉ እነርሱ ትዊት በማድረግ አባዜ ተጠምደዋል።” ይልና ጥቂት ወረድ ብሎ ደግሞ “…እኛ ግን ይህንን መልካም ሽማግሌ ፕሮፌሰር ተስፋ ያስቆረጠውን የአውሮጳ ኅብረት ፖለቲከኞች ‹ክፉ አመል› ለራሳችን ጉዳይ መጠቀሚያ ማድረግ እንችላለን። በመጪው ሰኞ [ጥር 2/2008] እነሱ ለስብሰባ ሲቀመጡ እኛ ደግሞ በኢትዮጵያ/ኦሮምያ አካባቢ ያለውን ቀውስ በማጋለጥ በትዊቶች እናጨናንቃቸዋለን።”

፩ – ሀሽታግ

ሀሽታግ ከትዊተር ዕድሜ ያላነሰ ጊዜ ትዊተር ላይ አገልግሎት ሰጥቷል፤ ነገር ግን አሁን-አሁን ፌስቡክን ጨምሮ በሌሎችም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ ሀሽታግ የሁለት ቃላት ጥምር ነው። ሀሽ (#) የተባለው ትዕምርት ሥያሜ ‹ታግ› ከሚለው እና ‹ባጅ› (ወይም ‹ልጥፍ›) ብለን ልንጠራው ከምንችለው ቃል ጋር ተጣምሮ ነው የተፈጠረው። ሀሽታግ አንድ ቃል ወይም ሐረግ በሀሽ ጀምሮ ሲጻፍ (ለምሳሌ ‪#‎ኢትዮጵያ‬) የሚፈጠር እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ሐሳብ ሲጽፉ ለመናበብ የሚጠቀሙበት መለያ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ለሀሽታጎች የየራሳቸውን ማያያዥያ (ሊንክ) ይሰጡትና ተመሳሳይ ሀሽታግ ተጠቅመው የተጻፉ ጽሑፎችን በአንድነት እንዲታይ ዕድል ይፈጥራሉ። ትዊተር በተመሳሳይ ሰዐት፣ ብዙ ሰዎች የተጠቀሙትን ሀሽታግ ከአንድ እስከ ዐሥር በደረጃ በማስቀመጥ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም ትኩረት እንዲሰጡት ያመቻቻል። በኢትዮጵያ በጣም የመታወቅ ዕድል ካገኙ ሀሽታጎች መካከል ‪#‎FreeZone9Bloggers‬ (የዞን 9 ጦማሪያን በታሰሩ ወቅት ወዳጆቻቸው እና ሌሎችም እንዲፈቱ የጠየቁበት ሀሽታግ) እና ‪#‎OromoProtests‬ (በቅርብ ጊዜ በድጋሚ በኦሮሚያ አካባቢዎች የአዲስ አበባ ማስፋፊያ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሰው የአደባባይ ተቃውሞን የተመለከቱ መረጃዎች የሚነገሩበት ሀሽታግ) ይገኙበታል።

፪ – ሀሽቲቪዝም

‹አክቲቪዝም› የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ብዙ ጊዜ በአማርኛ ‹አራማጅነት› ብለን ለመፍታት እንሞክራለን፤ አንድን ሐሳብ ሰዎች እንዲቀበሉት ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ ያሉትን የተግባር ሥራዎች ሁሉ ያካትታል። በአጥኚዎች፣ የሆነ ዘዴ ተከትሎ የሚፈፀም የአራማጅነት ሥራን ቃላት በማጣመር የተለያዩ ሥሞችን የመስጠት ባሕሉ አሁን-አሁን እየተለመደ መጥቷል። ለምሳሌ ሀክ የሚለውን የቴክኖሎጂ ሰርጎ መግባት ሥራ (በባሕሪው ሕገወጥ ቢሆንም)፣ አንዳንዶች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በደል ይፈፅማሉ በሚባሉ አካላት ላይ ሲፈፅሙት ‹ሀክቲቪዝም› ይሉታል፤ ሀክ በማድረግ የሚደረግ አራማጅነት እንደማለት ነው። ለምሳሌ ራሳቸውን የኦሮሞ ሀክቲቪስት እንደሆኑ የገለጹ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በቅርቡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና የድሬድዋ ዩንቨርስቲ ድረገጾችን ሰርገው ገብተው በማጥፋት የራሳቸውን መልዕክት አስተላለፈዋል። በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ድረገጽ ላይ ሀከሮቹ ያስተላለፉት መልዕክት ተቃውሞውን ተከትሎ የታሰሩ ሰዎችን ሥም በመዘርዘር ‹እነእከሌ ይፈቱ› የሚል መልዕክት ነው። ይህ ‹ሀክቲቪዥም› ይባላል።

በቅርቡ በጣም ዕውቅና እየተጎናፀፈ የመጣ የአራማጅነት ዓይነትም አለ። ‹ሀሽቲቪዥም› ይባላል። ሀሽቲቪዥም የሆነ ሀሽታግ ተጠቅሞ በአንድ ጉዳይ ላይ 1ኛ). አጋርነትን በማሳየት፣ 2ኛ). ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ እና 3ኛ). መረጃን በፍጥነት ለመላው ዓለም በማሰራጨት በጉዳዩ ላይ የሚፈለገው የተግባር ለውጥ እንዲመጣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በብዛት ከመቀመጫቸው ሳይነሱ የሚፈፅሙት የአራማጅነት ዓይነት ነው።

፫ – ሀሽቲቪዝም የት ያደርሳል?

ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ቶሎ ተስፋ ይቆርጣሉ። የሚታያቸው ስድድቦችና ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ውኃ የማይቋጥሩ ሙግቶች ብቻ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ የሰነፎች እና ከመተቸት በቀር ምንም መሥራት የማይችሉ ሰዎች መደበሪያ እንደሆነ ይናገራሉ። ሸምሱ ቢረዳ በሚል የብዕር ሥሙ የሚጦምረው እና በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ሽሙጥ ዐዋቂ፣ መጋቢት 2006 በጻፈው ጦማሩ ላይ ‹ኢትዮጵያዊ የትዊተር አራማጅ መሆን ምንም ሳያደርጉ ዕውቅና ለማፍራት መሞከሪያ መንገድ› እንደሆነ ተከራክሯል። ሸምሱ በጦማሩ፣ ‹ውሱን በሆነው የበይነመረብ (internet) ግንኙነት እና ተዳራሽነት የትዊተር አድራሻ ፈጥረው ከዕውቅ ተጠቃሚዎች ጋር ውይይት በመግጠም፣ የታሰሩ ሰዎችን ፎቶ በመለጠፍና ይፈቱ እያሉ በማለት ብቻ ራሳቸውን ለመጠነኛ ዕውቅና ከማብቃት በላይ› በአገራችን ፋይዳም ሥራም እንደማይጠይቅ ተናግሯል።

እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች በእኛ አገር ብቻ የተወሰነ አይመስልም። ባለፈው ዓመት ጆን ዋሊቦንጎ የተባለ የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጠኛ ሀሽቲቪዝም መሬት የማይወርድ እንደሆነ በተከራከረበት ጽሑፉ አንድ ምሳሌ አንስቷል። ፒተር ኬኔት በባለፈው የኬንያ የፕሬዚደንት ምርጫ ላይ ተወዳድሮ የተሸነፈ ፖለቲከኛ ነው። ነገር ግን እንደፌስቡክ እና ትዊተር ቢሆን ኖሮ ከሁሉም ተወዳዳሪዎች የበለጠ ወዳጅ እና ተከታይ የነበረው እሱ ነበር።

አዳዲስ ጥናቶች ግን በተቃራኒው ሀሽቲቪዝም ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ያመላክታሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታዩት ተስፋ አስቆራጭ ግለሰቦች ላይ ያተኮረ መሰዳደብ የሚበዛውም ይሁን አራማጆች የዚያ ልምድ ሰለባ የሚሆኑት ማኅበራዊ ሚዲያን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ባለማወቃቸው እንደሆነ ነው ጥናቶቹ የሚጠቁሙት። ‪#‎ThisIsACoup‬ (ይሄማ መፈንቅለ መንግሥት ነው) በሚል፣ የግሪክን ከአውሮጳ ኅብረት የመባረር አጀንዳ የተቃወሙት ሀሽቲቪስቶች፣ እንደዋዛ ባርሴሎና ላይ የጀመሯት አንድ ትዊት ተቀጣጥላ ዓለምን ማዳረሷን ተከትሎ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ሀሽታጉ በአንድ ሐምሌ ወር ብቻ 600 ሺሕ ትዊት (መልዕክቶች) ያስተናገደ ሲሆን፣ 140 ሺሕ ሰዎችም ሀሽታጉን ተጠቅመው መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል። ሀሽታጉ በዚህ መንገድ የበርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች እና ሚዲያዎችን መሳብ በመቻሉ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታለፍ እንዳይሆን በማድረግ ዲፕሎማሲውን ቀይሮታል።

በሚያዝያ ወር 2006 ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ በቦኮሀራም 276 ያህል ልጃገረዶች ተጠልፈው መወሰዳቸውን ተከትሎ ‪#‎BringBackOurGirls‬ (ሴቶቻችንን መልሳችሁ አምጡ) ሀሽቲቪዝም እየተካሄደ ነው። ሀሽቲቪዝሙ ይህንን ጽሑፍ እየያዙ ፎቶ ተነስቶ ከያሉበት ትዊተር ወይም ፌስቡክ ላይ መለጠፍን ይጨምር ስለነበር የአሜሪካ ቀዳማይ እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ የዓለማችን በርካታ ዕውቅ ሰዎች ተሳትፈውበታል። በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ሀሽታጉን የተጠቀሙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ትዊቶች በዓለም ዙሪያ ተላልፈዋል። ቦኮሀራም፣ እጅግ ብዙ ሰዎችን በናይጄሪያ እየገደለ እና ብዙ ጥፋት እያደረሰ የነበረ ቢሆንም የናይጄሪያ የብቻዋ የቤት ሥራ የሆነ ያህል በመላው ዓለም ችላ ተብሎ ነበር። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከ2 ሺሕ በላይ ልጃገረዶች በቦኮሀራም እንደተጠለፉ ሪፖርት ያወጣው ከዚያ በኋላ ነው። አሁን የዚህ ሀሽቲቪዝም ውጤት መላው ዓለም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረጉ ነው። ምንም እንኳን ልጃገረዶቹ እስካሁን ባይለቀቁም መላው ዓለም ለናይጄሪያውያኑ እና ለተጠላፊዎቹ ወዳጅ ቤተሰቦች ዘላቂ አጋርነታቸውን ማሳየታቸው በራሱ ተስፋ ቀጣይ መሆኑን ዘጋርዲያን ዘግቧል።

#OromoProtests የነጻ ሚዲያ እጥረት ባለባት ኢትዮጵያ ከኅዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን የአደባባይ ተቃውሞ ጠቅላላ ሁኔታ እና የደረሰውን የጉዳት መጠን ማወቅ ያስቻለ ሀሽታግ ነው። ብዙ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ሁኔታውን ሲዘግቡ ማኅበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ የነጻ ሚዲያ እጥረት የወለደውን ክፍተት እየሞላ እንደሆነ አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ተቃውሞውን አለባብሶ ሊያልፈው እንዳይችል ያደረገው፤ በመንግሥት የተገደሉትን ተቃዋሚዎች ማንነት እና ቁጥር እንዲሁም ተቃውሞ የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ዝርዝር በሙሉ በርካታ የውጭ ሚዲያዎች እና የአገር ውስጥ ጦማሪያን መዘገብ የቻሉት ይህንን ሀሽታግ በመከተል ነው። ተቃውሞው መሪ እንደሌለው በተደጋጋሚ ተነግሯል፤ መሪ አለው ከተባለ ይህ ሀሽታግ ይሆናል። ሁሉንም ዓይነት ተቃውሞውን የሚመለከቱ መረጃዎች በሙሉ በዚሁ ሀሽታግ አማካይነት ተላልፈዋል። ነጻ ሚዲያ በሚታፈንበት አገር የሀሽቲቪዝም ጥቅም ወደር የለሽ መሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ታይቷል።

#FreeZone9Bloggers: Global Digital Activism and the Local Politics in Ethiopia በሚል ርዕስ በሦስት ትልልቅ የአካዳሚ ተቋማት የተሠራ ጥናት #FreeZone9Bloggers በሚለው ሀሽታግ የተካሄደው የትዊተር ዘመቻ (ሀሽቲቪዝም) ‹የተለያዩ የዓለም ክፍል ማኅበረሰቦችን በአንድ አሰባስቧቸዋል› ይላል። ይህም ኢትዮጵያን የሚደግፉ መንግሥታት ተጽዕኖ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ጥናቱ ያትታል። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች ነገሩን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለማስተባበል መገደዳቸው የሀሽቲቪዝሙ ውጤት እንደሆነ ጥናቱ ያመላክታል፤ የወቅቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ሚኒስትር “የዓለም ዐቀፍ ተቋማቱ ጩኸት ጦማሪዎቹን አያስፈታቸውም” ብለው ማለታቸው የተፅዕኖው ማሳያ እንደነበር ነው ጥናቱ የሚጠቁመው።

እንዳለመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የመንግሥት ኃላፊዎች የማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ አይደሉም። አልፎ ተርፎም የበይነመረብ ተዳራሽነቱ 100 ሚሊዮን ዜጎች ባሏት አገር ውስጥ 3 ሚሊዮን አይሞላም። ነገር ግን የኢትዮጵያን መንግሥት የሚደግፉት አገሮች እና መግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው የአውሮጳ ኅብረት ፖለቲከኞች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአግባቡ ይጠቀማሉ። በኢትዮጵያ የሚደረገው ሀሽቲቪዝምም አጋርነትን ከማሳያነት፣ ግንዛቤ ከማስጨበጫነት እና መረጃ በፍጥነት ማሰራጫነት በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊ የሆኑ አገራት ፖለቲከኞችን በቀጥታ በማግኘት በውስጣዊው ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ተፅዕኖ ማድረግ ይችላል።

***
ይህ ጽሑፍ ዛሬ ጥር 7/2008 በተሰራጨው የአዲስ ገጽ መጽሔት ላይ የታተመ ነው።

ምንጭ:-ዞን ፱

Filed in: Amharic