>
1:24 am - Thursday July 7, 2022

የአባይ ፀሃዬ የለውበትም የት ያደርስ ይሆን? [ግርማ ሰይፉ ማሩ]

Abay-Tsehayeወዳጆች መቼም የዚህ ሀገር ነገር ግራና ቀኙ ጠፍቶዋል እንበል እንዴ? የፌዴራል ሹሞች የበታች ሹሞችን በፖለቲካ ውሳኔ በሚመጡ ጉዳዮ ጭምር እጃቸውን ወደታች መቀስር ጀምረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም አማርኛ ተናጋሪዎች ተለይተው ከመኖሪያቻው ሲፈናቀሉ፣ ተጠያቂ የተደረጉት “ጥቂት ኪራይ ስብሳቢ” የተባሉ የበታች ሹሞች ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ የአዲስ አበባና በዙሪያ ያሉ ከተሞች የተቀኛጀ ማስተር ልማት ይዞት የመጣው ጦስ በቀላሉየሚገላገሉት አይመስልም፡፡ ጎምቱ የሚባሉት ባለስልጣናትም ቢሆን ስህትት ከመስራት የሚያግዳቸው ኃይል ሊገኝ አልቻለም፡፡ የዛሬ ፅሁፌ መነሻ የሆነው ደግሞ አቶ አባይ ፀሃዬ በሚዲያ የሰጡት የመከላከያ መልስ እጅግ ስለአስገረመኝ ነው፡፡

ባጠቃላይ መንግሰት የሚባለው አካል እንደ አካል ይህ ጦሰኛ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ግራ አጋብቶታል፡፡ ግራ ተጋብቶ ግራ እያጋባን ይገኛል:: የአዲስ አበባ መሰተዳደር በግሉ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ያደርጋል የሚል ዜና የሰማነው የኦሮሚያ/የኦህዴድ ሰራ አስፈፃሚ የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ እንዳይሆን ውድቅ ባደረገ ማግስት ነው፡፡ አዲስ አበባ በተናጥል ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ሲያደርግ በዙሪያ ያሉት ከተሞች ላይ የሚያሰከትለው በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅህኖ እንዴት እንደሚታይ የነገረን የለም፡፡ ለማነኛውም ይህን እናቆይ እና ለፅሁፌ መነሻ ወደ ሆነው ጉዳይ ልግባ፡፡

በእኔ እምነት በኦሮሚያ አካባቢ ለተነሳው ንቅናቄ ዋነኛው ነገር ቆስቋሽና አቀጣጣይ የነበሩት አቶ አባይ ፀሃዬ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ኦቶ አባይ ፀሃዬ እጅ እና እግር የለሌለው ክስ በየደረጃው ወደሚገኙት የኦሮሞ ካድሬዎች ላይ አቅርበዋል፡፡ ወደዚህ ጉዳይ በዝርዝር ከመግባቴ በፊት ግን በዚህ ጦሰኛ ማስተር ፕላን ነገር ቆስቋሽና አቀጣጣይ ያልኩበትን ምክንያት ማስረዳት ይኖርብኛል፡፡

አቶ አባይ ፀኃዬ በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፖሊሲና ጥናት ጉዳዮች ማማክር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ስልጣና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን የነበረ አይደለም፡፡ ኦቶ አባይ ይህንንም ስልጣናቸውን የገለፁበት መንገድ ጠብ የሚፈልግ ካለ ወይም ከተገኘ ለጠብ የሚመች ነው፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትር የእለት ተእለት ስራ ስለሚበዛባቸው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንደንስራ ተመደብን” ሲሉ በመጀመሪያ ያድረኩት የህገ መንግሰቱን አንቀፅ 79 መመልከት ነበር፡፡ ይህ ህገ መንግስት ካልተቀየረ በሰተቀር የፖሊሲ ጉዳዮችን ሸክም የሚወስድላቸው ሌላ ሰው መድበው እርሳቸው በሌላ የእለት ተዕለት ስራ መጠመድ አይገባቸውም ነበር፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ በዚሁ ስልጣናቸው መነሻ ባለፈው ሁለት ዓመት ግድም በኦሮሚያ በተለይ አምቦ አካባቢ በተነሳው ግርግር ማግስት ቆም ብሎ የነበረውን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጉዳይ ከምርጫው በኋላ በአሸናፊነት መንፈስ ከኦህዴድ ካድሬዎች ጋር ባደረጉት ውይይት “ይህንን ፕላን በግዳቹ ትተግባራለችሁ ብለዋል የሚለው ነው”፤ ይህን አይሉም ሊባል የማይችለው የኦህዴድ ባለስልጣናትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራቸው አቋም ተግባራዊ ለማድረግ ምን እናድርግ? የሚለው እንጂ ተግባራዊ አናደርግም የሚል ሰለ አልነበረ ነው፡፡

ይህች በግድ የምትል ቃል እልህ አስገብታ ይህን ሁሉ እሳት የጫረች እንደሆነች መገንዘብ አያሰቸግርም፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ እልፈት በፊት ኦሮሚያ በእጅ አዙር ይቆጣጠሩት እንደነበር፤ ለዚህም እንደ አለማየሁ አቶምሳ እና ሙክታር የመሰሉ የመለስ ቀኝ እጆች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ሉሎችም አሉ፡፡ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የኦሮሚያ ባለስልጣናት ከህውሃት ሰዎች ጋር ትከሻ መለካከት እንደጀመሩ ብዙ ማሳየዎች አሉ፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ ከመለስ ሞት ማግስት ጀምሮ ከአንገታቸው ቀና ካሉት ሰዎች አንዱ ቢሆኑም በኦሮሚያ ሰፈር የተፈጠረውን ትከሻ መለካካት ያጤኑት አይመስለኝም፡፡ይህን ትከሻ መለካካጽ ልብ ብለውት ቢሆን ኖሮ “በግዳችሁ ትተገብራላችሁ” የምትለው ጦሰኛ ቃል አትውጣም ነበር፡፡ በግድ ማርም ቢሆን አይጥምም!!!

በእኔ እምነት አሁን በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው በዋነኝነት “እምቢ ማስተር ፕላን” ተቃውሞ በኦሮሚያ በሚገኙ ኦህዴድ ካድሬዎች ቀጥተኛ ድጋፍ እንዳለው ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ድጋፋቸውን የሚሰጡበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም፡፡ ኦህዴድ ዛሬ እንደ ከዚህ ቀደሙ በኢህአዴግ በሚቀመጥለት አቅጣጫ የኦህዴድ ካደሬዎችን አፍሶ እስር ቤት ማሰገባት የሚችል አይመሰለኝም፡፡ ዶክተረ ነጋሶ በአንድ ወቅት እንደነገሩን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎችን አባረው እና እስር ቤት አስገብተዋል፡፡ የዚያን ጊዜው ኦህዴድ አሁን ያለ አይመስለኝም፡፡ የአሁኑ ኦህዴድ ያለው እድል ካድሬዎቹን ተለማምጦ በስልጣን መቆየት ነው የሚኖርበት፡፡ ሰለዚህ አቶ አባይ እንዳሉት በግድ መተግበር ሳይሆን ማስተረ ፕላኑን መሰረዝ ነው፡፡

አቶ አባይ ፀሃዬ እራሳቸውን ሲቀጥልም እናት ፓርቲያቸውን ሕውሃትን ለመከላከል ብለው የሰጡት ምለሽ በእርግጥ ሌላ ዙር ቀውስ የሚጠራ ነው፡፡ ይህ የአባይ ፀሃዬ የለውበትም መልስ የት እንደሚያደርስ ግን አላውቅም፡፡ መልሳቸው ባጠቃላይ አሁን በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው ንቅናቄ መንስዔ “በኦሮሚያ የተለያየ እርከን የሚገኙ የኦህዴድ ሹሞች ሌቦች በመሆናቸው፣ ህዝቡ የሚጠይቀውን የመልካም አስተዳድር ምላሽ መሰጠት ባለመቻላቸው፣ ወዘተ” የሚል ነው፡፡ በዚህ የመከላከያ መልሳቸው በቀጥታ ላለመንካት የፈለጉት የኦህዴድ ከፍተኛ ሹሞችን ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት ከወረዳ እሰከ ዞን ብሎም ክልል ድረስ ያሉት ሹሞች ሃላፊነት የተሰጣቸው በኦህዴድ ከፍተኛ ሹሞች ነው፡፡ በክስ ውስጥ ሊዘሏቸው ቢፈልጉም የበታቾቻቸውን መከላከል ወይም አብረው መከሰሳቸው መረዳት ግድ ነው የሚሆነው፡፡ የኦህዴድ ባለስልጣናት አቶ አባይ ፀሓዬን የሚጠይቁት ጥያቄ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለማነኛውም አቶ አባይ ፀሓዬ ከግላቸው አልፈው ህውሃትም ሆነ ፌዴራል መንግሰት አሁን በተፈጠረው ጉዳይ አያገባውም ጉዳዩ የኦህዴድ እና የኦህዴድ ሾሞች ብቻ ነው ብለው እጃቸውን ለመታጠብ ሞክረዋል፡፡ ይህ በፍፁም የሚሳካ አይመስለኝም፡፡

በእኛ አረዳዳ ኦህዴድ የሚባል ፍጡር በኢህአዴግ በሚመራው ስርዓት ውስጥ የተለይ ነው ብለን አናምንም፡፡ ኦህዴድ የወሰዳቸው የግል ውሳኔዎች አሉ ብለን አናምንም ስለዚህ ሁሉም የኢህአዴግ አመራር አባሎች እና የፌዴራል መንግሰቱ ባለስልጣናት በዚህ ውሳኔ ውስጥ እንዳሉበት እናምናለን፡፡ ሰለዚህም አሁን አቶ አባይ ፀሃዬ ያቀረቡት መከላከያ ተቀባይነት የለውም፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት አንዳንዶቻችንም እንደምንስማማው የተቀናጀ ማስተር ፕላን በድፍኑ ክፋት የለውም፤ ክፋቱ የመጣው “በግድ ትተገብራላችሁ” የሚለው ማስፈራሪያ እና ጥቅም ካለው ማስገደድ እና ማስፈራራት ምን አመጣው? የሚለው እንደምታ ነው፡፡ ሰለዚህ ማርም ቢሆን በግድ ይመራል የምንለው!!!

በነገራችን ላይ ተጠያቂነት የሚባለው ነገር አቶ አባይ ፀኃዬ ከሃያ አራት ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላም እንዴት ሊረዱት ተሳናቸው? ለምን ይህን የሚያክል ሀገራዊ ውሳኔ ወደ ወረዳና ዞን ሹሞች ሊወረውሩት ፈለጉ? ሌላው ደግሞ በኦሮሚያ አለ የሚሉት “መሬት መሸጥ፣ የመልካም አስተዳድር እጦት፣ ሙስና፣ ወዘተ እኛን አይመለከትም፡፡ ሕዝቡ የጠየቀው ትክክለኛ ጥያቄ ነው መልስ መስጠት ሲያቅታቸው አባይ፣ ሕውኃት፣ ፌዴራል” ይላሉ ብሎ ከሃላፊነት መሽሽ ይቻላል ወይ?ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በእኔ እምነት አሁንም ቢሆንም ማስተር ፕላኑ ተተግብሮ ውጤት ቢገኝ ጭብጨባውን ለመውሰድ ወደኋላ እንደማትሉት ሁሉ በዚህ መነሻ ለተነሱት መሰረታዊ የመልካም አስተዳድርና የነጻነት ጥያቄ መልስ መስጠት ካቃታችሁም ተጠያቂነቱንም አብራችሁ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመጨረሻ አቶ አባይ ፀሃዬ የኦህዴድ የበታችና የመካከለኛ አመራር ላይ ክስ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ የኦህዴድ አመራሮች በድርጅት መስመር ሄደው ይህ ክስ በይፋ ይነሳልን፣ ስናስፈፅም የነበረው ከፍተኛ አመራሩ የሰጠን መመሪያ ነው ማለት አለባቸው፡፡ ካለበለዚያ ደግሞ በጋራ ጥያቄያቸውን በኢህአዴግ ፎረም ላይ አቅርበው ሊገማገሙበት ይገባል፤ የአቶ አባይ የግል ከሆነም ግለ ሂስ እንዲያወርዱ ማድረግ አለባቸው፡፡ መቼም ኢህአዴግም ሆነ ኦህዴድ ስልጣን መልቀቅ ስለማይወዱ ብዬ ነው ከስልጣን ይውረዱ ያላልኩት፡፡ ስልጣኑን በግድ እስኪለቁ ግለ ሂስ ያውርዱ ለማለት ነው፡፡

ቸር ይገጠመን!!!

girmaseifu32@yahoo.com

Filed in: Amharic