እኔ እንደዚህ የዲክታተሮች ማህበር የሚመቸኝ ስብሰባ የለም፡፡በአለም ላይ ከሚደረጉ የመሪዎች ስብሰባ እንደ አፍሪካኖቹ የሚመስጠኝና ልቤን የሚነካኝ የረዥም ግዜ ወዳጆች የሚገናኙበት የፍቅር ማህበር የትም አለም ላይ አላየሁም ፡፡
አሁን የአዉሮፓ ህብረት መሪዎች ተሰበሰብን ሊሉ ነዉ በናታችሁ ?! በአዉሮፓ ዛሬ ያያችሁት መሪ ነገ የለም እኮ! የአዉሮፓ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ስተሰበሰቡ ከአንድ ሀገር መሪ ጋር ጎን ለጎን ትቀመጡና ትንሽ ቀደዳ ቀዳቹ ፍሬንድ አገኘዉ ስትሉ በቀጣዩ ስብሰባ ተቀይሮ ይመጣል !ኤጭ !በት ሉክ አት አፍሪካንስ! ጀለሴ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ግን እንደዚህ አይነት ቀልድ የለም…. ሂር ፍሬንድስ አር ፎር ኤቨር …..ዛሬ ያያችሁት መሪ እስከእለተ ሞታችሁ አብሯችሁ ሊሰበሰብ ይቸችላል፡፡ በአፍሪካ ህብረት ”የመሪዎች” ሰብሰባ አንዳንዶቹ መሪዎች አብረዉ የተነሱት የልጅነት ፎቶ አላቸዉ የሚገርመዉ አሁንም ሸብተዉ እና ከዘራ ይዘዉ መሪነታቸዉን ቀጥለዉ ፎቶ ይነሳሉ….የዛሬ 30 አመት በብላክ ኤንድ ኋይት ፎቶ የተነሱ መሪዎች አሁንም ተቃቅፈዉ በ ስሪ ዲ ፎቶ ሲነሱ ትንሽ እንኳን ሼም አይዛቸዉም….
እነኚህ ኮሜዲያኖች በአፍሪካ ህዝብ ሲቀልዱ ይቆዩና በአመት ሁለት ግዜ በህዝቡ እንዴት ሙድ እንደያዙበት ለመነጋገር ይገናኛሉ ….በየአመቱ ከሚደረጉት ሁለት ስብሰባዎች አንደኛዉን ስብሰባ ሁል ግዜ ፊንፊኔ እንድታዘጋጅ የተስማሙ ሲሆን ሌላኛዉን ደግሞ ሙዱ የመጣ ሀገር ጥያቄ አቅርቦ ማዘጋጀት ይችላል፡፡ስብሰባዉን ሲያካሂዱ ግማሹን ለጋዜጠኞች ክፍት ሲያደርጉ ግማሹን ደግሞ ማንም ሳይሰማቸዉ በዝግ ያደርጉታል፡፡
እኔ በበኩሌ አምባገነኖቹ በጋዜጠኞች ፊት ፊደል እየቆጠሩ የሚያደርጉት ንግግር እና የፉጌ ስብሰባ ምንም አይመስጠኘም፡፡ ይልቁንስ የምታጓጓኝ እቺ በዝግ የሚያድርጓት ስብሰባ ነች፡፡ልክ በሩን ዘግተዉ ሲያበቁ በሳቅ እየተንከተከቱ ሙድ የሚይዙብን ነዉ የሚመስለኝ ፡፡
እሺ ሙጌ(ሙጋቤ) እንዴት ይዞሃል እባክህ?! አረጀህ እኮ!
አረ አንተም አርጅተሃል እኮ ያያ?! ህዝቡ አለ?!
አለ እባክህ የት ይሄዳል ብለህ ነዉ ሃሃሃ…?!….
አሪፍ ከዘራ ይዘሃል ከፈርንሳይ ነዉ ያስመጣሃት ….
ሪሁ እንዴት እያደረገህ ነዉ በናትህ?! ወዳጄ እኔ እኮ ይህቺ ስኳር እየተጫወተችብኝ ነዉ ገና በ88 አመቴ አጎበጠችኝ እኮ ሲያናድድ…..ስራ ልታስቆመኝ ነዉ…..
ያ ልጅህ ደህና ነዉ?! ባለፈዉ እንዲተካኝ አስቤዋለሁ ያልከኝ ……. ወዘተ ወዘተ ጫወታዉ ይደራል…..
የሚያናድደኝ ለእነኚህ ዲክታተሮች ሲባል ፌዴራል ከአስፓልት ሲጠራርገን ነዉ፡፡
ተሰብስበዉ አብረን እንነግድ በጋራ እራሳችን እንከላለከል …አፍሪካ የራሷን ችግር እራሷ ትፍታ ወዘተ ወዘተ ይባባሉና ሁሉም ቻይንዬ ስር ለመደፋት ይሯሯጣሉ ፡፡ የሚያስቀኝ እርስ በእርስ የሚነግዱትም ንግድ ከአለም ደረጃ ይዉጣለት ቢባል ከጀብሎ እና ሱቅ በደረቴ ያለፈ ደረጃ የሚሰጠዉ አለመሆኑ ነዉ……
ዘ ዲካታተርስ ተሰብስበዉ ተሰብስበዉ እኛንም ሲያስቸግሩ ከርመዉ ከተስማሙት ቁምነ ነገር አንድ ይዉጣ ቢባል ባለፈዉ የወሰኑት ”አይ ሲ ሲ(አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት) እኛን ብቻ እየያዘን ስለሆነ ከማህበሩ እንዉጣበት” የሚል ነዉ፡፡ እንደፈለግን እንግደል እና እንፍጅ ማንም እንዳይዘን ብለዉ ሲስማሙ ገመናችንን ”አፊሪካን ብራዘር ሁድ” በሚል ሙድ ሰዉ አይስማብን ብለዉ ሲተቃቀፉ ሰዉ ምን ይለናል እንኳን ብለዋል እንዴ?!
እኛ ተገዳዮቹ እና ምስኪኖቹ የአፍሪካ ህዝቦች ብንጠየቅ መሪዎቻችን ን አይ ሲ ሲ ይዞ ማሰር ብቻ ሳይሆን በርበሬ እያጠነ 40 ቢገርፍልን ደስ ይለን ነበር….. እነሱ ግን የሆነ የሬስ(ብላክ እና ኋይት ዲስክሪሚኔሽን) ጫወታ ተጫዉተዉ ከማህበሩ ወጥተንበታል አሉ …ሼመኞች….
በናታችሁ የዘንድሮዉን ዝግ ስብሰባ በሆነ በግርግዳ ቀደዳ ወይም በበር ስንጥቅ ዉስጥ ባየዉ ደስ ይለኛል(መቼም ቻይና የሰራዉ ነገር ቀዳዳ ምናምን አይጠፋዉም ብዬ ነዉ)….ሳስበዉ በራቸዉን ዝግትግት አድርገዉ ቀበቶቸዉን አላልተዉ ሙዛቸዉን እየበሉ
”እሺ ምን አዲስ ነገር አለ?! እ ሃይልሻ ካንተ እንጀምር?!”
ሲሉት ሃይልሻም እየተሸኮረመመ ”ምርጫዉን ደፈንኩት” ሲላቸዉ
” ሲሪየስሊ?! ምርጫዉን መቶ ፐርሰንት አሸነፍክ?! ይሄ ደግሞ አዲስ ሪከርድ ነዉ ገገማ ነህ ባክህ ህዝቡ ግን ምን አለ?!” …ሲሉት
” ያዉ ምን ይላል…አፍሪካ እኮ ነዉ ወደ ሳይሆን በግዱ ይቀበላላ ሃሃሃሃ?!”….
”ኡሁሩ አንተስ ጋር ምን አዲስ ነገር አለ?!”….
አሁሩም ጸጉሯን እያከከች….”ያዉ እንደምታዉቁት እድሜ ለእናንተ ለጀለሶቼ ያ ክስ እኮ ምስክር የለም ተብሎ ተዘጋልኝ” …ኦኦአአ እንኳ ደስ አለህ ባክህ እየተነሱ ያቅፉታል…”እኛ እራሳችን እኮ ለዛች ሺ ለማይሞላ ሰዉ ግድያ ስምህን እንደዛ ሲያጠፉት ደብሮን ነበር”…እያሉ በቆረጣ አልበሽርን ሲያዩት
አልበሽር ”አቦ አናንተ ደግመ በዚህ ነገር መቀለድ አይሰላቻችሁም እንዴ?! በየአመቱ አንድ ቀልድ ቆይ 150 ሺ ሰዉ መግደል ብርቅ ነዉ እንዴ?! አያለ ሲነጫነጭ ይታየኛል…..
”እሸ አትደበር በቃ ትተነዋል ፊልድ ማርሻል ”ሲሉት እንደገና አዳራሹ በሳቅ ይሞላል (የአልበሽር ፊልድ ማርሻል መባልና የሳሞራ ፕሮፌሰርነት እንዲሁም የሳልቫኪር ጄነራልነት ግርም ይለኛል)
እና ይህ የፍቅር ማህበር ከሌሎቹ የትኛዎቹም ስብሰባዎች መበረታት ያለበት የፍቅር ጉባኤ ነዉ ባይ ነኝ፡፡በአመት ሁለቴ የሚደረገዉን ስብሳባ መሌ እንኳን ሞት ሳይወስደዉ ለ22 አመታት በትንሹ 44 ግዜ ተሰብስቦታል …… ሶስቱ የአፍሪካ መሪዎች ዶሳንቶስ (አንጎላ) ሙጋቤ(ዚምባብዌ) እና ምባሶጎ(ኢ.ጊኒ) በድምሩ 104 አመት ገዝተዋል፡፡ 35 አመት በነብስ ወከፍ ማለት ነዉ፡፡ እነ መሌ ኢሳያስ ሙሴቬኒ ጋዳፊ ፖል ቢያ (ካሜሮን ) ኢዲሪስ ዴቢ (ቻድ) አልበሽር፡ ያህያ ጃሜህ (ጋምቢያ ) ከሀያ ሁለት አስከ ሰላሳ የገዙ ናቸዉ አሁንም ይገዛሉ ከመሌ በቀር(ለነገሩ እሱም በመንፈስ እየገዛ ነዉ)፡፡
አዚሁ አዳራሽ ዉሰጥ ስንቴ እንደተሰበሰቡ ስንቴ የቤተሰብ ወግ እንደተጫወቱ አስቡት…..
መሌም በህይወት እያለ
”እሺ መልሻ ልጅህ ሰማህል አደገች ?ት/ቤት ገባች? ብለዉ የጠየቁት መሪዎች እሱም በቀላሉ ስልጣን ስለማይለቅ እዛዉ አዳራሽ ዉስጥ ሰምሀል አገባች? ብለዉ የይጠይቁታል……. እነ ሙጋቤንማ ተዋቸዉ …..እሺ ሙጌ ልጅህ አደገ?!… አዎ……አገባ?! አዎ….. ወለደ?!….. አዎ….. የልጅ ልጅህስ አደገ?!….. አዎ አገባ ?! አዎ ወለደ?! አዎ ….አረ ሼም ነዉ!
ደግሞ የሚገርመኝ ”እንዲሁ እንዳለን አይለየን” እየተባባሉ ”ትንሽ ጋጥ ጋጥ አድርገን እንገናኛ ”ብለዉ ይለያያሉ ፡፡
አይ አፍሪካ?! በአፍሪካ መሪ በሀርድ እንጂ በካርድ አይቀየርም፡፡ መሪዎቹን የሚያሰጋቸዉ ካንሰር እንጂ ካርድ አይደለም፡፡ ዘንድሮም እንዲሁ እንዳለን አይለየን ብለዉ የሚለያዩ ይመስለኛል ፡፡እኛም ተስፋችንን በካንሰር ላይ ጥለን የምርጫ ካርዳችንን ግን እንዲሁ ወደ ኮሮጆዉ መጣል እንቀጥላለን፡፡
ይመቻችሁ…..
ዘ አፍሪካንስ [አንዱዓለም ቡከቶ ገዳ]
Filed in: Amharic