>
4:38 pm - Monday December 2, 1174

ሰማያዊ ፓርቲ:- በነገው ዕለት የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደነበረበት ቦታ ሲመለስ ህዝቡ በቦታው እንዲገኝና ክብሩን እንዲገልጽ ጥሪ አቅርቧል

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደነበረበት ቦታ መመለስ የህዝቡ ትግል ውጤት መሆኑን ሰማያዊ ገለጸ
ፓርቲው በነገው ዕለት ሐውልቱ ሲመለስ ህዝቡ በቦታው እንዲገኝና ክብሩን እንዲገልጽ ጥሪ አቅርቧል

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

NEgere Ethiopia Abune Petrosበአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር ግንባታ ምክንያት ሚያዝያ 24/2005 ዓ.ም ፒያሳ ማዘጋጃ ቤት አካባቢ ከነበረበት ቦታ እንዲነሳ ተደርጎ የነበረው የአርበኛ አቡነ ጴጥሮስ የመታሰቢያ ሐውልት ከሦስት አመት ገደማ በኋላ ነገ ጥር 29/2008 ዓ.ም ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ የህዝቡ ትግልና ያላቋረጠ ጥያቄ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ ገለጸ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት የአቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሐውልት መጀመሪያውንም ከቦታው እንዳይነሳ ህዝቡ አሳስቦ እንደነበር በማስታወስ ሐውልቱ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስም በተከታታይ ጥያቄውን በማንሳት ለታሪኩና ለባለውለታዎቹ ያለውን ተቆርቋሪነት እንዳሳየ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የቀላል ባቡሩ ስራ ሲታሰብ ዲዛይኑ ቅርሶችን በማይነካ መልኩ መሆን እንደነበረበት የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ነገሩ ከሆነም በኋላ ቅርሱ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ ህዝቡ ያደረገው ትግል የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

መንግስት የባቡር ስራው ተጠናቅቆ ወደስራ መግባቱን ተከትሎ ሐውልቱ እንደሚመለስ ያስታወቀው ከህዝቡ የተነሳበትን ጥያቄ ተከትሎ እንጂ ለቅርሱ ከመቆርቆር እንዳልሆነ ከመጀመሪያው በባቡር ዲዛይን ስራው ወቅት (ቅርሱን እንደሚነካው እየታወቀ) ያሳየው ግዴለሽነት አመላካች መሆኑን ኢ/ር ይልቃል ገልጸዋል፡፡ ሐውልቱ በነገው ዕለት ወደቦታው ሲመለስ ህዝቡ ከ5፡00 ጀምሮ ፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ በመገኘት ለሀገር ባለውለታው አርበኛ እና ለታሪኩ ያለውን ክብር እንዲገልጽም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ለጣሊያን እንዲገዙና ኢትዮጵያውያንም ለጣሊያን አሜን ብለው እንዲተዳደሩ እንዲቀሰቅሱና እንዲያሳምኑ በፋሽስት ቢጠየቁም እምቢ ለሀገሬ እና ለሐይማኖቴ በማለት እንኳንስ የኢትዮጵያ ህዝብ ምድሩም ለፋሽስት እንዳይገዛ በማውገዝ መስዋዕት የሆኑ ታላቅ አርበኛ ናቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ለዚህ የተጋድሎ ተግባራቸው ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም ዛሬ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ መታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ችሏል፡፡

Filed in: Amharic