>
5:13 pm - Thursday April 18, 7940

ጥያቄህን ልመልስ-ልጄ [ሰርካለም ፋሲል]

Eskindr Nega By Abebe Gelawለረጅም ግዜ ተራርቀን የማገኛቸው ጓደኞቼ ናፍቆትን ሲያዩት የሚጠይቁኝ “ያ ቃሊቲ የተወለደው ልጅ ነው በጣም አደገ” በማለት ነበር።

አንተም በተደጋጋሚ “ቃሊቲ” የምትለዋን ስም ስትሰማ፣ ቦታው ትምህርት ቤትም ሆነ መዝናኛ ስፍራ አለመሆኑን ጠንቅቀህ ስለምታውቅ፣ ጥያቄህ ፦

“ታስረሽ ነበር እንዴ ?…. እኔም ታስሬ ነበር?” የሚል ነው። ለብዙ ግዜ መልሱን በሽፍንፍን ነበር የማልፈው። ምክንያቴ ደግሞ፣ የመረዳት አቅምህን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር።

እስኪ ዛሬ ከ ዘጠኝ ዓመት በፊት ስለነበረው እውነተኛ ታሪክ ልተርክልህ። ምንም እንኳ አሁንም ትረዳኛለህ ባልልም።

ልጄ፣ “ታስሬ ነበር እንዴ እውነቱን ንገሪኝ?”…ለምትለኝ ፦

“አዎ። ለ9 ወራቶች ከማዕከላዊ -ቃሊቲ አብረን አሳልፈናል”

” ምን አድርጌ?… እጄ ላይ እንደ እስክንድር ብረት ገብቶልኝ ነበር?” ….

ጥያቄህ ብዙ እንደሚሆን እገምታለሁ … እኔም ብዙ መልስ አለኝ። ለዛሬው ግን የታሰርኩበትን የመጀመሪያውን ቀንና የምጧን ሰዓት ብቻ ላውጋህማ።

ከ97 ምርጫ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ችግር…(ታሪኩ ሰፊ ነው) እኔና አባትህን ጨምሮ፣ በርካታ ሰዎች ለሞት፣ለስደት እንዲሁም ለእስር ተዳርገው ነበር።

ጥያቄህ አያልቅምና “የእኔ ሚና በምርጫው ውስጥ ምን ነበር?” ትለኝ ይሆን?…

መልሴ ምንም ነው ፍቅሬ። ምንም ውስጥ የለህበትም።

“ታዲያ እንዴት አሰሩኝ?”…አቤት ጥያቄህ…

በርካታ ሰዎች በምርጫው ሰበብ ታስረዋል ብዬህም አልነበር?..አንተ በቀጥታ ባትታሰርም፣ እኔ ስታሰር አንተን በሆዴ ይዤ ነበር። የአንድ ወር ተኩል ነብሰ ጡር ነበርኩ። ያልረጋ ፅንስ ይዤ ነው የመከራን ህይወት አንድ ብዬ መግፋት የጀመርኩት። እስክትወለድ ግዜ ያሳለፍኩት ግዜያቶች…. አቤት ስቃይህ። አቤት ስቃዬ። ከቃላት በላይ።

እኔና አባትህ የተያዝንባት የመጀመሪያ ቀን!

ህዳር 18/1998 ዓ.ም። ዕለተ-ዕሁድ። ኃይሌ ገ/ሥላሴ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው “ታላቁ ሩጫ” የሚካሄድበት ቀን። (ምናለ በዚህ ቀን ባልታሰርኩና ይሄ ቀን በመጣ ቁጥር ባላስታወስኩት)…ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ። የአጥር በራችን በኃይል ይንኳኳል።…. ግቢው ውስጥ የነበረች አንዲት ዘመዳችን

“ማነው?…እረ መጣሁ..ቀስ በሉ” እያለች የግቢውን አጥር ከፈተች።…. በሩን ስትከፍት ያጋጠማት ግን፣ጉንጯ ላይ ያልታሰበ ጥፊ ነበር። …(የአጥር ግቢውን መንኳኳት ተከትሎ እኔና አባትህ ሁኔታዎችን በመስኮት እየተከታተልን ነበር) …ቁጥራቸውን ልገምትልህ እችላለሁ። ወደ 10 የሚጠጉ የፌዴራል ፖሊስ፣ቁጥራቸውን ማስታወስ የማልችል ሲቪል ለብሰው መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች በመንጋ(እንደ ንብ ) ግቢው ውስጥ ዘለቁ።

ክላሻቸውን ወድረው ቤታችን ውስጥ ተሰገሰጉ። ልጄ፣ በአንድ ግዜ ቤቱን ጦር ሜዳ አስመሰሉት። ከዚያስ?..ከዚያማ … አቤት የሰው ልጅ ጭካኔ!….(አባትህ በተደጋጋሚ ልጄ ጥላቻ ይዞ እንዳያድግ ይላል። ቃሉን ተግብርለት እሺ!)….አባትህን በአንድ ክፍል፣እኔን በሌላ ክፍል ነጣጥለው አስቀመጡን።….በዱላ ብዛት እነሱ ወይስ እኛ ደከመን?…እኔንጃ። የማስታውሰው ነገር እኔ ክፍል ያለው ጠብደል የፌዴራል ፖሊስ ሲጫወትብኝ ብቻ ነው። እዚህ ላይ ልብ በልልኝ…”ሲጫወትብኝ” እንጂ “ሲያጫውተኝ” አለማለቴን። ….ይመታኛል…ይመታኛል….ህምምም!!…
“ምንሽን መታሽ?” አትበለኝ ልጄ። በዱላ የቀረው የሰውነቴ ክፍል ስለሌለ ” እዚህ ጋር፣እዚያ ጋር ” አልልህም።…በዚህ መካከል ሁሌም የሚገርመኝንና የማልረሳውን ግን ሳልነግርህ አላልፍም። ከመታሰሬ 2 ዓመት ቀደም ብሎ ከባድ የጤና ዕክል ገጥሞኝ ነበር። በዚያ ህመም ብዙ ተፈትኜበታለሁ። በወቅቱ እዚያ የጤና ዕክል ያጋጠመኝ የሰውነቴ ክፍል ላይ እንኳንስ ሲመቱኝ፣ሲያወሩኝ ስሜቴን ይረብሸው ነበር። እናማ…ይሄ ቅልብ ፌዴራል ያንን ቦታ እየደጋገመ በርግጫ ይለኝ ጀመር። ህመሜን ያወቀ ይመስል።-ህምምም!… ቢጨንቀኝና የዱላውን ቦታ ቢቀይርልኝ ብዬ

“እዚህ ጋር አትምታኝ ኦፕራሲዮን አለኝ” አልኩልሃ…..

ይህ ጨካኝ ፍጥረት ምን አለኝ መሰለህ?…

“ሙቺበት”…

ድምፁ ጆሮዬ ላይ አሁን ድረስ አለ”ሙቺበት”…ህምምም! (እንግዲህ ያልተቆረጠለት ነብስ አይወጣ እንዴት ልሙትበት?….) በመጨረሻም ከዱላው ጋብ አለና ባደረገው የወታደር ከስክስ ጫማ፣በአንደኛው እግሩ የተረከዙ ጫፍ የእግሬ ጣቶች ላይ ቆሞ ተሸከረከረብኝ። (ማለትም፣ ማንም ሰው በአንድ እግሩ የተረከዙ ጫፍ ላይ ቆሞ መሽከርከር)….ከዚያ ምን ሆነ መሰለህ ልጄ …እግሬ ላይ ያለው ቆዳ በከፊል ተገሸለጠ። ቆዳ ሲላጥ ደግሞ፣ ደም እያቸፈቸፈ ማቃጠል ብቻ….እስኪ የእኔ ይብቃህና ወደ አባትህ ልመልስህ፦

ከላይ እንደገለፅኩልህ አባትህን ሌላ ክፍል ወስደውታል ብዬህም አልነበር?…የእኔ ዱላ ጋብ ሲል የእሱን አዳምጥ ገባሁልህ። ….ጓ…ጓ..ጓ… የፈጣሪ ያለህ! የማያቋርጥ ጓጓታ። … የእኔ ዱላ ካቆመ ቢያንስ ከ 15 ደቂቃ በኅላ፣ እኔ ያለሁበት ክፍል ይዘውት መጡ።

ልጄ፦ ከሰዓታት በፊት አጠገቤ የነበረው እስክንድር አልመስልሽ አለኝ።

“እና ማነው?”…ብለህ ትጠይቀኝ ይሆን?….ህምምም!

…ወደ ክፍሌ የዘለቀውማ አባትህ ነው። ግን፣ግን… ፊቱ በደም ተነክሯል። በተለምዶ አንጎል ብለን የምንጠራው የጭንቅላታችን ክፍል ላይ በቀኝም በግራም በኩል ብይ የሚያካክሉ ዕባጮች ይታዩኛል። …. ክፉኛ ጎድተውታል። ከጥቂት ደቂቃ በፊት እኔ ላይ የደረሰውን ሁሉ ዘንግቼ፣ ያ “ጨካኝ” የፌዴራል ፖሊስ አጠገቤ መቆሙንም ረስቼ ” አፈር ልብላልህ ” ስል መናገር….አላስችል ብሎኝ እንጂ ምነው በቀረብኝ።…ከየት መጣ ሳልል ሲቪል የለበሰ ግለሰብ “ሸርሙጣ” ብሎ በጥፊ ያጣድፈኝ ጀመር…ህምምም!(አባት ሆይ ጥላቻንና ቂምን ከእኔ አስወግድልኝ)….

እስክንድር እኔ በነበርኩበት ክፍል ብዙም አልቆየ። ያመጡትም የእጅ ስልኩን (ሞባይሉን) እንዲሰጣቸው ነበር። የእኔንም አብረው ወሰዱት። ከዚያማ….እኔን ሲደበድበኝ ለነበረው የፌዴራል ፖሊስ “ጠብቃት”ብለው እስክንድርን ይዘውት ወጡ። ከቤት ብቻም ሳይሆን ከግቢ። ….በግምት ከ1 ሰዓት በኅላ እኔ ወዳለሁበት ክፍል አንድ ሲቪል የለበሰ ግለሰብ፣ለፖሊሱ “ይዘሃት ና” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈና በፍጥነት ወጣ።
“ተነሽ ቀጥይ”የፌዴራል ፖሊሱ ድምፅ።
እንዴት ልቁም… ሰውነቴ ዛል ብሏል። …. “ውሃ ጠጥቼ ልውጣ?” ስል ተማፀንኩት። አልከለከለኝም። በቁሜ አንድ ብርጭቆ ውሃ ጠጣሁናበእሱ አጃቢነት ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ።
ከአንድ ሰዓት በፊት ከእኔ የተለየው እስክንድር የፌዴራል ፖሊስ መኪና ውስጥ ቁጭ ብሎ አየሁት። የት አድርሰው መልሰውት ይሆን?…. እኔም እዚያ መኪና ውስጥ እንድገባ ተደረኩ። ምንም እንኳ ከሰዓታት በፊት አሰቃቂ ግፍ ቢፈፀምብንም፣ ሁለታችንም ስንተያይ ፈገግ አልን። ባዶ ፈገግታ። እክንድርና ኔና “አይዞሽ፣አይዞህ ” መባባል ስንጀምር ፣ምንም ዓይነት ንግግር ማድረግ እንደማይፈቀድልን አንዱ ሲቪል ለባሽ ቆጣ ብሎ ነገረን። ….ጉዞ ወደ ማዕከላዊ።
ማዕከላዊ እንደደረስን አንድ ቢሮ ደጃፍ ላይ ሁለታችንንም እንድንቀመጥ አድርገውን እኛን ያመጡን”ጀብደኞች” ጥለውን ሄዱ።
በዚህ መካከል ለአባትህ ሁለት ጥያቄ አቀረብኩለት

“አንጎልህ ላይ በምን መቱህ?”

“በሰደፍ”

“ከቤት ከወሰዱህ በኅላ የት ቆይታችሁ ነው ወደኔ በድጋሚ ያመጡህ?”

“ቦታውን አላውቀውም…በፍጥነት እየነዱ አደባባይ አሽከረከሩኝ”
(ካለፈ በኅላ “የእኛማ ሙሽራ”…ስል አንጎራጎኩ። እኔ አደባባይ ሲዞር የማውቀው ሙሽራ እንጅ እስረኛ ባለመሆኑ )

ልጄ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አንተን በሆዴ ይዣለሁ። ታሪክህ ይኸው ነው። ግን አልጨረስኩም። ይህንን ነገር ወደ ኅላ ተመልሼ ስተርክልህ ስሜት ውስጥ እንዳልገባና የነበረውን ዕውነታ ብቻ ነው በተቻለኝ መጠን የምገልፅልህ። አልጨረስኩም ዘንባባዬ እቀጥልልሃለው።

ጥያቄህን ልመልስ-ልጄ (ክፍል 2)

ማዕከላዊ ግቢ ውስጥ አንድ ቢሮ ደጃፍ ላይ እኔና አባትህ መነጋገር እንደጀመርን ከቢሮው ውስጥ አንድ ፀይም ሲቪል የለበሰ ግለሰብ ወጥቶ በቁጣ ምንም ዓይነት ንግግር እንዳናደርግ አስጠነቀቀን። በዚህ ብቻም አላበቃ…አንድ ጠባብ መዝጊያ ወደሚገኝበት በር በእጁ እየጠቆመ ወደዚያ እድገባ አዘዘኝ። ማማ ላይ ለሚጠብቅ ፖሊስም ” ሁለት ቁጥር አስገባት” ሲል ተናገረ….ቤቱን አውቀዋለሁ ። ከዚህ ቀን በፊት ለአንድ ቀን ውዬበታለሁ። (ታስሬበታለሁ)…አባትህን በተቀመጠበት ድንጋይ ላይ ትቼው …”ቻው እስክንድር፣ቻው ሰርክዓለም አይዞሽ” ብቻ ተባብለን ተለያየን።…የመጨረሻ ስንብት!!….(ከዚህ በኅላ ያለውን መፃፍ ከጀመርኩ ማብቂያም የለውምና ቃል ወደገባሁልህ የምጧ ቀን እንዋብ….

Serkalem-and-Eskinder with Nafkotልጄ ስታሰር ” የአንድ ወር ተኩል ነብሰ ጡር” ነኝ ማለቴን አልዘነጋከውም…. ፅንሱ(አንተ) እያደግህ…እያደግህ…መጣህና 8 ወር አካባቢ ስትደርስ…. መጠነኛ ህመም አጋጠመኝ። ጉዞ ፖሊስ ሆስፒታል። እዚያም፣ ከፍተኛ ደም ግፊት እንደያዘኝ፤ በእርግዝና ግዜ ማንም ሴት ላይ እንደሚያጋጥም፣ በቂ ክትትል ካልተደረገለት ግን ፅንሱን ሊያጨናግፍ እንደሚችል በዶክተሩ ተገልፆልኝ መተኛት እንዳለብኝ ተነገረኝ።….

በዚህም፣በፖሊስ ሆስፒታል ለብቻዬ አልጋ እንድይዝ ተደረገ።….ይሁን እንጅ፣ የጥበቃው ነገር ግን እጅግ የሚያም ነበር። ጠዋትና ማታ በሁለት ሽፍት በሶስት ወንዶችና በአንድ ሴት ፖሊስ እጠበቃለሁ። ሴቲቷ እክፍሌ ውስጥ አብራኝ ስታድር፣ወንዶቹ በሩ ላይ ይቀመጣሉ። በአጠቃላይ በ4 ወታደሮች ማለት ነው።….ልጄ እውነት እልሃለው ረጅም ዕድሜ እመኝለታለሁ እኔን ሲከታተል ለነበረው ዶክተር።….ጠዋት እኔ ጋር በመጣ ቁጥር በር ላይ መሳሪያ ይዘው ከከበቡኝ ፖሊሶች ጋ ጭቅጭቅ ውስጥ ይገጥማል…
.” እንዲህ ሆና የት ትሄዳለች ብላችሁ ነው በሩን የምትከቡት…በመስኮት መዝለል ትችላለች?ራቅ በሉ …እርጉዝ ፊት መሳሪያ አይያዝም”…በዕየለቱ የምሰማው ክስተት….እሱም መናገሩን አያቆም፣እነሱም አሰራራቸውን አይቀይሩ። …. በዚህ ሂደት ውስጥ ሳለን ነበር አንድ ሌሊት የማላውቀው ስሜት ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ።….. ቁርጠት ልበለው ወይስ ሌላ ስያሜ?… እንጃ። ስለሁኔታው ማንን ልጠይቅ?…ማርገዜን እንጅ፣ስለምጥ ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበረኝ። በቀን ውስጥ ለ20 ደቂቃ መጥታ እንድትጠይቀኝ ከተፈቀደላት እናቴ ጋርም በዚህ ጉዳይ አላወራም።ስለማፍራት… እናማ ልጄ… ከቁርጠት መሰል የማላውቀው ስሜት በመቀጠል ሽንቴ የመጣ መሰለኝ…ከአልጋዬ ተነስቼ ሽንት ቤት ሳልደርስ…. ወይ መበላሸት…

ክፍሌ ውስጥ ወደተኛችው ሴት ፖሊስ ተመለከትኹ…. ጥሩ እንቅልፍ ላይ ናት። …በር ላይ ከሚጠብቁት አንዱ ሁኔታዬን ያየ ክፍሌ ገባ… መንገርም አላስፈለገኝ። የሆነውን አየ።
” ተረኛ ነርስ እንዲጠራልኝ፣ከዚያ በፊት ግን መወልወያ እንዲያቀብለኝ ጠየኩት። (በክፍሌ ትይዩ ባለ ክፍል ውስጥ መጥረጊያና መወልወያ..ሌሎችም ቁሳቁሶች ፅዳቶች ሲያገቡና ሲያወጡ በመመልከቴ)….ፖሊሱም መወልወያውን አቀብሎኝ ነርሷን ጠርቶልኝ መጣ!…

ቁርጥ ነው ልጄ መምጣት ፈልገሃል..መፈታት
አምሮሃል…የቃሊቲ ኑሮ ሰልችቶሃል…

ለነርሷ የገጠመኝን ሁሉ ነገርኳት ….”ምጥ ሊጀምርሽ ነው..መንገድ እየጠረገ ስለሆነ አትንቀሳቀሺ… እየመጣን እናይሻለን” ብላኝ ወጣች። በጣም ደነገጥኩ። ምጥ …ምጥ…ኡፍፍፍፍ!…

ልጄ ያቺ ሌሊት ከቀን የጀመረች ይመስል ረዘመችብኝ።…. አንተም ማስጨነቅህን ጨምረሃል። እረ ብሶብሃል….እንዲሁ በሃሳብ ዓዕምሮዬ እንደተበጠበጠ ለራሱ ሲል ነጋ።…..
ጠዋት ዶክተሬ እኔ ጋር ከመድረሱ በፊት የሆነውን ከተረኛ ነርሶች ሰምቶ ኑሮ፣ “አይዞሽ” በማለት፣ ለነርሶቹ…እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ክፍሌ ውስጥ እንድቆይ፣ከ 10 ሰዓት በኋላ ማዋለጃ ክፍል እንድወሰድ…እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ እንዳምጥ፣ 4 ሰዓት ድረስ መውለድ ካልቻልኩ ተደውሎ እንዲጠራና በቀዶ ጥገና እንደሚያዋልደኝ ገልፆ ወጣ።…
ልጄ… አሁን እናቴ፣(አያትህ) ስንቋን ቋጥራ እኔ ጋር ሆስፒታል ውስጥ ትገኛለች።ሌሊት የሆነውን ሁሉ ገለፅኩላት።… ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። አቅም በማጣቷ። ልትወልድ የምታምጥ ልጇን ምንም ዓይነት እርዳታ ሳታደርግላት ትታት እንደምሄድ በማወቋ። ህምምም!…

“የማርያም ሃራስ ባዶ ቤት ትቼሽ ልሂድ…ወይኔ ” ትላለች ሽንፈት ያጋጠማት እናቴ።
ምንም ችግር እንደሌለና በፅሎቷ ብቻ ታስበኝ ዘንድ አረጋግቼ ገለፅኩላት።…. የመጠየቂያ ሰዓቷም አልቆ ግንባሬን ስማ ወጣች።….10 ሰዓት ሆነና እኔም በአልጋ(ስትሬቸር) እየተገፋሁ ጉዞ ማዋለጃ ክፍል…

ልጄ….መምጣትም ፈልገህ፣ መውጣትም ጠልተህ…. በቃ የምጥ ስቃይ እንጅ ወፍ የለም። አዳከምከኝ።… በዚያ ስቃይ ውስጥ እንደምንም ምሽት 4 ሰዓት ሞላ…. ዶክተሬ ሊደወልለት። ግልግል። ….አሁን ሁሉ ነገር ከአቅሜ በላይ ነው። ተዳክሜያለሁ። ከዚህ በኅላ የማውቀው ዶክተሩ መጥቶ ኦክስጅን አፍንጫዬ ላይ ተክሎ ወደ ኦፕሬሽን ክፍል ስናመራና እንደወትሮው በዶክተሩና በዋርድያው መካከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ መፈጠሩን ነው። (በዚያ ሰዓት አቅም ቢኖረኝ ከት ብዬ በሳቅኹ)….

“ደግሞ የምን ጭቅጭቅ ተፈጠረ ?”….ካልከኝ..

.ወደ ኦፕሬሽን ክፍል አብሬ ካልገባሁ በሚል ዋርድያና በዶክተሩ መካከል….

“ከዚህ ማለፍ አይፈቀድም”…ዶ/ሩ

“እስረኛ እኮ ናት”…ዋርድያ

“ኦፕራሲዮን ክፍል የምትገባው አንተ ነህ ኦፕራሲዮን የምታደርግልኝ?” ዶ/ሩ

“እንዲያውስ እዚህ ጋር ቁሙና ለአለቃዬ ላሳውቅ”..ዋርድያ

ስልክ ደውሎ ሁኔታውን ገለፀ …

ከዚያኛው ወገን ያለውን ምላሽ መስማት ባንችልም፣ፖሊሱ ባለበት መቆሙን ከተኛሁበት አልጋ(ስትሬቸር ) ላይ ማረጋገጥ ችያለሁ። …

በመጨረሻም ልጄ፣ ከማደንዘዣ ስነቃ …አጠገቤ አልነበርኽም። ወለድሽ ተባልኩ እንጅ፣ መልክህን አላየሁትም። ወለድሽ ተባልኩ እንጅ ጡት አላጠባሁህም። ወለድሽ ተባልኩ እንጅ እንደእናት አላቀፍኩህም። ወለድሽ ተባልኩ እንጂ …
.መፈቻህን ብቻ እቀጥልልሃለው…”

ጥያቄህን ልመልስ -ልጄ (ክፍል 3)

Ethiopian mother Serkalem Fasil with her child Nafkotቀጣዩ ጥያቄህ ” ከወለድሽኝ በኅላ ካላቀፍሽኝ የት አስቀመጥሽኝ?… ለማን ሰጠሽኝ?..” ይሆናል ብዬ ገምቻለሁ። …ልጄ የዚያን ቀን ለማንም አልሰጠኹህም። ማንም አላቀፈህም። አንድ ቤት ውስጥ ብቻህን ተቆለፈብህ እንጂ…ህምምም!!…(ዓይኖቼ እምባ አዘሉ)…ልጄ ስትወለድ ከኖርማል ኪሎ በታች ነበርክ። በዚህም በአስቸኳይ ኢኒኩቤተር ውስጥ መግባት ነበረብህ። ይህ ደግሞ፣ የሀኪሞች ውሳኔ ነው።….እኔ የወለድኩህ “ፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ ነው” ብዬህ ነበር።… እዚያ ሆስፒታል ደግሞ ይሄ መሳሪያ የለም።….

“እናስ… ምን ሆንኩኝ?”…የማያልቅ ጥያቄ…

እናማ …መሳሪያው ወደ ሚገኝበት ጥቁር አምበሳ ሆስፒታል በዚያ ውድቅ ለሊት ተወሰድክ…. ግን፣ልጄ የወሰደህ አምቡላስ ይዞህ ተመለሰ።…

“ለምን?”…

ምክንያቱማ…እናትህ ወይም አባትህ ኃላፊነቱን ወስደው እዚያ መሳሪያ ውስጥ እንድትገባ መፈረም ስለነበረባቸው።

“ለምን አልፈረማችሁልኝም?” ….ልትለኝ ይሆን?…ተረጋጋና ልመልስልህ…
ከላይ እንደነገርኩህ እኔ፣ ከማደንዘዣ ባለመንቃቴ።ግን ፣ ነቅቼ ቢሆንስ?…..አባትህ ደግሞ እስረኛ ስለነበር ውሎና አዳሩ ቃሊቲ በመሆኑ ።ህምምም!..የጥቁር አምበሳ ሀኪሞች አባትህ መጥቶ እንዲፈርም ቢጠይቁም፣ እነዚያ ከሰው ተፈጥረው እንደሰው ማሰብ ያቃታቸው፣ የልጆች አባት ሁነው ልጅ የሚጠሉ አሳሪዎቻችን ” አሻፈኝ አናስወጣውም” በማለታቸውና ፈራሚ በማጣትህ ነው ተመልሰህ የመጣኸው።…ህምምም!….እናም… ፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ ክፍልህ በኤሌትሪክ ሶኬት እየሞቀ ለ 15 ቀን እንድትቆይ ተደረገ።….(መድሂያለም ከእነእናትህ አብዝቼ እወድሃለው። አብዝቼ አመልክሃለው፣አንተን ስክድ የቆምኩበት መሬት ይክዳኝ)….ከስሜት ልውጣ…አሳዛኙ የህይወት ታሪክህንና ፍቺህን አሁን ላይ አቃተኝ…

Filed in: Amharic