>

እጅ በደረት ኣድርገህ ንዳ ! የታክሲ ሹፌሮች እዳ [ሄኖክ የሺጥላ ]

Henok Yeshitilaየኣንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ኣንድ ኣምባ ገነን መምህር ነበረኝ። ኣያሌው ይባላል ። ሰውየው በጎማ መጋረፍ ይወድ ነበር ። መፈራት ይወድ ነበር ። ከኣምባገነንነቱ ብዛት የክፍል ስራ ሰጥቶ እጅ በደረት ይለን ነበር ። ያ ኣልበቃ ብሎ በክፍል ውስጥ እየተዘዋወረ የክፍል ስራውን ያልሰራ ተማሪ ኣስወጥቶ በጎማ ይገርፍ ነበር ። በሱ ክፍለ ጊዜ በጎማ የማይገረፈው እሱ ብቻ ነው ። ታዲያ ኣንድ ቀን እንደለመደው የክፍል ስራ ሰጥቶን ወዲያው « እጅ በደረት!» ብሎ ኣዘዘን ። ዱላው የሰለቸን ጥቂት ነውጠኛ የተባልን ተማሪዎች ቀደም ብለን ተሰብስበን ተማክረን ነበር ። እንደተለመደው እጅ በደረት ብሎ ሲያዝ እኔ ጥያቄ ኣቀረብኩለት ። «ቲቸር! »ኣልኩ ትንፋሼን ሰብሰብ ኣድርጌ ። « ምን ኣባህ ፈለክ!!!» ኣለኝ ። ለራሴ ራሴን « በርታ !» ኣልኩት ። « ቲቸር እጃችን በደረታችን ላይ ከሆነ ፥ የክፍል ስራውን እንዴት እንስራው? በምን እንስራው ? » ኣልኩት ። ማንም እንዲህ ደፍሮ ጠይቆት ስለማያውቅ በጣም ተናደደ ። « ና! ና! ውጣ!» ኣለኝ በቁጣ ። ከትምህርት ቤቱ ያትክልት ማጠጫ ላይ ቆርጦ ባዘጋጀው የውሃ ጎማ ቀኝ እግሬን ባቴ ስር በሃይል መታኝ ። ጎማው ከባቴ ላይ ሙዳ ስጋ ይዞ ተነሳ ። ምክንያቱን ባላውቀውም ኣላለቀስኩም ። ይበልጥ ተናደድኩ « ቲቸር » ኣልኩት እልህ በተናነቀው መንፈስ ውስጥ ሆኘ « ቲቸር ፥ እጃችን በደረታችን ላይ ከሆነ የክፍል ስራውን እንዴት እንስራው ?!» ፊቴ ላይ ንዴቴ ይታይ ነበር ። መምህሩ መብረቅ እንደመታው ሰው በቆመበት ሲያንስ ታየኝ ። የውሃ ጎማውን ኣስቀመጦ ከክፍል ይዞኝ ወጣ ። ወደ ውጭ ስንወጣ ከታፋዬ ስር የሚፈሰውን ደም ኣስተዋለ ፥ በዝምታዬ ፍፁም ተረብሿል ። ሊያባብለኝ ሲሞክር ፥ ኣሁንም ለጥያቄ መልስ እንዲሰጠኝ ኮስተር ብዬ ተመሳሳይ ጥያቄ ለሶስተኛ ግዜ ተየኩት ። «እሺ እመልስልሃለሁ መጀመሪያ ና ሻይ ክበብ እንሂድ» ብሎ በትምህርት ቤታችን ካለው የሻይ ክበብ ወስዶ ዳቦ እና ሻይ ገዛልኝ ። መብላት እንደማልፈልግ ነገርኩት ።ልበላ የምችለው ግን ተማሪዎቹን በሙሉ ይቅርታ ከጠየቀ ብቻ እንደሆነ ነገርኩት ። ምናልባት ሰውነቴ ላይ ያደረሰው ኣደጋ እጅግ ኣስፈርቶት ይሆን ኣላውቅም ተስማማ ። እኔም ወደ ቤት ስሄድ ቁስሉ ስጫወት ወድቄ እንደሆነ ተናገርኩ ። እጅ በደረት ከዚያን ቀን ጀምሮ ለኛ ቀረ !

Henok Yeshitla - metatifየወያኔንም ሁለት እጃችሁን መሪ ላይ ኣድርጋችሁ ንዱ የሚለው ህግ የዚህን መምህሬን ታሪክ ኣስታወሰኝ ። መምህሬ እጅ በደረት እያለ ሲገርፍ ነበር የኖረው ፥ የፈለገውን ማሰር የለመደ መንግስት « ኣንድ እጅን ከመሪ ላይ ኣውርዶ መኪና መንዳት ያስቀጣል » ያለው ያው እንደ መምህሬ ነፃነት መቀማት ልምድ ሆኖበት ነው! መኪና መንዳቱን ትተን እጃችንን ኪሳችን ውስጥ ኣድርገን ወክ ስናደርግ (ስንራመድ ) ቢያይ እንዲህ ያለው ስርኣት « እጅ በኪስ ውስጥ ከቶ መሄድ ኣይቻልም !» የሚል ህግ ያወጣል ፥ ምክንያቱም የህዝብ ነፃነት ስለሚያስፈራው ።

ሁለት እጅህን ከመሪ ላይ ሳታነሳ ንዳ የሚለው የትራፊክ ህግ ፥ እጅህን በደረትህ ላይ ኣድርገህ የክፍል ስራውን ስራ ከሚለው መምህር ጋ በምን ይለያያል ? ሁለት እጄን ከመሪ ላይ ሳላነሳ እንድነዳ የሚፈልግ መንግስት ” መስኮት ፥ በር ፥ ቴፕ ፥ ማርሽ ፥ ወንበር ፥ የሙቀት መቆጣጠሪያ፥ የዝናብ መጥረጊያ ፥ የውሃ ማስቀመጫ ፥ የስልክ ቻርጀር መሰኪያ ፥ የሲጃራ መለኮሻ ያለው መኪና እንድነዳ የፈቀደልኝ ፥ እጄን በደረቴ ላይ ኣድርጌ የክፍል ስራዬን እንድሰራ ከሚያዘኝ መምህሬ ጋ ኣንድ ኣይነት ስለሆኑስ ኣይደለም ?” እጄን መሪዬ ላይ ባላደርግ ጥፋቱ የኔ ኔው ወይስ መስኮት ፥ በር ፥ ቴፕ ፥ ማርሽ ፥ ወንበር ፥ የሙቀት መቆጣጠሪያ፥ የዝናብ መጥረጊያ ፥ የውሃ ማስቀመጫ ያለው መኪና ወደ ሃገር ሲገባ «ኣይሆንም!» ያላለው መንግስት! ?እነዚህን ሁሉ ነገሮች የያዘ መኪና ወደ ሀገር ሲገባ እያየ ዝም ያለው መንግስታችን ነው መቀጣት ያለበት ወይስ እኔ እነዚህ ነገሮች እንዳልተፈጠሩ ቆጥሬ እጄን መሪ ላይ ሰክቼ እንድነዳ የተፈረደብኝ ? ያኔ መምህሬን « እጄን በደረቴ ኣድርጌ እንዴት የክፍል ስራውን ልስራው » እንዳልኩት ፥ ዛሬ ደሞ « የዝናብ መጥረጊያውን ፥ ማርሹን ፥ መስኮቱን እና ወዘተውን ምን ኣድርጌው ነው ሁለት እጄን መሪ ላይ ለጥፌ የምንዳው ?» ብዬ መንግስቴን ለመጠየቅ የተገደድኩት ለዚያ ነው ።
ደሞ ሁሉም ነገር እኮ በሁለት እጅ ኣይሰራም ። ማለቴ በሁለት እጅ መንዳት በሁለት እጅ እንደመስረቅ ኣይመችም ። በሁለት እጅ መኪና መንዳት እና በሁለት እጅ ክላሽ መያዝ እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው ። ክላሹ የዝናብ መጥረጊያ የለው ፥ የውሃ ማስቀመጪያ የለው ፥ መስኮት የለው ፥ ወንበር የለው ። ክላሹ ኣንድ መሃይም፥ ህዝቦቹ ላይ መተኮስ የማይቀፈው ባለ ሁለት እጅ ስንኩል ወታደር ያስፈልገው ይሆናል ፥ ታክሲው ግን የሚያስፈልገው መኪና «ባግባቡ» የመንዳት ብቃት ያለው ሹፌር ይመስለኛል። ክላሹ ማርሽሁም ፍሬኑም ፥ ፍሪሲዮኑም ቃታው ብቻ ነው ፥ ሃይሉን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም እና ኢላማውን ላለመሳት ኣእምሮውን ሳይሆን ሁለት እጆቹን ብቻ ሲጠቀም የኖረ ገዳይ ብቻ ነው የሚፈልገው ። የታክሲ ሹፌሩ ግን ተሳፋሪውን ኣነጣጥሮ ኣይተኩስ ፥ ወይም ደሞ የተሳፋሪው ኪስ ውስጥ ሲገባ ኣልተያዘ ፥ የህጉ እንድምታ ምን ይሆን ?
ሌላው እና እጅግ የገረመኝ ህግ ደሞ « የፍሳሽ ውሃ መርጨት» ያስቀጣል የሚለው ነው ። እነዚህ ሰዎች የት ሄደው ይንዱ ? ኣሁን ማን ይሙት እኛ ሃገር ከመንገዱ ጉድጓዱ ኣይረዝምም ? ዝናብ በዘነበ ቁጥር በየቦታው የሚነፋረቁት የከተማው ቦዮች ለቅጣት ምክንያት ከሆኑ ፥ መቀጣት ያለበት ጥራቱን ያልጠበቀ መንገድ የሚሰራው መንገድ ትራንስፖር ( መንግስት ) ነው ወይስ ደረጃውን ባልጠበቀ መንገድ ላይ ነድቶ ውሃ የረጨው ሹፌር ?

ብቻ ትንሽ ቆይታችሁ እጅ በደረት ኣድርጋችሁ ንዱ ኣንዳትሉን ! ወይ ዘመን !ያ

Filed in: Amharic