>
6:59 am - Saturday July 31, 2021

ጠቅላይ ሚንስትራችን ከአንዳንድ ምሁራን ጋር . . . .[ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ]

Dr. Bedilu Waqjira (2)ሰሞኑን ጠ/ሚንስትራችን ከምሁራን ጋር ስብሰባ እንዳደረጉ በዜና ማሰራጫዎች ሰማሁ፡፡ አዋዋሌ የምሁራን ቀዬ ተብሎ በሚመሰከርለት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቢሆንም፣ የኢህአዴግን የደረጃ ምደባ አላለፍኩም መሰል ጥሪው አልደረሰኝም፡፡ ጠ/ሚንስትርን ያህል ባለስልጣን ሲሰበስብ ባለመጠራቴ፣ ለምን? ብዬ አንድ ሁለት የቅርብ አለቆቼ ዘንድ ደወልኩ፤ ሁለቱም አልሰሙም፡፡ በማግስቱ፣ ‹‹ከረዳት ፕሮፌሰር በላይ ካሉ ምሁራን በጥንቃቄ መርጣችሁ ላኩ፣ ተብሎ ከላይ ነው በጥንቃቄ ምሁራን የተመረጡት›› የሚል ወሬ በቀዬአችን ተናፈሰ፤ የማእረግ ደረጃው ቢኖረኝን የጥንቃቄ ምርጫውን አላለፍኩም፡፡ አልፌ ቢሆን፤ ተሰብስቤ ቢሆን፣ ብዬ ጠቆጨሁ ስለሀገሩና ስለሀገሩ ህዝቦች የማያስጨንቅ ጤንነት ምንድነው?
.
ክቡር ጠቅላይ ምኒስትር፣ ‹‹ብሄራዊ መግባባት›› ላይ መድረሳችሁን፣ ከተሳታፊዎች ስስማ በምሁራኑ ቀናሁባቸው፡፡ እኔ ይኸው ትልቁ ችግሬ ከኢህአዴግ በብዙ ጉዳዮች አለመግባባቴ ነው፤ መቼም ‹‹መግባባት ላይ ደረስን›› ከተባለ፣ ከስብሰባው በፊት አትግባቡም ነበር ማለት ነው፡፡ እና በአንድ ቀን ስብሰባ እንዲህ መግባባት ከተቻለ፣ ምነው እኔም እጣው ደርሶኝ፣ ተግባብተን ተኝቼ ባደርኩ!
.
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፣ ተስብሳቢዎቹ፣ ‹‹መንግስት ምን እንደሚሰራ፣ የአላማውንና የልማቱን ግብ ከስብሰባው ስለተረዳን፣ ከመንግስት ጎን ቆመን እንሰራለን፤ ለወደፊቱም በየመንፈቁ በስብሰባዎ አይርሱን›› አይነት ንግግር ሲያደርጉ፣ በኢቲቪ ሰማሁ፡፡ እውነት እሎታለሁ! አይመኗቸው! ዋሽተዋል! እንኳን ረዳት ፕሮፌሰሮቹ፣ በጥቃቅን የተደራጁትና ጉልት ቸርቻሪዎቹም፣ ኢህአዴግ ምን እንደሚሰራ፣ አላማና ግቡ ምን እንደሆነ ያውቃሉ፤ ቲቪውና ራዲዮው ጆሮ በጥጥ ቢደፈን እንኳን፣ አናት በርቅሶ ያሰርፃል፤ ደግሞ ስላልተረዳን ነው! ለምን ይዋሻያል!! ለነገሩ ለመሸዋወድ ካልሆነ እርሶም አያምኗቸውም፡፡
.
ክቡር ጠ/ምኒስትር፣ እኔ እርስዎን ብሆን፣ ጨንቆኝም ይሁን ደስ ብሎኝ፣ ምሁራንን ማነጋገር ብፈልግ፣ ‹‹ሁሉንም ጥሩልኝ›› ነው የምለው፤ አዳራሽ ካልበቃ ደግሞ፣ ‹‹የሚጠሉንንና የሚተቹንን መርጣችሁ ጥሩልኝ›› ነበር የምለው፡፡ እኔ የምልዎት፣ እነዚህ ምሁራን ከቀዬአቸው የራቀውን ትተው፣ የዩኒቭርሲቲዎቻችንን ውድቀት፣ በጎሳ ፍሬም የተቀነበበው ሁለንተናዊ አስተሳሰባችን እያበቀለ ያለው ቀንድ ብሄራዊ ህልውናችንን ዘንጥሎ ሊጠለው እንደሚችል ነግርዎታል? ቆይ ብዙ ህይወት ስለጠፋበት (ንብረቱን የተውኩት ሰው በህይወት ካለ እንደ አቅሙ ንብረት ማፍራቱ አይቀርም ብዬ ነው) የኦሮምያ ጉዳይስ አነሱ? ካነሱ ምን አሉ? ስለድርቁስ? ከድርቁ በላይ የጣርነት ያህል ህዝቡን እየፈጀው ስላለው የመኪና አደጋስ? ስለሙስናውስ? በለምኖ አዳሪዎችና በሚሊየነሮች መካከል እየተፈጠረ ስላለው አስፈሪና ዘግናኝ የልዩነት ገደልስ አንስተዋል? እና በነዚህ ሁሉ ተግባባችሁ? ካልተግባባችሁ ጥሩ ነው! እስክትግባቡ ትወያያላችሁ፤ ትከራከራላችሁ፤ በተጠየቅ የተደገፈ ውይይት ደግሞ ሀሳብን ስለሚያስቀድም ባያፋቅርም ማግባባቱ አይቀርም፡፡ ችግሩ እንዳላቹሁት ተግባብታችሁ ከሆነ ነው፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርና የኢትዮጵያ ምሁራን፣ ስለምናውቃት ኢትዮጵያ አንድ ቀን ተነጋግረው በብሄራዊ ደረጃ ከተግባቡ፣ ከሁለት አንዱ ስለኢትዮጵያ የማያውቁ፣ ከጨረቃ የወረዱ መሆን አለባቸው፡፡
.
ክቡር ጠ/ሚንስትር፣ መነጋገር ጥሩ ነው፤ በተለይ በሀገርና በህዝቦች ጉዳይ፤ ሀገር የሁላችንም ህዝቦችም ራሳችን ነን፡፡ ይህ ስብሰባ የሚያሳየው አንድ በጎ ነገር ቢኖር የመነጋገርን ፍላጎት ነው፡፡ እና ውይይቱ በተለያዩ ምክንያቶች በኢህአዴግ ላይ ምሬት ከሚያቀርቡ ህዝቦች ጋር ቢሆን፣ የተሰነጣጠቀ መሬት የሚያርስ አይነት ጠብታ ሊገኝ ይችላል፡፡ ካልሆነ በጥንቃቄ መርጠን የምናደርገው ውይይት ትርፉ የራስን ድምጽ መስማት ነው – ገደል ማሚቱ! የገደል ማሚቱ ደግሞ ያርድ፣ ያንቀጠቅጥ፣ ስንጥቅ ያሰፋ ካልሆነ፣ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡

Filed in: Amharic