>
5:01 pm - Thursday February 2, 2023

የሽብርተኛ ትርጉም [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroየሚማር የለም እንጂ የሚማር ቢኖር የሽብርተኛነትን ትርጉም ሰሞኑን በቤልጂክ እያየንና እየሰማን ነው፤ በኢትዮጵያ ያሉ የእውቀት ምልክቶችን በዶላር እየገዙ ስማቸው ላይ የለጠፉ ጉልበተኞች ተናገርክ(ሽ) ብለው ብቻ ሳይሆን አሰብህ(ሽ) ብለው ሰፋፊ እስር ቤቶች እያሰሩ ወጣቶችን ሲያጉሩበት ምክንያታቸው ሽብርተኛነት ነው፤ ሽብር ማለት ሰሞኑን በቤልጂክ አውሮጵላን ጣቢያና በባቡር ጣቢያ ላይ እንደታየው ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ አልታየም፤ ከታየም በአገዛዙ ኃይሎች የተፈጸመ ነው፤ ለብዙ ዓመታት ሲፈጸም የቆየ ነው፤ የኢትዮጵያ ጉልበተኞች ከቻሉ ሊያስተውሉት የሚገባ አንድ ነገር አለ፡- ሽብርም ነጻነትን ይፈልጋል፤ በቤልጂክ ሽብሩን የፈጸሙት ሁሉ ነጻነትን ፈልገው ከአገራቸው የተሰደዱና በአገራቸው ያላገኙትን ነጻነት በሰው አገር እየተሞላቀቁበት እንደሆነ የሚያመለክት ነው፤ ትርጉሙ፡- ነጻነት በሌለበት ሽብር አይኖርም፤ እንዴት ብሎ? የት ተደብቆ? የት ሸምቆ?

ሽብርን የጸነሰውን እንዳያስብ አፍኖ፣ እንዳይናገር አንደበቱን መርጎ፣ እንዳይንቃሳቀስ በዳኛ ትእዛዝ ወህኒ ቤት ውስጥ ቆልፎ ሽብርን ማቆም አይቻልም፤ የሚቻለው፣ እየሆነ ያለውም ዝንባሌው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለሽብር ትምህርት ወደአውሮፓና ወደአሜሪካ እንዲሄዱ የሚገፋፋቸው ነው፤ የዚህን ግፊት ውጤት የኢትዮጵያ ጉልበተኞች የሚወዱት አይመስለኝም፤ መጠቃት እንደማጥቃት አያስደስትም!

የእኝ ጉልበተኞች ሽብር ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡

የእኛ ጉልበተኞች በንግግርና በተግባር መሀከል ያለውን ልዩነት አያውቁም፤ በቤልጂክ ሽብር የተባለው ሠላሳ አንድ ያህል ሰዎች የሞቱበት፣ ወደሦስት መቶ ሠላሳ ያህል ሰዎች የተጎዱበት ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ደርሶ ያውቃል? እንዴታ! በዙ ጊዜ፤ ግን ሽብርተኞች በተባሉትና በታሰሩት አይደለም፤ በተመቻቸውና ሕግ በማይደርስባቸው ሌሎች ጉልበተኞች የተፈጸመ ነው፡፡

የእኛ ጉልበተኞች በፍርሃት የደነዘዘው አንጎላቸው ዓይናቸው እውነቱን እንዲያይ፣ ጆሮአቸው እውነትን እንዲሰማና ልባቸው ወደመወያየትና ወደእርቅ እንዲያቀና አያደርጋቸውም፤ ወላጆቻቸውን ንቀው ብቻቸውን የቆሙ ስለሆኑ መካሪ የላቸውም፤ መንፈስ ስለሌላቸው መንፈሳዊ አባት የላቸውም፤ ያሳዝናሉ፡–

ሀሳቤን አንዱ ግጥሜ ይገልጽልኛል መሰለኝ፡– የሞተ ኅሊና

የማይጣላ ኅሊና ያለው

እንዴት የታደለ ነው!

እግዜር ብቻ ነው ኅሊና የሌለው፤

የማይሳሳት የማየወቆጨው፡፡

ሰው ሰውነቱ፣ ጭንቀቱና ልፋቱ፣

ኅሊናው ከስሜቱና ከፈላጎቱ መጣላቱ፣

የሚረሳ የሚሳሰት፣ የማይታየው የፊቱ፣

የሚወድ፣ የሚጠላ፣ የሚፈራ፣ ኧረ ስንቱ!

ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ ዳኛ መሆን

እንዴት ይችላል መበየን?

ሲያፍነው ግን ኅሊናውን

አይለይም ጨለማውን ከብርሃን!

ኅሊናውን ገደለ ሰው

ማን ሊቀረው? ምን ሊያቅተው?

የጉልበቱ መሣሪያ ነው፤

ጊዜ ጉልበቱን እስቲሰብረው! … …

እውነተኞቹ ሽብርተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከሥልጣን ውጭ አይደሉም፤ ከሥልጣን ውጭ ሆነው ቅራኔ የሚያሰሙ ጉልበታቸው እዚያው ላይ ያበቃል፤ በምድረ ኢትዮጵያ ሽብርን መቃወም ሽብርተኛ ያደርጋል፤ ወህኒ ያስገባል፤ ተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንድር ነጋ፣ አብርሃ ደስታ፣ … በወህኒ ቤት የሚማቅቁት ቅንጣት የሚያህል የሽብር ተግባር ፈጽመው አይደለም፤ ሽብር እንዳይፈጸም ስለታገሉ ነው፤ ሽብር ከነገሠ ሰላም ወንጀል ይሆናል፤ በኢትዮጵያ ሰላም ዋጋ እያጣ መሄድ ላይ መሆኑን የሚጠራጠር የለም፤ ከባሕር ማዶ የተጀመረው ቀረርቶ ወደተግባር ሲለወጥ መፍራት ፋይዳ የለውም፤ ለጉልበተኞቹ የሚያዋጣው የፍርሃት ጊዜው አሁን ነው! እንደሳዳም ሁሴንና እንደጋዳፊ እንደአይጥ ከተሸጎጡበት ስርቻ እየተጎተቱ ሲወጡ አይደለም፡፡

Filed in: Amharic