>
6:48 pm - Sunday July 3, 2022

“ከመሞት መሰንበት” ~ መገርሳ [በበፍቃዱ ኃይሉ]

BefeQadu Z. Hailu

ዓይን የሚፈታተን ደብዛዛ ብርሃን ያለበት ክፍል ውስጥ አስገብተው ከኋላዬ ወፍራሙን የብረት በር፣ ልብ በሚያደባልቅ ጓጓታ ድብልቅ አድርገው ዘጉት፡፡ ወደመታሰሪያ ክፍል የገባሁት እንዲህ ነበር፡፡ ሰዓቱ ከምሽቱ 3፡00 ወይም 4፡00 ሰዐት ገደማ ነው፣ ሚያዝያ 17፣ 2006፡፡ ከውስጥ መሬት ላይ የተኙ ሰዎች ይታዩኛል፡፡ በእጄ ያንጠለጠልኩትን ፌስታል እንደያዝኩ ተራ በተራ አየኋቸው፡፡ አንደኛው ከተኛበት ተነስቶ ቁጢጥ አለ፡፡ ‹ካቦው ይሄንኛው ነው ማለት ነው› አልኩ በልቤ፡፡ ‹የሻማ ሲጠይቁኝ ኪሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ሰጥቼ ለመገላገል ፈልጌያለሁ› እነርሱ ግን የሻማ አልጠየቁኝም፡፡ ‹አረፍ በል› አሉኝ፡፡ ጠርዝ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ‹ራት በልተሃል?› አሉኝ፤ ‹አዎ በልቻለሁ›፡፡
‹ምን አድርገህ ነው?› ‹ጸሐፊ ነኝ፡፡› ‹አሃ፣ ጋዜጠኛ ነህ?› ‹አይ፣ ኢንተርኔት ላይ ነው የምጽፈው፡፡› ‹ሙስሊም ነህ?› ‹አይ አይደለሁም፡፡›
የሚያስፈራ ዝምታ ሰፈነ፡፡ ‹እናንተስ?› አልኳቸው፤ ዝምታውን ለመስበር፡፡
ቁጢጥ ያለው፣ ‹እኔ እና እሱ› አለ ወደ አንደኛው ልጅ እየጠቆሙ ‹በሙስሊሞች ጉዳይ ነው፤ እነሱ› አለኝ ወደሌሎች ሦስት ልጆች እየጠቆመ ‹ከጋምቤላ ነው የመጡት፤ እኚህ ከሶማሊ ክልል ነው የመጡት፡፡ ያኛው› ወደጥግ ወዳለው እየጠቆመ ‹በግንቦት ሰባት ነው የተጠረጠረው› አለኝ፡፡ ሰባት ነበሩ፡፡ እኔ ስምንተኛ ሆንኩላቸው፡፡ በሳይቤሪያ የዘጠኝ ቁጥር እስረኛ ሆኜ ተቀላቀልኳቸው፡፡ ማብራሪያውን የሰጠኝ ረደላ ሸፋ ነበር፡፡ ሦስቱ አኙዋኮች ኡማን ኝኬው፣ ኡጁሉ ቻም እና ኝጎ ኩምቻሬ ነበሩ፡፡ ሶማሌው፣ እኔ በገባሁ በሁለተኛው ቀን ስለተፈታ ዘነጋሁት፡፡ የረደላ አባሪ ሐሰን ነው፡፡ ጥግ ላይ የነበረውና በክፍላችን ብቸኛው የግንቦት ሰባት ወታደርነት ተጠርጣሪ የነበረው አበበ ካሴ ነበር፡፡
ኒጎ ኩምቻሬ እሱ ተኝቶባት የነበረውን ፍራሽ ለቆልኝ እስከመጨረሻ ድረስ የቆየሁባትን ጥግ ላይ ያለች ምቹ ቦታ አወረሰኝ፡፡ ‹በቃ፣ አሁን ተኛ እና ነገ እናወራለን› አሉኝ፡፡ እሺ አልኳቸው፡፡ እነርሱ ተኙ፡፡
አበበ ካሴ እኔ በገባሁበት ሰዐት ምርመራ ጨርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን በአስፈሪ ዝምታ የተዋጠ ሰው ነበር፡፡ ተሰብስበን ኮንከር (ካርታ) ስንጫወት ብቻ፣ እየዳኘ በተራው ይጫወታል፡፡ እየቆየን ስንመጣ ግን ቀስ በቀስ ያዋራኝ ጀመር፡፡ ጠርጣራ ስለነበር፣ ድምፁን በጣም ዝቅ አድርጎ በእርጋታ ነበር የሚያዋራኝ፡፡ ምርመራ አምሽቼ ስመጣ፣ እልሄን የምወጣው እነሱ ጋር ነበር፡፡ ያሉኝን ብስጭቶችና ብሶቶች ሁሉ እነርሱ ላይ እዘረግፈዋለሁ፡፡ እነርሱም፣ አብዛኞቹ ምርመራቸውን ጨርሰው ክስ የሚጠባበቁ ስለነበሩ፣ እኔን ከበው ማፅናናት ብቻ ሆነ ሥራቸው፡፡ አበበ አንድ ቀን ማታ መጥቼ እንደለመድኩት ‹ሊገሉኝ ነው፤ ካልገደሉኝ አይለቁኝም› እያልኩ ሳማርር፡፡
‹አሁን ይቺን ተመታሁ ብለህ ነው?› አለኝ፡፡
በአባባሉ ተናድጄ መልስ ከመስጠቴ በፊት የእጆቹን አይበሉባ አሳየኝ፡፡ ‹ጥፍሮቼን እያቸው› አለኝ፡፡ ጥፍሮቹ ጣቶቹ ላይ የሉም፡፡ ‹እኔ እንኳን እንዲህ አድርገውኝ ዋጥ ነው ያደረግኳት፡፡ ወንድ ልጅ ቻል ነው ማድረግ ያለበት፡፡ ወንድ አደለህ እንዴ?› እኔ የወንድነት ጀብድ የምመኝበት ጊዜ ላይ አልነበርኩም፡፡ ይልቁንም እሱ እኔን ለመምከሪያ ያሳየኝ ጣቶቹ ማስፈራሪያ ሆነው አረፉት፡፡ እኔም ባለተራ ነኝ ብዬ አሰብኩ፡፡
አበበ ካሴ ቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበረ፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተዋጋ፣ ከዚያ በኋላ ግን ለቅቆ ግንቦት ሰባትን የተቀላቀለ ወታደር ነበር፡፡ ሲራመድ ያነክሳል፡፡ ‹ምን አርገውህ ነው?› ስለው ‹ምኑን አውቄ› አለኝ፡፡ ሲደበደብ ራሱን ይስት ነበር፡፡ አበበ ካሴ ከኤርትራ ጎንደር የዘመዱን ሠርግ ለመታደም መጥቶ ነው የተያዘው፡፡ በምርመራ ወቅት የግንቦት ሰባት ወታደር መሆኑን በፍፁም አላመነም ነበር፡፡ ያደገበት እና የኖረበት ኩራት በዱላ ፊት መንበርከክ አልፈቀደለትም፡፡ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ ግን ለፍርድ ቤቱ “አዎ፣ የግንቦት ሰባት ወታደር ነኝ፤ የሆንኩትም አምኜበት ነው” ብሏል፡፡
አበበ ካሴ ከኔ ክፍል ተቀይሮ ተስፋለም ታስሮበት ወደነበረው 4 ቁጥር የተዛወረው ከአጭር ቀናት በኋላ ነበር፡፡ ነገር ግን መልሰን ቂሊንጦ ዞን ሁለት ተገናኘን፡፡ አበበ መጀመሪያ የተከሰሰው በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ በአንቀጽ 4 ቢሆንም፣ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከተደመጡ በኋላ ተቀይሮለት 7/1 ሆኖለታል፡፡ የዛኔ ‹እንኳን ደስ አለህ› ልለው ክፍሉ ሄጄ ነበር፡፡ ሳቀብኝ፡፡ ‹ታስሬ እያለሁ ቁጥር ተቀነሰልኝ ብዬ የምደሰት ይመስልሃል?› ስሜቱን አላጣሁትም፡፡
እንደአበበ ካሴ በቂሊንጦ አስተዳደር የሚጠላ የፖለቲካ እስረኛ አልገጠመኝም፡፡ አበበ ሕክምና ተከልክሎ እግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸመቀቀ አጥሮ ግቢ ውስጥ በምርኩዝ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ብልቱ ላይ በምርመራ ወቅት በደረሰበት ጉዳት የሚያዥ ነገር ተከስቶበት ሕክምና ሲጠይቅ ተከልክሏል፡፡ በጥቅሉ የሰው ልጅ ላይ የሰው ልጅ ሊያደርስበት የሚችለው በደል ሁሉ እየደረሰበት ነው፡፡ አበበ ካሴ አሁን 7 ዓመት ከዘጠኝ ወር ፅኑ እስራት ተፈርዶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ገብቷል፡፡
እንደ አበበ ሁሉ አዱኛ እና መገርሳም በየቀኑ ሐሳቤ ናቸው፡፡ ማዕከላዊ ሳይቤሪያ የሚባለው ወንዶች ክፍል፤ ዘጠኝ ቁጥር ውስጥ ሁለት ሳምንት ከቆየሁ በኋላ ከክፍላችን የሚወጡ ሰዎች በዙ፡፡ ከሦስቱ የአኙዋ ልጆች አንዱ – ኝጎ ኩምቻሬ – ጓደኞቹ ላይ ሊመሰክር ተስማምቶ ወደጣውላ ክፍል ተዛወረ፡፡ ኡማን እና ኡጁሉ ክስ እስኪመሠረትባቸው ድረስ ወደሚቆዩበት ሸራተን ተዛወሩ፡፡ የሶማሊ ክልሉ ሰው ተፈታ፡፡ በምትካቸው ግን ብዙ ሰዎች መጡ፡፡
የአዳማ ዩንቨርስቲው አዱኛ ኬሶ መጣ፡፡ ገብረሚካኤል እና ሌላ ሥሙን የዘነጋሁት ሰው ከትግራይ ክልል መጡ፡፡ ሌላም ሰውዬ ከሶማሊ ክልል መጡ፡፡ አጀሌ ከቤንሻንጉል/ጉምዝ መጣ፡፡ ሁሉም የተጠረጠሩት በሽብርተኝነት ወንጀል ነው፡፡
ከሁሉም ሳቂታና ተጫዋች የነበረው አዱኛ ኬሶ ነበር፡፡ አዱኛ ከተያዘ 19 ቀናት እንደሆነው ነገረን፡፡ ‹የት ቆየህ?› አያውቀውም፡፡ ምክንያቱም፣ ወደቆየበት ቦታ ሲሄድም ሆነ ወደእኛ ሲመጣ ዓይኖቹ በጨርቅ ተሸፍነው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደሽንት ቤት ሲወሰድ እና ሲመለስ ዓይኖቹ በጨርቅ ይሸፈኑ ነበር፡፡ አዱኛ ወደኔ ክፍል ሲመጣ ግራ ዓይኑ ስር የበለዘ ነገር ነበረው፡፡ ‹ምንድን ነው?› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹ሲይዙኝ በቡጢ የነረቱኝ ነው› አለኝ፡፡ አሁን ድረስ ያ የቡጢ አሻራ ጠባሳ ሁኖ ቀርቷል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ በፖሊስ ተደግፎ መጥቶ፣ በፖሊስ ተደግፎ 8 ቁጥር (የብቻ ጨለማ ቤት) ሲወጣና ሲገባ የቆየው መገርሳ ወደእኛ ክፍል ገባ፡፡ መገርሳ ወርቁ የሐሮማያ ዩንቨርስቲ ተማሪ ነበር፡፡ መገርሳ መጀመሪያ የተያዘው ሐረማያ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ቦምብ ተሳትፈሃል በሚል ተጠርጥሮ ነበር፡፡ መገርሳን ሐሮማያ ከተማ ተደብድቧል፡፡ ድብደባው እርቃን ነበር፡፡ እጆቹ በገመድ ተጠፍረው ጉልበቱን ያቅፍና በእጆቹ መታጠፊያ እና በቋንጃው መካከል እንጨት ያልፍና ይሰቀላል – ወፌ ይላላ፡፡ ከዚያ ይደበደባል፡፡ መገርሳ ይህንን ይነግረኝ የነበረው፣ እግሮቹ መታጠፊያ ላይ የቀረውን ሰምበር የመሰለ ነገር እያሳየኝ ነው፡፡ ‹ተንጠልጥዬ እየተሰቃየሁ ብልቴን ይጎትቱታል› ብሎኛል ሲነግረኝ፡፡ በመሐሉ ራሱን ይስታል፡፡ ‹ከዚያ ቅዝቅዝ ሲለኝ እነቃለሁ፤ ስነቃ አውርደውኝ አገኛለሁ፡፡ አሁንስ ታምናለህ አታምንም ይሉኛል፡፡ የማምነው ነገር እንደሌለ ሲያውቁ መልሰው ይሰቅሉኛል፡፡› አለ፡፡ በመጨረሻ ግን መገርሳ ተረታ፡፡ ‹ሳስበው ከምሞት፣ ዕድሜ ልክ ተፈርዶብኝ በሕይወት ብኖር ይሻለኛል ብዬ አሰብኩ› አለ፡፡ ‹አዎ፣ እኔ ነኝ ቦንቡን የወረወርኩት› አላቸው፡፡ መርማሪዎቹ ተደሰቱ፡፡ ራቁቱን የሆነ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ አጋድመውት ሄዱ፡፡ ከዚያ ‹በሕይወቴ የማይዘነጋኝ ዘግናኝ ነገር ተከሰተ› ብሎ የሚከተለውን አጫወተኝ፡፡ ቤቱ ውስጥ የዶሮ ጫጩቶች ነበሩ (የአንዱ የደህንነት ሰራተኛ መኖሪያ ቤት ውስጥ ይመስለዋል ያለው)፡፡ ጫጩቶቹ መጥተው እየተራመዱ እላዩ ላይ ይወጡበታል፡፡ መገርሳ እነርሱን “እሽ” ብሎ የሚያባርርበት አቅም አልነበረውም፡፡ እግራቸው ይበላዋል፡፡ ሲነግረኝ ‹ጫጩቶቹን ጠላኋቸው› ነበር ያለኝ፡፡ ግን ምንም ሊያደርጋቸው አልቻለም፡፡
በማግስቱ በካሜራ ፊት ሐረማያ ዩንቨርስቲ ግቢ ውስጥ የፈነዳውን ቦምብ ያፈነዳው እሱ እንደሆነ አመነ፡፡ እሱ በወቅቱ ዩንቨርስቲው ግቢ ውስጥ አልነበረም፡፡ እንዲያውም የታቀደ ረብሻ እንዳለ መረጃው ቀድሞ ደርሶት ለዩንቨርስቲ ግቢው የኦሕዴድ ጽ/ቤት ደውሎ ማስጠንቀቁን ነግሮኛል፡፡ ያ ሁሉ አልፎ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ ነገር ግን፣ እሱ ወደአዲስ አበባ እየመጣ እያለ ፖሊስ የእውነትም ቦንቡን ወርውሮታል ብሎ ያመነበትን ሰው ያዝኩኝ አለ፡፡ ነገር ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ ባይ መንግሥት መገርሳን ከመክሰስ አልተመለሰም፡፡ ጽፈኸዋል በተባለው ግጥም ክስ ተመስርቶበት ‹ተከላከል› ተብሎ፣ መከላከያ ምስክሮቹን አስደምጦ ‹የነጻ› ወይም ‹ጥፋተኛ› ብይን እየተጠባበቀ ነው፡፡ አዱኛ ኬሶም በተመሳሳይ መዝገብ ‹በቄሮ አባልነት› ተከላከል ተብሎ መከላከያ ምስክሮቹን እያስደመጠ ነው፡፡
ታስሮ መፈታት ቅጣት ነው፡፡ ሰቅጣጭ በደል በሚፈፀምባት ከተማ፣ አገር ሠላም ብሎ ከሚኖር ሰው ጋር ምንም እንዳላየ፣ ምንም እንዳልሰሙ መስለው የመኖር ቅጣት፡፡
ማዕከላዊ ምርመራ ወጥቼ ስገባ፣ መታሸት ሲያስፈልገኝ ሲያሸኝ፣ ጨዋታ ሲያመምረኝ ሲያጫውተኝ የነበረው ረደላ ሸፋ እና አባሪው ሀሰን ሁለቱም ‹ነጻ ለመውጣት ወይም ጥፋተኛ ለመባል ተከላከሉ› ተብለው መከላከያ ምስክሮቻቸውን ለማስደመጥ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ የቤንሻንጉሉ አጄላ አራት ዓመት ተፈርዶበት ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስዷል፡፡ አቦይ ገብረሚካኤል ‹ተከላከሉ› ተብለው መከላከያ ምስክር እያስደመጡ ነው፡፡ ኡማን እና ኡጁሉም ‹ጥፋተኛ› ተብለው ፍርዳቸውን ለመመቀበል ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡
እስረኞች ይመጣሉ፣ ከሰሜን ይመጣሉ፣ ከደቡብ ይመጣሉ፣ ከምሥራቅ ይመጣሉ፣ ከምዕራብ ይመጣሉ፡፡ በሕዝብ ጥቅም ሥም ጦር መዝዞ ሥልጣን የተቆጣጠረው መንግሥት ዛሬም የፖለቲካ እስረኞች የሉኝም ይላል፡፡
Filed in: Amharic