>
8:21 pm - Tuesday January 31, 2023

ኩሩው ፕሮፌሰር እና እሳቤዎቻቸው [በ ውይይት]

Prof Mesfen Weldemariam 86 - by Weyeyt com

የአደባባይ ምሁሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም 86ኛ የልደት በዓል በአዲስ ቪው ሆቴል ሚያዝያ 16፣ 2008 በአድናቂዎቻቸው አዘጋጅነት ተከብሮ ውሏል። ይህ ጽሑፍ ከዚያ በፊት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው ቃለ-ምልልሶች እና የልደት በዓላቸው ዕለት ከተናገሩት ተሰባስቦ የተሰናዳ ነው።

86 ዓመታቸውን ዘንድሮ የደፈኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። በራሳቸው አነጋገር “ከሸዋ እና ከወሎ፣ ከየጁ” የመጡት ወላጆቻቸው አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው እርሳቸው ስድስት ኪሎ ላይ ተወለዱ። ነገር ግን በሥራቸው ጠባይ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያን ገጠራማ ስፍራዎች ሳይቀር በመርገጣቸው “ልቤ እና ስሜቴ ለገጠሩ ሕዝብ ያደላል” ይላሉ። በአገራችን ኢትዮጵያ የእርሳቸውን ያክል ቢያንስ ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ያክል ያለመሰልቸት በአገራችን ስርዓት የተጣመመው እንዲቃና በአደባባይ በመወትወት (advocacy) ሥራ ፕሮፌሰሩን የሚወዳደራቸው ምሁር አይገኝም። ከሦስቱም ያለፉት የኢትዮጵያ መሪዎች ጋር እጅ ለእጅ ቢጨባበጡም፣ መሪዎቹ ከፕሮፌሰሩ ትችት አልተረፉም። በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጊዜ ለ8 ቀናት እና በኢሕአዴግ ዘመን ለአንድ ወር እና ለሁለት ዓመት ሁለት ጊዜ ታስረዋል። ከ15 በላይ መጽሐፍትን አሳትመው ለሕዝብ አብቅተዋል። በተለይ በስተመጨረሻ የጻፏቸው መጽሐፍት እጅጉን አነጋጋሪ ነበሩ። ሦስቱንም ስርዓት በታዛቢ ዓይናቸው እየገረመሙ ያሳለፉ በመሆናቸው ስለመንግሥታዊ ስርዓቶች የሚሰጧቸው አስተያየቶች ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና መንግሥታቱን እርስበር የማነፃፀር ችሎታቸው ችላ አይባሌ ነው። ዕድሜ ያልገደበው የለውጥ አራማጅ ጸሐፊነታቸው አሁን በፈረንጁ ዓለም ትውፊታዊ (traditional) ከሚባለው ሚዲያ እስከ ዘመናዊው ማኅበራዊ ሚዲያ (new media) ድረስ ዘልቋል። ፕሮፌሰር መስፍን ዘመን ሲታደስ ከዘመኑ ጋር እየታደሱ የመጡ፣ “ዘመን አልፎበታል” ሊባሉ የማይቻሉ አነጋጋሪ ምሁር ናቸው።

ልጅነት

ፕሮፌሰር መስፍን በልጅነታቸው በአንድ በኩል ተናዳጅ እና ጠበኛ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለተቸገረ እና ለተበደለ ሰው በጣም አዛኝ እንደነበሩ ይናገራሉ። ተናዳጅ እና ጠበኝነታቸውን በፀሎትና በኳስ መግራታቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰር በሌሎች ስቃይ መጨነቁ ግን ከነፍሳቸው ተዋህዶ ለሕዝብ ጥቅም፣ ለአገር ጉዳይ ሦስቱንም መንግሥታት በሐሳብ እየሞገቱ፤ ዕድሜያቸውን ሁሉ ጨርሰውበታል።

ፕሮፌሰር መስፍን ፈረንጆች ‘formative age’ የሚሉት አፍላ ዕድሜያቸው ላይ፣ የአምስት ዓመት ልጅ ገደማ እያሉ ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረችበት ጊዜ ነበር። አርበኝነት የሚያደንቀው እና ‹ባንዳነትን› የሚጠየፈው ማንነታቸው የተቀረፀው ምናልባትም የዛን ጊዜ በልጅነት ልቦና ደጋግመው ይሰሟቸው ከነበሩ ትርክቶች በመነሳት እንደሆነ ይገመታል። ከልጅነት ጊዜዎቻቸው በአንዱ፣ አንድ ጣልያናዊ አንድ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ እግሩን አነባብሮ ሲያነብ ተመልክተው፣ ምን እንዳነሳሳቸው ሳይታወቃቸው ድንጋይ አንስተው በመወርወር ቅልጥሙን ብለውት ሲሮጡ፣ ጣሊያኑ ተከትሎ አባርሮ ይዞ በእርግጫ የደበደባቸው ከልጅነት ጊዜ ትዝታዎቻቸው አንዱ ነው። “ምናልባት እቤቴ ሲወራ የምሰማው ነገር ቂም አስቋጥሮኝ ይሆናል” ይላሉ። ጣልያን በየካቲት 12 ባደረገው ጭፍጨፋ ወቅት ምንም እንኳን የ5 ዓመት ልጅ ቢሆኑም፣ እናታቸው “ጣልያን ወንድ ነው የሚያጠቃው” በሚል አልጋ ስር እንደደበቋቸው ይተርካሉ።

ከድቁና እስከ ፕሮፌሰርነት

ፕሮፌሰር መስፍን አሁን የደረሱበትን የሊቅነት ደረጃ ስንመለከት ከአፍላነታቸው ጀምሮ በትምህርት ፍቅር የተነደፉ ሊመስል ይችላል። እርሳቸው ግን እንደሚናገሩት መጀመሪያ ቁስቋም ቄስ ትምህርት ቤት ሲላኩ ትምህርት ጠልተው እምቢ በማለታቸው በእግር ብረት ታስረው፣ በግድ ነበር ትምህርት ቤት የሚሄዱት። ቀስ በቀስ ግን የትምህርት ጣዕሙ እየገባቸው ሲመጡ፣ ያለ እግር ብረት ትምህርት ቤት መሄድ ጀመሩ። በቄስ ትምህርት ቤት ድቁና ተቀብለዋል። ከዚያ በኋላ ወደአስኳላ ትምህርት የገቡት በወቅቱ የፈረንሳይን የትምህርት ስርዓት ይከተል የነበረው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት (ቲ.ኤም.ኤስ) ነበር።

ቲ.ኤም.ኤስ. በፈረንሳይ ትምህርት ደምብ መሠረት፣ ከአሁኑ ደምብ በተቃራኒ ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አንደኛ ክፍል ድረስ ነበር የሚያስተምረው። እርሳቸው በመግቢያ ፈተና ውጤታቸው መሠረት ከ7ተኛ ክፍል የተፈሪ መኮንን ትምህርታቸውን ጀመሩ። ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ ሲከፈት ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት ተማሪዎች አንዱ ነበሩ። ይሁን እንጂ በራስምታት እና በነስር ሕመም ምክንያት የኮሌጅ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወጥተው እቴጌ መነን (በወቅቱ) የሴቶች ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት ተቀጠሩ። ከዓመታት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት ሕንድ አገር የትምህርት ዕድል አግኝተው ሄደው ፑንጃብ ዩንቨርስቲ ውስጥ የፍልስፍናና እና የጂኦግራፊ ትምህርታቸውን በመቀጠል የመጀመሪያ ዲግሪ ያዙ። ከዚያ መልስ በ1948 ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ ከክላርክ ዩንቨርስቲ በካርታ አነሳስ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። በዚሁ መሥመር በቄስ ትምህርት ቤት የተጀመረው ትምህርታቸው በቀለም ትምህርት እና ምርምር ቀጥሎ ለፕሮፌሰርነት ማዕረግ አብቅቷቸዋል።

የሥልጣን ጥላቻ

ፕሮፌሰር መስፍን ስለሥልጣን አባላጊነት አበክረው ይናገራሉ። ዕድሜ ልካቸውን ሲታገሉ የሥልጣን ጥም ፈፅሞ እንዳልነበረባቸው ተናግረዋል። “የሥልጣን ተዋረድ ጉዳይ፣ የሥልጣን አጠቃቀም ከወግና ፎርማሊቲ፣ ከመሠረታዊ ዓላማ ጋር መያያዝ ወይም አለመያያዝ፤… ሥልጣን ለሕሊና መሥራት ለሚፈልግ ሰው የሚገጥሙት እልህ አስጨራሽ እንቅፋቶች በግልጽ” እንደሚታዩ የተረዱት የመነን ትምህርት ቤት መምህር በነበሩበት ጊዜ ነው።

እርሳቸው መምህር በነበሩበት ጊዜ የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የነበሩት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ለወሊድ ወደእንግሊዝ አገር በሄዱበት ወቅት ወጣት መስፍን ክፍተቱን የሞሉ መስሏቸው ከላይ እስከታች ይህ ሥራ የኔ ነው፣ የእከሌ ነው ሳይሉ ሲሠሩና ሲወስኑ ይቆያሉ። ወ/ሮ ስንዱ ከእንግሊዝ አገር ሲመለሱ፣ በሥራዬ እመሰገናለሁ ብለው ሲጠብቁ ወ/ሮዋ ግን በንዴት እና ቁጣ አስተናገዷቸው። በዚህ የተናደዱት መስፍን “እኔ ገና የሃያ ዓመት ጎረምሳ ነኝ፤ እርስዎ አለቃዬ ከመሆንዎ ሌላ፤ እናቴም ለመሆን የሚችሉ ነዎት፤… የርስዎን ሥራ ስለሰራሁልዎት ያመሰግኑኛል እንጂ ይቀየማሉ ብዬ አልገመትሁም ነበር፤ ከአሁን ወዲያ ከእርስዎ ጋር አልሠራም” በማለት ነበር ከመጀመሪያ ሥራቸው በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት። ከሁለተኛ መሥሪያ ቤታቸው የካርታ እና ጂኦግራፊ ድርጅት እና የምክትል ዳይሬክተርነት ኃላፊነታቸው የተነሱት ለአገር ቀናኢነት በማሳየታቸው ከአሜሪካዊ ባልደረቦቻቸው ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ነው። “የወቅቱ ባለሥልጣናት ለአሜሪካኖቹ አድልተው” የዝውውር ደብዳቤ ሰጧቸው። ከዚያም በዩንቨርስቲ መምህርነታው ቀጠሉ።

ፕሮፌሰር መስፍን በዐፄ ኃ/ሥላሴ ጊዜ፣ በ1965 ለ8 ቀናት ታስረው ነበር። የታሰሩት በዚሁ በሥልጣን ሽሽት ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ነገሩ የሚጀምረው፣ ፕሮፌሰሩ በወቅቱ ለነበረው የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ኅብረት በአፍሪካ አንድነት አዳራሽ ውስጥ ‹የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ይህን ትመስላለች› የሚል ጥናታዊ ንግግር ያቀርባሉ። ‹ይህንን ተከትሎ› ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን ገጠመኙን “የጎረምሶቹ መንግሥት” እያሉ ከሚጠሯቸው ከኢሕአዴግ እና ከደርግ መንግሥት ጋር የዐፄውን እያወዳደሩ፣ ‹ለምን እንዲህ ተናገርክ የሚል ክስ አልመጣብኝም፤ ይልቁንም ‹የጊምቢ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነህ ተሾመኻል› ነው የተባልኩት ይላሉ። ሹመቱን ፕሮፌሰሩ አልቀበልም አሉ። “የንጉሡን ትዕዛዝ አልተቀበልክም” በሚል ነው ስምንት ቀን የታሰሩት። የኋላ ኋላ ሹመቱን በግዳቸው ተቀብለዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ጥናታዊ ንግግሮች ባቀረቡበት ወቅት “በኢትዮጵያ ኃላፊነቱ ያልተወሰነ አክስዮን ማኅበር እንጂ መንግሥት የለም” የሚል ነገር በመናገራቸው ሹመቱ ግዞት እንጂ ሹመት እንዳልሆነ ገብቷቸው ነበር። የ1966ቱ አብዮት መፈንዳት ፕሮፌሰሩ እንደግዞት ከቆጠሩት ሹመት ገላግሏቸዋል። ፕሮፌሰር ከዚያም በፊት ያልተፈለገ ማኅበር በማቋቋማቸው ጦስ የጊሚራ አውራጃ አስተዳዳሪ በመባል በሹመት ተግዘዋል።

የመርማሪ ኮሚሲዮን ሊቀመንበርነት

የፕሮፌሰር መስፍን ተቺዎች እርሳቸው ላይ ከሚያቀርቡባቸው ትችቶች አንዱ አብዮቱ የፈነዳ ሰሞን ተቋቁሞ የነበረው የዐፄ ኃይለሥላሴ ሹማምንት ላይ ምርመራ አድርጎ ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመው በወንጀል የሚያስጠይቅ ነገር ሠርተው ከሆነ ለክስ የሚያበቃው ኮሚሲዮን ውስጥ በሊቀመንበርነት እያገለገሉ እያሉ ባለሥልጣናቱ በደርግ መረሸናቸውን ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ግን ይህ ዓይነቱ ትችት የሚመነጨው ስለኮሚሲዮኑ ካለማወቅ እንደሆነ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ስህተት የሚጀምረው ኮሚሲዮኑ የተቋቋመው በደርግ ነው ከሚል ነው። የኮሚሲዮኑ 15 አባላት ሥራቸውን የሚጀምሩት በዐፄው ፓርላማ ተመርጠው በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ፊት ቃለ መሐላ ፈፅመው ነው። ደርግ በተለይም ሊቀመንበሩ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ‹የአብረን እንሥራ› ጥያቄ ለርሳቸው በግል አቅርቦ እንደነበር ፕሮፌሰር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በግላቸውም፣ በኮሚሲዮኑም የድምፅ ብልጫ የመንግሥቱ ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ይናገራሉ።

ደርግ የዐፄውን ባለሥልጣናት የረሸነው በገዛ ፈቃዱ ነበር። የባለሥልጣናቱን መረሸን እንደሰሙ ፕሮፌሰር መስፍን ወዲያውኑ ከኮሚሲዮኑ ሊቀመንበርነት እና አባልነትም ጭምር ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብተዋል። ይሁን እንጂ ከኮሚሲዮኑ በዚህ ምክንያት መልቀቃቸው ለደኅንነታቸው አደጋ እንደሚጥል የኮሚሲዮኑ አባላት ስለሰጉ ፕሮፌሰሩን በማግባበት ከሊቀመንበርነታቸው ተነስተው በአባልነት እንዲቀጥሉ አድርገዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አሁን፣ አሁን ሲያስቡት የኮሚሲዮኑ አባላት የመንግሥቱ ኃ/ማርያምን ‹አብረን እንሥራ› ጥያቄ ተቀብሎ ከደርግ ጋር ቢሠሩ ኖሮ ምናልባት ነገሮች (ደርግ ከመኢሶን ጋር ሠርቶ ከሆነው) የተሻለ ይሆን እንዴ እያሉ ይጠራጠራሉ።

ስለ ‹ያ ትውልድ›

ፕሮፌሰር መስፍን ከክፍሉ ታደሰ መጽሐፍ በተውሶ ‹ያ ትውልድ› እየተባለ የሚታወቀውን ትውልድ “ችኩል ትውልድ” እያሉ በመተቸት ይታወቃሉ። እነብርሃነ መስቀል ረዳ እና የ‹ያ ትውልድ› ወጣቶች ሲነሱ፣ “እነዛ ልጆች ራሳቸውን ቢጠብቁ ዛሬ ለኢትዮጵያ እንዴት ያሉ ሰዎች ይሆኑ ነበር። ራሳቸውን ባለመጠበቃቸው እነሱ ጠፉ። ከነሱ በኋላም ሰው ጠፋ።” በማለት ይቆጫሉ። ‹ለሥልጣን ችኮላ ነው ለዚህ ያበቃቸው› ብለውም ያምናሉ።

የ‹ያ ትውልድ› ልጆች ይላሉ ፕሮፌሰር “ማርክሲስት-ሌኒኒስት እምነቱን አይፈልጉትም። እምነቱ በጡንቻ ሥልጣን ለመያዝ ስለሚፈቅድ ብቻ ይጠቀሙበታል” ይላሉ።

ነጻነት እና አገዛዝ

ፕሮፌሰር መስፍን በሥልጣናዊ መባለግ ላይ የተመሠረተን ስርዓት ‹አገዛዝ› እያሉ ይጠሩታል። አገዛዝ በሳቸው አተረጓጎም፣ ‹ጥቂቶች ከሕግ በላይ ሆነው አገር የሚያምሱበት ስርዓት ነው›። እስካሁን ድረስ ‹ኢትዮጵያ አገዛዞች እንጂ መንግሥት አላየችም› የሚሉትም በዚህ የአገዛዝ ትርጓሜያቸው ላይ ተመሥርተው ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን “የኢትዮጵያ ገበሬ ነጻ ካልወጣ በኢትዮጵያ ችጋር ይቀጥላል” በማለት በአፍሪካ ድርቅ (drought) እና ችጋር (famine) ላይ ጥናት አድርገው ‹ነጻነት ልማት ነው› የሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሱት ዕውቁ የምጣኔሀብት ሎሬት አማርትያ ሴን ጋር ተመሳሳይ ድምዳሜ ይሰጣሉ። ፕሮፌሰር መስፍን፣ የኢትዮጵያ መንግሥታት ሊደብቋቸው ይፍጨረጨሩ የነበሩትን ከ1951 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ድርቆች እና ችጋሮችን እርዳታ በማስተባበር ሲመለከቱ ኖረው ነው ‹የኢትዮጵያ ገበሬ ነጻ ካልወጣ በኢትዮጵያ ችጋር ይቀጥላል› የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱት። (የፕሮፌሰር መስፍን ድምዳሜ ከአማርትያ ሴን ይቀድማል። ፕሮፌሰር መስፍን እንደገለጹት አማርትያ ሴን ‹ነጻነት እንደ ዴሞክራሲ› (Freedom As Development) የሚለውን መጽሐፍ መጀመሪያ ያወጣው ‹Entitlement› በሚል ርዕስ ነበር። እርሳቸው፣ ችጋርን የሚያጠፋው ነጻነት እንደሆነ በአማርኛ ያሳተሙት በ1972 ነው። የእንግሊዝኛው ‹Rural Vulnerability to Famine› የሚለው ይህንኑ ድምዳሜ የያዘ መጽሐፍ ካሳተሙ በኋላ፣ አማርትያ ሴን የመጽሐፉን ርዕስ ‹Freedom As Development› በማድረግ አሳተመው። የሎሬትነት ማዕረጉን ያገኘውም በዚህ ጊዜ ነው።)

በፕሮፌሰር ብያኔ መሠረት ድህነት ለባርነት መንስኤ ነው። “ድሀ መሆን ወደልመና ይወስዳል እንጂ ወደ ጌትነት አይወስድም” ይላሉ። ነጻነት ማለት ለፕሮፌሰር፣ ‹ሰው የራሱ ጌታ ሲሆን ነው። ደሀ መሆን ደግሞ ለራሱ የማይሆን ሰው መሆን ነው። ምክንያቱም ድሀ በጌታው ላይ ጥገኛ ነው። የሚያለብሰውም፣ የሚያበላውም ጌታው የሆነ ሰው ነጻ ሊሆን አይችልም› ይላሉ።

ፕሮፌሰር መስፍን ስለነጻነት ሲናገሩ፣ “…ነጻነት በቀላሉ የሚገኝ ሀብት አይደለም። አንድ ሰው ነጻነት ለማግኘት፣ ራሱን ‹ሰው ነኝ› ብሎ ማሳመን እና ማመን አለበት። ሰው ነኝ የሚል እምነት ካለው፣ ከዚያ በኋላ ነጻነቱን ማንም ሊነፍገው አይችልም። መሬቱ፣ ገንዘቡ፣ ሹመቱ፣… ይቀራል እንጂ ሰው ሆኖ ነጻ ሆኖ ይኖራል። የሰውነት የመጨረሻ ሀብቱ፣ ነጻ መሆኑ ነው። እንደፈለገው ሐሳቡን ለመግለጽ፣ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት፣… ይሄ ነጻነት ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሌለው…” ይላሉ።

“ጭቆና ተሸካሚ ትከሻ ይፈልጋል” የሚለው የፕሮፌሰር ንግግር በጣም ታዋቂ ነው። ይህ አባባላቸው ‹ሕዝብ የሚመጥነውን መሪ ያገኛል› ከሚለው አባባል ጋር ይመሳሰላል። በእኛ አገር የሚደረጉ ትግሎች የማይሳኩት “ጭቆናን ለማጥፋት ሳይሆን፣ ተረኛ ጨቋኝ ለመሆን” ስለሆነ ነው በሚል ‹ታጋይ ነን› ባዮች ሁሉ ሐቀኛ እንዳይደሉ በመናገር የሰላ ትችታቸውን ይሰነዝራሉ።

የመስፈሪያ ነገር…

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የፖለቲካ ስርዓትን ብቻ ሳይሆን ለኋላ ቀርነት ዳርጎናል ብለው የሚያስቧቸውን ማኅበራዊ ልማዶች በመተቸት ይታወቃሉ። ገጠር ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ከታዘቡት እና ለኋላ ቀርነት ዳርጎናል ብለው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከሚናገሩት ነገር ውስጥ መደበኛ (standard) የመስፈሪያ ወይም መለኪያ የሌለን መሆኑን ይጠቅሳሉ። ገጠር የሚያገኙትን ሰዎች ሲጠይቁ የመሬታቸውን ልክ በክንድ ቁጥር ይነግሯቸዋል። ፕሮፌሰር ‹በማን ክንድ?› ብለው ይጠይቃሉ። ምን ያህል እህል ከዚያ መሬት ይሰበሰባል ለሚለው ጥያቄ ‹ይሄን ያህል ቁና› ወይም ‹እንቅብ› የሚል መልስ ያገኛሉ፤ ‹ቁና›ው ወይም ‹እንቅቡ› ከቤት ቤት አንድ አይደለም። የጊዜ ልኬታችንም ከዚያ የተሻለ አይደለም። ፕሮፌሰር መስፍን የመስፈሪያ ወይም ልኬት አልባነታችን ብዙ ነገሮችን በፕሮግራም እና በዕቅድ እንዳናከናውን ካደረጉን የድህነታችን መንስኤዎች ውስጥ ያስቀምጡታል።

ስለመደራጀት…

ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያውያን ማኅበር መመሥረት አይሆንልንም ይላሉ። “በማኅበር መደራጀት ለአበሻ አስቸጋሪ ነው።… ማኅበር ውስጥ ኃይል የለበትም። እኛ አለንጋ ለምደናል። አለንጋ በሌለበት በዕኩልነት ተባብረን መቀመጥ ያዳግተናል” ይላሉ። ሆኖም ተስፋ ቆርጠው እጅና እግራቸውን አጣምረው አልተቀመጡም። እንዲያውም ፕሮፌሰር በዕድሜዬ ሠራሁት የሚሉት ብቸኛው ሴራ (conspiracy) ማኅበር ለመመሥረት ያደረጉት ሴራ ነው።

ይህ ሴራ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበርን ለማቋቋም የተደረገ ሴራ ነው። በወቅቱ ማኅበራት ማቋቋም በሕግ የተፈቀደ ነገር አልነበረም። ስለዚህ በድብቅ ከሌሎች ጋር በመተባበር ኋላ ለአብዮቱ አስተዋፅዖ ማድረግ የቻለውን ማኅበር አቋቋሙ።

ፕሮፌሰር መስፍን ካቋቋሟቸው ማኅበራት ቀድሞ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ይባል የነበረው፤ የአሁኑ ሰመጉ ይገኝበታል። ኢሰመጉ የተቋቋመው መስከረም 29 ቀን 1984 ነበር። “ኢሰመጉ የተመሠረተው [ሕወሓትን] ለማገዝ ነበር” ይላሉ። ኢሕአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት ሰው እየገደሉ በየመንገዱ መጣል የተለመደ ነበር፤ አሁን ግን ያ ነገር በኢሰመጉ ጥረት ተቀርፏል። ነገር ግን ኢሕአዴግ ይህንን እንዳልወደደው ይናገራሉ።

የፕሮፌሰር መስፍን ማኅበራት ላይ ማተኮር በሠላማዊ ትግል ላይ ካላቸው ቁርጠኝነት የመነጨ ይመስላል። ፕሮፌሰር በሩ የቱንም ያክል ቢጠብ እንኳን አማራጩ ሠላማዊ መሆን አለበት የሚል አቋም አላቸው።

ስደትን መቃወም

ፕሮፌሰር መስፍን ለስደት የመረረ ተቃውሞ አላቸው። ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹት ይስተዋላሉ። ሌላው ቀርቶ ከወንዞች ተርታ እንኳን አዋሽን “ብቸኛው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ወንዝ” ይሉታል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈልቆ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠልቅ በመሆኑ።

“ኢትዮጵያዊ ማነው ይላሉ ግራ የገባቸው፣

አዋሽ ንገራቸው፣

ኢትዮጵያ ተወልዶ፣ ኢትዮጵያ ያደገው፣

ድንበሩን ሳያልፍ አፈር የሚገባው፣

እኔ ነኝ በላቸው።…” የሚል ግጥምም አላቸው።

“በስደት ከሕሊና ጋር መኖር አይቻልም፤ ከዚህ አገር ፈርቶ ቢሸሽ እዛ ሆኜ ብታገልስ ኖሮ ማለቱ አይቀርም” ይላሉ። ችግርን “ሸሽቶ ከአገር መውጣት ከችግሩ አካልነት አያስጥልም። ችግሩን በውስጥህ ይዘኸው ነው የምትሰደደው” በማለት ስደት ለችግሮች መፍትሔ አለመሆኑን ይከራከራሉ።

“አማራ የለም”

ፕሮፌሰር መስፍን በጣም አነጋጋሪ ከሆኑት አቋሞቻቸው ሁሉ “አማራ” የሚባል “ጎሳ” የለም የሚለው ቀዳሚው ነው። አሁን በሕወሓት ዘመን ‹አማራ› እየተባለ የሚጠራው ማኅበረሰብ በፊት ራሱን ‹ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ተጉለቴ፣ ወዘተ.› እያለ የሚጠራ እንጂ “አማራ” ነኝ የሚል አይደለም። ‹አማራ› የሚለው ቃል ‹ክርስቲያን› የሚለውን የተካ ቃል ነበር ብለው ይከራከራሉ። ይህ ክርክራቸው ከዘውግ ተኮር ፖለቲከኞች ጋር በቅራኔ ውስጥ አቆይቷቸዋል። ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን ክርክራቸውን በጽሑፍ ከማስፈራቸው በፊት በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ክርክር ላይ ቀርበው ከሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ ጋር የተከራከሩበት ጉዳይ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት

ፕሮፌሰር መስፍን ምንም እንኳን የሥልጣን ፍላጎት ባይኖራቸውም የፖለቲካ አባል ሆነው ያውቃሉ። ይኸውም በ1996 ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመሆን ቀስተዳመና ፓርቲን ሲያቋቁሙ ነው። ፓርቲው ኋላ ላይ ከቅንጅት መሥራቾች አንዱ ሆኗል። በፓርቲያቸው በኩል ትልቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ቢችሉም፣ የፓርቲው ምክር ቤት አባል ከመሆን በቀር ምንም ዓይነት ኃላፊነት አልወሰዱም። በተጨማሪም፣ ለምርጫ 97 እጩ ሆነው አልቀረቡም ነበር። ይህ ግን ከምርጫው በኋላ የቅንጅቱ አመራሮች ተጠራርገው ሲታሰሩ እሳቸውን አላስተረፋቸውም። ሁለት ዓመት በዚህ ሳቢያ ታስረው ተፈትተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን እና ተቺዎቻቸው

የፕሮፌሰር መስፍን ነቃፊዎች ከሚሰነዝሯቸው ትችቶች መካከል ‹ትችት አይቀበሉም› የሚለው ደምቆ የሚሰማው ነው። ፕሮፌሰር በሚዲያ ለሚነሱላቸው አንዳንድ ትችት አዘል ጥያቄዎች ‹መጽሐፌን አንብብ እንጂ እኔ መልስ አልሰጥህም› ይላሉ ይባላሉ። ፕሮፌሰር መስፍን ግን ይህን ትችት አይቀበሉም። “ትችቶች የጻፍኩትን ሳያነቡ ሊሰነዘሩብኝ አይገባም፤ አብዛኛዎቹ ተቺዎች የሚያደርጉት ያንን ነው” ባይ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ፕሮፌሰር ትችት አዘል ጥያቄ ሲሰነዘርባቸው በቁጣ የሚመልሱት የሚሠነዘሩላቸው ጥያቄዎች በእርሳቸው ልኅቀት ደረጃ ባለመሆኑ እንደሆነ ግምታቸውን ይሰጣሉ።

‹ትልቅ ሰው እርግጫ ይበዛበታል› ይባላል። ፕሮፌሰር መስፍን ላይም የሚሰነዘሩባቸው ትችቶች ከሚሠሯቸው ሥራዎች አንፃር ሊጋነኑ የማይገባቸውን ያክል ነው የሚጋነኑት። የትችቶቹ መኖር ግን የፕሮፌሰር መስፍንን ታላቅነት አይቀንሰውም።

የደርጉ የደኅንነት ሹም ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ስለፕሮፌሰር መስፍን የተናገሩት የሚከተለውን ነው፡- “መስፍን እንዲህ ነው፣ እንዲህ ነው የሚባለው ነገር ከጥላቻ ይመስለኛል እንጂ እሱ በንጉሡ ጊዜ የነበረው አቋም፣ በደርግ ጊዜ የነበረው አቋም፣ አሁንም በኢሕአዴግ ያው ነው። አልተለወጠም። ኢትዮጵያ፣ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ አላት ብዬ የምለው ሰው [እሱ] ነው።”

Filed in: Amharic