>

ወያኔ ለሕዝብ የሚያከፋፍላቸው አደንዛዥ ዕፆች [ፍርዱ ዘገዬ]

እያንዳንዱ መንግሥት በተለይ ደግሞ ዴሞክራሲን የሚጠየፍ አምባገነን መንግሥት የሚገዛውን ሕዝብ የሚያደነዝዝበት የተለያዩ ሥልቶችን ይነድፋል፤ እነዚህንም ሥልቶች እያፈራረቀና እንዳስፈላጊነቱም በጅምላ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በብልግናና በኢሞራላዊ ምግባራት የተሞሉ የሙዚቃና የፊልም ኢንዱስተሪዎችን ማስፋፋትና በአደንዛዥ ዕፅ በተለይ ወጣቱን ትውልድ መበከል ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እግር ኳስንና የውሸቱን የነፃ ትግል ትርዒት (wrestling) የመሳሰሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንም በዚሁ የሕዝብን የትኩረት አቅጣጫ ማስለወጫ መንግሥታዊ “ጥበቦች” ውስጥ ማካተት ይቻላል፡፡ የዛሬውን አያድርገውና በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት የነቮድካን ዋጋ እጅግ በማርከስና ማንኛውንም የውጭ ሚዲያ ዝግ በማድረግ ሕዝቡን አደንዝዘው ይገዙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ወያኔ ግን የመጠጦችንም ዋጋ ከሰማይ አዝልቆ እየሰቀለ መደበሪያና መቆዘሚያም እያሳጣን ነው – የ330ሚ.ሊ ቢራ በዚያን ክፉ ዘመን ሊያውም ተወደደ ተብሎ በ40ሣ. እንዳልተጎነጨናት ዛሬ በዝቅተኛ ሆቴሎች ባማካይ ከ16 ብር በታች አልገኝ ብላለች፤ እሷም ባቅሟ ተንጠባረረችብን፡፡ ያገር ተወላጇ ካታማይሲን(ቁንድፍት) ራሷ ከንፈርን ለማታረጥብ ቀልበ-ቢስ መለኪያ 3 ብር እንከፍላለን – በቅርቡ ከዚያ ከዓመታት ሁሉ ተለይቶ ባይፈጠር የሚሻለው 97ዓ.ም የምርጫ ወቅት በፊት በስሙኒ ነበር የምንቸልሳት፡፡ ባይገርማችሁ የቼልሲ ደጋፊ ነኝ – የማታ ቸልሲ እንጂ ለቅሪላ ደንታም የለኝ ታዲያ፡፡

በቀጥታ ወደ ሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ እንግባና የሀሽሽ ዓይነቶችን እንመልከት፡፡ ወያኔዎች በተንኮል ሥራ እጅግ የተጠበቡና የተራቀቁ አማካሪዎች እንዳሏቸው (ከሚሠሩት ወንጀልና ጥፋት አንጻር) ከዕድሜያቸው መንዘላዘል ብቻ ሣይሆን ዘወትር ከሚያከናውኗቸው ነገር ግን ከነርሱ በፍጹም ሊጠበቁ ከማይችሉ ዕኩይ ተግባሮቻቸው በሚገባ መረዳት ይቻላል፡፡ ጎሣን ከጎሣና ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማጋጨቱን የተበላ ዕቁብ ይዘን ቤተሰብን እስከማፋጀት የሚደርሰውን የሸር ሥራቸውን ስናጤን  በማይምነትና ምናልባትም በየዋህነት የምናውቃቸው  እነዚህ ወንድሞቻችን ይህ ሁሉ ከተዓምር ያላነሰ ድርጊታቸው ካላንዳች ረዳት እንደማይሆን እንገነዘባለን፡፡ ለኛ ከማይተኛ ትልቅ ኃይል ጋር እንደሚሠሩ ለማወቅ ነቢይነትን አይጠይቅም፡፡ የዋህ ታዛቢ ግን ወያኔዎች ብቻቸውን የሚገዙን እየመሰለው በኛ በብዙዎች “ፍርሀትና ትግስት” መደነቁ አይቀርም፡፡

እናም ሕዝብን በዚህና በዚያ ከማናከሱና የተወሰነ ፖለቲካዊ ትርፍ ከማጋበሱ በተጓዳኝ ዜጎች እንዲደነዝዙ የሚያድርጉበት ከፍ ሲል የተጠቀሱትን የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ዘዴዎች አሏቸው – ወያኔዎችም ሆኑ ጌቶቻቸው፡፡ ዓለማችን አእምሮን በሚቆጣጠሩ መሠሪዎች ተወጥራለች፤ የጓድ መንግሥቱን አነጋገር ልዋስና – ብታምኑም ባታምኑም “የምትናገረውን ቀርቶ የምታስበውን ደርሰንበታል” በሚሉ የስምንተኛው ሺህ ሐሣይ መሲሆች ተወረናል፤ ደፍረውናል፤ ንቀውናል፡፡

በበክት ስሙ ማለቴ በክት ስሙ ሕወሓት የምንለው የኛው ወፍዘራሽ ፍጡር ሕዝቡን የሚያደነዝዝባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው፡፡ የዐዋጁን በጆሮ እንዳይሆንብኝ እንጂ ቀዳሚው የወያኔ ሀገርን ማውደሚያ የቆረጣ ሥልት ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ከትምህርት ገበታ መለየት ወይም እዚህ ግባ በማይባል የትምህርት ሥርዓት ማደደብና ዲግሪ እንኳን ይዘው ስማቸውን አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ የምሁር ማይማን ማድረግ ነው፤ ይህ በተግባር ተፈትኖ ፍሬያማ የሆነላቸው ትልቁ ሥልታቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጠፋውን ትውልድ ለመመለስ ወደፊት ብዙ መማሰን ይኖርብናል፡፡

የውሸት ቱሪናፋና የሀሰት ዘገባ እያቀረቡ ሕዝቡን በባዶ ጩኸት ጆሮውን ሲጠልዙ የሚውሉ ቲቪዎችንና ራዲዮኖችን ማስፋፋት ደግሞ ሌላኛው ሀሽሽ ነው፡፡ ስሙን እንደሸሚዝ ከሚለዋውጠው ኢቲቪ ጀምረህ ኢቢኤስን፣ ናሁን፣ ዋልታን፣ ቃናን፣ ቲጂን …ኤፍኤሞችን፣ አይጋፎረምን የመሰሉ ድረገፆችን፣  ጋዜጦችን … ብትመለከት ሁሉም የወያኔ ሕዝብን የማደንቆሪያ ሀሽሾች ናቸው፡፡ በብዙ ጫና ውስጥ ከሚያልፉ በጣም ጥቂት የኤፌም ፕሮግራሞች በስተቀር አብዛኛዎቹ በሬ ወለደ ዓይነትና ከሕዝብ ችግር ጋር ጭራሽ የማይገናኝ ዝግጅት ነው የሚያቀርቡት፡፡ አንድም የረባ ነገር ሲሠሩ አታይም፡፡ የሚያወሩት ሁሉ ከወሲብና ከስፖርት ያውም በአብዛኛው ከእግር ኳስ አይወጣም – እግር ኳስ ስልህ ደግሞ ተጫዋቹ ስንት ግራም ቁርስ እንደበላና ከሚስቱ ጋር ስንቴ እንደተሳሳመ ወይም… ሳይቀር መዘክዘክን ይጨምራል – “ራሷን በልቷት እግሯን ያኩላታል” አሉ? እንደ ወላይታ ሶዶ ዳጣና እንደሸዋ ሚጥሚጣ ስለሚፋጀው የኑሮ ውድነትና የሙስና መረብ ግን አንድም ትንፍሽ አይሉም፤ ጉዶች! የሕዝብን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግር ነቅሶ የሚያወጣና መፍትሔ እንዲገኝ የሚያደርግ ጋዜጠኛም ሆነ የሚዲያ ተቋም በሀገራችን የለም – ሁሉም ተለባብሶ መጓዝን፣ ከወያኔ ጋር ተሞዳምዶ የግል ብልግና ማለትም ብልጽግና መሻትን መርጦ እውነትን አርቆ እየቀበራት ይገኛል፡፡

አሁን አሁን ብዙ የሣተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭቶች አየር ላይ እየዋሉ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል የሁሉም ዓላማ አንድና አንድ ነው –  ባጭር ታጥቆ ወያኔን ማገልገል፡፡ እውነትን መደበቅ፣ ሀሰተኛ ሀገራዊ ምስል በመፍጠር ወያኔ ልማታዊ መንግሥት እንደሆነ መስበክና በተለይ በውጪ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊና ስለኢትዮጵያ ቀናውን የሚያስብ የዓለም ዜጋን ማታለል፣ ወጣቱን በሙዚቃና ዳንኪራ ቱማታ ጠምዶ ሌት ከቀን ማስጨፈር፣ ርሀብንና ጥምን፣ በሽታንና ዕርዛትን ግን መደበቅ … ዋና ተልዕኳቸው ነው፡፡ እንግዲህ እኔ አዲስ አበባ እንደመኖሬ እነዚህ ቱልቱላዎች የሚያሳዩትንና በገሃድ እየሆነ ያለውን ሰቅጣጭ ሀገራዊ ምስል በሚገባ አውቃለሁና በነሱ አስነዋሪ ድርጊትና በኛ አስከፊ የሕይወት ገጽታ መካከል ያለውን ልዩነት በማንበብ በሰው ልጅ በተለይም በዘመናችን በምንገኝ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ዋሾነትና መስሎ አዳሪነት ከልክ በላይ ማዘኔ አልቀረም – ውሸት እንደባህል ተወስዶ ትውልድ ሁሉ በውሸት እንዲቀረጽ መንግሥታዊ በጀት የተመደበበት ብቸኛ የዓለም ሀገር ቢኖር ሀገራችን ኢትዮጵያ ትመስለኛለች፡፡ እውነትን ከመናገር አንጻር ሰው ኅሊናውን በሆዱ ከለወጠ የመጨረሻው ቆርጦ ቀጥል ይሆናል – እንደዚያ መስፍን በዙ እንደሚሉት አጋሰስ ሰውዬ ማለት ነው፡፡ (እንዴት ያለው ሆዳም መሰላችሁ እናንተዬ፤ ሰው ማማት ስለማልወድ ግን ስለዚህ የወያኔ ቅጥር ሚዲያ-ገዳይ፣ ስለዚህ እምብርት የለሽ ሆድ-አደር የወያኔ አጨብጫቢ አሁን ምንም መናገር አልፈልግም፡፡ ስለግለሰብ ማውራት ከሞራል አኳያም ቢታይ ትክክል አልሆንምና ስለዚህ ባለጌና ስድ አደግ ሰውዬ ትንፍሽ አልልም፡፡ ስለሆነም ሌሎቻችሁም ብትሆኑ ስለነዚህ ዓይነቶቹ የሀገር አራሙቻዎችና የታሪክ አተላዎች ማውራት የለባችሁም – የደርግ አማርኛ እንዴት ትዝ አለኝ እባካችሁ?)

ዛሬ ኢትዮጵያንሪቪውን ስዳስስ አንድ ጽሑፍ ቀልቤን ሳበውና ገለጥኩት – አነበብኩትም፡፡ ያን መሰል ጽሑፍ ልጽፍ ካሰብኩ ደግሞ ቆይቻለሁ – በይዘት የሚመሳሰል፡፡ ይህ ሰው – ኢድሪስ ሙክታር የተባለ ዜጋ – ቀደመኝና አወጣው፡፡ ዕጥር ምጥን ባለ አቀራረብ ግማሽ ገጽ እንኳን በማትሞላ ወረቀት ስለቃና ቲቪ አደገኛነት አፍረጥርጦ ነገረን – ቢገባን፡፡

እኔ ደግሞ ኅያው ምሥክር ነኝ፤ ልጽፍ የነበረውም በዚሁ ጦሰኛ ጣቢያ ምክንያት  የደረሰብኝን የራሴን ተሞክሮ ነበር፡፡ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ጓዶች!!

ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን – ቀልድ አይደለም እውነቴን ነው – ባለፈው ሰሞን ሥራ ውዬ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ቤቴ እገባለሁ – ድክም ብዬ፡፡ ሣሎን ውስጥ ባለቤቴና ልጆቼ ያው እንደዱሮው ይሄን የፈረደበት ቃና ቲቪን ይመለከታሉ፡፡ እኔ በጣም እርቦኛል፡፡ ራት ትሰጠኛለች ብዬ ወደባለቤቴ አቅጣጫ እያማተርኩ ብቁለጨለጭ እሷ ያለችው እነኦማርና ጁሊያን ጋር ናት – ቃና ውስጥ – “ውስጤ ነው” በሚሉት አዲስ ፈሊጥ ተወስዳለች፡፡ አፍ አውጥቼ ራት ብዬ ተናገርኩ – ማንን ወንድ ብላ! መልሱ ዝም ጭጭ ሆነ፡፡ ትንሹ ልጄ ሰማኝና “እየተሠራ ስለሆነ ትንሽ ጠብቅ አለኝ፡፡ ያኔ ብልጭ አለብኝ፡፡ እንደዱሮው ቢሆን በዚያ ቅጽበት ውስጥ የባለቤቴ ጉንጮች ከደረሰባቸው መብረቃዊ የአይበሉባም በሉት የቃሪያና የበርበሬ ጥፊ የማጥቃት እርምጃ  የተነሣ ማበጥ ጀምረው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ወንድም ሴትም አልለይ ብሎን ሁለት አባውራ ባንድ ቤት ውስጥ መኖር ተጀመረና አዛዥና ታዛዥ ጠፋ፡፡ ወደኪችን አፍንጫየንና ፊቴን ባዞር ገና የተመታ ሽሮ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል – ዱሮ  በደህናው ቀን እኮ አንድ ዓይነት ይቅርና ሲመቻትና ከልደታ እስከባታ አካባቢ ሁለትም ሦስትም ዓይነት ወጥ ሠርታ ገና የበሩን ደፍ ሳላልፍ ታቀርብ ነበር፡፡ አሁን ዕድሜ ለቃና – ቅንቅን ይውረሰውና – የሚጠበቀው ዐረፋው እስኪከትና ጥሬ ሽሮው እስኪጠፋ ኖሮ በ15 ቁጥር ምሥማር ጥርቅም አድርገው ዘጉኝ – ቤተሰቦቼ፡፡ የቡና ዘነዘና አንስቼ ቲቪውን የዶጋመድ ላደርገው ቃጣኝ፡፡ ግን አንድ ሞኝ ወገናችን አንድ ወቅት በራሱ ላይ የወሰደው የቂል እርምጃ ወዲያው ትዝ አለኝና ተውኩት – (ያ ሞኝ ሰው ምን አደረገ መሰለህ – ባለቤቱ እጅግ ቀናተኛ ነበረችና በወጣ በገባ ቁጥር “ከእገሊት ጋር እንዲህ እንዲህ ስታደርግ ቆይተህ ነው አይደል ያመሸኸው? አልተነቃብኝም ብለህ ነው አይደል? በላ ምን ይዘጋሃል?” እያለች ትነዘንዘው ገብታለች፡፡ ሰውዬው ስልችት አለው፡፡ ከቀን እቀን እየባሰ የሄደው የፍቅር አይሉት የጠብ ንዝነዛዋ በዛበት፡፡ አይፍረድባችሁ ወገኖቼ፡፡ አንድ ቀን ግን ስሜቱን መቆጣጠር አቃተውና የሚስቱን የተሣለ የሽንኩርት ቢላዎ አንስቶ ያን የቅናት መንስዔ የሆነ የአካል ክፍሉን ከመባቀያው ጀምሮ ይሸረክትና “በይ የኔ እህት ከእንግዲህ አትነዝንዢኝ፤ ንብረትሽ ይሄውልሽ፤ ብትፈልጊ አዝለሽው ዙሪ… ከፈለግሽም ቀቅለሽ ብይው…”ይልና አለቬርባል ያስረክባታል፡፡ በዜና ነው የሰማሁት – ኢትዮጵያ ውስጥ መሰለኝ የሆነው፡፡) እኔ ግን በጣም ከመናደዴ የተነሣ ወጥቼ ሄድኩ፡፡ ዕውር ቢሸፍት ጓሮ ለጓሮ እንዲሉ ሆኖ ግን ምሽቱ ስለጠነነብኝ ሩቅ መሄድ አልቻልኩምና ሠፈር ውስጥ ጥቂት ተንጎራድጄ ተመለስኩ፤ ያቺኑ ሽሮየንም በልቼ ነገር በሆዴ ይዤ እያብሰለሰልኩ ተኛሁ – እልኹ ስላለ ሌሊቱ አልበረደኝም፡፡ ለዚያ ያበቃኝ እንግዲህ ይሄ ቃና የሚሉት ከይሲ ቴሌቪዥን ነው – ትናጋውን የሚዘጋ ነገር ፈጣሪ ከላይ ይላክበት እንጂ ትዳርን ሳይቀር እየበተነ ነው፡፡ እሱው ላይ ተጎልታ ውላ ዋናውን የትዳሯን ምሰሶ አናጋችው – ከያ ቀን ወዲህ አሁንም ድረስ ኩርፍ ነን፡፡ እኔ ችየው እንጂ “የነገር አባትሽንና ነፍስ አባታችንን ጥሪና ያለያዩን፤ አሁንስ አበዛሽው!” ብል እችል ነበር፤ ግን በዚህ ዘመን እንኳንስ ተፋትተው ተጋብተውም አልሆነ፡፡ የቃና ጣጣ ብዙ ነው፡፡

ለመሆኑ ቃናን ማን ፈትቶ ለቀቀብን? ጣቢያው ምን እያደረገ ነው?

በመሠረቱ ይህ ጣቢያ ብዙ የተለፋበትና የተደከመበት መሆኑ ያስታውቃል፤ ብዙ ወጪም ሳይጠይቅ አልቀረም፡፡ ጅምሩ ደግሞ በጣም ጥሩ ነው፤ እኔ በበኩሌ አቀራረቡንና ዝግጅቱን ወድጄዋለሁ፤ በዘርፉ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አይሆንም፡፡ ይህ ዓይነቱ ጣቢያ እንደኛ ባለው በዕውቀትም በንቃተ ኅሊና ደረጃም በማኅበራዊ ሥነ ልቦናና በመሳሰሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ዳዴ ለሚል ማኅበረሰብ ሣይሆን ለሠለጠነ ሕዝብና ሀገር ነው ግሩም የሚሆነው፡፡ እኛ እኮ ፍላጎታችንን ራሱን በመፈለግ የምንባዝንና ማናችንም የምንፈልገውን ነገር ሳናገኝ ወይም ያገኘን ሳይመስለኘን ከዚህች ዓለም የምንሰናበት ነን፤ አንዳንዶቻችን እኮ ያቺ የዱሮው ሁለተኛ ነው ሦስተኛ ክፍል የአማርኛ መጽሐፍ ውስጥ እንዳለችው አላዋቂ ኮራጅ ጦጣ ነን – ኩረጃን እንኳን የማናውቅ ፋራዎች – ግን ግን የሰለጠንንና ያወቅን የሚመስለን ግብዞች፡፡ አማራጮችን በአግባቡ መርምሮ የሚሆነውን ማለትም የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው ለይቶ ጥሩውን ለመያዝ በቅድሚያ የግንዛቤ ማዳበሪያ ትምህርት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሕጻን ልጅ ማርና መርዝ ቢቀርቡለት ማሩን ትቶ መርዙን ሊመርጥ ይችላል፡፡ ማኅበረሰብም አንዳንዴ እንደሕጻን ቢቆጠር ለርሱ ከመጨነቅ አኳያ ነውና እኔን መሰሉ አስተያየተኛ ሊነወር አይገባም፡፡ ወያኔና ደርግ ቁልቁል እንጂ ሽቅብ እንድንሄድ አላደረጉንም፤ ማጣትን እንጂ ማግኘትን አላስለመዱንም፡፡ ድንቁርናን እንጂ ዕውቀትን አላወረሱንም፡፡ ትዕቢትን እንጂ ትህትናን አላሳዩንም፡፡ ስለዚህ ማንም ቅራቅንቦውን እያመጣ ቢደፋብን በጣም እንጎዳለን፤ በሂደት ከሀገርና ከሕዝብ ደረጃም ልንወጣ እንችላለን፡፡ ዴንማርክ ሄደህ ይህን መሰል ቲቪ ብትከፍት ምንም ማት አይደለም – The society is well informed and knows what is bad and good – እንዴ፣ እኔስ እንግሊዝኛ  አያምረኝም እንዴ? ምርጫውን የሚያውቅና ስለምርጫም ግንዛቤ ያለው ሕዝብ ነውና ተጎጂ ጭራሹንም አይኖርም ባይባልም መጎዳቱን የሚረዳና ከአጓጉል ነገር ራሱንና ቤተሰቡን የሚጠብቅ ብዙ የነቃና የተደራጀ (የታጠቀም ልበል ይሆን?) ሕዝብ ስላለ ሀገር በቀላሉ አትፈረካከስም፤ ትውልድም በመጤ ባህል እንደኛ በዋዛ አይፍረከረክም፡፡ እዚህ ግን … እስኪ ተወኝ ወንድሜ፡፡

kana logo - imagesቃና አንዱ የወያኔ መርዝ ወይም ሀሽሽ እንደሆነ ያመንኩት እንግዲህ እኔን ጦም ለማሳደር የገባውን ቁርጠኝነት ስታዘብ ነው – በኔ ውስጥ ደግሞ ሚሊዮኖችን፣ በሚሊዮኖች ውስጥ ደግሞ “እንኳንስ ዘምቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ”ን ውድ ሀገሬን ኢትዮጵያን አየሁ፡፡ በርግጥም ስናስበው ቃና በአንድ ምሥኪን ሰው ቤት ገብቶ ይህን ዓይነት ተዓምር ከሠራ በሀገር ደረጃማ እንዴት ዓይነት ጉድ አይሠራ፡፡ ኢድሪስ እንዳለው በቅርቡ ሥራም ትምህርትም ቀጥ ሳይል አይቀርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሰው ሁሉ እየተጃጃለ ነው፡፡ ሆዱን ሳይሞላ ራሱን በፊልም እያታለለ ይኖራል፡፡ በዚህ መሀል ስለ ሀገር ማሰብ፣ ስለኑሮ መጨነቅ፣ ግፈኛውን የወያኔ አገዛዝ ስለማስወገድ ማሰብ፣ ስለነፃነት ማሰብ፣ ስለሕይወት መሻሻል ማሰብ፣ ስለትምህርት ማሰብ፣…. ዕርም ሊሆን ነው፡፡ ይህ ችግር ቦሃ ላይ ቆረቆር እንደማለት ነው – ዕንቅርትም ላይ ጆሮ ደግፍ፡፡ እንኳንስ ቃናን የመሰለ የጼጼ ዝምብ (tsetse fly) ታክሎብን ዱሮውንም ብዙዎቻችን እንቅልፋሞች ነን፡፡ ወያኔ ደግሞ ኢቲቪው ሲፈልግ ሰሚና ተመልካች አጥቶ ድርግም ይበል እንጂ እንደቃና ያሉ ቲቪዎችን እየደጎመም ቢሆን ለምልመው እንዲኖሩ ያደርጋል – ጥሩ ቫሊየሞች ናቸዋ! ጥሩ babysitters ናቸዋ! ግሩም lullabies ናቸው እኮ! – ምድረ አበሻን ከገረድ እስከ ፕሮፌሰር ጥልቅ እንቅልፍ አስወስደው ሀገረ ቱርክንና ሩቅ ምሥራቅን በምናብ የሚያስጎበኙ ትክክለኛ አስማተ ዲያብሎስ ናቸው፡፡ አቤት ሀገራችን የገባችበትን ማጥ ሲያስቡት!

ቃና ቲቪ በተዛዋሪ ኢሳትንም ከአየር እያወረደው ነው፡፡ ወያኔ መለኛ ነው፡፡ በነዚያ ጮንጯና የቻይና ቴክኒሻኖችና በሼህ እንትናዬ ገንዘብ ኢሳትን ከአየር ማውረድና መስቀል ሲሰለቸው ጊዜ ሌላ ዘዴ አመጡ – መላ ካልተፈለገለት እጅግ በጣም አደገኛ ዘዴ ተከሰተላቸው፡፡ እኔ ለምሣሌ ኢሳትን ከማየት ተከልክያለሁ – በወያኔ ሳይሆን በእንቅልፋሙ ቤተሰቤ ነው የተከለከልኩት – “እንቅልፋሙ” ስል ፍካሬያዊውን እንቅልፍ እንጂ እማሬያዊውን አትዩ፡፡ ወደምኝታቸው ሄደው ሲተኙልኝ ብቻ ነው የማየው፡፡ አለበለዚያ ይሄ ቃና ከመጣ ወዲህ አብሶ ምንም አላይም፡፡ እርግጥ ነው በድረገፅ ሁሉን ነገር እከታተላለሁ፡፡ በቲቪ ኢሳትን ልይ ብል “እንዴ! የጀመርኩት ፊልም አለ፤ ጥቁር ፍቅርን ጀምሬያለሁ፤ የውበት እስረኞችን ጀምሬያለሁ” እያሉ ቤተሰዎቼ ከግራ ከቀኝ ይንጫጫሉ፡፡ ያኔ እበሳጭና እተኛለሁ፡፡ እነሱ እሚፈልጉትም ያን ነው – እኔንም እንቅልፋም ማድረግ፡፡ ወያኔ በቤቴ ተሳክቶለታል፡፡ ለነገሩ በቅርቡ የራሴን ቲቪ መግዛቴና መገላገሌ አይቀርም – ጥሩ አማራጭ፤ ዲሹን በጋራ ሪሲቨርንና ቲቪን በግል፡፡ ደሞስ የራሴን ሣተላይት ቲቪ ብከፍትስ? ይሄውና ያ አንዱ ብርቅዬ ልጃችንስ በቅርቡ ጄቲቪ ብሎ ጀምሮ የለ? ምን ይጎለኛል፡፡ ጆሲን ግን አደራችሁን ተከታተሉለት፤ እደግ ተመንደግ በሉት፡፡ ግሩም ልጅ ነው፡፡ የልጅ ዐዋቂ፡፡ እነቴዲንና እነጆሲን ይባርክልን፡፡ እነሁሉን ላገር አሳቢና ተቆርቋሪዎች ይጠብቅልን፡፡

ግን ግን ምን እንሁን? ምን ይብቃን? ወዴትስ እንሂድ? ከወያኔ ሀሽሽ እንዴት እንዳን?

ቀደም ብዬ የጠቀስኩላችሁን አጭር ጽሑፍ እዚሁ እንድታገኙት ከዚህ በታች አኑሬላችኋለሁ፡፡

ቃና የሚባል የቴሌቪዥን ፕሮግራም መላ ካልተበጀለት በቅርብ ቀናቶች ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እውነታዎች

1) ከፍተኛ የሆነ የትዳር መቃወስ ይፈጠራል
2) ትምህት ቤቶች ይዘጋሉ(የቤት ስራ የሚባል ነገር ይቀራል
3) መስሪያ ቤቶች የስራ ሳይሆን የእንቅልፍ ቦታ ይሆናሉ
4) የሚወለዱ ህፃናት በሙሉ ዘሀራ ወይም ቻንድራ የሚል ስም ይወጣላቸዋል
5)EBC  “ ebc ውስጤ ነው#” በሚል logo ይቀይራል
6) አውቶብሶች በሙሉ ዲሽ ያስፈልገናል በሚል አድማ ይመታሉ
7) መንገዶች በሙሉ ቃና ቃና በሚል እግረኞች ይጨናነቃሉ
8) ፍቅረኛሞች እወድሻለው የሚል ቃል ቀርቶ ውስጤ ነህ በሚል ቃል ይተካል ይመ አስተናጋጆች      ሜኑ ሲጠየቁ ቃናም አለ ይላሉ
10) የካፌ፡የሆቴል የምግብ ዋጋ በ3እጥፍ ይጨምራል
11) ሳያዙ ሳይሆን ” እነ እንትናን ሊያዪ መቀመጥ ክልክል ነው “በሚል ማስጠንቀቂያ  ሬስቶራቶች   ይጨናነቃሉ …
12) የሰዓት መለኪያችን ቃና ላይ በሚታዩት ፊልሞች ይሆናል ማለትም “ፍሬንዴ ሰዓት ሲባል   ባክ ገና ነው ጥቁር ፍቅር አልጀመረም” መባባላችን የማይቀር ነው
13) የፌስ ቡክ ፕሮፋይል ፒክቸሮች በነቻንድራ,በነ ኦማር,በነ ጁሊያ..  ምስል ይቀየራል
14) በአንፃሩም የፌስ ቡክ የፕሮፍይል ስሞች በቃና ፊልሞች ስሞች ይቀየራሉ በአብዛኛው  የሴቶች ስም ለምሳሌ;አበሩ ኦማር ጋል፣ኪዱ ጁሊያን ወጥመድ…..ሌላው ደግሞ    ከበፊቶቹ  የተበረዙስሞች ጋር ..ቻንድራ ብሪዚ ብራውን…. በሚል መቀየራቸው        የማይቀር ነው
“ባጠቃላይ ሀገሪቷ እንቅልፋም፡የደነዘዘ፡…… ዜጋን ማምረት ትጀምራለች”

 

Filed in: Amharic