>
4:38 pm - Thursday December 2, 7047

”የግንቦት 20 ፍሬዎች” (አጎቴ እንደነገረኝ) [አንዱዓለም ቡከቶ ገዳ]

image - a penአጎቴ በእድሜው ገፋ ያለ ነው፡፡ በደርግ ሰአት ብዙ መከራ አይቻለው ባይ ስለሆነ ስለ”ግንቦት ሃያ ፍሬዎች ” አውርቶ አይጠግብም፡፡ እቤቱ ስገባ በቴሌቪቭን ስለግንቦት ሃያ ”ወፍሪ ቴዎድሮስ” የሚል የትግርኛ ዶክመንታሪ ፊልም እያየ ሲያለቅስ አገኘሁት፡፡
ትግርኛ አይችልም ግን ለኢሃዲግ ካለው ፍቅር እና ቀበሌያችን በትግራዋይ አለቃ ስር ለባለፉት 25 አመታት ከመስራቱ የተነሳ ትግርኛ እንደሚናገር ያስባል ፡ በዛ ላይ ”አቡነ አረጋዊን” ብሎ ከማለ ማለ ነው! የካቲት 11 ነጭ በነጭ ለብሶ አደባባይ መውጣቱ ሳያንስ ለግንቦት ሃያ ከሆኑ የአድዋ ሰዎች ጋር በሬ አርዶ ቅርጫ ያስገባል፡፡አሁን ባለበት ደረጃ አጎቴን ትግሬ አለመሆኑን እና የባሌ አሮሞ መሆኑን ከማስረዳት እና ከማሳመን በስኳር ኮርፖሬሽኑ ስም የተዘረፈውን 77 ቢሊዮን ብር መኩሪያ ሃይሌ ጠፉብኝ ካላቸው 88 ብሎኮች ውስጥ በአንደኛው ስቱዲዮ በጆንያ ታስሮ በሜቴክ ሻለቃዎች ሲጠበቅ ማግኘት ይቀላል፡፡

ግን ወያኔ የምሩን ነው!? ይሄ ሁሉ ብር ጠፋብኝ ብሎ ዝም የምንለው ይመስለዋል?! አንድ የህዳሴ ግድብ የሚገነባ ብር ቅሞ ሲያበቃ ”ብሩ የታለ?!” ሲባል ምድረ ሃላፊ ተሰብስቦ ሎተሪ ይቆርጥልኛል! እኔ በልጅነቴ ገበያ ተልኬ ብር ጠፍቶብኝ ”በጨ ጠቆረ” ተጫውቼ ለማስመለስ ያደረኩትን የጅል ጥረት አስታወሱኝ….. አይደብሩም?!

አንዱ ጓደኛዬ እነ ጠሚው የቆረጡትን ሎተሪ እንቁረጥ ስለው ምን ቢል ጥሩ ነው ? ”ሞኝ ነህ እንዴ የኢሃዲግ ባለስልጣናት የ16 ሺ ብር ሎተሪ ቆርጠው አንተ የሚደርስህ ይመስልሃል?! ምርጫ 100 ፐርሰንት አሸንፌያለሁ ከሚል ገገማ ፓርቲ ጋር ደግሞ በብሬ ቁማር ልጫወት?” …ሰው አምርሯል…፡፡

ግን ይሄን ሁሉ ብር የሸቀለው ሎተሪ ሻጭ ኖርማል ”ሸበላው” አይመስለኝም….. ቁምጣ ሲያለብሱት ተምታታብኝ እንጂ የሆነ የወጣት ሊግ ስብሰባ ላይ በቲቪ ያየሁት ይመስለኛል….ሎል

ቆይ ግን ወያኔ እየተማረች ሰትሄድ እየባሰባት ነው እንዴ የምትሄደው? (ድሮ ኢሃዲጎች በሚኒስትሪ ካርድ እንቁልልጬ እንዳልተባባሉ ዶክትሬቱን መቀለጃ አደረጉት እኮ! ባለፈው የዛፓ(የፖሊስ) አለቃ የነበሩት አቶ ጎልድነህ ገበየሁ እንኳን ዶ/ር ተብለው በቲቪ አየኋቸው…..አቤት 97 ስንቱን አሳየሽን?!……ያኔ እነ ብሬ ዶክትሬቱን እንቁልልጬ ሲሏቸው ኢሃዲጎች ቂጣቸውን ደፍነው(በቪኖ ቡሽ ይመስለኛል) ”ቸክለው ” ሲያበቁ ይኸው በአጭር ግዜ ዶ/ር አርከበ፡ ዶ/ር ወርቅነህ……ምናምን ሆነው ቁጭ አሉዋ!……እስከነተረቱስ ”ምቀኛ ጎረቤት እቃ ያስገዛል!” አይደል የሚባለው!(አቤት እኔ ግን ቅኔ ዉዉወው! ዋሸራ መኖር የነበረብኝ ልጅ ጎተራ ምን እንደምሰራ እኮ ነው የሚገርመኝ!)፡፡

በነገራችን ላይ አጎቴ እንባውን እያባበሰ መክሰስ ቀረበለት…. ጭራሽ ”ጥህሎ” ነው የሚበላው….አሁንስ አስጠላኝ …..ማርያምን!

ወደ አጎቴ ጭውቴ ሳልመለስ ይህቺ የትምህርት ነገር ላይ የምትገርመኝን አንድ ነገር ልንገራችሁ…..ያኔ ገቨርንመንት ሃውስ (መንግስት ቤት) ስሰራ መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ት/ት ጀመርኩ…ለ15 ቀን የቲዎሪ ት/ት ክፍል ውስጥ መጎለት ነበረብኝ…ጊዜ (ታይም) ከየት ይምጣ? የገቨርንመንት ስራ ፋታ አይሰጥም ….ማታ ራሱ ወደ ሆም ፋይል ይዘን ሄደን መስራት ነበረብን…….የአስራአምስት ቀኑ ት/ት አመት ፈጀብኝ… በዚህም ተጽእኖ ከዛ ሁሉ ት/ት ዛሬ ትዝ የሚለኝ ”ዜብራ ክሮሲንግ” ብቻ ነው፡፡ እና ኋት ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ….. እኔ ያኔ በነበረኝ ትንሽዬ (0) ሀላፊነት እንደዛ ታይም አጥቼ ለአስራአምስት ቀን የመንጃ ፍቃድ ት/ት ስቸገር እነ ወርቅነህ ወላ ሚኒስቴር ወላ ኮሚሽነር ሆነው ዶክትሬታቸውን የሚሰሩት በምን ተአምር ነው…..? አሜዚንግ ይላል ፈረንጅ (አስገራሚ ነው ለማለት ፈልጎ ነው፡፡) እርግጠኛ ነኝ እኚህ ዛፓ የነበሩት ሰውዬ በዛፓነት ጊዜያቸው ከሆነ ት/ቱን የጀመሩት አንድ ሰው በጠረባ አንሳፈው ወደመሬት እስኪመለስ ጊዜ ላለመፍጅት የሆነች ሃንድ አውት ነገር እያነበቡ ይጠብቁ ነበር እንጂ በምንም ተአምር የአንድ የአንባገነን ስርአት የፖሊስ አለቃ ግዜ አግኝቶ ዶፍተር ሆነ ቢሉኝ አላምንም….አለማመን መብቴ ነው፡፡(እስኪያንሳፍፉኝ ድረስ)

አጎቴ እራቱን በልቶ እንደጨረሰ ነጭ ጠላ ቀረበለት፡፡”ይገርምሃል ከግንቦት ሃያ በፊት ኢትዮጲያ ገሃነም ነበረች!”፡፡ አለኝ የትግርኛ ቃና በተጫነው ድምጽ…(የትግርኛውን ዘዬ በግድ ስለአመጣው ልክ ተመስገን በየነ ዜና ላይ ያለችሎታው ”መቀለ” ሲል የሚያወጣው አይነት የሚያሥጠላ ቅላጼ አለው)

”አከሚቲ አከና ና ን ጄቹ ደንዴቺ?”(እንዴት እንደዛ ልትል ቻልክ?) አልኩት በኦሮምኛ

”ሀራይ! ” ብሎ ቀጠለ…..ጭራሽ

”ይገርምሃል በደርግ ሰአት እኮ ሰው መንገድ ላይ መዘዋወር እንኳ አይችልም ገና ከቤትህ በራፍ ብቅ ስትል የደርግ ህዝብ ገዳይ ኮሚቴ (ደህገኮ) በጥይት ቅልብ ነበር የሚያደርግህ አለኝ ፊቱን አጨፍግጎ፡፡ለምን ማለት አላስፈላጊ ጭቅጭቅ ስለሚያመጣ ተውኩት፡፡

”ደርግ ገበያ ላይ ቦንብ ስለሚጥል ሰው ገበያ ሄዶ መገበያየት አቆመ ”….ኢ ቤይ” የሚባል የኢንተርኔት የንግድ ስርአት የመጣው በዛ ፍራቻ ነው…..ይገርምሃል ማንም ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው መናገር አይችልም…በማንነቱ ይሸማቀቅ ነበር ጋምቤሎች እራሳቸውን ”ጥቁር ጎንደሬ” ብለው ነበር የሚጠሩት አረ ውውው! ስንቱን ግፍ አውርተን እንችለዋለን!?” አለና ነጩን ጠላ ሳብ አደረገ፡፡

”ይገርምሃል አያትህ ያኔ ከጉራግኛ ውጭ ጆሮዋን ብትቆርጣት አትሰማም ነበር እና ጆሮዋ ታመመ እና የጆሮዋ የላይኛው ክፍል በድን ሆነ ጋንግሪን ነው ተባለና ጆሮዋ ተቆረጠ….. ምንም አልተሰማትም….እና የዚህች አያትህ ባል ኦሮሞ ነው ጥቂት አማርኛ ቃላት ብቻ ነበር የሚያውቀው ሃኪም ቤት ሄዶ እግሩን ታሞ ”ምንህን ነው ያመመህ?” ቢሉት ”እግር” የሚለውን ቃል ከየት ያምጣው …. ያኔ ደሞ የነፍጠኛ ስርአት ስለነበረ ካለ አማርኛ መናገር አይቻልም! በቃ አይኑ እያየ እጄን አመመኝ አላቸው ቀኝ እጁን ቆረጡት! አቤት ግንቦት ሃያ እኮ ያልቀየረው የግፍ ታሪክ የለም….”.አጎቴ ትክዝ አለ(ወይም ትክዝ ያለ መሰለ)

”ሰው በቋንቋው አይዳኝም ነበር! ስንቱ ወላይታ እና ሲዳማ ፍርድቤት ለፍታብሄር(ገንዘብ ነክ ክርክር) ሄዶ በቋንቋ ችግር ሞት እየተፈረደበት አለቀ መሰለህ! አይ ደርግ….አይይይ!!” አጎቴ የሚያወራት የደርግ ጊዜ ኢትዮጲያን ማሰብ ከበደኝ……

”እናት እኮ ”መላኩ ተፈራ የሞት ታናሽ ወንድም የዛሬን ማርልኝ ከእንግዲህስ አልወልድም!” ያለችበት ግዜ ነበር፡፡ ደርግ ገና እናቶች ሲያረግዙ ልጆቻቸው የሶስት ወር ጽንስ እያሉ እንኳን ለብሄራዊ ውትድርና መመልመል ጀምሮ ነበር….የሰራዊቱ አመራር የሆኑ ሻለቆች ጋንዲ በር ላይ እየጠበቁ እናቶች ገና ልጅ ወልደው ሲወጡ ልጆቻቸውን እየቀሙ ወደ ብላቴ እና ብርሸለቆ ይልኩ ነበር….እንቢ ያለ ህጻን ቂጡን በሳንጃ ይወጋ ነበር….ውርጃ ያጋጠማቸው እናቶች ”ወታደር በማስኮብለል” ተብለው ሲረሸኑ ትዝ ይለኛል……አረረረ ደርግ !”አጎቴ ተንገሸገሸ….

ወይ ደርግ! ግንቦት ሃያን ወደድኩት፡፡ድንገት ቲቪው የትግርኛ ስፖርት ፕሮግራም ሲጀመር ምሩጽ ይፍጠር ኢንትሮው ላይ ታየ(ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ኦሮምኛ ስፖርት ቀነኒሳን ትግርኛ ስፖርት ምሩጽን አሳይተው መጀመራቸው ነው)

”ይገርምሃል ምሩጽ ያኔ በደርግ ሰአት ሀገራችንን ወክሎ በሶሻሊስት ሀገራት ውድድር ላይ ሲሮጥ በሰው በላው ስርአት እምነት አልነበረውም….ያለፍላጎቱ ሩጫ ይጀምርና ሲጨንቀው ሊጠፋ በማሰብ አራት መቶ ሜትር ሲቀረው ዙሩን አክርሮ ከስታዲየሙ ለመፈትለክ ይሞክራል….በሩን እንዴት ያግኘው? ….ብቻ ሲጨርስ ፈረንጅ ”ይፍተር ዘ ማርሽ ሺፍተር” ብሎ ይከበውና ማምለጫ ጊዜ አሳጥቶ ወደ ሀገሩ ይመልሰዋል …ዋአይ ምሩጽ!” አለና አጎቴ ጠላውን ለበደ

እንደ አጎቴ አወራር ወያኔ ሀገሪቷን ሲቆጣጠር አንድም ሰው ከተማ ውስጥ ተርፎ ማግኘቱ ይገርማል፡፡ ይሄን ሃሳቤን አጋራሁት፡፡
”ምን የአባትህ ታናሽ ወንድም እንዴት እንደሞተ አታወቅም እንዴ?!” ብሎ ጀመረ…..”አብዮት ጠባቀዊች መንገድ ላይ ያዙትና በአንድ ጥይት ልንገድልህ ስለሆነ የጥይት አምስት ብር ክፈል አሉት የለኝም አላቸው እንዴት በአብየቱ ገንዘብ ላይ ትጨማለቃለህ ብለው በብዙ ጥይት በሳሱት…..”

ግርም አለኝ….አጎቴ እየተነቃቃ መጣ ”…..ደርግ እኮ መተንፈስ ነው የከለከለን ብዙ ሰው በ66 የካቲት ያቆመ ግንቦት 20 ከሰአት በኋላ ነው የተነፈሰው ..በዚሁ ነው አበሻ ውስጥ የሳምባ በሽተኛ የሚበዛው!” አለና …ጠላውን በአንድ ትንፋሽ ለበደ …..እኔም በአጎቴ ወሬ ስለተማረርኩ ሁለት ጣሳ ለበድኩ ሞቅ አለኝ….ሶስተኛየን ስለብድ ለአጎቴ ያለኝ ንቀት ጨመረ
”ገሩ ማ አከነቲ ሶብዳ?” እልኩት
”ቡዴና ኪያ ዋን ተ ኤፊ!” አለና ዝም አለ
አሳዘነኝ፡፡ አጎቴን ለማየት የሚፈልግ ”የግንቦት ሃያ ፍሬዎች” በቲቪ ሲቀርቡ የሚጠየቁት ሰዎች ውስጥ ፈልጉት
ይመቻችሁ ፡፡

Filed in: Amharic