>
2:25 am - Thursday July 7, 2022

መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ብሎ ሞተ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfin Weldemariamመንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፣ ይቅናችሁ ማለት ነው፤ ለልማት ለሚሰማሩ ሰዎች ምርቃት ይሆናል፤ ለጥፋት ለሚሰማሩ ሰዎች እርግማን ነው፤ እርግማን ብቻም አይደለም፤ የጥፋት ምኞትም ነው፤ ሰዎች ለጦርነት ሲዘጋጁ፣ ሰዎች ሌሎች ሰዎችን ለመግደል ሲሰናዱ፣ ሰዎች እርስበርሳቸው ለመገዳደል ጦራቸውን ሲስሉ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ማለት ከጀግና አንደበት የሚወጣ አይደለም፤ ብዙ ሰዎች ለእንጀራ ብለው ሕይወታቸውን ወደአጥርነት ለውጠው ሕይወቱን የሚጠብቁለት ሰው ጦር ቢወረወር አይደርስብኝም ብሎ ሌሎችን ለሞት ቢዳርግ አይደንቅም ይሆናል፤ አጥሩን ጥሶ ወደሱ የሚገሰግስ ሞት ሲያይ ቢፈረጥጥም አያስደንቅም፤ ሆኖም የሞት መንገድ ከጎን ብቻ ሳይሆን ከላይም ሊሆን እንደሚችል አለማወቁ ቀላል አለማወቅ አይባልም፡፡

ባህላችን ገዳይን የምናከብር፣ ለገዳይ የምንዘፍን ሕዝብ ቢያደርገንም፣ በድንቁርና ዘመን የነበረውን ይዘን ዛሬ ትንፋሽ የማትችለዋ ቢምቢ ሰውን መግደል እንደምትችል እያወቅን ለገዳይ ብንዘፍን ለሰውነታችን ውርደት ይሆናል፤ ይህንን ብለን ጉዳዩን እንዳንዘጋው በመግደል ልቡ የደነደነ፣ በድን ያልሆነለትን ሁሉ መግደል ልማዱ የሆነ፣ ከመግደል በቀር እምነቱን የሚገልጽበት መንገድ የሌለው፣ ከመግደል ሌላ እንጀራ የሚበላበት ሙያ የሌለው … እንዲህ ያሉ ሰዎች ሁሉ ተሰባስበው መገዳደልን የኑሮአቸው ዓላማና ዘዴ ሲያደርጉ በዝምታ መቀበል፣ ማለት አባቱ ሲገደል ልጁ ዝም ሲል፣ ባልዋ ሲገደል ሚስት ዝም ስትል፣ … ማንም ሰው አለፍርድ ሲጠቃ እያዩ ዝም ማለት ገዳዮችን ያራባል እንጂ ግድያን አያቆምም፤ እንዲህ ያለው በመንፈስ የሞቱ የበድኖች ዓለም ነው፤ በአውሬዎች ዓለም ጉልበት ያለው ደካማውን እየበላ ይኖራል፤ የተፈጥሮ ሕግ ነው፤ የሰው ልጅ በዚህ በአውሬዎች የተፈጥሮ ሕግ አይመራም፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሮ ሕግ የማይመራበት ምክንያት ምንድን ነው? አውሬዎች አያስቡም፤ የሰው ልጅ ግን ያስባል፤ የሰው ልጅ አእምሮ አለው፤ አእምሮ ስላለው ያስባል፤ ያስባል ማለት ከተግባር በፊት ትክክለኛውንና ስሕተት ያለበትን ለይቶ ያውቃል፤ ይህ የተፈጥሮ ሕግ አይደለም፤ የሰው ልጅ ሕግ ነው፤ ያሰበውንም ይናገራል፤ የሚወደውንና የሚጠላውን ስሜቱን ለይቶ ይናገራል፤ የሰው ልጅ ኅሊናም አለው፤ ‹‹ሌሎች ለአንተ እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን አንተም ለሌሎች አድርግ!›› ይላል፤ ይህ የተፈጥሮ ሕግ አይደለም፤ የሰው ሕግ ነው፤ ስለዚህም መግደል፣ በተለይም የመግደል ሱስ፣ የአራዊት እንጂ የሰው ልጅ የችግር መፍቻ ዘዴ አይደለም፤ አራዊት የሚገድሉት ሊበሉ ነው፤ ሰውም ወደአራዊትነት ሲለወጥ የሚገድለው ሊበላ ነው፤ እዚህ ላይ ሰውና አራዊት ይመሳሰላሉ፡፡

በመሠረቱ የመግደል ዓላማ ዝም ለማሰኘት ነው፤ ድንቁርና ነው እንጂ ካፍ ከወጣ አፋፍ ነውና የሚጠሉት ሀሳብ በሌላ ሰው አንደበት ይደገማል፤ መግደል የመጨረሻውን ዝምታ የሚያስከትል ቢሆን ክርስትናም እስልምናም 2007 ዓ.ም. አይደርሱም ነበር፤ ገዳዮች ሰዎችን ሁሉ ጨርሰው ብቻቸውን በመቅረት የሚያገኙት ጥቅም እንደሌለ ስለሚያውቁ የመግደል አማራጮች በሆኑ ሌሎች ዘዴዎች ይጠቀማሉ፤ አንዱ ማሰቃየት ነው፤ ሌላው ማሰር ነው፡፡

ሰዎችን በሀሳብና በእምነት ገባር ለማድረግ ጉልበተኞች የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መግደል፣ መግደል አላዋጣ ሲል ማሰቃየት፣ ማሰቃየት አላዋጣ ሲል ማሰር፣ ማሰር አላዋጣ ሲል አስሮ ማሰቃየት ነው፡፡

አውሬነትን የተላበሱ ሰዎች የማይገባቸው አንድ ነገር አለ፤ የሚጠሉትና ሰዎችን እስከመግደል፣ እስከማሰርና ማሰቃየት የሚያደርሳቸው ነገር በውስጣቸው ተቀብሮ አለ፤ ነፍሳቸው ከዚያ ነገር ጋር ተቆራኝታለች፤ በመጨረሻም የሚሸነፉት በዚያው ነፍሳቸው ውስጥ በተቀበረው ነገር ነው፤ በውስጣቸው የተቀበረው ነገር አስገድሎ አስገድሎ በመጨረሻ ይገድላቸዋል፤ ጥላቻም አስገድሎ አስገድሎ ይገድላል! በጥላቻና በመጋደል ሰላም አይገኝም፤ ‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር!›› (ኢሳይያስ 48/22)
መንገዱን ጨርቅ ያድርግልን! ለሰላም!
መንገዱን ጨርቅ ያድርግልን! ንስሐ ለመግባት!
መንገዱን ጨርቅ ያድርግልን! ይቅር ለእግዚአብሔር ለመባባል!
የዛሬ ዕብሪተኞች የሙሶሊኒን (ተዘቅዝቆ የተሰቀለውን)ና የጋዳፊን ቦይ ውስጥ ተወትፎ የተገኘውን አስበው ልባቸውን ለምሕረትና ለእርቅ እንዲከፍቱና ለልጆቻቸው የፍቅርና የመተማመን ዘመን እንዲያውጁ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ወኔ ይስጣቸው፡፡

Filed in: Amharic