የተገኝ ባልቻ ግድያን አስመልክቶ ከአርበኛ እስክንድር ነጋ የተሠጠ የሀዘን መግለጫ

የሀዘን መግለጫ ለተገኝ ባልቻ!!

አርበኛ እስክንድር ነጋ፣
ከትግል ሜዳ።
/
ጤና ይስጥልኝ። የከበረ ሰላምታዬ ለሁላችኹም ይድረሳችኹ።

ዓርብ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በአገዛዙ ፖሊስ በተፈፀመ የተለመደ ፋሺስታዊ ድርጊት፣ ወጣት ተገኝ ባልቻ መተኪያ የሌላትን አንድ ህይወቱን መነጠቁን ስሰማ በመጀመሪያ ሀዘን፣ ከዚያም ቁጭትም፣ ብሎም እልህም ሊባሉ የሚችሉ ስሜቶች ተመላልሰውብኛል።

የወጣት ተገኝ ባልቻ ሞትን አስመልክቶ የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ሠራዊት በሁለት ግለሰቦች መካከል የነበረ ፀብ ውጤት አድርጎ ለመሳል እየሞከረ ይገኛል። “ከግድያው ጋር በተያያዘ የተሸፋፈነ ጉዳይ አለ ወይ?” ብለው የሚጠይቁ አካላትን “ድብቅ የፖለቲካ ተልዕኮ ያነገቡ ናቸው” ብሎም እየወነጀለ ይገኛል።

አዎ፣ ከወጣቱ ሞት ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ጥያቄ እያነሳን እንገኛለን። ይህን በማድረግ የመጀመሪያዎቹ አይደለንም። በሀገረ አሜሪካ ሩድኒ ኪንግ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ እጅ መገደሉ ታላቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወልዷል። እንቅስቃሴው አሜሪካ እንደ ሀገር ራሷን ለመመርመር መነሻ ሆኗት፣ DEI የተባለ ታላቅ ሀገራዊ መዋቅራዊ ፍተሻ እና ማስተካከያ ለማድረግ በቅታለች።

ከ15 ዓመታት በፊት፣ በቱኒዚያ አንዲት ሴት ፖሊስ አንድን ነጋዴ በጥፊ መምታቷ የአረቡን ዓለም ከዳር እስከ ዳር ያዳረሰ አብዮት መቀስቀሱን ማን የማያውቅ የዘመናችን ሰው አለ? በጥፊ የተመታው እና በዚያ ብስጭት ራሱን ያቃጠለው የመሐመድ ቦዚዛ ስምም ከታላላቅ የታሪክ ሰዎች ተርታ እየተጠራ ነው እኮ።

የተገኝ ባልቻን ስም ስንጠራ የተለየ ተንኮል፣ የተለየ ፍላጎት፣ የተለየ ሴራ ስላለን አይደለም። ስሙን የምንጠራው በእሱ ውስጥ መሐመድ ቦዚዛ ወለል ብሎ ስለሚታየን ነው። መሐመድ ቦዚዛን ያጠቃችው አንዲት ፖሊስ ብቻ አልነበረችም ። ፖሊሷን የፈጠረው ሥርዓት፣ ሥርዓቱን የወለደ እሳቤ ነበር ዋናው አጥቂው። በተገኝ ባልቻ ውስጥም ተመሳሳይ እውነት ይታየናል።

ተገኝ ባልቻም መሐመድ ቦዚዛም አንሰተኛ ነጋዴዎች ነበሩ። ፖለቲካ ጋር ድርሽ ብለውም አያውቁም። ሁለቱንም የሚኖሩበት ፖለቲካዊ ሥርዓት ግን “አትሰሩም” ብሏቸዋል። እነሱ ወደ ፖለቲካ አልሄዱም። ፖለቲካ ግን አሳዶ አግኝቷቸዋል። የመሥራት መብታቸውንም ነጥቋቸዋል።

ለምን ይነጥቋቸዋል? ብለን ስንጠይቅ፣
የኢትዮጰያ እና የቱኒዚያ ፖለቲካ ብዙ ልዩነቶች ቢኖራቸውም፣ የሁለቱም ሀገራት ገዢዎች ግን ፖለቲካን ከንግድ፣ ንግድን ከፖለቲካ በማጋባቱ ረገድ አንድ መሆናቸውን እንደርስበታለን። ይህ አካሄድ “ፖለቲካ ለንግድ፣ ንግድ ለፖለቲካ” ሊባል የሚችል ነው። ሁለቱም ሥርዓቶች ፖለቲካን የሀብት ምንጭ አድርገው፣ እላይ ካለው ባለ ሀብት እስከ ሱቅ በደሬቴው ድረስ ማን እንደሚነግድ መምረጥ እና መሾም የሚፈልጉ ናቸው። መሐመድም ተገኝም ሳይመረጡና ሳይሾሙ ነበር ወደ ንግድ የገቡት። ዋጋም አስከፍሏቸዋል።

ለመሐመድ የፖለቲካ አላዋቂነቱ፣ ለተገኝ ብሄሩ ለመመረጥ እና ለመሾም አላበቃቸውም። መሐመድ የገዢው ፓርቲ አባል ቢሆን ኖሮ በተመረጠ ቦታ ለመነገድ ፍቃድ ያገኝ ነበር። የተገኝ ባልቻ ከበድ የሚል ነው። ባለንበት ዘረኛ ሥርዓት በተመራጩ ብሄር ውስጥ አልተወለደም። ስለዚህም፣ ሱቁ ሲፈርስ ያለውን እንዳያጣ አልታገዘም። እንዲያውም፣ ወደ ውድቀት አዙሪት ውስጥ ነው የገፈተሩት።

ከዚህ የምንማረው አለ። ከፖለቲካ መደበቅ ትችላለህ። ሁሌም ቢሆን ግን ፖለቲካ ፈልጎ ያገኘሃል። በተለይ በተለይ ለአዲስ አበባ ህዝብ ይህ ግልፅ ሊሆንለት ይገባል።በአዲስ አበባ እንደ ተገኝ የብሄርን መሥፈርት የማያሟላ ነጋዴ ወሎ አድሮ በሩ መንኳኳቱ አይቀርም። ይህ ሥርዓት እስካለ ድረስ የግዜ ጉዳይ ብቻ ነው። አዲስ አበባ መኖር በራሱ ፖለቲካ የሆነበት ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነው በዚህ ወቅት ያለነው።

ገዢዎቻችን አዲስ አበባን “ባለቤቱ” ለሚሉት ለመመለስ እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ በፖለቲካ ወይም በህግ ሊፈፀም እንደማይችል ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። የወለዳቸው እና ያሳደጋቸው ኢህአዴግ ክርክርን አላስተማራቸውም። ልምምጥም ክብራቸውን ይነካባቸዋል። ያላቸው ብቸኛ ዘይቤ እና አማራጭ ኃይል ሆኗል ማለት ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ እዚህ ጋር ነው ትልቁ ስዕል ውስጥ የሚመጣው። አዲስ አበባ ፖሊስ የገዢዎቻችን ህልም ማስፈፀሚያ መዶሻ ነው።

የፖሊስ ሁለት ዋና ዋና ተግባራት ህብረተሰቡ ከቤቱ በሰላም ወጥቶ እንዲመለስ ማስቻል እና ወንጀልን መከላከል ናቸው። እንዲህ ዓይነት የፖሊስ ኃይል እንዲኖር ከተፈለገ የመከላከያ ጄኔራል አናቱ ላይ እንዲቀመጥ አይደረግም። ባለሙያ እንዲመራው ነው የሚደረገው።

እንደ ሌተና ጄኔራል አሥራት ዲኔሮ ዓይነት የመከላከያ ጄኔራልን ከጦርነት ሜዳ አውጥተህ በአዲስ አበባ አናት ላይ የምታስቀምጥ ከሆነ፣ የምትፈልገው የጦር ሠራዊት እንጂ ፖሊስ አይደለም ማለት ነው። ጦር ሠራዊት የሚያስፈልገው ደግሞ፣ ለጦርነት እንደሆነ ግልፅ ነው። ይህ መንፈስ ነው በአዲስ አበባ ፖሊስ ውስጥ በተለይ ባለፉት 7 እና 8 ዓመታት የሰፈነው። ይህ መንፈስ ነው ተገኝን የቀጠፈው። የፖሊሱ ድርጊት የዚያ መንፈስ መገለጫ ነው። ድርጊቱ እንጂ ግለሰባዊ መንፈሱ መንግሥታዊ ነው።

የአዲስ አበባ ችግር ሥርዓታዊ ነው። ህገ መንግስቱ የወለደው ነው። መፍቴውም ሥርዓታዊ እና ህገ መንግሥታዊ ነው። ይህ ቋጠሮ እስከሚፈታ ድረስ ብዙ ተገኝ ባልቻዎችን አይተናል፣ ወደፊትም እናያለን።

የአዲስ አበባ ህዝብ ሆይ—መታገል አለብህ፤ አውቀቱም፣ ችሎታውም፣ አቅሙም አለህ።

ቸሩ ፈጣሪ የተገኝ ባልቻን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን፣ ቤተሰቦቹን እና ወዳጆቹን ብርታቱን እና መፅናናቱን ይስጥልን።

ፈጣሪ ሀገራችንን ይጠብቅልን!!!
/
ግንቦት 2፣ 2018 ዓ.ም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.