ከድር ጠንክር ከመርካቶ
ሰሞኑን ቴዲ አፍሮ በለቀቀው አዲስ ዘፈን፤
አለመታደል ሆኖ በበሉበት የሚጮሁና፤ አይምሯቸው በጮማ የተደፈነ፤ የሥነ ጥበብን*1 ምንነት፤የመረዳት አቅማቸው እጅግ የወረደ ከማለት በከፋ መልኩ፤ በእጅጉ የዘቀጡ ሰዎች፤ የቴዎድሮስ ካሳሁን (የቴዲ አፍሮን) ዘፈን፤ ሰዎች በነፃነት እንዳያዳምጡትከልክለዋል ::
የዘፈን ዜማን በጆሮ በማንቆርቆር፤ ውበትን በማድነቅ፤ ስነ ጽሁፍን በመመርመር፤ ለስነ ሥዕል ትኩረት በመለገስ፤ በግጥም በመደመምን፤ በፈጠራ የድርሰት ሥራ፤ (በሥዕላዊ ወይም ታሪካዊ ድርሰት)፤ ሃሳብን በሃሳብ እያሞሻለቁ፤ አይምሯቸውን በመሞረድ፤ የሰው ልጆች እራሳቸውን እንደገና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገና አልተረዱም ::
ሰው በእህል ብቻ አይኖርም….. !!! የሰውል ልጅ መንፈሱን እያስራበ፤ ሥጋውን ብቻ ለማደለብ፤ ክምር ያህል እየበላ፤ ሽንትቤት የሚሞላ እበት ለመጣል ብቻ አልተፈጠረም ::
በሥነ ጥበብ፤ መንፈሱን መመገብና ማለምለም፤ የመፈጠሩ የመጀመሪያው ምእራፍ እንደመሆኑ ሁሉ፤ለመጨረሻው ግብዓተ መሬቱም መሸኛው ነው ::
ለስነ ጥበብ የአይምሯቸውን በር ዘግተው፤ በጨለማ ውስጥ መኖርን ለመረጡ የምንላቸው፤
ሥነጥበብ :
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ምሁራን ተብዬዎች ሁሉ : አጎንብሰው እንብርታቸውን ሲያስተናግዱ፤ ጭው ባለው በረሃ፤ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ : ድምጹን ከፍ አድርጎ፤ በድፍረት ሃቁን የተናገረ፤ የጥበብ ባለሞያ ነው !!
ቴዎድሮስ ካሳሁን፤
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በኢትዮጵያ የፈጠራ ሥራ ሞቶ በተቀበረበት፤ በህወሃት (ወያኔና)፤ በአሁኑ የኦህዴድ መደመር (መደበር) የዓብይ አህመድ አምባገነን አገዛዝ ዘመን፤ የፈጠራ ሥራውን በድፍረትያቀረበ፤ ሰው በጠፋበት ዘመን፤ ሰው ሆኖ የተገኘ የጥበብ ሰው ነው ::
ጭው ባለው በረሃ፤ ድምፁን ከፍ አድርጎ፤
ሳይደብቅ፤ ዕውነትን የሚናገር፤ ፍቅርን የሚሰብክ፤ ሃቀኛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ !!
እንደ መዝጊያ፤
የተፈጥሮ ህግ ሆኖ፤ ይመሻል ይነጋል፤ እያንዳንዱ ቀንና ሌሊት፤ የራሱ የሆነ ቅራንቅንቦ በማግተልተል፤ ተሸክሞ ይሁን አዝሎ፤ አንጠልጥሎ ይሁን ታቅፎ፤ እየሳበ ይሁን እየገፋ፤ ብቻ እንዳመቸውና እንደቻለው፤ እንደወደደውና እንደፈቀደው፤ ጓዙን ሸክፎ ወይምጠቅልሎ ይነጉዳል::
አንዳንዴ በተቃራኒው፤ ለሰው ፍቃድና ይሁንታ ሳይገዛ፤ በፈጣሪ ይሁን ወይ በአንድ ባልታወቀ ሃይል ሳይገደድ፤ ሌሎች በቀደዱለት ቦይ ለመፍሰስ እምቢ ብሎ፤ እራሱ በፈጠረው ምህዋር ዙሪያ እየተሽከረከረ፤ የጊዜን የፍሰት ቀመር ከተለምዶ ሁነቱ ውጪ በመለካት ዜናን ያበስራል ::
አቆጣጠርና አለካኩ፤ ሰዓትን በሴኮንድና በደቂቃ፤ርቀትን በሜትርና በኪሎሜትር፤ ክብደትን፤ በግራምና በኪሎግራም፤ ዕድሜን ከወራትና ከዓመታት፤ አቆጣጠር ውጪ : የራሱ በሆነ ምህዋር ዙሪያ ያሽከረክራል ::
ታዲያ ያን ጊዜ : ሊነጋ ሲል መጨለሙን ያበስራል !!
ምርጫው በእጃችን ነው
ወይ በድንቁርናችን አብረን እንጠፋለን !!
ወይ በብልህነታችን አብረን እንኖራለን ::
ለራሳችን ስንል እንጣፍጥ !!
ቴዲ !
እኛ የአራዳ ልጆች በሙሉ፤
አብሽር !! አብሽር !! ብለናል
እንዳልከው ባንዲራውን ከፍ አድርገን የምናነሳበትን…ወ…ቀ…ሰ….ደ……. ::
የእናንተው ከድር ጠንክር ከመርካቶ ::
ይችን መልክቴን ያነበባችሁ፤ እንዳለፈው ጊዜ : ለሌሎች ወገኖቻችን፤ በድረ ገጾቻችሁ፤ በዩ ትዩብ፤ በቲክቶክ፤ በፌዝቡክ፤ በፈረስ፤ በጋሪ በእግር እየሄዳሁ አድርሱልኝ :: አደራ !!
ሥነ ጥበብን*1
ሙዚቃ፤ዘፈን፤ ግጥም፤ ሥዕል፤ ስነጽሁፍ (ልብ ወለድ፤ታሪካዊ)፤ ተውኔት ቲያትር፤ ጭፈራ፤ ዳንስ፤ ሽለላ፤ ፉከራ፤ ሙሾ …..ወዘተ























