>
3:01 pm - Friday January 21, 2022

ሕግ እንደ መንግስታዊ አሸባሪነት በአፓርታይድ ኢትዮጵያ፣ [ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም]

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

ttplf terror4የጸሐፊው ማስታዋሻ፡ ይህ ትችት “አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ በተከታታይ እያወጣሁት ያለው ሶስተኛ ክፍል ሲሆን መደበኛ በሆነ መልኩ በግንኙነት መስመር በድረ ገጽ እንደሚወጣ እጠብቃለሁ፡፡

የዚህ “አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ በተከታታይ የሚወጣው ትችት ሁለቱ ጥንድ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡

1ኛ) በአሁኑ ጊዜ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) አድራጊ ፈጣሪነት ተመስርቶ እየተቀነቀነ ያለው አውዳሚ የፖለቲካ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የብዙሀኑ የጥቁሮች ሕዝብ የበላይ አገዛዝ ስርዓት ከመፈጠሩ በፊት በጥቂት ነጮች የዘረኝነት የበላይ አገዛዝ ከነበረው የአፓርታይድ ዘረኛ አገዛዝ ተሞክሮ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ከምንም ጥርጣሬ በላይ ለማመላከት እና

2ኛ) ጥልቀት እና ስፋት ያለው ክርክር እና ውይይት በማካሄድ ከጎሳ ዘረኝነት የጸዳች አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመገንባቱን አስፈላጊነት ለመፍጠር እንዲቻል የኢትዮጵያን የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡

በዚህ “የጎሳ አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ ተቀናብሮ በሚቀርበው ተከታታይ ጽሑፍ የፖለቲካ እና የሕግ ትንተና፣ የምሁራን እና የአካዳሚክ ሁኔታን ከመመርመር ባለፈ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሀት አገዛዝ ስር ወድቃ በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ አጠቃላይ ሁኔታ መዳሰስን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁት ለኢትዮጵያ አቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ጥሩምባ በመንፋት እንዲህ የሚል ጥሪ ለማቅረብ ነው፡ “ጠንክራችሁ እንድትሰሩ እና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እና የጭቆና አገዛዝ ታሪክ እንዲሆን ማረጋገጥ አለባችሁ” የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ለመላው የዓለም ሕዝብ 13 ወራት ሙሉ ብርሀን በምትሰጠው ሀገሩ ቀበቶውን ጠበቅ በማድረግ እና ጠንክሮ በመስራት ከተራራው ጫፍ ላይ ከተማዋን እንዲመሰርት ተማጽዕኖየን አቀርባሁ፡፡

የአፓርታይድ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ለማሸማቀቅ የጸረ ሽብር ሕጉን እንዴት ይጠቀምእንደነበር፣

ጆን ዱጋርድ “ሰብአዊ መብቶች እና የደቡብ አፍሪካ የሕግ ስርዓት“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1978 ባሳተሙት መጽሕፋቸው ገጽ 136 ላይ በሀገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የጭቆና ስርዓት ለዘለቄታው ጠብቆ ለማቆየት ሲባል የሕጉን ጨቋኝነት እንዲህ በማለት ፍጹም በሆነ መልኩ አጠቃለው በመጭመቅ አቅርበውት ነበር፡ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተዘጋጀ ቢሆንምቅሉ .. 1967 የሽብርተኝነት ድንጋጌ እራሱ የሽብርተኝነት መሳሪያ እና የጭቆና ተምሳሌት ሆኖ ቀረበ፡፡

እ.ኤ.አ በ1948 በደቡብ አፍሪካ በጥቂት ነጮች ተደርጎ የነበረው ፓርላሜንታዊ ምርጫ በለውጥ የታጀበ ነበር፡፡ አናሳዎቹ ነጮች ሁለት ምርጫዎች ተሰጥተዋቸው ነበር፡፡ ዩናይትድ ፓርቲ የዘር እኩልነት አይቀሬነትን የሚቀበል የፖለቲካ መንገድ ሰጠ (ይኽ ካልሆነ ግን የብዙሀኑ ጥቁር ሕዝብ አገዛዝ እንዲኖር) እና በጣም ጨቋኝ የሆኑ እና የጥቁር ሕዝቦችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ ሕጎች እንዲቀነሱ የሚል የተማጽዕኖ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ የብሄራዊ ፓርቲው/National Party ደግሞ ፍጹም የሆነ የዘር መድልኦ እንዲኖር እና ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ሙሉ በሙሉ የሚያገል ስርዓት እንዲኖር መረጠ፡፡ ብሄራዊው ፓርቲ ምርጫውን አሸነፈ እና በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ፍጹም የሆነ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ እንዲጠናከር የአፓርታይድን ተከታታይነት  ያላቸው ሕጎች በማውጣት በስራ ላይ ማዋል ጀመረ፡፡

እ.ኤ.አ በ1950 የአፓርታይድ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ መንግስት “እ.ኤአ. በ1950 የወጣው የኮሙኒዝም መጨቆኛ ድንጋጌ ቁጥር 44 (ከሶስት አስርት ዓመታታ በኋላ ደግሞ “የ1982 የውስጥ ደህንነት ድንጋጌ“ ተብሎ የተሰየመ እና ይህም ድንጋጌ የመንግስትን ደህንነት ከአደጋ ላይ በሚጥል ወይም ደግሞ የሕዝብ ስርዓትን  በሚያውክ በማንኛውም ዜጋ ላይ ተፈጻሚነት እንዲኖረው“) የሚያደርግ ነበር፡፡

ከአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ፣ ከደቡብ አፍሪካ የሰራተኛ ማህበር እና ከሌሎች አጋሮች ጋር ታቅፎ እ.ኤ.አ በ1921 የደቡብ አፍሪካ ኮሙኒስት ፓርቲ ተመስርቶ የዘር አድልኦን እና አፓርታይድን ተቃወመ፡፡ የኮሙኒዝም የጭቆና ድንጋጌ ማንኛውንም የፖለቲካ፣ የኢንዱስትሪ፣ የማህበራዊ ወይም ደግሞ የኢኮኖሚ ለውጥ ረብሻዎችን ወይም ስርዓተ አልበኝነትን በማስፋፋት ውትወታውን መወንጀል ጀመረ፡፡ በተግባር የጥቂት ነጮች የበላይነትን ለመተቸት ወይም ደግሞ ለመገዳደር ድፍረቱ ያለው እንደ ኮሙኒስት ተቆጥሮ ይታሰር ነበር፡፡ እ.ኤ.አ የ1963-64 የሪቮኒያ የፍርድ ቤት ሂደት የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ መሪዎች በነበሩት በኔልሰን ማንዴላ፣ ዋልተር ሲሱሉ እና ጎቫን ኢምቤኪ ላይ የውንጀላ ክስ በመመስረት በዋናነት በዚህ ድንጋጌ መሰረት ተፈጻሚነትን አግኝቶ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድንጋጌ መሰረት በሺዎች የሚቆጠሩት ሌሎች ተራ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየቀረበ (በእንቅስቃሴዎቻቸው፣ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎቻቸው እና በማህበሮቻቸው ላይ) ፍጹም የሆነ ክልከላ ይጣልባቸው ነበር፡፡

የአፓርታይድ አገዛዝ የሰላማዊ አመጸኞችን እና ተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴዎች ፍጹም በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር ሌሎች ሕጎችን ማውጣት ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ በ1953 የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ድንጋጌ ቁጥር 8 በጨቋኝ ሕጎች እና በፖሊሲዎች ላይ ይደረጉ በነበሩት የሕዝብ ተቃውሞዎች ላይ ቀጥተኛ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ጭቆና ማካሄዱን ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ በ1961 ተሻሽሎ የወጣው ጠቅላላ የሕግ ድንጋጌ ቁጥር 39 ሕገወጥ የመንግስት እስራትን በሕግ አግባብ መከላከል እንዳይቻል እና ዋስትና በማሳጣት ለ12 ቀናት የዘፈቀደ እስራትን ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 የወጣው ጠቅላላ የሕግ ድንጋጌ ቁጥር 37 በኮሙኒስታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጠርጣሪ በሆነ በማንኛውም ዜጋ ላይ ዋስትና ለሌለው በቁጥጥር ስር የመዋል እና የእስራት ቅጣቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ተፈቀደ፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 በወጣው የተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ድንጋጌ መሰረት የ180 ቀናት ዋስትና የለሽ እስራት ተግባራዊ እንዲደረግ ጸደቀ፡፡

እ.ኤ.አ የ1967 ድንጋጌ እስከሚወጣ ድረስ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግስት በደቡብ አፍሪካ የወሰን ድንበሮች ላይ የሽብር ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው በማለት ተከታታይነት ያላቸውን ጥያቄዎች ማንሳት ጀመረ፡፡

እ.ኤ.አ በ1967 የወጣው የሽብርተኝነት ድንጋጌ (የ1967 ድንጋጌ ቁጥር 83) በደቡብ አፍሪካ ከውስጥ እና ከውጭ የሚሰነዘረውን ሽብርተኝነት ለመቆጣጠር እና ለማዳከም የወጣ ሕግ ነበር፡፡ ድንጋጌው ጥቁር አፍሪካውያንን ለማሸበር ሲባል የወጣ ብቸኛ እና ጨቋኝ ሕግ ሆኖ ጸደቀ፡፡

በአሸባሪነት ሕግ ድንጋጌው መሰረት “አሸባሪ” ማለት፡

ሀ) በሬፐብሊኩ ውስጥ የሕግ ጥበቃ እንዳይኖር እና ስርዓት እንዳይጠበቅ አደጋ ለማድረስ ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ ለሽብርተኝነት ድርጊት የሚያነሳሳ፣ ትዕዛዝ የሚሰጥ፣ ለዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች እርዳታ የሚያደርግ፣ ምክር የሚለግስ፣ ለተፈጻሚነታቸው የሚያደፋፍር፣ ወንጀልን እንዲፈጽም ማንኛውንም ሰው ገዝቶ ለሽብር ማሰማራት… ወይም ደግሞ

ለ) የሕግ ጥበቃ እንዳይኖር እና ስርዓት እንዳይጠበቅ አደጋ ለማድረስ በስልጠና ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ… ወይም፣

ሐ) ማናቸውንም ሊፈነዱ የሚችሉ ነገሮችን፣ ጥይቶችን፣ ጠብመንጃዎችን ወይም ደግሞ የጦር መሳሪያዎችን ይዞ የሚገኝ እና እንደዚህ ያሉትን ነገሮች ይዞ ላለመገኘቱ ከምንም ጥርጣሬ በላይ ለማረጋገጥ የማይችል እና ለሕጋዊ ዓላማ ብቻ ያልያዘ ማንኛውም ሰው ማለት ነው…ይላል፡፡

የሽብርተኝነት ድንጋጌ በደርዘኖች የሚቆጠሩ የሚከተሉትን የሽብርተኝነት ድርጊቶች ያካትታል፡

ሀ) ሕግን ከመጠበቅ እና ስርዓትን ከማስከበር አኳያ ጥረት በሚያደርግ ሰው ላይ ችግር የሚፈጥር እና ማንኛውንም አደጋ የሚያደርስ ማንኛውም ሰው፣

ለ) የማስፈራራት ድርጊትን በመጠቀም የእራሱን ዓላማ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ጥረት ማድረግ፣

ሐ) ጠቅላላ የሆነ የማፈናቀል፣ ረብሻ የመፍጠር ወይም ደግሞ ስርዓተ አልበኝነት እንዲንሰራፋ ምክንያት መሆን ወይም ደግሞ እንደዚህ ያሉ ድርጊቶች እንዲስፋፉ ጥረት ማድረግ፣

መ) በማንኛውም ቦታ ማንኛውንም የኢንዱስትሪ ወይም ደግሞ የምርት ወይም የሸቀጦችን ወይም የምግብ ሸቀጦችን ስርጭት ሽባ እንዲሆኑ ሙከራ ወይም ጥረት ማድረግ፣

ሠ) በመንግስት ወይም በግዛት አስተዳደሩ ላይ ሕዝባዊ አመጽ እንዲነሳ ወይም ደግሞ የኃይል የእምቢተኝነት እርምጃ እንዲወሰድ ምክንያት መሆን ወይም የሚያበረታታ ድርጊት መፈጸም፣

ረ)  የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት ማንኛውንም የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ለውጥን ማምጣትን ጨምሮ በኃይል ወይም ደግሞ በግዳጅ ለማስፈጸም የሚያበረታታ ድርጊት መፈጸም፣

ሰ)  በሰው አካል ላይ ጉዳት ለማድረስ ምክንያት መሆን ወይም ደግሞ የማንኛውንም ሰው ደህንነት ከአደጋ ላይ  የመጣል ድርጊት መፈጸም፣

ሸ) በማንኛውም ሰው ወይም በመንግስት ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብክነት እንዲደርስ ምክንያት መሆን፣

ቀ) በሬፐብሊኳ ውስጥ በሚኖሩት በነጮች እና በሌሎች ኗሪዎች ላይ የጥላቻ መንፈስ እንዲሰራጭ ምክንያት መሆን ወይም ደግሞ እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎችን የሚያበረታታ ድርጊት መፈጸም፣

በ) በማንኛውም ቦታ በሚገኝ የመብራት፣ የኃይል፣ የነዳጅ፣ የምግብ ሸቀጥ፣ ውኃ፣ ወዘተ አቅርቦት ወይም ስርጭት ላይ ጉዳት የሚያደርስ፣ የሚያወድም፣ ወዘተ ድርጊት መፈጸም፣

ተ) በየብስ፣ በባሕር ወይም በአየር ላይ የሚደረግ በማንኛውም የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ችግር የመፍጠር ወይም ደግሞ ለአደጋ የሚያጋልጥ ድርጊት፣

ቸ) በመንግስት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ችግር የመፍጠር ድርጊት መፈጸም ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው፡፡

የድንጋጌው ክፍል 6 በሽብርተኛ ተጠርጣሪው ያለምንም ዋስትና ለ60 ቀናት (ሊታደስ ይችላል) መታሰር እንደሚችል እና ኮሚሽነሩ ተጠርጣሪ እስረኛው ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ሁሉ በሚሰጠው ምላሽ ርካታ አግኝቶ መፈታት እንዲችል ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ ወይም ደግሞ በቀጣይነት ማሰሩ ምንም ዓይነት ጠቃሚ ዓላማ እስከሌለው ድረስ ወይም የተጠርጣሪው መፈታት እስከሚታዘዝ ድረስ ድንጋጌው ለፖሊስ ሙሉ እና ከጥያቄ ውስጥ የማያስገባ ስልጣን ሰጥቶታል፡፡ በሌውቴናንት ኮሎኔልነት ወይም ከዚያ በላይ ማዕረግ ያለው ፖሊስ እና አንድ ሰው አሸባሪ ነው የሚል እምነት የሚኖረው ከሆነ ያንን አሸባሪ ነው ብሎ የጠረጠረውን ሰው በቁጥጥር ስር በማዋል እንዲታሰር ትዕዛዝ ለመስጠት ይችላል፡፡ ማንኛውም ፍርድ ቤት ቢሆን በእራሱ ትዕዛዝ በእራት ላይ ያሉትን እስረኞች ለመፍታት አይችልም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው እና የመጨረሻው ስልጣን ያለው የፍትህ ሚኒስትር ብቻ ነው፡፡

ድንጋጌው ማንኛውንም የሕግ መጥሪያ ወይም ደግሞ የፍርድ ቤት የክስ ሂደት የሚያገል ሲሆን እንዲያውም ከዚህ በላይ በውንጀላ በተያዙት ተጠርጣሪዎች ላይ የመብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው እና የማሰቃየት ድርጊትም ሲደረግባቸው ምንም ዓይነት ጣልቃ በመግባት የሚሰራው ስራ የለም፡፡ በአሸባሪነት ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ መረጃ እንዳይወጣ በመያዝ የታሳሪዎቹ ማንነት እና ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለሕዝብ ላይገለጽ ይችላል፡፡ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ እና ተጠርጣሪዎቹ በቀላሉ እንዲሰወሩ (የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን/Truth and Reconciliation Commission የተሰወሩትን ጥቂት ተጠርጣሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ እና የት እንደሚገኙ ፈልጎ እስከሚያገኝ ድረስ) በርካታዎቹ ታሳሪዎች በቀላሉ ተሰውረው የት እንደሚገኙ ሳይታወቅ ይቆያል፡፡

የሽብርተኝነት አዋጁ በሽብርተኝነት ከተጠረጠረ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት የተገኘ መረጃ በፍርድ ቤት የእምነት ቃል እንደተሰጠ የሚቆጠር መሆኑን ይፈቅዳል፡፡

ማንኛውም ሰው በቀጥታም ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በሽብርተኝነት ከተጠረጠረ ሰው እርዳታ አግኝቷል ተብሎ ከተጠረጠረ በሽብርተኝነት ከተጠረጠረው ሰው ቅጣት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ቅጣት ይፈጸምበታል፡፡ የሽብርተኝነት ውንጀላው የትም ቦታ ይፈጸም የት ጉዳዩን የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ወይም ደግሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሊዳኘው ይችላል፡፡

የሽብርተኝነት ድንጋጌው በማስረጃ የማረጋገጡን ሸክም ለፍርድ ቤቱ ወይም ደግሞ ለፖሊስ አልሰጠም፣ ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ የተሰጠው ለተከላካዩ ነው፡፡ በሽብር ወንጀል የተጠረጠረ ሰው እራሱ ከሽብርተኝነት የውንጀላ ክስ ነጻ መሆኑን እስካላረጋገጠ ድረስ ድንጋጌው የሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

ለአስርት ዓመታት ያህል የሽብርተኝነት ድንጋጌው በአፓርታይድ ፖሊሶች እና የደህንነት ኃይሎች ለእስራት፣ ለማሸማቀቂያነት፣ ለማስፈራሪያነት፣ ለማሰቃያነት እና ጥቁር የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ መሪዎችን እና ድርጅቶችን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲታይ በማድረግ በስራ ላይ ከመዋሉም በላይ ተራ የሆኑ ተቃዋሚዎች እና ዜጎች፣ የሰራተኛ መሪዎች፣ የቤተክህነት ሰዎች እንዲወገዱ በማድረግ የማሳለጥ ስራ ሰርቷል፡፡ ዊኒ ማንዴላ፣ ስቴቭ ቢኮ እና ክሪል ራማፎሳ ከበርካቶች በጥቂቱ በድንጋጌው አንቀጽ 6 ንኡስ ርዕስ ስር እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ በጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ በአፓርታይድ ተፈጽሞ የነበረው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ አስፈሪው እና አስደንጋጩ በእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ታላላቅ ሶስት ጥራዞች ተዘጋጅቶ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ህወሀት ኢትዮጵያውያንን ለማሸበር የሚጠቀምበት የጸረ ሽብርተኝነት ሕግ፣ 

የመጀመሪያው የማያወዛግብ እውነታ፡ ዘ-ህወሀት እራሱ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት ውስጥ ስሙ በአሸባሪነት ተመዝግቦ የሚገኝ የተረጋገጠ አሸባሪ ድርጅት ነው፡፡

ስለሆነም ምንም ይሁን ምን ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ እንደ መዥገር በስልጣን ኮርቻ ላይ ተጣብቆ የሚገኝ አሸባሪ ድርጅት ነው!

እንግዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪነቱ የተረጋገጠ ሽብርተኛ ድርጀት የጸረ ሽብርተኝነት ሕግ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ሌሎችን አሸባሪዎች በማለት ለመጥራት የሚችለው? (ይኸ ጥያቄ የብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ጥያቄ ነው!)

ሁሉም የሽብርተኝነት ነገር ሁሉ አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት ወሮበላ የዘራፈ ቡድን ስብስብ መሪ በነበረው በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2000ዎቹ ከአምላክ የተላከ ነገር ነበር፡፡ አሸባሪነት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጆሎቹ እንዲላቀቅ እና ከዩናይትድ ሰቴትስ ከፍተኛ የሆነ የልመና እርጥባን ለማግኘት የሚያስችል መሳሪያ ነበር፡፡

የአፓርታይድ አገዛዝ አሸባሪነት ከጎረቤት ሀገሮች ደቡብ አፍሪካን አቋርጦ ይገባ ነበር የሚለው እ.ኤ.አ በ1967 የአሸባሪነት ድንጋጌ ከመጽደቁ በፊት እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ አምባገነኑ መለስም በሶማሊያ የጂሀዲስቶች ሽብርተኝነት የሚል የይስሙላ ምክንያት በመስጠት የጸረ ሽብርተኝነት እርምጃዎችን ሲወስድ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ህዳር 2006 “ጂሀዲስቶች እየመጡ ነው“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችት አምባገነኑ መለስ እርሱ በሰው ልጆች ላይ በተለይም እ.ኤ.አ 2005 በኢትዮጵያ ተደረገ ተብሎ በነበረው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በእርሱ ትዕዛዝ ቅጥር ነብሰ ገዳዮችን አሰማርቶ ፈጽሞት የነበረውን እልቂት የሕዝብ ትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ የሶማሌን አሸባሪነት ለሽፋንነት ይጠቀም እንደነበር ሞግቸ ነበር፡፡ ሽብርተኝነትን መዋጋት በሚል ሽፋን አምባገነኑ መለስ የእራሱን ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለበት ሁኔታ በሶማሌ ውስጥ ሊያካሂድ የነበረውን ጦርነት እንዲህ በማለት ተቃውሜ ነበር፡

“ትልቁ የኢትዮጵያውያን ችግር ሁለቱንም ጦርነቶች በአንድ ጊዜ ለመዋጋት አይችልም፡ በዜናዊ እና በእራሱ አገዛዝ የታወጀባቸውን በፖለቲካ ጦርነት መከላከል እና በሩቁ ባለችው እና በማይታይ ጠላት በጨነገፈችው ሶማሌ ላይ ጥቃት መሰንዘር፡፡“

እ.ኤ.አ ታህሳስ 2006 በባይደዋ የሽግግር መንግስት እየተባለ የሚጠራ መንግሰት በመመስረት ለማገዝ ሲባል አምባገነኑ መለስ ሶማሌን ወረረ፡፡ መለስ በሶማሌ ላይ የከፈተውን ጦርነት እራሴን ለመከላከል ነው በማለት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፡ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ሲባል ሳይወድ በግድ ወደ ጦርነት ገብቷል፡፡ ለሶማሌ እኛ መንግስት ልናቋቁምላቸው አይደለም የምንሄደው፣ ወይም ደግሞ የሶማሌን ውስጣዊ ችግር ለመሸምገል አይደለም፡፡“

እ.ኤ.አ በ2008 በሶማሌ የዩናይትድ ስቴትስን የውክልና ጦርነት ለማከናወን ቃል ገብቶ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የመለስን የማሳመኛ ዲስኩር ውሸት እና ተራ ቅጥፈት መሆኑን አጋልጫለሁ፡፡ ሆኖም ግን አምባገነኑ መለስ እርሱ ከሌለ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ከፍተኛ የሆነ አደጋ እንደሚደቅን እና የእስልምና አክራሪነት የአፍሪካ ቀንድን እንደሚያጠፋ በመግለጽ የሸፍጠኝነት የሕዝብ ግንኙነት ስራውን ቀጠለ፡፡

አምባገነኑ መለስ እና የእርሱ ዘ-ህወሀት የሶማሌን ሕዝብ አሸብረዋል፣ እናም “አስፈሪ የሆነ ሁኔታ፡ የጦር ወንጀለኝነት እና የሶማሌ ውድመት“ በሚል ርዕስ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ለመናገር የሚዘገንን ኢሰብአዊ ወንጀሎች መፈጸማቸውን መዝግቦ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ አድርጓል፡፡ የአምባገነኑ መለስ ሽብርተኝነትን የመደምሰስ የሶማሌ የውክልና ጦርነት ዓላማ ከሽፏል፣ እናም እ.ኤ.አ የዘ-ህወሀት ጦር እንደ አበደ ውሻ ጅራቱን በጉያው ወትፎ ሀፍረቱን ተከናንቦ ወደመጣበት ተመልሷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 አምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ የአሸባሪነት ፍርሀት አነገሱ፡፡ ማናቸውም ግለሰብ ወይም ድርጅት መለስን እና ዘ-ህወሀትን የሚተች፣ የሚቃወም፣ የማይስማማ መሆኑን ወይም ደግሞ ሰላማዊ አመጽ የሚያደርግ ከሆነ “አሸባሪ” ተብሎ ይፈረጃል!

ዘ-ህወሀት “የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2009“ እየተባለ የሚጠራውን አምባገነናዊ መግለጫ (አሁን በህይወት የሌለው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የግል ትዕዛዝ) አሸባሪዎችን ለመቀፍቀፍ እና ሽብርተኝነትን ለመፈብረክ ሰላማዊ ዜጎችን ለማጥቂያነት ተጠቅሞበታል፡፡ ያ አምባገነናዊ መግለጫ በይስሙላው ፓርላማ 286 ለ91 በሆነ ድምጽ ጸድቋል፡፡ ያ አምባገነናዊው መግለጫ እጅግ በጣም ጨቋኝ በመሆኑ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ በ2009 ረቂቁን “አዲስ እና የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ነጻ በሆነ መልኩ የመንግስትን ፖሊሲ የሚተቹትን ለመጨቆኛ የሚያገለግል ጠንካራ መሳሪያ“ ነው በማለት ተችቶታል፡፡

ዘ-ህወሀት ይህንን አዋጅ ላለፉት ሰባት ዓመታት ፕሬሱን ለማፈን፣ ነጻ ጋዜጦችን ለመዝጋት፣ ሰላማዊ አመጽን ለመጮቆን እና የፖለቲካ ተቃዋሚ መሪዎችን እና ፓርቲዎችን ለማግለል ተጠቅሞበታል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዘ-ህወሀት ተቃዋሚዎች በግልጽ ክስ የተመሰረተባቸው እና፣ ጥፋተኛም የተባሉ ሲሆን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረጉ በዘ-ህወሀት የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ እንዲበሰብሱ ተደርገዋል፡፡

አሸባሪነት በማሕበራዊ የመገናኛ ድረ ገጽ!

ዮናታን ተስፋዬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነው፡፡ የ29 ዓመቱ ወጣት የዘ-ህወሀት የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ የቅርብ ጊዜ የጥቃት ሰለባ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ዘ-ህወሀት በዮናታን ላይ በርካታ የሽብርተኝነት ክሶችን መስርቷል፡፡ የእርሱ የውንጀላ ክስ የማህበራዊ የግንኙነት ድረ ገጽ በመጠቀም አመጽ የመቀስቀስ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲኖር ለማድረግ ጥረት ማድረግ እና  ኢህአዴግን (የዘ-ህወሀት መደበቂያ ሸል) ተችቷል የሚል ነው፡፡

ዮናታንን በአሸባሪነት ከወነጀሉት የአሸባሪነት ውንጀላዎች በእርሱ የማህበራዊ ግንኙነት ድረ ገጽ በለቀቀው ላይ የሚከተሉት ይገኙበታል፡

የሙስሊም ወገኖቻችን የአምልኮት ቦታዎቻቸውን በመከልከላቸው ቅሬታ በማቅረብ ላይ ናቸው፣ “ድምጻችን ይሰማ በማለት በመጮህ ላይ ናቸው፡፡“

የኦሮሞ ዜጎቻችን ከመሬቶቻቸው በኃይል በመፈናቀላቸው ቅሬታዎቻቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡ እንዲህ ይላሉ፣ “የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን አንፈልግም፡፡“

የአማራ ሕዝብ እንዲህ ይላል፣ “የጎሳ ክፍፍልን በመሞከራቸው ምክንያት እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ በገዛ ሀገራቸው መኖር የማይችሉ ከሆነ ወዴት መሄድ ይችላሉ?“

የጋምቤላ ሕዝቦች ከመሬታቸው እንዲነቀሉ ተደርገዋል፡፡ እንዲህ ይላሉ፣ “በመንደር መሰባሰብ አንፈልግም፡፡“

ኢትዮጵያውያን በትግራይ፣ በአፋር፣ በወሎ፣ በሀረርጌ እና በሶማሌ ክልሎች በረሀብ በመሞት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ይላሉ፣ “እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፡፡“

ወጣት ኢትዮጵያውያን በበረሀዎች እና በባህሮች እየቀለጡ ነው፡፡ አሸባሪዎች አንገቶቻቸውን ይቀሏቸዋል፡፡ እንዲህ ይላሉ፣ “አትግደለኝ፡፡ ለደኃይቱ እናት ሀገሬ ልኑርላት፡፡“

ኢትዮጵያውያን መብቶቻቸው እየተረገጡ፣ እየተዋረዱ፣ እየተሰወሩ እና እየተሰደዱ ነው፡፡ በጭቆና እየተሰቃዩ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፣ “ይበቃናል፡፡“

ከሁለት ሳምንታት በፊት ዘ-ህወሀት በበቀለ ገርባ እና በሌሎች 21 ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ የሸፍጥ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

የዘህወሀት ጦጣ ታያለች፣ ታደርጋለች የጸረ ሽብር ሕግ፣

አምባገነኑ መለስ የጸረ ሽብር አምባገነናዊ መግለጫው በዓለም ላይ ምርጡ ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን እንከን የለሽ ነው ይላል፡፡ አዎ እንከን የለሽ የምትለዋን ቃል አምባገነናዊ መግለጫ ለመግለጽ ተጠቅሞበታል!

አምባገነኑ መለስ ፍጹም የሆነ የውሸት ምሁር እና የሀረግ ቀበኛ ነው፡፡ ስለሕጉ ምንም ነገር የማያውቅ አስደንጋጭ ሁኔታ ነው፡፡

አምባገነኑ መለስ በጅምላ የጽሁፍ ስርቆት፣ በሸፍጥ ቃላቱ፣ ሀረጎች፣ ዓረፍተ ነገሮች እና አንቀጾች ከተለያዩ ሀገሮች የጸረ ሽብርተኝነት ሕጎች እንከን የለሽ የሆነ ለእራሱ መቅረጽ የሚችል እንደሆነ አድርጎ ያምናል፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 2012 አምባገነኑ መለስ የእርሱን የሚከተለውን እንከንየለሽ የጸረ ሽብር ሕግ ገለጻ (ከዚህ በታች ተተርጉሞ በአማርኛ ለፓርላማው የመለስ የቪዲዮ መግለጫ) እንዲህ በማለት ሰጠ፡

የጸረ ሽብር ሕጋችንን በምናረቅበት ጊዜ በዓለም ላይ ያለውን የጸረ ሽብር ሕግ ቃል በቃል ነው የገለበጥነው፡፡ ከአሜሪካ፣ከእንግሊዝ እና ከአውሮፓ ሞዴል የጸረ ሽብር ሕጎች ወስደናል፡፡ ከእነዚህ ሶስት ምንጮች በመውሰድ ነው የጸረ ሽብር ሕጉንያረቀቅነው፡፡ 

ከእነዚህ የተሻሉትን መርጠናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ ሕጎች በሙሉ አንድ ድርጅት ስልጣን ባለው አካል አሸባሪ የመባልዕጣ ፈንታ ሊደርሰው ይችላል፡፡ እንደዚህ ያለውን ውሳኔ ባለስልጣኑ መወሰን የለበትም በማለት አሻሽለነዋል፡፡ የሸረ ሽብርንትርጉም ቃል በቃል ወስደናል፡፡ አንድም ቃል አልተለወጠም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓረፍተ ነገሮች መካከል የሚገኘውን ስርዓተነጥብ እንኳ አልቀየርንም፡፡ ለምን ቃል በቃል እንደወሰድነው የእራሱ ምክንያት አለው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሕዝቦችየዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ልምዱ አላቸው፡፡ ምክንያቱም ልምዱ አላቸው፣ እናም ከእነርሱ ብንማር ወይም ደግሞ ብንወስድምንም ዓይነት አሳፋሪ ነገር አይደለም፡፡ ከጥሩ መምህር መማር ይጠቅማል እንጅ ጉዳት የለውም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚያሳፍርነገር የለውም፡፡ የጸረ ሽብር ሕጉ በየትኛውም መለኪያ እንከንየለሽ ነው፡፡ በዓለም ላይ ካሉት የጸረ ሽብር ሕጎች ሁሉ የተሻለነው፣ ሆኖም ግን በማንኛውም መንገድ ቢሆን ከማናቸውም ያነሰ አይደለም…” 

አምባገነኑ መለስ እነዚህን ቃላት በቪዲዮ ሲናገር በሰማሁ ጊዜ የሳቅሁ ወይም ደግሞ ያለቀስኩ ለመሆኔ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

የሸክስፒርን አባባል በመዋስ የመለስ ምላስ “በናይል ወንዝ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም ነብሳቶች እንደሚበክል“ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን የእርሱን የጨለምተኛ እና ፍጹም የሆነ ሕጉን ያለማወቅ ድንቁርና የቪዲዮ ምስክርነት ለመስማት ዝግጁ አልነበርኩም፡፡

ከዚያም እንዲህ የሚለውን የጎቴን መርህ አሰብኩ፣ “በተግባር ከድንቁርና የበለጠ አስፈሪ ነገር በፍጹም የለም፡፡“ በተግባር ሲታይ ከአምባገነኑ መለስ እና ዘ-ህወሀት የድንቁርና ተምሳሌዎች ከመሆን የበለጠ ሌላ ፍጹም የለም፡፡

ገና በመጀመሪያ ጊዜ አምባገነኑን መለስን ለማስተማር ሙከራ በጀመርኩበት ጊዜ መስሎ መታዬት የአስመሳይነት ከፍተኛው ደረጃ መሆኑን እና እንከንየለሽ በእርግጠኝነት የህሊናየለሽነት አምባገነንነት መገለጫ ባህሪ መሆኑን ለማሳየት ሞክራያለሁ፡፡ የእርሱን የቆርጦ ቀጥል የአሸባሪነት ሕግ ኩረጃ እንዲህ ከሚለው የስነ ሕይወት ምዕናባዊ ፍጡር ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ለማመላከት ሞክሪያለሁ፡

የቀጭኔን በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ረዥም አንገት ከጠንካራው የጅብ መንጋጋ፣ ፈጣኑን የአቦ ሸማኔ እግሮች እና ግዙፉንየዝሆን ቅርንጫፍ አንድ ላይ በማያያዝ ማንም ቢሆን አንበሳን ሊፈጥር አይችልም፡፡ የጫካው ንጉስ ከሁሉም የተለዬ አውሬነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ማንም ቢሆን ብጥስጣሽ የጸረ ሽብር ሕጎችን ከየትም ለቃቅሞ በመውሰድ እና እንደ ደኃ ከረጢትደራርቶ አንድ አምባገነንነትን የያዘ ሰነድ በማዘጋጀት በማንኛውም ረገድ እንከንየለሽ በማለት ቅዱስ አድርጎ ማቅረብ ቅዱስነቱንአያረጋግጥም፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን መለስ የጸረ ሽብር ሕጉን እንከንየለሽ ብሎ የመፈረጁ ሁኔታ አንድ ጥራቱ የወረደ የአልማዝ ቅንጣትም እንከንየለሽ አልማዝ ነው ከማለት ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡

ለመለስ እና ለዘ-ህወሀት ታዛዥ ሎሌዎቹ በሙያው ተገቢ የሆነ አስመሳይነት የሚል ስም ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ሆኖም ግን የጻፍኩት ቃል ምን ማለት እንደሆነ አይገነዘቡትም ብዬ እጠራጠራለሁ!

ለመሆኑ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ ወይም ደግሞ በአውሮፓ ቃላትን በማህበራዊ የግንኙነት ድረ ገጽ እንዲታተም በማድረጉበየትኛው ቦታ ነው በቁጥጥር ስር የሚውለው እና ለእስራት የሚዳረገው? ንገሩኛ እኮ የት ቦታ?!

እንከንየለሽ የጸረ ሽብር ሕግ፣ የእኔ እግር!

በእርግጥ መለስ በዓለም ላይ ምርጥ የሆነውን የጸረ ሽብር ሕግ ቃል በቃል አልገለበጠውም፡፡ መለስ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እና ከአውሮፓ በጣም ምርጥ የሆነውን ነገር አልወሰደም፡፡

ይልቁንም እ.ኤ.አ በ1967 በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ከተዘጋጀው የጸረ ሽብር ሕግ ፍጹም መጥፎ የሆነውን መርጦ ወስዷል፡፡

በጸረ ሽብር ሕጉ የዘህወሀት አሸባሪነት፣

እንደ 1967ቱ የአፓርታይድ የአሸባሪነት ድንጋጌ የዘ-ህወሀት የጸረ ሽብር አዋጅ በክፍል (3) ስር ማንኛውም ግለሰብ ወይም ደግሞ ቡድን የፖለቲካ፣ የኃይማኖት፣ ወይም የርዕዮት ዓለም ዓላማን ለማራመድ ወይም መሰረታዊ የፖለቲካ፣ የሕገ መንግስት ወይም በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የኢኮኖሚ ወይም የማህበራዊ ተቋማት እንዳይረጋጉ ወይም እንዲደመሰሱ እና በሕዝብ ንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በአካባቢያዊ ስነምህዳር ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም የሕዝብ አገልግሎትን ያደናቅፋል…

በአዋጁ ድንጋጌ ክፍል (5) የዘ-ህወሀት ሕግ ማንኛውም ብልሀት፣ ሙያዊ ክህሎት ወይም የሞራል ድጋፍ ምክር የሰጠን… በማንኛውም መልኩ ማንኛውንም ንብረት፣ የፋይናንስ ወይም ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎቶች እንዲገኙ ያደረገ… ማንኛውንም ስልጠና፣ ትዕዛዝ ወይም መመሪያ የሰጠ አሸባሪ በማለት ያወግዛል፡፡ ክፍል (6) ማንኛውም ጽሁፍ ወይም መግለጫ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሽብር ድርጊትን የሚያበረታታ ሆኖ ከተገኘ የአሸባሪነት ድርጊት ተብሎ ይወነጀላል፡፡ ክፍል (7) ማንኛውም ለሽብርተኛ ድርጅት ለሽብር ተልዕኮ ጉዳይ የሰው ምልመላ የሚያካሂድ ከሆነ ወይም ደግሞ የሽብር ድርጊትን የሚፈጽም ከሆነ በአሸባሪነት ይወነጀላል፡፡

እንደ አፓርታይድ የ1967 ድንጋጌ የዘ-ህወሀት የጸረ ሽብር አዋጅ ለምርመራ እና በቁጥጥር ስር ለመዋል ዋስትና ያሳጣል፡፡ ክፍል (14) በሽብርተኝነት ከተጠረጠረ ሰው ጋር በስልክ፣ በፋክስ፣ ራዲዮ፣ ኢንተርኔት፣ ኤሌክትሮኒክ፣ የፖስታ እና ሌሎች ተመሳሳይ ግንኙነቶች ላይ የዋስትና የለሽ ምርመራ ስልጣንን ይሰጣል፡፡ በድብቅ ማንኛውንም ግንኙነት ለማቆም ወይም ደግሞ መሳሪያዎች እንዳይሰጡ በማድረግ ማሰናከል ይቻላል፡፡ (ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የመንግስትን ሚስጥሮች ለመጠበቅ ከቻይናዎች ሕግ እ.ኤ.አ በ1988 የዲጅታል ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ የሰጠ ይመስላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሽብርተኝነት ድርጊት ተፈጽሟል ብሎ የሚጠረጥር የፖሊስ ኃላፊ መኪናን እና መንገደኛን በድንገት በማስቆም በማንኛውም ሰዓት መመርመር እንዲችል ተገቢ የሆኑ ማስረጃዎችን እንዲይዝ ተፈቅዶለታል፡፡

የዘ-ህወሀት አዋጅ ክፍል (19) ማንኛውም የፖሊስ ኃላፊ ምንም ዓይነት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ደብዳቤ ሳይዝ በሽብርተኝነት የሚጠረጥረውን ማንኛውንም ዜጋ መያዝ እንዲችል ስልጣን ይሰጣል፡፡ ክፍል (20) ፖሊስ ወይም ደግሞ አቃቤ ሕግ በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው እና የምርመራ ስራቸውን ማካሄድ እንዲችሉ ፍርድ ቤቶች ማቋረጫ የሌለው ቀጠሮ እና ማስተላለፍ እንዲያደርጉ ይፈቅዳል፡፡ ክፍል (23) ያልተረጋገጠ የደህንነት ዘገባን፣ ያልተረጋገጠ ወሬን ወይም ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ የምርመራ ማስረጃ፣ የውጭ ሕግ አስፈጻሚ አካላት እና ተጠርጣሪዎች በግዳጅ የእምነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይፈቅዳል፡፡ ክፍል (25) የተወካዮች ምክር ቤት አንድን ድርጅት አሸባሪ ድርጅት በማለት አንድን ድርጅት የመመዝገብ ወይም ደግሞ ያለመመዝገብ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ክፍል (37) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ተፈጻሚ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ደንቦችን ለማውጣት ተፈቅዶለታል፡፡ (በሌላ አገላለጽ አባት ሕግ ያወጣል ልጅ ይፈጽማል፡፡)

የዘህወሀት የጸረ ሽብር ሕግ ተፈጻሚነት፣

አዋጅ ቁጥር 652/2009 እንደ አፓርታይድ የአሸባሪነት ድንጋጌ በተመሳሳይ መልኩ ግልጽ ባልሆነ፣ ድብቅ እና አደናጋሪ በሆነ ቋንቋ የታጀለ ነው፡፡ በዚህ አስቸጋሪ አዋጅ መሰረት ማንኛውም ድርጊት፣ ንግግር፣ መግለጫ እና ሃሳብም እንኳ ቢሆን ያስቀጣል፡፡

ማንኛውም እንደሚያምነው ወይም ደግሞ ወደፊት እንደሚያምነው የዘ-ህወሀት ዓቃቤ ሕግ/ፖሊስ ፖለቲካን፣ ኃይማኖትን ወይም ርዕዮት ዓለምን ለማራመድ እና በመንግስት ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር፣ ሕዝቡን የማሸማቀቅ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን መሰረታዊ የሆኑትን የፖለቲካ፣ የሕገ መንግስት፣ የኢኮኖሚ ወይም የማህበራዊ ተቋማት እንዳይረጋጉ ወይም እንዲደመሰሱ በማድረግ የረዥም ጊዜ እስራት ወይም የሞት ቅጣትን ያወግዛል፡፡

ይህንን ዓይነት ነገር ነበር እንግዲህ የአፓርታይድ አሸባሪነት ድርጊት በእርግጠኝነት ያደረገው፡፡ የአፓርታይድ ፖሊሶች እና ዓቃብያነ ሕጎች ጥፋት ለመሰራቱ ቅንጣት ያህል ማስረጃ ሳይኖራቸው ማንኛውንም ሰው መክሰስ ይችላሉ፡፡

መግለጫ መስጠት ወይም ደግሞ ማውጣት ሸብርተኝነትን ማበረታታት መስሎ እስከታየ ድረስ የሚያስቀጣ ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም በወንጀለኝነት የተጠረጠረን ሰው በሞራል የደገፈ ወይም ደግሞ ምክር የሰጠ ወይም በሸባሪነት ድርጊት ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሰው የአሸባሪነት ደጋፊ ተብሎ ይፈረጃል፡፡ ይህ ነበር እንግዲህ የአፓርታይድ አገዛዝ የአሸባሪነት ድንጋጌውን በከተሞች አካባቢ የሚኖሩትን እና በጸረ አፓርታይድ የሚጠረጠሩትን ሰዎች ሁሉ ሲያጠፋ የነበረው፡፡

በዘ-ህወሀት አዋጅ ማንኛውም የሚጽፍ፣ የአርታኢ ስራ የሚሰራ፣ የሚያትም፣ ጽሁፍ የሚያሳትም፣ ለህዝብ መግለጫ የሚያወጣ፣ ጽሁፎችን የሚያሰራጭ፣ የሚያሳይ፣ ማንኛውንም ጠንካራ መግለጫ በማውጣት የሚያደፋፍር፣ የሽብርተኝነትን ድርጊት የሚደግፍ ወይም ደግሞ የሚያራምድ እንደ አሸባሪነት ይፈረጃል፡፡ አገዛዙን የሚተቹ ጠንካራ ትችቶችን ጽሁፎችን ጽፎ በባነር ይዘው የሚወጡ ሰላማዊ አመጸኞች ሽብርተኝነትን ድርጊትን በማስፋፋት እና በመደገፍ ተብለው የሽብርተኝነት ክስ ይመሰረትባቸዋል፡፡ ማንኛውም የሕዝብን አገልግሎት የሚያደናቅፍ ሰው እንደ አሸባሪ ይቆጠራል፣ (ክፍል 3ን ልብ ይሏል) እናም በስራ ሁኔታ በሕጋዊ መንገድ ቅሬታ የሚያቀርቡ እና የስራ ማቆም አድማ የሚያደርጉ በስራ አደናቃፊነት ሰበብ በሽብርተኝነት ይከሰሳሉ፡፡ ይህ እንግዲህ የአፓርታይድ አገዛዝ የአሸባሪነት ድርጊትን ለማጥፋት በሚል ሰበብ ሰላማዊ አማጺዎችን፣ ተማሪዎችን፣ የሰራተኛ ማህበራትን፣ የፖለቲካ ወትዋቾችን፣ ጋዜጠኞችን እና ሌሎችን አመጸኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚጠቀምበት የሸፍጥ ዘዴ ነበር፡፡

በዘ-ህወሀት አዋጅ ማንም ሰው በጎረቤቱ፣ አብሮት በሚሰራ የስራ ጓደኛው ወይም ደግሞ በሌሎች በሽብርተኝነት የሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ወዲያውኑ መረጃ ወይም ማስረጃ ለፖሊስ ካልሰጠ ዘገባ ባለማቅረቡ ምክንያት እስከ 10 ዓመታት የሚያስቀጣ እስራት ይበየንበታል፡፡ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች እና በሽብርተኝነት ድርጊት ጋር ከሚጠረጠር ሰው ጋር ግንኙነት ካላቸው ሽብርተኝነትን ለመፈጸም በሚል የሸፍጥ ክስ ይመሰረትባቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው እንግዲህ የአፓርታይድ አገዛዝ በአሸባሪነት ድርጊት የቤተሰብ አባላትን፣ ጎረቤቶችን፣ ጓደኛሞችን እና በሽብርተኝነት ድርጊት የሚጠረጥራቸውን ሰላማዊ ሰዎች በአሸባሪነት እየወነጀለ ሲያሰቃይ የቆየው፡፡

ሕጋዊ የፍትህ አሰራር ሂደት መብት እና ተከሳሹ ዋስትና የማግኘት ሕገ መንግስታዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ ስምምነቶች ላይ የተመለከተው መብቱ በዘ-ህወሀት ገሸሽ ይደረጋል፣ ይሸረሸራል፣ ይጣሳል እና ሕጉ እንዳለ ይተዋል፡፡ ፖሊስ ያለምንም የፍርድ ቤት ማዘዣ ትዕዛዝ የሽብርተኝነት ድርጊት ይፈጽማል ወይም ደግሞ ፈጽሟል ብሎ የሚጠረጥረውን በቁጥጥር ስር በማዋል ድብቅ በሆነ ቦታ አስሮ ማቆየት ይችላል፡፡ ፖሊስ በሸብርተኝነት ተጠርጣሪ ማንኛውም ሰው ላይ በአጋጣሚ እና ድንገተኛ በሆነ መልኩ ፍተሻ ለማካሄድ እና ለመያዝ ይችላል፡፡ ፖሊስ በሽብርተኝነት የተጠረጠረን ማንኛውንም ሰው ስልክን፣ ፋክስን፣ ሬዲዮን፣ ኢንተርኔትን፣ የአሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን፣ ፖስታን እና ሌሎችን ተመሳሳይ የመገናኛ መሳሪያዎችን በማቋረጥ ምርመራዎችን ማካሄድ ይችላል፡፡ ፖሊስ በሽብርተኝነት የተጠረጠረን ማንኛውንም የመንግስት ተቋም፣ ባንክ፣ ወይም ደግሞ የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ ሰነዶችን ፣ ማስረጃዎችን እና መረጃዎችን ለመመርመር ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ የአፓርታይድ የሽብርተኝነት ድንጋጌ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩትን ሰዎች የመያዝ እና የመመርመር ፍጹም የሆነ ስልጣን ተሰጥቶት ነበር፡፡

በሽብርተኝነት የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ክስ ሳይመሰረትበት መረጃ ለመሰብሰብ ለተጨማሪ ቀናት እየተባለ ምንም ዓይነት ገደብ በሌለው መልኩ ለ28 ቀናት በእስር ቤት ሊታጎር ይችላል፡፡ በሽብርተኝነት ተጠርጣሪው ላይ በአሸባሪነት በአገዛዙ ዓቃቤ ሕግ የሚቀርብ ማስረጃ፣ የእምነት ቃል መስጠትን (በማሰቃየት የተገኘ ማስረጃ)፣ ባልተጣራ ወሬ፣ ቀጥተኛ ያልሆነን መረጃ፣ ዲጂታል እና የኤሌክትሮኒክ ማስረጃዎችን እና የስለላ ዘገባዎችን በመያዝ ዘገባው ምንጩ ከየት እንደሆነ ወይም ደግሞ መረጃው ተገኘ የተባለበትን ዘዴ (በማሰቃየት የተገኘን መረጃ) ሳይገልጽ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ሕጉ ማንኛውም የውንጀላ ክስ የተመሰረተበት ሰው ጥፋተኛነቱ በሕግ እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ ነው የሚለውን ዓለም አቀፍ መርሆ በመጣስ ተጠርጣሪውን አሸባሪ በማለት በቁጥጥር ስር በማዋል የጥፋተኛነት ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በአፓርታይድ የአሸባሪነት ድንጋጌ የአሸባሪነት ተጠርጣሪ ያለምንም ዋስትና ለ180 ቀናት (በፖሊስ እና በዓቃብያነ ሕግ ባለስልጣኖች ትዕዛዝ የሚታደስ) በእስር ቤት ሊቆይ ይችላል፡፡ ማንኛውም ማስረጃ በግዴታ የተሰጠን የእምነት ቃል እና ሁለተኛ ማስረጃ ጨምሮ በፍርድ ቤት እንደ ማስረጃ ሊያገለግል ይችላል፡፡ እንደ አፓርታይድ አሸባሪነት ድንጋጌ ሁሉ የዘ-ህወሀት አዋጅ ዳኞች በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ጣልቃ በመግባት በውንጀላ ክስ ተይዘው በእስር ቤት ውስጥ ባሉት እስረኞች ላይ ከሕግ አግባብ ውጭ ስልጣንን በመጠቀም በእስረኞች ላይ ስቃይ ሲፈጸም እንኳ ድርጊቱን ለማስቆም ውሳኔ ማሳለፍ የማይችሉ ናቸው፡፡

በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ እና በኢትዮጵያ አፓርታይድ ውስጥ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩት ሁሉ በዝንጀሮው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የዘ-ህወሀት እስር ቤቶች በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ በጋዜጠኞች፣ በወትዋቾች እና በሰላማዊ አመጸኞች በሀሰት በሸፍጥ ክስ ተከስሰው ወይም ደግሞ አሸባሪዎች ተብለው ክስ ተመስርቶባቸው በመሰቃየት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በሀሰት የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በማጎሪያው እስር ቤት ውስጥ በመሰቃየት ላይ ከሚገኙት በሺዎች ከሚቆጠሩት የሚከተሉት ይካተታሉ፡ እስክንድር ነጋ፣ በቀለ ገርባ፣ አህመዲን ጀቤል፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አንዷለም አራጌ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ እማዋይሽ ዓለሙ፣ ደልዴሳ ዋቆ ጃርሶ፣ ኦኬሎ አኳይ ኡቹላ፣ የዞን 9 ጦማርያን፣ወዘተ፡፡ አምባገነኑ አገዛዝ ከዚህ አልፎ ድንበር በመሻገር የስዊድን ጋዜጠኞች የነበሩትን ጆሀን ፔርሰንን እና ማርቲን ሽብየንም በቁጥጥር ስር በማዋል የበርከታ ዓመታት እስራት ከበየነ በኋላ በኃያላኑ መንግስታት ግፊት ሳይወድ በግድ ፈትቶ የለቀቃቸው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የዘ-ህወሀት የፖለቲካ እስረኞችን ስም ዝርዝር ለመመልከት ከዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

ለተጨማሪ ዘርዝር ከዚህ ጋ ይጫኑ፡፡

የዘህወሀት የጸረ ሽብርተኝነት ሕግ ሰለባዎች፣

የዘ-ህወሀት የጸረ ሽብርተኝነት አምባገነናዊ የአዋጅ ሰነድ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ጋዜጠኞች ትችት ማቅረብ እንዳይችሉ ለመሸበብ፣ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ድርጅትን የማጠናከር ስራ እንዳይሰሩ፣ ተራ ዜጎች መናገር እንዳይችሉ፣ የሲቪክ ድርጅት አመራሮች ህዝቡን ማነቃነቅ እንዳይችሉ፣  መምህራን እውቀታቸውን ማካፈል እንዳይችሉ፣ ዳኞች ነጻ በሆነ መልኩ ፍትህን እንዳያሰፍኑ፣ ምሁራን ትንታኔ እንዳይሰጡ እና ጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ የእርሱን አምባገነናዊ አገዛዝ እንዳይጠይቅ ዓላማ ያደረገ ነበር፡፡ የአሸባሪነት ሕጉ ንግግርን ለመወንጀል፣ ሀሳብን ለመገደብ፣ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡትን የህትመት ውጤቶች ከሕግ ውጭ ለመዝጋት፣ ልብን ለማሸበር፣ መንፈስን ለመደምሰስ፣ አዕምሮን ለማሸበር እና በሕገ መንግስቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋስትና ያገኙትን የሰብአዊ መብቶች ለመደፍጠጥ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በፖሊስ መንግስት በምትተዳደረው ኢትዮጵያ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ድርጅት መሪዎች እና ሰላማዊ አመጸኞች በ24/7 ምርመራ ውስጥ ያሉ እና በመንገድ ላይ የሚገኘው ተራው ሕዝብ ደግሞ የማስፈራራት፣ የማሸማቀቅ እና የማሰቃየት ድርጊቶች ይፈጸሙበታል፡፡ በገጠር እና በከተማ ባለው ህብረተሰብ ውስጥ የተንሰራፋው የፍርሀት ከባቢ አየር እና ከታችኛው የአስተዳደር እርከን ከቀበሌ ጀምሮ እየተፈጸመ ያለው ጭቆና ሰላማዊ አመጽን ወይም ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግን ከልክሎ ይገኛል፡፡ የዘ-ህወሀት የቀድሞው ፕሬዚዳንት እና ከዚያ በኋላ ደግሞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የነበሩት ዶ/ር ነጋሲ ጊዳዳ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመንግስት አሸባሪነት ደረጃ በጣም አስፈሪ እና ለእንደዚህ ዓይነቱ ተመሳሳይ ነገር በሶቬት ህብረት በስታሊን ጊዜ ከነበረው ጋር በማመሳሰል እንዲህ በማለት አቅርበውታል፡

ፖሊስ እና የደህንነት ኃላፊዎች ከእያንዳንዱ አባወራ ቤት በሌላ መንገድ መረጃዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ከእነዚህ መንገዶች አንዱሻኔ እየተባለ የሚጠራውን ድርጅቶችን ወይም ደግሞ መዋቅራዊ ደረጃዎችን መጠቀምን የሚያካትት ሲሆን ይህም በኦሮምኛትርጉሙ አምስት የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡ አምስት አባወራዎች በአምስቱ አባወራዎች ላይ መረጃዎች የመሰብሰብ ስራ የሚሰሩእና በአንድ ላይ ሆነው በአንድ መሪ ስር ይመደባሉ የደህንነት ኃላፊው የሰበሰበውን መረጃ ከሱ በላይ ላለው ለከፍተኛውየአመራር አካል ለቀበሌ አለቃው ያስተላልፋል፡፡ እርሱም በበኩሉ ያገኘውን መረጃ ለወረዳ ፖሊስ እና ለደህንነት ኃላፊውያስተላልፋል፡፡ እያንዳንዱ አባወራ እንግዶች እና ጎብኝዎች በሚመጡበት ጊዜ የጉብኝታቸው ምክንያት ምን  እንደሆነ፣የሚቆዩበት የጊዜ ርዝመት ምን ያህል እንደሆነ፣ ምን እንዳሉ እና በምን የስራ ተግባት ላይ ተሰማርተው እንደቆዩ እንዲዘግብይጠበቃልኦፒዲዮ/ኢህአዴግ የብዙሀን ማህበራትን (ሴቶች፣ ወጣቶች እና የአነስተኛ ብድር ቡድኖች) እና የፓርቲ ህዋሶችን(አባቶች፣ እናቶች እና ወጣቶች) ያንቀሳቅሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና እና የኃይማኖት ተቋማትለተመሳሳይ ተግባር ያገለግላሉ…“

አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ እና የዘህወሀት መንግስታዊ ሽብርተኝነት፣

የሕግ የበላይነት በሰፈነበት እና ነጻ ዳኝነት ጠንካራ በሆነበት ማንኛውም ሀገር አምባገነናዊነት ቦታ አይኖረውም፡፡ ሆኖም ግን በዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች፣ በይስሙላ ፓርላማዎች እና በቀልተኝነት እና ኢፍትሀዊነት ባለበት፣ የአንድ ሰው አምባገነናዊነት በተንሰራፋበት ሀገር አንድ ፓርቲ እራሱ የሀገሪቱ ሕግ ይሆናል፡፡ ስለሆነም እ.ኤ.አ በ2016 ኢትዮጵያ እንዲህ የሚለውን የ1984ቱን ጆርጅ ኦርዌል ሆናለች፡ ማሰብ አሸባሪነት ነው፡፡ ሰላማዊ አመጸኝነት አሸባሪነት ነው፡፡ በስልጣን ላይ ላሉት እውነታውን መናገር አሸባሪነት ነው፡፡ ህሊና ያለው መሆን አሸባሪነት ነው፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ አሸባሪነት ነው፡፡ የአንድን ሰው ነብስ መሸጥ መቃወም አሸባሪነት ነው፡፡ ለዴሞክራሲ እና ለሰብአዊ መብት መጠበቅ መቆም አሸባሪነት ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን መጠበቅ አሸባሪነት ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ መንግስታዊ ሽብርተኝነትን መገዳደር በእራሱ ሽብርተኝነት ነው፡፡

መንግስታዊ ሽብርተኝነት ኃይልን እና ጭቆናን መጠቀም፣ ማስፈራራት፣ ማሰር እና ማሰቃየት፣ በሕዝብ ውስጥ ውስን የሆነ የፖለቲካ መልዕክት እና ውጤት ለማምጣት የፍርሀት ድባብ እንዲሰፍን ምቹ ሁኔታን መፍጠር መንግስታዊ ሽብርተኝነት የሚጠቀምባቸው እንዲህ የሚሉ ስልቶቹ ናቸው፡ መገዳደር ከንቱ ነገር ነው! መገዳደር ይደቆሳል! ምንም ዓይነት መገዳደር አይኖርም!

መንግስታዊ ሽብርተኝነት ሁሉንም ህብረተሰብ ሽባ ያደርጋል፣ እናም ፍርሀትን በማንገስ የዘፈቀደ ስልጣንን በመጠቀም እና በጣም ጭካኔ የተመላበት ተግባር በመፈጸም ማህበረሰቡ ድርጊት አልባ ስዕል እንዲኖረው እና እንቅስቃሴው ሁሉ እንዲገደብ የግለሰቦችን አቅም ሽባ ያደርጋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የፍርሀት ከባቢ አየር ድባብ እና ጥላቻ በእያንዳንዱ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ህይወት ውስጥ የሚሰራጭ ነገር ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ የፍርሀት ከባቢ አየር ድባብ የ13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ያለባትን ሀገር ወደ 13 ወራት ፍርሀት፣ ጥላቻ፣ ጨለምተኝነት እና ጨለማ ወደተንሰራፋባት ሀገርነት አሸጋግሯታል፡፡

መንግስት ሕጉን ዜጎችን ጸጥ  ለማድረግ እና ኃይልን በመጠቀም ሰላማዊ አመጸኞችን ለማፈን፣ ለማሰር እና ሰላማዊ አመጸኞችን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን ለብቻቸው ነጥሎ ማሰር፣ ፕሬሱን መጨቆን እና ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ ማሰር፣ ሰብአዊ መብትን ያለተጠያቂነት መደፍጠጥ፣ የሕግ የበላይነትን ሽባ ማድረግ፣ የሕገ መንግስታዊ ተጠያቂነትን መናቅ እና የመሳሰሉትን ሁሉ መፈጸም የሚችል መንግስት ታዲያ ሽብርተኛ ምንግስት አይደለምን?

ወደ አፓርታይዲቱ ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጡ! 

(ይቀጥላል)

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ግንቦት 6 ቀን 2008 .

 

Filed in: Amharic