>

ግብዣው ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ [በዕውቀቱ ስዩም]

ካገሩ የወጣ ካገሩ እስኪመለስ
ቢጭኑት ሶፍትዌር ቢለጉሙት ሆረስ

bewketu Siyum 3ከዘፋኞች ቡድን ጋር አሜሪካ ከገባን ማግስት ዘፋኞች በዶላር ከበሩ፡፡ እኔ አጥብቄ ተቸገርኩ፡፡ በወይዘሮ የሺሻ- ወርቅ ናይት ክለብ ውስጥ፤ ፋሲል ደመወዝ የጣውላ ክላሹን አነግቶ “አረሡት የሁመራን መሬት ” ብሎ ዘፍኖ ፤ ሁመራን ለመሸመት የሚበቃ የሽልማት ዶላር ይዞ ሲወርድ፤ እኔ ግጥም ለማንበብ ወደ መድረክ እወጣለሁ፡፡ ተዝያ በግጥም ደብተሬና በእኔ ማህል የቆመውን ወፍራም የሺሻ ጭስ ባይበሉባየ ገለል አድርጌ፤
“ዓለማዊ ልቤ ለበሰልሽ ዳባ ምናኔ ተመኘ
በእናቴ ቀብር ላይ የጠፋብኝ እምባ ፊቴ ላይ ተገኘ“ ብየ ስጀምር አያስጨርሱኝም፡፡

“ምናኔ ደሞ ምንድነው?” ትለኛለች ፤ከጥግ ቁጭ ብላ ሺሻ የምትጠባ ደንበኛ ፡፡ ብልጭ ይልብኛል ፤ ግጥሜን ላንብብ ወይስ አንቺን አማርኛ ላስተምር?

“አቦ !ይሄ ልጅ ያስቃል ሲባል አልነበረም እንዴ?ምንድነው እዚህ ”ቀብር“ ምናምን እያለ የሚያለቃቅስብን?”ይላል ሌላው የሚወረወር ነገር ባካባቢው እየፈለገ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከኢትዮጵያ ያስመጣኝ ፕሮሞተር በኔ ቆረጠ ተስፋ ፤ ጥረህ ነድተህ ብላ ብሎ ጥሎኝ ጠፋ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ አማርጥ የነበርኩት ሰውየ አሜሪካ ውስጥ ያለ ፈቃዴ በተከታታይ እጦም ጀመር፡፡ አሜሪካ የመብል አገር ናት፡፡ እንዲያውም አሜሪካ አገር አይደለችም፡፡ ዲሞክራሲያዊ የግብር ማብያ አዳራሽ ናት ማለት ይሻላል ፡፡ ጠዋት የቤቴን በር ስከፍት ከነ ጃንቦ ጆቴ ክፍል መአት ዓይነት የፕላስቲክ አገልግል፤ የሰርዲን ጣሳ፤ ድርብ ሰረዝ የመሰለ በርገር፤ እንዲሁም የቢራ ጠርሙስ እየተጠረገ ሲወጣ አያለሁ፡፡ ከጎረቤቴ የምቾት ተረፈ- ምርት እየተግተለተለ ሲወጣ እየተመለከትሁ ያለማቋረጥ አዛጋለሁ፡፡ ልክ ጓድ ኮምጨ አምባው መፈክር ሲያሰማ ያደርገው እንደነበረው፤ እጄ የምድርን ኮርኔስ እስኪነካ ድረስ እየተንጠራራሁ አዛጋለሁ፡፡

ሲብስብኝ ማንኛውንም የምሳ ግብዣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል ጀመርኩ፡፡ ዘፋኞች ”ተጋባዥ ገጣሚ “በማለት ይጠሩኝ ጀመር፡፡ አንድ ቀን ቨርጂንያ አውራ ጎዳና ዳር ቆሜ በጥሞና አሰላስላለሁ፡፡ ፊቴ ላይ የሚታየውን ጥልቅ ጥሞና የተመለከተ ሰው ስለ ቀጣይ ያገራችን እጣ ፈንታ እንጂ ስለ ቀጣዩ ምሳ እያሰበ ነው ብሎ አይገምትም፡፡

”ሃይ በእውነቱ “ የሚል የሴት ድምጽ ካሳቤ አባነነኝ ፡፡

አንዲት ያገሬ ልጅ መኪናዋን አቆመችልኝ ፡፡ ስሟን ጉዲት ልበላት፡፡ ዓይኔ ደረቷ ላይ ተተከለ፡፡ የዛን ሰሞን ፤ ፈርዶብኝ ከሴቶች አከላት ውስጥ አስቀድሞ ትኩረቴን የሚሰርቀው ጡታቸው ነበር፡፡ አንድ ጡት፤ ጡት መሆኑ በባለቤቱ ይረጋገጥ እንጂ አላማርጥም፤ከጡት ጡት አላበላልጥም፡፡ ድቡልቡል ጡት- ሁለት መላጣ ራስ የሚመስል ጡት- ዝርግ ጡት- የጥንት ካቦርት ኮሌታ የመሰለ ጡት- ደረት ለመሆን ትንሽ የቀረው ጡት- አብስትራክት ጡት- የምታምነው ግን የማትዳስሰው ጡት፡፡

-ምን ዓይነቱ ሸፋዳ ብትሆን ነው ርቦህ እንኳ ጡት የምትሾፈው ?የሚል አንባቢ አይጠፋም ፡፡

ወገን!ጉዳዩ ሽፍደት አይደለም፡፡ ጡት ማየት ልክ ሞሰብ እንደመክፈት ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ከምግብ ጋር የተዋወቅነው በሴቶች ጡት በኩል መሆኑን አንርሣ ፡፡

ትንሽ ከተደናነቅን በኋላ፤
”ለምን ምሳ አብረን አንበላም?“አለቺኝ ጉዲት፡፡

ገና”ለምን ምሳ… “የሚለው ሐረግ ባየር ላይ እያለ መኪናዋን ከፍቼ ከኋላ ወንበር ቁጭ ብያለሁ፡፡ ትንሽ እንደ ሄድን ጉዲት መኪናዋን ካንድ ጣቢያ አጠገብ አቆመች፡፡ የሆነ ዐራት ማእዘን ሰውየ ገብቶ አጠገቧ ተቀመጠ ፡፡ ከዝያ ዞር ብሎ “ የማን አባቱ ጉቶ ነው” በሚል አይነት ገላመጠኝ ፡፡ ወድያው ግን በድጋሜ ከተመለከተኝ በኋላ“ አጅሬ አንተነህ እንዴ?ለመሆኑ ወደ ሥነጽሁፍ ዓለም እንዴት ገባህ?“ እያለ በባዶ ሆዴ ያደርቀኝ ጀመር፡፡

ቤት ገብተን ጉዲት ምሳ ለመሥራት ወደ ጓዳ ገባች፡፡ ሰውየው የፍቅርና የትዳር ታሪኩን ባጭሩ…. ለሁለት ሰዓት ያህል… ተረከልኝ ፡፡ አዲሳባ ውስጥ በፍቅር እንደኖሩ ከዚያ እሱ ወደ አሜሪካ እንደተሰደደና እሷን በስንት ውጣውረድ እንዳመጣት ነገረኝ፡፡ በቅጡ አልሰማሁትም፡፡ ከሰውየው ትረካ በላይ ጥርት ብሎ የሚሰማኝ ከጓዳ የሚመጣው የመክተፍያ ድምጽ ነበር፡፡ ጉዲት በያይነቱ ሠርታ ጨረሰች፡፡ ግን ቶሎ አልቀረበም፡፡ እኔን ራብ እየሞረሞረኝ ባልና ሚስቱ ስለኣቀራረብ ስታይል ይራቀቃሉ፡፡ ስንግ ቃርያው የሚቀመጠው ከቲማቲሙ በስተቀኝ በኩል ነው በስተግራ በኩል ነው ? በሚለው ዙርያ ለሃያ ደቂቃ ያክል ተከራከሩ፡፡ እኔ ወደ ማእዱ ለመሄድ ትንሽ ሲቀረኝ ማእዱ ከፊቴ ቀረበ፡፡

”ይገርምሃል ለመጀመርያ ጊዜ ሲዲህን የሰማሁት ደሳለኝ ቤት ሆኘ ነው” አለችኝ ጉዲት ከጠረጴዛው ላይ ብርጭቆ የሞላ ውሀ እያስቀመጠች ፡፡

” ደሳለኝ? ደሳለኝ ማን ነው?“አለ ሰውየው የህጻን ብርድልብስ የሚያክል እንጀራ ሰሀኔ ላይ እያነጠፈ፡፡
”ደሳለኝ፡፡ ተከራይቶ የሚኖር ልጅ ነበር፤ እኛ ግቢ!”

” ኦኬ!ምን ልትሠሪ ቤቱ ገባሽ?“ባሉካ ባረቀ፡፡
” ቲቪ ልመለከት ነዋ!! የደሳለኝ ብቸኛ ሀብቱ ግዙፍ ቴሌቪዥኑ ነበር፡፡ ይገርምሀል!(ወደ እኔ እያየች) ቤቱ ውስጥ ወንበር እንኳ አልነበረውም”

“ወንበር ከሌለው ምን ላይ ተቀምጠሽ ቲቪውን ዓየሽው?”ሰውየው አፈጠጠ፡፡
“ እምም…. አልጋው ጫፍ” አለች ፈገግታዋ እንዳያመልጣት ከንፈሯን እየጨቆነች ፡፡

ሰውየው ለመደባደብ ያሟሙቅ ጀመር፡፡ ብድግ ብየ ” ተው እንጂ ነውር ኣይደለም እንዴ? ” ምናምን እያልሁ በማሃላቸው ገባሁ፡፡“ነውር ኣይደለም እንዴ?አትሊስት ምሳየን እስክበላ ድረስ ለምን አትታገስም?“ አልኩ በልቤ፡፡

”አሜሪካ እንዳለህ አትርሳ፡፡ ጫፌን አትነካኝም!“አለች ጉዲት ከመጤፍ ሳትቆጥረው፡፡

እውነቷን ነው፤አሜሪካ ውስጥ ሴትን ጫፍ መንካት ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ እና ወንዶች ንዴታቸውን የሚወጡት ግድግዳ በቴስታ በመምታት የመኪና ጎማ በካልቾ በመጠለዝ ነው፡፡ ሰውየው በንዴት አረፋ እየደፈቀ ዞር ሲል ከግድግዳ የተሻለ ማስተንፈሻ ተመለከተ፡፡ ቁልቁል ዐየኝ፡፡ ቀጥሎ የተከሰተው ብዙ ነገር ተረስቶኛል፡፡ ብቻ፤ “ አቦ ወደ እዛ ዞርበልልኝ ” ሲልና የመጥረቢያ ዛቢያ የመሰለውን ክርኑን ወደ አንገቴ ሲሰነዝር ትዝ ይለኛል፡፡ አንገቴ ወደ ቀድሞው ጤንነቱና ውበቱ ለመመለስ፤ ላንድ ሳምንት የቢትልስ ሹራብ ኰሌታ የመሰለ ጀሶ ድጋፍ ማግኘት ነበረበት ፡፡እና እስከዛሬ ድረስ ” አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር“ የሚለውን የቴዲ አፍሮ ዘፈን በሰማሁ ቁጥር ይሄ ልጅ የኔን ታሪክ ማን ነግሮት ይሆን ?እላለሁ፡፡

Filed in: Amharic