>
10:27 pm - Thursday May 19, 2022

የወያኔ ሰልፍ በፍራንክፈርት እና ግንቦት 7 ![በልጅግ ዓሊ]

ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በፍራንክፈርት የዶክተር ብርሃኑ ነጋን መምጣት አስመልክቶ በተጠራ ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደ ቦታው አምርቼ ነበር። የስብሰባው ቦታ ከወትሮ በተለየ በፖሊስ ተከቦ ከሩቅ ተመለከትኩና ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ወደ ቦታው ጠጋ አልኩ። ጥቂት ግለሰቦችም ከወዲህ ወዲያ ይራወጣሉ፣ ግርግር ይስተዋላል። ይበልጥ እየተጠጋሁ ሲሄድ አንዳንድ የማውቃቸውን የወያኔ ደጋፊዎችን ለመለየት ቻልኩ። እውነቱን ለመናገር በመጀመሪያ የወያኔ አባላት የዶክተር ብርሃኑ ስብሰባ ለመቃወም ያዘጋጁት ስልፍ ነው ብዬ  ለማመን አልቻልኩም ነበር። እንዲያውም ስብሰባውን አትካፈሉም ተብለው የተከለከሉ ሰዎች ተቃውሞ መስሎኝ ነበር።

TPLF-Frankfurt -በልጅግ ዓሊፍራንክፈርት ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ ሲቀነቀንባት የነበረች ከተማ፣ አያሌ ታላላቅ የተቃዋሚዎች ስብሰባ የተካሄደባት ከተማ ፣ የወያኔ አባላት አንገታቸውን ደፍተው የኖሩባት ከተማ፣ ዛሬ ወያኔ የልብ ልብ አግኝቶ፣ አፉን ከፍቶ፣ ለይቶለት አደባባይ ወጥቶ የተቃውሞ ስልፍ ያካሂድባታል ተብሎ ፈጽሞ አይታሰብም ነበር። አንድ ቀን ልንደፈር እንችላለን ብሎ የጠረጠረ ተቃዋሚ ከቶ ኖሮስ ያውቅ ይሆን? ወያኔ ሰርጓጅ ጦሩን ወደ ጀርመን አስርጎ ቅኝ ግዛቱን ያስፋፋል ብሎስ ማን አሰቦ ያውቅ ይሆን? እነዚህ የጎጠኞች ማዕድ ፍርፋሪ የሚለቅሙ፣ ሳይጠሩ አስቀድመው በወያኔ ደጀሰላም በራፍ ላይ ለዳረጎት የሚኮለኮሉ፣ በሚገባቸው አባባል፣ የልማት አጋር ኢንቨስተሮች፣ እንዲህ በድፍረት ለተቃውሞ ይወጣሉ ብሎ ማንስ አስቦ ያውቅ ይሆን? https://www.youtube.com/watch?v=ywugKQfWVn4

(ይህ ቪዲዮ ወያኔ ከለጠፈው የተገኘ ነው ። ለፕሮፖጋንዳ ሲባል ብዙ ተቆርጧል።)

ያም ሆነ ይህ ያልነበረው ታዬ! ያልተደፈረው ተደፈረ፣ ያልተደረገው ተደረገ፣ … ከውስጥም ከውጭም ሁሉም ይጮሃል። የትላንቱ አባራሪ ዛሬ በተባራሪነት ይጫወታል። ትላንት ወያኔ ሌባ! … ወያኔ ዘረኛ! .. ወያኔ አምባገነን የነበር መፈክር፣ ዛሬ ቅኝቱ ተለውጦ “ግንቦት7 ሌባ! …ግንቦት7 አሸባሪ! ብረሃኑ ሌባ! ተራራውን ያንቀጠቀጠው ትውልድ ያሸንፋል፣ ደርጋዊነት ይወድማል ወ.ዘ.ተ“ በሚል ተቀይሯል። በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም የማይቻለው ፣የማይታሰበው መፈጸም ከጀመረ ሰንብቷል።

ለእኔ የሰለፈኞቹን ማንና ምንነት  ለመለየት ብዙም አላዳገተኝም። ገና ወያኔ የትግራይ ክልል ሰንደቅ ዓላማ የሚለውን አንድ ባልቴት ተሸክማው ሳይ ነው እነማን መሆናቸውን ያወቅሁት። መቼም በጥቅምና በዘረኝነት ያበደ ካልሆነ ይህንን የዘረኝነት ምልክት በአደባባይ ይዞ የሚወጣ አይኖርም። በዚህ በወያኔ ግርግር ላይ አለፍ’ አለፍ እያለ “የኢትዮጵያ”(ባለ ሃምባሻው)፣ እንዲሁም የጀርመን ሰንደቅ ዓላማዎች ነበሩ።

ወደ ቦታው ጠጋ አልኩ። ከመሃል አንዱ እዚሁ ፍራንክፈርት አካባቢ የሚኖር ወያኔ ስለለየኝ፣ ወዲያውም “አምሃራይ” ብሎ ጮኸ። የከበቡት ሁሉ እሱን ተከትለው “ አምሃራይ ሌባ ፣ ግንቦት 7 ሌባ ! ደርግ ሌባ ! ብርሃኑ ሌባ !“ እያሉ አዋከቡኝ። እንደ ልማዳቸው ብዙ ፎቶም አነሱኝ። በመካከላችን የጀርመን ፖሊሶች ጣልቃ ገቡ። ቆሜ በደንብ ለመስማት ፍላጎት ቢኖረኝም ፖሊሶቹ አዋክበው ወደ ስብሰባው አዳራሽ አስገቡኝ። እንኳን ፌደራል አልሆነ ፣ እንኳን አጋዕዚ አልሆነ . . .!…  እንኳንም ቃሊቲ አልኖረ ፣ እንኳንም በነፃው ዓለም በጀርመን ሃገር ሆነ! . . .  ባይሆን ኖሮ እንደ ቀይ ሽብሩ ዘመን “ አምሃራይ “ ብሎ ያጋለጠኝ ሶለግ …..! ሳይቦጫጭቀኝ መች ይቀር ነበር። ያችስ ብትሆን. . .  ድምጽዋ እስከሚዘጋ በሰሜን ቅላጼ ጀርመንኛ የምትሞክረው ባልቴት እኔን ለመንከስ አለያም አስቀፍድዳ ለማስገረፍ ወደ ኋላ መች ትል ነበር። ይሁን እስኪ “ማምሻም እድሜ ነው” . . . እዚሁ አብረን ስለምንኖር እንተዋወቃለን።

ለነገሩ የተጮኸብኝ ስለማይመለከተኝ አልገረመኝም። የግንቦት 7 አባል አይደለሁምና፣ ደርግም አይደለሁም፣ ብርሃኑም አይደለሁም። ወያኔዎቹ ግን ጥላቻቸው ከሁላችንም ጋር እንደሆነ አውቃለሁ። ወያኔ የወንጀለኞች ቁንጮ፣ የዘረኝነት ሁሉ የበላይ፣ የሕዝብ ጠላት መሆኑን አውቃለሁ። በሃገሬ ያጣሁትን ነጻነት በጀርመን ሃገር ሊያሳጡኝ መሞከራቸውም ከቶ አልገረመኝም ። ቢቻላቸው ከዛም በላይ ይሞክራሉ። ከእነዚህ ዓይን ከማይሞሉ ህዳጣን፣ የያዙትን መፈክር እንኳ አስተካክለው ማንበብ ከማይችሉ ማይማን ሌላ አይጠበቅም። ከእነዚህ በዘር ልጓም ተሸብበው ዞሮ ማያ አንገት የሌላቸው ሆዳሞች፣ ሌላ ምን ሊጠበቅ ይችላል?   አብረን እዚሁ ፍራንክፈርት ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የኖርን ሰለሆንን እንተዋወቃለን። እንኳን የጀርመንን ሕግ፣ ዴሞክራሲና ሥነ ስርዓት ሊረዱ ይቅረና ስማቸውን አስተካክለው እንደማይጽፉ አውቀዋለሁ። በተለይ ደግሞ “አምሃራይ” ብሎ ሌሎቹ እንዲጮኹብኝ የቀሰቀሰውን አስለኳሽ ጋሻ ጃግሬ አብረን የኖርን ስለሆንን ድፍን ቅልነቱን እረዳዋለሁ። እርሱ ይረሳው እንደሆን እንጂ ከ20ዓመታት በፊት ይህ ማይም ከሻብዕያ አባላት ጋር ሆኖ ያደርግ  የነበረው የምዘነጋው አይደለም።

ወያኔዎቹ እንዳለሙት፣ የወያኔ ቆንስላ እንደተለመው፣ ብዙዎቻችንን በምንም ሊያስፈራሩን አይችሉም። ማስፈራራት የሚችሉት መሬትና ኮንደሚኒየም ይሰጠናል ብለው ማንነታቸውን ሸጠው እጅ የሚነሱላቸውን ባንዳዎችን ብቻ ነው። እነርሱ ደግሞ ስብሰባ አይመጡም።  ማስፈራራት የሚችሉት በሁለት እጃቸው የሚጨብጧቸውን የዘመኑ ሆዳም “ኢንቨስተሮችን“ ብቻ ነው። ልማታዊ ካድሬዎቻቸውን። ሌሎቻችንማ ደረታችንን ገልብጠን፣ ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል! እያልን ፣ ዘረኝነት ይወድማል! እያልን ፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! እያልን ወደ ስብሰባው አዳራሽ ገብተናል።

አዳራሹ ውስጥ ስገባ የግንቦት ሰባት አባላትና ደጋፊዎች መሪያቸውን ዶክተር ብርሃኑን ከበው መፈክር ያሰማሉ። ተናጋሪው “ ዛሬ ትግላችን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋገረ” ብሎ በድምጽ ማጉያው ይናገራል። ውስጥ ያለው ሁኔታ በብዛትም በጩኸትም ከውጭው በጣም ይበልጣል ። ለጥቂት ደቂቃዎች የውስጡን ከውጩ እያወዳደርኩ ተቀመጥኩ። የሃገሬ የወደፊት ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል በማጤን ለትንሽ ጊዜ ቆዘምኩ። በአዕምሮዬ አንድ ሃሳብ ፣ አንድ ጥያቄ እየተመላለሰ አወከኝ።

ውነት ዛሬ ወያኔ በፍራንክፈርት ተቃውሞ የወጣው ስለደከመ ነው? ወይስ ስለጠነከረ ?

ይህ ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው ። በእውነቱ ከሆነ ወያኔ በአሁኑ ወቅት በብዙ ቅራኔ የተወጠረበት ወቅት ነው ። ደክሟል ! በውስጥ ክፍፍል ተጎድቷል፣ በስልጣን ሽኩቻ ጉልበቱ ዝሏል ፣ ጉድጓዱ የተማሰ ነው፤ ፍራሃትም አለበት ። ትንንሹንም ችግር ቢሆን እንደ ቀልድ አይመለከተውም ። እርምጃ መውስድ ይሞክራል ። ዶክተር ብርሃኑ ስብሰባው ላይ እንደተነተነው የተቃውሞ ግርግሩን ከዚህ አንጻር ሊታይ ይቻል ይሆናል።  የግንቦት ሰባት ከኤርትራው መሪ ኢሳያስ ጋር መግጠም ሊያስፈራው ይችላል። ነገር ግን ግንቦት ሰባት ከኢሳያስ ጋር መግጠሙ ዛሬ የመጀመሪያው ቀን አይደለም። ወያኔ ከደከመ ሰነባብቷል። ለምን ታዲያ ወያኔዎች ዛሬ ሰልፍ ለመውጣት ደፈሩ? ብለን መጠየቅ ደግሞ ብልህነት ነው።

እንደኔ ከሆነ ፍርሃት ብቻ አይመስለኝም ። ወያኔ ፍራንክፈርት አካባቢ ብዙ ሥራ ሰራሁበት፣ ብዙ አባላት 5 ለ 1 ጠረነፍኩበት የሚለው ክልሉ ነው። እዚሁ ፍራንክፈርት ውስጥ ባለፉት ሁለት አስር ዓመትት ወያኔ መሬትና ኮንደሚኒየም ለመደለያ በመስጠት አያሌ ዜጎቻችንን ከፋፍሏል። ቀንደኛ የወያኔ ተቃዋሚ ነን ይሉ የነበሩ ግለሰቦቸች ሳይቀሩ የወያኔ ደጅ ጠኝ ሆነዋል። ብዙ ጠንካራ ዜጎቻችንን በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ክፍፍል ስላስጠላቸው ከትግሉ ገለል ብለዋል፣ ወያኔ በትምህርት ስም ብዙ ወጣት ደጋፊዎቹን አምጥቷል፣ በስደተኛ ስም ብዙ አባሎቹን አስርጓል ። በዚህ ክልሌ ነው በሚለው ፍራንክፈርት የልብ ልብ የበላይነት ይሰማዋል ። ቀደም ሲል ጠንካራ የነበሩት ተቃዋሚዎች እነ መድህን ፣ እነ መኢአድ ፣ እነ ኢሕአፓ ዛሬ የሉም፣ በእነርሱ ቦታ በኮንደሚንየም ፣ በመሬት ጥቅም ምክንያት 5 ለ 1 የተጠረነፉ ሆዳሞች ቦታውን ሞልተውታል ። ለእኔ ወያኔን የልብ ልብ የሰጠው ይህ የሆዳምነት፣ የመከፋፈል፣ ከትግል የመሸሽ አዝማሚያ ብዙዎቻችንን በመልከፉ ሳቢያ ይመስለኛል ።

በሌላ በኩል ደግሞ በተቃዋሚዎች መካካል ወደሚያስማማን ሳይሆን ወደሚያለያየን የሚደረገው ጉዞ እንደቀጠለ መሆኑ ለወያኔዎች የልብ ልብ ሰጥቶታል። በተለይ የኤርትራ ጉዳይ በተመለከተ በሕዝብ መሃል የተፈጠረውን የአቋም ክፍፍል ወያኔ በውል ያጤነው ጉዳይ ነው። የኤርትራ መንግስት በነ ተስፋዬ ገብረ እባብ የተነደፈለትን ኢትዮጵያን የመከፋፈል ፖሊስ ቀረጾ ፕሮፖጋንዳውን ማጧጧፉ ለማንም ድብቅ አይደለም። ይህንን ወያኔም ይገነዘበዋል። ወያኔ እኔ ከሌለሁ አማራጫችሁ ተስፋዬ ገብረ እባብ፣ ጃዋር እና መሰሎቹ ናቸው ብሎ መቀስቀስ ከጀመረ ሰነበተ። ሁኔታውን ሲያጤኑት ደግሞ ጉዞው ወደ መሳፍንት ዘመን ይመስላል። እንደተለመደው ወያኔም ይህችንን የአቋም ክፍተት መጠቀም መፈለጉ ግልጽ ነው። በዘር እንደነገደ፣ በዓባይ ግድብ እንደነገደ፣ ዛሬም በኤርትራ፣ ዛሬ ጽንፈኛ ሆኖ  በጽንፈኞች፣ ዘረኛ ሆኖ እሱን እንስከጠቀመ ድረስ  ዘረኞች አውግዞ ሊነግድ ይሞክራል።

በሰልፉ ላይ ደርግና ደርጋዊነት ሲኮነኑ ነበር። በተለይም ደግሞ የደርግ ባለስልጣናት የነበሩ በተቃውሞው የትግል መድረክ ላይ ወጣ ወጣ እያሉ በመምጣታቸው ወያኔ ይህን እንደ በጎ አጋጣሚ ሊጠቀምበት መፈለጉ ከወያኔ ሰልፍ መፈክር መረዳት ይቻላል። የደርግን ፋሽሽትነትን ለማመልከት የገባችው መፈክር የማንን  ልብ ለማማለል እነደሆነ አስቀድማ ትሸተናለች። በእውነት ቢሆንማ ኖሮ ከወያኔ ከራሱ ጋር ዛሬም ድረስ የሚሰሩ ብዙ የደርግ ባለስልጣናት ባልኖሩ ነበር ።

በፍራንክፈርቱ የወያኔ ሰልፍ የተገነዘብኩት ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ እየተስለመለመ ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የደም ደብዳቤ በማረቀቅ ላይ የሚገኘው ወያኔ፣ በቀቢፀ ተስፋ የጎሳ እንጉርጉሮ እያዜሙ የሚጓዙ አጋር ድርጅቶቹና ወዶገብ አባላቱ የኢትዮጵያዊነትን ህዋስ ከውስጣችን አሟጦ ለማስወጣት እየተሄደበት ያለው እርቀት ምን ያህል እንደሆነ ከወያኔ የተቃውሞ ሰልፍ መገመት አያዳግትም። በሰልፉ ላይ አብዛኛዎቹ የትግራይ  ሰዎች እንደነበሩ ቢታወቅም፣ በዶክተር ብርሃኑ ስብሰባ ውስጥም የትግራይ ልጆችንም በብዛት እንደነበሩ እዚህ ፍራንክፈርት ለኖርነው ግልጽ ነው። ይህ የፍራንክፈርቱን የተቃውሞ ሰልፍ ከአንድ ዘር አቅጣጫ ለማያያዝ የሚከብደውም ለዚሁ ነው። ይህንን የወያኔን ሰልፍ ከወያኔ አቅጣጫ ብቻ ነው ማያያዝ ያለብን የሚል እምነት አለኝ።

የፍራንክፈርት ነዋሪ የሆንን ሁሉ በውል ልናጤነው የሚገባ አንድ ነገር አለ። አሱም እነዚህ ዛሬ የወያኔ ደጋፊ ሆነው ስብሰባ ለማደናቀፍ የሞከሩ፣ በስብሰባው ላይ የተገኘነውን ፎቶ አንስተው ለወያኔ ለማስተላለፍ የሞከሩትን ዝም ብለን ማለፍ የለብንም። በተቻለን መጠን ለጀርመን መንግስት በወያኔ ስለሚደርስብን ማስፈራራት (erpressung) ማሳወቅ ይኖርብናል። በሃገር ውስጥ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን መከራና ስቃይ አልበቃ ብሎ ዛሬ እዚህ እኛን በጀርመን ሃገር ለማሰቃየት መሞከራቸውን ዝም ብለን ማለፍ የለብንም። ፍራንክፈርት ወያኔ ቆንስላ ዛሬ የዲፐሎማቲክ ስራውን ትቶ የስለላና የማስፈራራት ተግባር መጀመሩ የሚያስፈራ ወንጀል ነው። ሊጠየቅ ይገባል። በስደተኛነት ስም ተቀምጠው የስለላ ስራ የሚሰሩትንም ዝም ብለን ማየት ከቶ የለብንም። የጀርመን መንግስት ለእኛ ለስደተኞች በሃገሩ በነጻነት እንድንኖር እንዲያደርግ ጥያቄችንን ማቅረብ አለብን።

በሌላ በኩል የግንቦት 7 መሪዎችም ከዚህ ስልፍ መማር የሚችሉት ወያኔን ለመጣል የኤርትራ ድጋፍ ማግኘቱ ብቻ  በቂ አለመሆኑን ነው። በውጭ አፋቸውን ለማዘጋት እቤታቸው ድረስ እየመጣ ያለውን ተቃውሞ ለመቋቋም መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያሻል። ያን ለማድረግ ደግሞ የሕዝብን ልብ ማማለል መቻል ይጠይቃል። ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎቻቸውም የሚያነሱትን ጥያቄ ለምን እንደሆነና መፍትሄው ምን እንደሆነ በግልጽ ወጥተው መናገር አለባቸው። ለጊዜያዊ ፖለቲካ ጥቅም ሲባል ከነተስፋዬ ገብረ-እባብና ከእነ ጀዋር መሀመድ ጎን መሰለፍ፣ ድጋፍ ሊያሳጣ እንደሚችልም ከወዲሁ መገንዘብ ትልቅ ሒሳብ ስሌት አይደለም። አሁንም በግንቦት ሰባት ሊመለሱ የሚችሉ ጥያቄዎች እንዳሉ በስብሰባው ውስጥ በጥያቄና መልሱ ወቅት በጉልህ የታየ ጉዳይ ነው ። የሰጎን ፖለቲካ የሚያዋጣ አይሆንም ። አንገትን አሸዋ ውስጥ ደብቆ አካላት እንዳሪ ሆኖ መደበቅ አይቻልም። እነ ተስፋዬ ገብረ-እባብ የሚቀሰቅሱትን አማራን ለማጥፋት የሚደረግ መጠነ ሰፊ የተቀነባበረ ዘመቻ የኤርትራ መንግስት የለበትም የሚለው ማሳመኛ ነጥብ ውሃ አይቋጥርም።

የፍራንክፈርቱ የወያኔ ሰልፍ ሁለት ገፅታዎች አሉት። አንዱ ግንቦት ሰባት እና ኢሳት እንደሚነግሩን የትግላችን ጥንካሬን ምን ያህል ወደፊት እየተወነጨፈ እንዳለ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ አጉልቶ የሚያሳየን የድክመታችንን ፣ የሸንፈታችንን፣ የክፍፍላችንን ጥልቀት ጭምር ስለሆነ በዚህ ላይ የቤት ሥራው እየከበደ ነው ማለት ነው። ለእኔ ዛሬ የወያኔ ትግል ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት የተሸጋገረበት ነው። ይህ ደግሞ በቀላል ለማስቆም የሚቻል ነው። በሁሉም አቅጣጫ በቅንጅት ከፍተኛ ሥራ ካልተሰራ ወያኔ አሁንም ዳግም ፈልፍሎ ቀዳዳ ማግኘቱ የማይቀር ነው። ቀባሪ የሌለው ሞት እንዳንሞት ማስተዋል ያስፈልጋል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

beljig.ali@gmail.com

ፍራንክፈርት

Filed in: Amharic