>
8:37 am - Sunday January 29, 2023

ስለሜሪ የማውቀውን ያህል እንዲህ ልናገር [ኤሊያስ ገብሩ]

Meron Alemayehu by Elias Gebiru 25062006ሜሮን ዓለማየሁ (ሜሪ)ን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወኳት እኔ በዕንቁ መጽሔት ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኜ ስሰራ ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም በነበረው ታላቁ ሩጫ ላይ ‹‹የተቃውሞ ድምጽ አሰምተዋል›› ተብለው ‹‹የጣይቱ ልጆች›› የሚል ስያሜ የነበራቸው የሰማያዊ ፓርቲ ዘጠኝ ሴት አባላት በፖለስ ቁጥጥር ስር ውለው ለቀናቶች ታስረው ነበር፡፡ በወቅቱም ይህ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ የ‹‹ጣይቱ ልጆች›› ከእስር ከተፈቱ በኋላም፤ ለሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ኃላፊ ይድነቃቸው ከበደ ደወልኩለትና ከልጆቹ መካከል ቢያንስ አንዳቸውን ቃለ-ምልልስ ልናደርግላቸው እንዳሰብን ነገርኩት፡፡ ይድነቅም፣ ከሜሮን ጋር ከተነጋገረ በኋላ ስልኳን ልኮልኝ ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ሆና ፒያሳ ተቀጣጠርን፡፡ ሜሪም ከአንድ የሴት ጓደኛዋ ጋር አብራ መጥታ ተገናኘንና አንድ ጸጥ ያለ ባርና ሬስቶራንት ውስጥ ቁጭ አልን – ለቃለ-ምልልስ፡፡

ሜሪ፣ ለማነሳላት ጥያቄ ይበልጥ አንገቷን አቀርቅራ ነበር ትመልስልኝ የነበረው፡፡ በወቅቱ ትንሽ የመደንገጥና የመጨነቅ ስሜት ይታይባት ነበር፡፡ በእርግጥም አይን አፋርነት በተወሰነ ደረጃ አይቼባታለሁ፡፡ ሜሪም ‹‹ቃለ-ምልልስ ሳደርግ የመጀመሪዬ ነው›› አለችኝ፤ ተረዳኋት፡፡ …ቃለ-ምልልሱም አልቆ ለህትመትና ለንባብ በቃ፡፡

ከዚያም በኋላ ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ ቪው ሆቴል አድርጎት በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ብዙዎቹ የ‹‹ጣይቱ ልጆች›› ተመሳሳይ አበሻ ቀሚስ ለብሰው ፕሮግራሙን ሲያደምቁት ነበር፡፡ አንዷ ሜሮን ዓለማየሁ ነበረች፡፡ በዕለቱ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት የነበረው ብርሃኑ ተክለ ያሬድ ሞቅ አድርጎ መድረኩን ይመራ ነበር፡፡ ብርሃኑ ዛሬ እስር ቤት ነው፡፡ ፍቅረማርያም አስማማው ካሜራ ማን ነበር፡፡ እሱም ዛሬ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ዮናታን ተስፋዬ ከድምጽ ጋር የተገኛኙ ቴክኒካል ነገሮችን ሲቆጣጠር ነበር፡፡ እሱም ዛሬ እስር ቤት ነው፡፡ እየሩሳሌም ተስፋው ለጨረታ የቀረቡ የአጼ ቴዎድሮስ ትልቅ ፎቶ ግራፍ ከሜሪ ጋር ይዛ ለታዳሚው ታሳይ ነበር፡፡ እሷም ዛሬ እስር ቤት ትገኛለች፡፡ …ዛሬ የዘነጋኋቸው ሰዎችም ይኖራሉ፡፡

ሜሮን ከትግል አጋሮቿ ጋር በመሆን የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች እና የሰልፍ ቅስቀሳ ላይ ተገኝታ ተደብድባለች፡፡ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢዎችንም ታስራ ተመልክታለች፡፡ ሜሪ ትታሰራች፣ ትፈታለች፡፡ ዳግም ትታሰራለች፡፡ መታሰር መፈታት አንዱ የህይወት አኳላ ነበር ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ ታስራ ጠይቄያትም አውቃለሁ፡፡ ይመሰረትባታልባታል፡፡ ፍርድ ቤት ትመላለሳለች፡፡ ብቻ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር ሆና መከራዋን አይታለች – በሀገሯ፡፡

እውነተኛ አሸባሪ የሆነው አይ ኤስ አይ ኤስ ኢትዮጵያኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉን ተከትሎ ለተቃውሞ በተጠራ ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ አስነስተሻል›› ተብላ ታስራ በዋስ ከተፈታች በኋላ በፍርድ ሂደት ስድስት ወራት ተፈርዶባት የእስር ጊዜዋን ቃሊቲ ጨርሻ ወጥታለች፡፡ የፍርድ ቤት የመጨረሻ ቀጠሮ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፤ ፒያሳ ከጓደኞቼ ጋር አግኝታት ነበር፡፡ ‹‹አይዞሽ ፈጣሪ ያውቃል›› ብለናት ነበር፡፡ ‹‹የመጣውን እቀበላለሁ›› ነበር ምላሿ፡፡ እንዳለችውም የመጣባትን በጽናት ተቀበለች፡፡

ወንድሟ ፍቅረ ማርያም አስማማው ከጓደኞቹ ብርሃኑነ ተ/ያሬድና እየሩሳሌም ተስፋው ጋር ወደኤርትራ ሊሄዱ ሲንቀሳቀሱ ጎንደር ላይ ተይዘው አሁንም ድረስ እስር ቤት ነው የሚገኘወ፡፡ ወላጅ አባቷ በጤና ምክንያት እንደሚታመሙ ሜሪ አጫውታኝ ታውቃለች፡፡ ወንድሟና ጓደኞቹም ታስረው ከማዕከላዊ ወደአራዳ ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርቡ ለጥብቅና ተማም አባቡልጉ እንዲቆምላቸው ‹‹እስኪ አነጋግርልኝ›› ብላኝም ተማምን ተይቄው ተማምና ባልደረባው የነበረው ዳዊት አራዳ ፍርድ ቤት ተገኝተው ዳዊት በችሎት ተከራክሮላቸው ነበር፡፡ሜሪሪ ከጭምት ባህሪዋ የተነሳ የምትፈልገውን ነገር ሰው ለመጠየቅ እንኳን የምትጨነቅ ልጅ ነበረች፡፡ ለዚህ ነውም ‹‹ተማምን አነጋግርልኝ›› ያለችኝ፡፡

ሜሪን ሳውቃት በጣም ጭምት፣ ትሁት፣ ሰላማዊ፣ ሰውን አክባሪ፣ ረጋ ያለች፣ የሆዷን በሆዷ መያዝን የምትመርጥ፣ ድምጿ ብዙም የማይሰማ፣ ለፈገግታና ለሳቅ ቅርብ የሆነች፣ ተስፋ መቁረጥ የማይታይባት፣ ሰውን በሙሉ አይኗ ለማየት ብዙም የማትደፍር፣ በጣም ዝምተኛ ልጅ ነች – በእኔ እይታ፡፡

እንግዲህ ይህቺ ጭምት እና ሰላማዊ ነፍስ የነበራት ልጅ፣ ‹‹ለሀገሬ ነጻነት ብረት አንስቼ ልዋጋ!›› ማለትን መርጣለች፡፡ ያቺ እርጋታን የተላበሰች ልጅ፣ በረሃም ወርዳ የታጋይ ስከርፍ አንገቷ ላይ ጠምጥማ፣ ወታደራዊ መለዮናልብስ ለብሳና ጥልፍልፍ የፕላስቲክ ጫማን ተጫምታ ጠብ-መንጃ በመያዝ በማኅበራዊ ሚዲያ ሰሞኑን አየናት፡፡ ያቺ ሰውን በሙሉ አይኗ ደፍራ ማየት የሚያስጨንቃት አይናፋር ልጅ ዛሬ በድፍረት ብረት አንስታለች፡፡ በሜሪ ፎቶግራፍ ላይ የምር የሆነ ስሜትን አንብቤያለሁ፡፡ ያቺ ርህራሄ ቅርቧ የነበረ ልጅ ዛሬ ጨክናለች፤ አምርራለች፡፡ በረሃ ላይ የተነሳቸውን ፎቶ ግራፍ አቅርቤ ሳየው፤ ትናንት ለሰላማዊ ትግል ደፋ ቀና ስትል የማውቃት ሜሪ በአይነ-ህሊናዬ መጥታ ውስጤ ተረበሸ፡፡ አሁን ይቺን ጽሑፍ እየከተብኩኝ ሳለሁ እንኳ፣ አይኖቼ እንባ አርግዘዋል – ብዙ ፈተናዎችን ማለፏን ሳላዘነጋ፡፡

እንደሜሪን አይነት ፍጹም ሰላማዊ ሰው፣ ያውም ሴት – ጨርቄን ማቄን ሳትል፤ የወጣትነት የፍቅር ህይወትን፣ ቤተሰብ መስርቶ መኖርን፣ እንደእኩዮቿ መዝናናትን ወደጎን ትታ፣ ውድ ቤተሰቦቿን እርቃ ደረቷን ለጥይት ልትሰጥ ስትወስን ማየት፣ ለገዥው ኃይል የምር አንደምታው ከባድ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል!

‹‹ሜሪ እግዚአብሄር ይጠብቅሽ!›› የሚለው ቃል፤ የመጨረሻ ወንድማዊ መሻቴ ነው!

Filed in: Amharic