>
5:13 pm - Friday April 20, 4868

በውቀቱ ስዩም - ከኢትዮጵያ

Bewketu Seyoumይህ ግጥም በቅርቡ ከሚለቀቀው “ራሴን በራሴ ካላንቆለጳጰስኩት ማን ያንቆለጳጵስልኛል ”ከተባለው የHip Hop አልበሜ የተወሰደ ነው 🙂 ይሄው::

በውቄ ሥዩም በዳዳ ደስታ ወየሣ
ዘብሔረ ማንኩሣ
ተጉዋዥ እንደሲራራ ፤ በራሪ እንደ ሽመላ
ስደቱ የላሊበላ
እግሩ የፉየገላ፤
ቪላ ነቅሎ፤ ቤቱን ጥሎ ፤ የሸማ ዳስ የሚቀልስ
ሲሻው ራሱን የሚያግዝ፤ ሲሻው ራሱን የሚመልስ
ሲወጣ የሣለውን ኮቴ፤ ሲገባ የሚደመስስ።

እሣት ከጭድ ፤የሚያዛምድ
ቅል ከዱባ
የሚያጋባ
ተኩላ ከበግ የሚያላምድ
ባንዲት ብርጭቆ ጠላ፤
ባንዲት ስኒ ቡና ተድላ
ራሱን ሚያቀማጥል
በጮማ ቤት እንደመናኝ፤ የጎመን ፍሪዳ ሚጥል
አቀርቅሮ ደስታ ነዥ፤ ተኮሳትሮ ፈገግታ አዳይ
“So proud to live so proud to die”
በበረት የማይወሰን፤ በእረኛ የማይመራ
የዱር በግ የዱር ፍየል ፤ባሻው የሚሰማራ
ከባብ ጋር የሚደንስ ፤ በርግብ ጉባየ የሚታደም
ነገሩ የጥንቅሽ ወዝ፤ ቃሉ የሸንኮራ ደም

ሞአ እንቦሣ ዘእምነገደ አዳ
አገሩን የማያምን፤ አገሩን የማይከዳ
ሜዳልያው የሌት ኮከብ፤ ባንዲራው የጸደይ ሜዳ
(ሰኔ 28, ሸገር፤ ሃያ ሁለት መዞርያ)

Filed in: Amharic