>
5:16 pm - Tuesday May 23, 4873

ኢህአዴግ ወጣት ሀብታሙ አያሌው'ን ለመግደል ስለ ማሴሩ ሌላ ምን ማሰረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል??

Ato Habtamu Ayalewዳንኤል ሺበሺ

ለማስታወስ ያህል (በእሥር ቤት):-

1ኛ. ማዕከላዊ በነበረበት ህክምና ተከለከለ፤

2ኛ. ቂሊንጦም ተመሳሳይ እርምጃ ተወሰደበት፤

3ኛ. ከዘዉዲቱ ሆስፒታል የህክምና ዶክመንቶቹ እንዲጠፋ ተደረገ

4ኛ. በሥር ፍ/ቤት (ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት) መከላከል ሳያስፈልገው፣ ያለ ልዩነት በሶስት ዳኞች በነፃ የተሰናበተውን ንፁህ ዜጋ በታሪክ ተሰምቶ በማይታወቅ ውሳኔ፤ ውሳኔው ታግዶ ለተጨማሪ ለ7-ወራት እንዲታሰርና በበሽታ መድቀቁ ከተረጋገጠ በኀላ ፈተው የለቀቁበትን አግባብ ስናይ፣

እንዲሁም ከህግ አግባብ ውጪ የመንቀሳቀስ መብቱን በማገድ ለተጠቀሰው ውስብስብ ችግር ሀብታሙንና ቤተሰቡን መዳረጋቸው፤

ከእስር ከተፈታ በኀላስ…

5ኛ. ሀብታሙ ስለ ጤናው መታወክ በየቀጠሮውና በየችሎቱ አቤት ከማለት በፍጹም ቦዝኖ አያውቅም፡፡ በአልጋ ላይ ከወደቀ ወዲህም ዓለም እየጮኸለት ይገኛል፡፡
የሚገርመው ነገር ከአገር እንዳይወጣ የተጣለው ዕቀባ እንዲነሳለት የሃኪም ማስረጃ አቅርቡ ተባልን፡፡ በዘርፉ በታወቁ ዶክተሮች የተፈረመ ሜዲካል ሰርተፊኬት አቀረብንላቸው፡፡ ፍ/ቤቱም (ዳኞቹም) ሃሳባቸውን ቀየሩና እንደ ገና የቦርድ ውሳኔ ካቀረባችሁ በዕለቱ እንወስናለን አሉን፡፡ እምነት ጥለን ያዘዙንን አቀረብን፡፡ በተለይ ለኔ እውነት መሰለኝ፤ እንደ ጠቅላያችን “የደቡብ ጎመን” አይደለሁ ! ምን ይደረጋል ፡ የፖለቲካ ቁማሩ ሲቀጥል ዳኛ የለም የሚል ስስና አስቂኝ ምክንያት እየሰጡንና እያጓተቱ አቆዪን፡፡
ዛሬ ደግሞ በሶስት ዳኞች የተጠበቀው (ከህግ አንፃር) በህክምና ቦርዱ ውሳኔ መሠረት የመጨረሻውን ውሳኔ እንሰማለን የሚል ጥቂት ተስፋ ይዘን ደጅ ጠናን፡፡ ይሁን እንጂ ሐቁ የተግላብጦሽ ሆነና ዐ/ህግ ካለበት ተፈልጎ የቃል ክርክር ያደርግ የሚል እጅ እግር የሌለዉ ዉሳኔ ጠበቀን፡፡ በርግጥም እንዲህ መባሉ ሀብታሙ ወደ መቃብር እየተገፋ መሆኑን ግልፅ አደረገልን …፤

6ኛ. ዳኞች ብዙ ርቀት ተጓዙ ቢባል እንኳን የቦርዱን ውሳኔ ኮፒውን ዐ/ህግ እንዲያውቀው ከመስጠት በዘለለ ቀርበህ የቃል ክርክር አድርግ በማለት ያውም ራሱ ዐ/ህግ ቅሬታ ባላቀረበበት ሁኔታ የሀብታሙን ስቃይ ለማራዘም “እባክህን መላ ፍጠርልኝ” አይነት ብይን መሰጠቱ የጨዋታው ህግ የበለጠ ግልፅ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል፤

7ኛ. አንድ በሽተኛ፡- በሃኪም ሪፈር ሲባል እና ጉዳዩ ወደ ቦርድ ሲመራ መልዕክቱ ምን ማለት እንደ ሆነ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ሪፈር ሲባል (በሀገር ውስጥ) ከጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታል፤ ከጠቅላላ ሆስፒታል ወደ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ እንደ ማለት ሲሆን፣ የቦርድ ውሳኔ የሚፈለገው ሁልጊዜም ለውጭ ህክምና መሆኑ ገና ከጅምሩ (by default) መረዳት የሚያሰችል እንደ ሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፤

8ኛ. ሀብታሙ ሲጀመር በፍፁም ከሀገር የመውጣት ፍላጎት የለውም፡፡ ለዚህ እኮ ነዉ ወደ ባህል ህክምና ጎራ ያለው፣ ለቄሱም ለፓስተሩም ሆነ ለሼኹ ምልጃና ተማጽኖ ልቡን የከፈተው፤ በሀገር ዉስጥ ወዳሉ የተለያዩ አምስት ትላልቅ የጤና ተቋማት (ሆስፒታሎች) ያመራው፡፡ አንዱ ወደ ሌላው ከአቅሜ በላይ ነው እያሉ ሲያንከባልሉ ቆዩና አሁን ደግሞ ጭራሹኑ ወደ ባሕር ማዶ ካልሄደና “በኮሎ ሬክታል ሴንተር” ካልታከመ ተስፋ የለዉም ተባለ፡፡ ከሀገር እንዳንወጣ የተጣለው እግድ እኔንም ይመለክተኛል፡፡ አንድም ቀን ዕግድ ይነሳልኝ ጥያቄ አቅርቤላቸው አላውቅም /አናውቅም/፤ ምክንያቱም የምጠይቅበት <ምክንያት> የለኝምና፡፡ ለሀብታሙ ግን ከበቂ በላይ ምክንያት አለው ፡፡ የሕይወት ነገር፡፡ የሥርዓቱ ቂመኛ ልሂቃን ግን ይህን እውነት መዋጥ ቸገራቸው፡፡
***
ሳጠቃልለው፡- አንድ፣ሁለት … ጥያቄዎችን ላንሳና ላብቃ፦
ሀብታሙ ህክምና ለማግኘት ይህንን ያህል ዋጋ መክፈል አለበት ወይ?
በህወሓት በኩል አንድም እንዲሞት፣ አለያም እንዲሰቃይ ወይም ለዘላቂ ጤና እክል እንዲዳረግና ዕድሜው እንዲያጥር የተወጠነ አይመስላችሁም???
የዘረኝነት ነገርስ መኖሩን አላስታዋላችሁምን??? በርግጥ ሃብታሙ እንዲህ የተጨከነበት የዉክልና ሞት እንዲሞት ታስቦ አይመስላችሁም ?

የዘገየ ፍትሕ፣ ፍትሕን እንደ መንፈግ ይቆጠራል!!!

Filed in: Amharic