>
2:50 am - Wednesday February 1, 2023

የ 'ወንድ በር' ለነጻድቃን! እንዴት? [ክፍሉ ሁሴን]

Kiflu Hussain.1የጻድቃንን ስንክሳር criss cross እያደረኩም ቢሆን ያነበብኩት ከማልጠብቃቸው ወገኖች ይልቁንም አስተያያታቸውን፣ ብሎም ትንተናቸውን ከማከብርላቸው ወዳጆቼ በጎ አስተያየት ስለተሰነዘረ አንዳንድ ነጥቦች ላይ ተመላልሼ ቃኝቼዋለሁ።

Shewan Dagne ጻድቃን በወያኔ በግፍ የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ፣ ካሳም ይከፈላቸው ብሏል ያለበትን ላገኝ አልቻልኩም፤ መከለሴ ስለማይቀር አገኘው ይሆናል እነጻድቁ መላኢክት ጻድቃንን እንደ ስሙ እንዲኖር አመላክተውት ብሎ ከሆነ።

ወደ ይዘቱ ስመጣ እሽኮለሌ፣ ቀልድ የማያውቀው ወዳጄ Mustafa Omer የጻድቃንን ጽሁፍ ለምን እንዳደነቀ ገባኝ። (በነገራችን ላይ በኢንግሊዝኛ አንብቦ ለመረዳት የታደላችሁ የሙስጣፋን ጽሁፎች ስሙን ጉግል በማድረግ እንድታነቡ ትመከራላችሁ)

ለማንኛውም የጻድቃን ጽሁፍ ወያኔነት የሚጫነው ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ከወያኔ ቱባ ልሂቃኖች በትግራይ ሕዝብ መነገድ እንደማያዋጣ፣ የትግራይ ሕዝብም ወያኔ (ኢህአዴግ ነው የሚለው እሱ) ወይም የመከላከያ ሰራዊቱ ያድነኛል ብሎ በወያኔ ማዕቀፍ ስር አሁን በራሱም ሆነ በሌላው ኢትዮጲያዊ ወገኑ ላይ ለተጋረጠው አደጋ መፍትሄ እንዳይፈልግ ይመክራል። ወያኔ በትግራይ ሕዝብም እንዴት እንደሚነግድ ወይም ስልጣኑን ለማራዘም እንዴት እንደሚጠቀምበት፤ ይህም በተቀረው ሕዝብ ላይ የፈጠረውን ምሬት ባልተለመደ ሁኔታ ይተነትናል።

ሆኖም ወያኔነት ይጫነዋል ባልኩት ላይ ስመጣ ወያኔ ከጅምሩ ዴሞክራሲያዊ ራዕይ ነበረው የሚለው አቋሙ፣ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጲያ ሕዝብ ተነጥሎ የተለየ ጥቅም ለማግኘት ተመኝቶ አያውቅም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ እሱና ጓደኞቹ ግን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ” ብለው በለስ እየቀናቸው ሲሄድ በፈበረኳቸው የ”ብሔር ብሔረሰብ” አሻንጉሊት ድርጅቶች ገዢና ዘራፊ ሆነው ሲንሰራፉ በሌላው ኢትዮጲያዊ ላይ የተፈጠረውን ስሜት ለማለባበስ ይዳዳዋል። ከወያኔ ውጪ የሆኑ በዘር ያልተደራጁ በርካታ ድርጅቶችን፣ በአገራቸው ጉዳይ ተሰሚነት ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋሞች አግለው ያጸደቁትን “ሕገ መንግስት”ም የኢትዮጲያ ሕዝብን ይሁንታ እንዳገኘ አድርጎ ሊሸጥልን ይሞክራል።

በወያኔ ክፍፍል ጊዜ የተባረሩትን ቱባ ወያኔዎች ለትግራይ ብሎም ለ”ኢትዮጲያ” የታገሉ ጀግኖችን ያዋረደ ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንደሆነ ይነግረንና ወያኔ ገና ስልጣን እንደያዘ ግን ለአገራቸው ዳር ድንበርና አንድነት መከበር እድሜ ልካቸውን በየበረሃው የተንከራተቱን የ”ደርግ ኢሰፓ ጨፍጫፊ ጦር” በሚል ትግራይ ተዋግተው የማያውቁትን ጭምር ኤርትራ ላይ ብቻ በሻዕቢያ ላይ ዘምተው የነበሩትን እያሳደዱ ያዋረዱበትን፣ በእስር ያጋዙበትን፣ በክረምትና በአውደ ዓመት ጭምር ከመኖሪያ ቤታቸው እያወጡ ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር እዳሪ የጣሉበትን ትቶ እነ ስዬን ማሰር፣ እነ ገብሩ አስራትን ማባረር ሁለተኛው የወያኔ ከዴሞክራሲ ያፈነገጠበት ሂደት እንደሆነ ይነግረናል።

ሌላው የ97ን ምርጫ ቀውስ ያነሳና የቅንጅት አመራር በፖሊሲ ደረጃ በይፋ በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘረኝነት የእልቂት ቅስቀሳ ያደርግ እንደነበረ ይነግረናል በተለመደ የወያኔ ቅጥፈት እና ያላንዳች ማስረጃ!

በመጨረሻም አሁን የተፈጠረውን ቀውስ የውጪ ጠላቶች እንዳይጠቀሙበት እያለ የውጪ ጠላቶች የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ሳይጠቅስ ድፍረት ባጣ ግልፅነት ደጋግሞ አሳስቧል። ጻድቃን ያው የጥንት ወያኔነቱ ወይም አሁንም ውስጥ ውስጡን ያልተላቀቀበቱ ወያኔነቱ አልተወው ስላለ በተለመደው እናሞኛችሁ ጨዋታ ጨዋ መስሎ ሊነግረን የሚፈልገው ስለ ቀድሞ ወዳጃቸው ሻዕቢያና ግንቦት ሰባት እንደሆነ ግልፅ ነው።

ጻድቃን ከምሩ የኢትዮጲያን ሕዝብ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ከመዓት ለመታደግ ከፈለገ ከሻዕቢያም ከግንቦት ሰባትም ጋር ከመሰሪነት የፀዳ ድርድር እንዲኖር መምከር አለበት። ከዚያ በመለስ ራሱ እንዳለው የደርግን ስህተት መድገም ብቻ ሳይሆን የላቀ ጥፋት መጋበዝ ነው። ከሻዕቢያ ጋር ያለውም አተካራ ሆነ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት መፈጠር ዋናው መንስዔና ተጠያቂ ወያኔ ነው።

ይህን ካልን በኋላ “ሲታጠቡ ከክንድ፣ ሲታረቁ ከልብ” በሚለው የአገራችን ይትበሃል መሰረት የወያኔ ሰዎች ከመሰሪነት የፀዳ የእርቅ መንፈስ ይዘው ከመጡ ደግሞም ንስሃ ከገቡ የ”ወንድ በር” አንነፍጋቸውም።

በነገራችን ላይ ጻድቃን በኢትዮጲያ መመስረት ስላለበት የመከላከያ ሰራዊት ገና በሽግግሩ ጊዜ ፈረንጅ ሁሉ በተገኘበት በተደረገ ስብሰባ ወረቀት አቅርቤ ነበር በሚለው የሂልተን ሆቴል ስብሰባ ላይ በአካል ተገኝቼ ነበር። ይህንኑ የሚያመላክቱ ፎቶግራፎች ሁላ ነበሩኝ። ምናልባት እንደስፈላጊነቱ በዚህ ላይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።

ኢትዮ ሪፈረንስ:- ቀጥሎ ያለውን ሊንክ በመጫን የጄኔራሉን ጽሁፍ ማንበብ ይችላሉ።

 

Filed in: Amharic