>
9:44 pm - Tuesday June 15, 2021

"ወልቃይት የማነው?!" (ኣብርሃ ደስታ)

እንዲህም ተብሏል “ወልቃይት የማነው? የሚል ጥያቄ ለመመለስ የፈራህ ይመስለኛል”

Abrha Desta 30.07.2016የፈራሁ እንኳን አይመስለኝም። የሚመለስ እንጂ የሚፈራ ጥያቄ ሊኖር አይገባም። ደግሞ በስንቱ ፈርተን እንችለዋለን? የነፃነት ትግል እውነትን መርህ ያደርጋል። እውነት ደግሞ አያስፈራም። በነፃነት ትግል ፍርሓት የለም። እናም “ወልቃይት የማነው?” የሚለውን ጥያቄ ትኩረት ያልሰጠሁት ስለሚያስፈራ ሳይሆን ስለማይረባ ነው።

የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ተገቢ ነው። እንዲያውም የማንም ህዝብ ጥያቄ ተገቢ ነው። የህዝብ ጥያቄ (የወልቃይትን ጨምሮ) ስህተት ሊሆን አይችልም። ስህተት የሆነ የህዝብ ጥያቄ የለም። ስለዚህ ማንኛውም የህዝብ ጣያቄ መልስ ይፈልጋል። ለዚህም ነው መንግስት የሚመሰረተው። መንግስት የተቋቋመው የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ነው (ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ)። የህዝብን ጥያቄ መመለስ ያልቻለ መንግስት መንግስት ሊባል አይችልም። ምክንያቱም የመንግስት ስራ ህዝብን ማስተዳደር ነው። ማስተዳደር ደግሞ የህዝብን ጥያቄ መመለስ ነው። ህዝብ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ አቅርቧል ቢባል እንኳ ህዝቡን ማስረዳት፣ ማሳመንና ወደ ተለመደው ህይወቱ እንዲመለስ ማድረግ ይገባል። የህዝብን ጥያቄ መመለስ ያልቻለ መንግስት ብቃት የለውም፤ ስለዚህ ለመንግስትነት አይበቃም። እናም ስልጣኑ ማስተዳደር ለሚችል አካል ማሰረከብ አለበት። ስለዚህ የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄ እደግፋለሁ። ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝም ጥረት አደርጋለሁ።

የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄ ተገቢ ሁኖ “ወልቃይት የማነው?” የሚለው ጥያቄ ግን አይረባም። “ወልቃይት የማነው?” ስንል “ወልቃይት” ምንድነው የሚወክለው? መሬቱ ነው ወይስ ህዝቡ? “ወልቃይት” የሚለው ቃል ህዝብ የሚወክል ከሆነ ወልቃይት የማነው ? ተብሎ አይጠየቅም። ምክንያቱም ወልቃይት ህዝብ ከሆነ ወልቃይት የማነው? መልሱ ቀላልነው። የወልቃይት ህዝብ ነዋ። ወልቃይት መሬት የሚወክል ከሆነ … መሬቱ የማነው? የወልቃይት ነዋ። ባጭሩ ወልቃይት የማነው? የወልቃይት ነው። ወልቃይት የወልቃይት ነው። የተፈለገው ወልቃይት አማራ ነው ወይስ ትግራይ የሚል ይመስላል። ይህን ጥያቄ የወልቃይትን ህዝብ ራሱ ነው የሚያውቀው።

እንደኔ ግን አማራና ትግራይ አስተዳደራዊ ክልሎች ናቸው። ክልሎች ለአስተዳደር ዓላማ የተዋቀሩ ናቸው። ኣንድ ህዝብ ለአስተዳደር ሲባል ከአንዱ በአንዱ ይሆናል። ክልል አስተዳደራዊ እስከሆነ ድረስ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፤ በአንድ ኢትዮጵያ እስካመንን ድረስ። ትግራይ ይሁን አማራ ኢትዮጵያ ነው። ሌላ ሀገር አይደለም። ስለዚህ የአከላለል ጉዳይ ነው የሚሆነው። ስለ አንድ ኢትዮጵያ የሚያስብ ሰው ስለ ወልቃይት ትግራይ ወይ አማራ መሆን ሳይሆን ስለ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነፃነትና እኩልነት ነው ማሰብ ያለበት።

እናም የወልቃይትን ህዝብ አማራ ወይ ትግራይ ወይ ኦሮሞ ወይ ሌላ መሆኑ ወይ አለመሆኑ አይደለም ወሳኙ ነገር። የወልቃይትን ጉዳይ በሀገራችን የፖለቲካ አጀንዳ ለመሆን ወልቃይቶች ኢትዮጵያውያን መሆናቸው በቂ ነው። ለኔ የማንም ኢትዮጵያዊ ብሄር ኢትዮጵያ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ በነፃነት ሲኖር የፈለገውን ስም ወይ ብሄር ወይ ቋንቋ ወይ ሀይማኖት መያዝ ይቻላል። ስለዚህ ወልቃያት አማራ ወይስ ትግራይ ወይስ ኦሮሞ … የሚለውን አያሳስበኝም። ኢትዮጵያዊ መሆኑ በቂ ነው።

ስለ ወልቃይት የሚያሳስበኝ ቢኖር ህዝብ ጥያቄ ሲያቀርብ አገባብነት ያለው መልስ ያገኛል ወይ? ፍትሕ ያገኛል ወይ? ነፃነት አለው ወይ? ያለ ምንም አድልዎ በእኩልነት ይገለገላል ወይ? መብቱ ይከበርለታል ወይ? ወዘተ የሚል ነው። ምክንያቱም አንድ ህዝብ የሚያስፈልገው ነፃነት ነው፣ ልማት ነው፣ ፍትሕ ነው፣ እኩልነት ነው። እነዚህ ነገሮች ለማግኘት ሀገር ያስፈልገዋል። ህዝባዊ (ዴሞክራሲያዊ) መንግስት ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ነፃነት የሚጠበቀው በሀገር ነው፤ በመንግስት ነው። ህዝብ ነፃነት ካለው የፈለገውን ብሄር ወይ ጎሳ ወይ ሌላ (ከጠቀመው) መሆን ይችላል። ብሄር መምረጥ መብት ነው። የህዝቡ የራሱ መብት። ነፃነትና እኩልነት ከተከበረ የሚጣስ መብት አይኖርምና ነው።

እኔ የመንግስትነት ስልጣን ቢኖረኝ ኑሮ (በህዝብ ከተመረጥኩ ማለቴ ነው) ጥያቄው ከጅምሩ አጠፋው ነበር ወይም እንዳይወለድ አደርገው ነበር። የህዝብን ጥያቄ እንዴት ይጠፋል? እንዳይፀነስስ ይደረጋል? የህዝብን ጥያቄ ማጥፋት የሚቻለው ጠያቂዎቹ በማስፈራራት ወይ በማሰር ወይ በመግደል ወይ በሰልፍ አይደለም፤ ተገቢውን መልስ በመስጠት እንጂ።

አንድን ህዝብ ሲጠይቅ መልስ መስጠት ግድ ይላል። ህዝብ ማስፈራራት፣ ማፈን፣ መግደል፣ ባጠቃላይ የሓይል እርምጃ መውሰድ ጥያቄውን ያባብሳል፣ ያከረዋል እንጂ አይፈታም። ስለዚህ አግባብነት ያለው መልስ በመስጠት የህዝብን ጥያቄ ማጥፋት አልያም ደግሞ የሚጠበቅብህን አገልግሎት ሁሉ በመስጠት ጥያቄው እንዳይፀነስ ወይ እንዳይወለድ ማድረግይቻላል ። ይህን ሁሉ ማድረግ ካልቻልክ ስልጣንህን በአግባቡ አልተጠቀምክንና ለህዝቡ መልሶ ማስረከብ፤ የህዝብ ጥያቄ መመለስ ለሚችል አካል መስጠት፣ ስልጣን ማስረከብ።

ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ በጉልበት መጋፈጥ ጥያቄው ስር እንዲሰድና ከቁጥጥር ዉጭ እንዲሆን በመጨረሻም ዉድመት እንዲያደርስ መፍቀድ ነው። አሁን በወልቃይትና ጎንደር አከባቢ የደረሰው ውድመት የዚሁ የህወሓት የተሳሳተ የህዝብን ጥያቄ በጉልበት የመጨፍለቅ ስትራተጂ የወለደው ነው። ህወሓት የወልቃይትን ጉዳይ በአግባቡ መመለስ ቢችል ኑሮ ይህን ሁሉ ችግርና ስጋት አይፈጠርም ነበር።

የወልቃይትን ህዝብ ችግር መንስኤው የማንነት ጥያቄ ነው ብዬ አላምንም። መነሻው የፍትሕ እጦት ነው። ህወሓት የወልቃይትን ህዝብ (የትግራይን ህዝብ ባጠቃላይ) በድሏል፣ ዓፍኗል። የትግራይ ህዝብ (ትግራይ ክልል ዉስጥ የሚገኝ በሙሉ) በህወሓት ድንቁርና መሰረት ያደረገ ጭቆና ተማሯል። የፍትሕ ችግር፣ የነፃነት ችግር፣ የአገልግሎት ችግር፣ የእኩልነት ችግር፣ የልማት ችግር ወዘተ በመላው ትግራይ ተንሰራፍቷል። ህዝብ አገልግሎት ይፈልጋል፤ ህወሓት ደግሞ ይበዘብዛል። አሰቃቂ ነው። እናም የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄ ማስነሳቱ አይደንቅም። ምክንያቱም በሁሉም የትግራይ አከባቢዎች ተመሳሳይ ቅሬታ አለ፤ የዓድዋ ህዝብ እሮሮ፣ የእምባስነይቲ ህዝብ ጥያቄ፣ የሸኸት (ኣብዓላ) ህዝብ ሽሽት መውሰድ እንችላለን።

የዓድዋ ህዝብ በህወሓት ተማሯል። ግን የት ይሂድ? ትግራይ አይደለሁም ይበል? የእምባስነይቲ ህዝብ አምርሮ አልቅሷል። ምን ያድርግ? ከትግራይ ለመውጣት ይጣር? (የህወሓትን አገዛዝ ለመሸሽ ሲባል)። ግን የዓድዋና የእምባስነይቲ ህዝብ ዶብ አከባቢ ስለማይገኝ ወደ ሌላ ክልል አዛውሩኝ አላለም። የሸኸት ህዝብ ከዓፋር ክልል ጋር ስለሚዋሰን ከዓፋር ክልል ጋር ይሻለኛል ብሎ ክልሉን ቀይሮ “ኣብዓላ” ተብሎ ዓፋር ክልል ዉስጥ የሚኖረው ትግራይ ስላልሆነ አይደለም። የህወሓትን አገዛዝ ስላልፈለገ ነው። እናም ከትግራይ ጋር መሆን አልፈልግም የሚል ሁሉ ትግራይ ስለሆነ ወይ ስላልሆነ አይደለም። የህወሓትን አገዛዝ ስላንገሸገሸው ብቻ ነው።

የወልቃይት ጉዳይም የአስተዳደር ጉዳይ እንጂ የብሄር ጥያቄ አይደለም። ስለዚህ የወልቃይት ህዝብ ከአማራ ክልል ጋር ብሆን እመርጣለሁ ካለ ትግራይ ውስጥ ያለው ስርዓት አልፈልግም እያለ እንጂ ሌላ አይደለም። የወልቃይትን ህዝብ የፈለገው ብሄር ይሁን ሌላ ትግራይ ክልል ዉስጥ ዴሞክራሲ ቢኖር ኖሮ ይህን ጥያቄ አያነሳም ነበር። ምክንያቱም እንበልና “ወልቃይት አማራ ነው” ወልቃይት አማራ ሁኖ ትግራይ ውስጥ መኖር አይችልም እንዴ? ትግራይ ሁኖ ኦሮምያ ውስጥ ይኖር የለምዴ? አማራ ሁኖ ኦሮምያና ደቡብ የሚኖር የለም? በትግራይ ክልል ለመኖር ትግራይ ብቻ መሆን አይጠበቅብህም። ኢትዮጵያዊ መሆን በፈለከው የኢትዮጵያ ክልል ለመኖር ያስችላል፤ የሚፈለገው ነፃነት ነው፣ እኩልነት ነው፣ ዴሞክራሲ ነው፣ ልማት ነው፣ ፍትሕ ነው። ስለዚህ የብሄር ጉዳይ ወሳኝ አልነበረም።

ግን የኢህአዴግ መንግስት በስልጣን ለመኖር ሲል “የከፋፍለህ ግዛ” ስትራተጂ በመከተል በሄር በመለያየት፣ የተለያየ ስም በመስጠት፣ መሬት ለብሄር በማወጅ ሁላችን እርስበርስ እንድንጠራጠርና እንድንጋጭ ጥረት በማድረጉ ምክንያት እነዚህ ችግሮች ተፈጥረዋል። የወልቃይት ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ እንዲኖር ስላልተደረገ፣ መሬት ለግለሰብ ሳይሆን ለብሄር ስለተስጠ እነሆ በመሬት ጉዳይ ችግር እየተፈጠረ ይገኛል።

የወልቃይትን ጉዳይ ለመፍታት መንስኤው ማየት አለብን። መንስኤው የፍትሕ ችግር ነው። ፍትሕ የለም። አገልግሎት የለም። የመሬት ጉዳይ ነው። መሬት የሀገርና የግለሰብ መሆን ሲገባው የብሄር (የክልል) ነው ተባለ። ይባስ ብሎም መሬት የመንግስት ሆነ። መሬት የመንግስት በመሆኑ ህወሓት የፈለገውን መሬት ከአርሶ አደሮች እየነጠቀ ለሚፈልጋቸው ካድሬዎች መስጠት ሲጀምር ከህዝብ ተቃውሞ ተነሳ። ችግሩ ከመፍታት ይልቅ ሰልፍ እየጠሩ ህዝብን ማስፈራርት ጀመሩ። ጥያቄው ሲባባስ የህዝብን ተወካዮች ማፈንና ባለሃብቶች መግደል ተጀመረ። አሁን ጥያቄ አንስተው ወደ ከፋ ችግር ገባን። የወልቃይት ህዝብ ኮሚቴ አባላት ከብአዴን ኢህአዴግ ጎን ተሰልፈው የሚገኙ ከህወሓት የተሳሳተ የዓፈናና የግድያ ስትራተጂ ለማምለጥ ሲሉ እንደሆነ መረጃ አለኝ።

ስለዚህ የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ የህወሓት የተሳሳተ አሰራር ነው። ሁሉም በጉልበት ለመፍታት መሞከሩ ነው። ጉልበት ችግርን ያባብሳል እንጂ መፍትሔ ሁኖ አያውቅም። ስለዚህ የህወሓት ካድሬዎች ይህንን የህወሓት ስትራተጂ እንደማያዋጣ ተገንዝባቹ ህዝብን ለማዳን ከህዝብ ጎን ተሰለፉ። ህወሓት በተሳሳተ መንገድ ላይ ነው የሚገኘው። ህወሓት ለማንም መድሓኒት ሊሆን አይችልም። ህወሓት ጥፋት ነው። ይሄው እያጠፋ ነው። አንድ የፓርቲ አባል የፓርቲውና የህዝብ ፍላጎት ካልተጣጣመ ከህዝብ ጋር መወገን አለበት። የወልቃይት ጉዳይም በዴሞክራሲ ነው የሚፈታው። ህወሓትን የህዝብን ጥያቄ መመለስ ስላቃተው ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ አለበት።

የወልቃይት ጉዳይ የማንነት ጥያቄ መስሎ የቀረበው መፍትሔ ባለማግኘቱ እንጂ ወደዛ የሚያደርስ አልነበረም። ምክንያቱም ወልቃይት የፈለገው ብሄር ቢመርጥ (ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለ ድረስ) የግጭት መንስኤ መሆን አልነበረበትም። የወልቃይት የማንነት ጉዳይ ምልክት እንጂ መንስኤው አይደለም። ትኩረታችን መንስኤው ላይ መሆን አለበት።

በህወሓት ኢህአዴግ አገዛዝ ትግራይ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይደለችም። ትግራይ በህወሓት ዘመን ተጠቃሚ ብትሆን ኖሮ ከትግራይ ጋር ለመተዳደር የሚፈልግ እንጂ ከትግራይ ለመውጣት የሚጠይቅ ህዝብ ባልኖረ ነበር። ምክንያቱም የትግራይ ክልል ተጠቃሚ (በልማት፣ በዴሞክራሲ ወዘተ) ብትሆን ወልቃይት ይሁን ሌላ ትግራይን ይፈልግ ነበር። እናም ወልቃይቶች ጥያቄ ማስነሳታቸው አይገርመኝም።

ትግራይ ከህወሓት ያገኘችው ጥቅም የለም። እናም ህወሓት ቢቀየር ትጠቀም እንደሆነ እንጂ አትጎዳም። ምክንያቱም የሌለው ምንም አያጣም። ግፋ ቢል መጥፎ አገዛዝ በህዝባዊ አስተዳደር ቢቀየር ነው።

የህዝብና የፓርቲያችን ፍላጎት ቢጋጭ ከህዝብ ጋር እንሰለፋለን። ህዝብ ከፓርቲ ይቀድማል። ምክንያቱም መነሻችንም መድረሻችንም ህዝብ ነው።

It is !!!

Filed in: Amharic