>
4:38 pm - Saturday December 1, 3404

የማለዳ ወግ...ማስተዳደር አልቻላችሁም፣ ኢትዮጵያን ልቀቋት! [ነብዩ ሲራክ]

ማለዳ ወግ…ማስተዳደር አልቻላችሁም፣ ኢትዮጵያን ልቀቋት!
* ግፍ ሲያንገሸግሽ…ማነው የተጋድሎው ባለቤት ?
* ሀገሬው ከላዩ ላይ ያሽቀነጠረው ፍትሐት …
* የሃገርና የወጣቱን ተስፋ እያጨለማችሁ ነው !
* ኢትዮጲያ የወጣቱ ናትና እባካችሁ ልቀቋት!
* ኢትዮጵያን ታደጓት …

ግፍ ሲያንገሸግሽ …ማነው የተጋድሎው ባለቤት ?

yemaleda weg...by Nebiyu Sirakወደድንም ጠላንም ሃገራችን ኢትዮጵያ ሰማይ ስር ላለፉት ጥቂት አመታት ህዘብ በገዥው የኢህአዴግ መንግሰት ለመምራት ፍላጎት አለማሳየቱ በተለያየ መንገድ ተገልጿል ። የሰማ ግን አልነበረም … ህዝባዊ እምቢተኝነት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአብዛኛው ኦሮሞያ ተመልክተናል ። የዚህ ተቃውሞ ባለቤት በመሬቱ ነዋሪ ህዝቡ እንደሆነ ጭብጥ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል ። ተቃውሞውን መልክ ለማስቀየር ሚኒሶታ ሆኖ መረጃ በሚያቀብለው ፖለቲከኛ ጃውሃር መሐመድ የሚመራ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ባይ ነኝ። መብት ጠያቂው ህዝቡ ነውና !

ሀገሬው ጭቆናው ፈንቅሎት ” እንቢ ” ማለቱን በመረጃ መረቡ ከምቃርመው መረጃ ባለፈ የእንቅስቃሴው እማኝነት ከቀናት በፊት በአንድ የሳውዲ ክፍል ያገኘሁት ወንድም አጫውቶኛል ። ከኦሮሚያ ክልል ሸሽቶ ከሳውዲ ኮረብታማ ክፍል ከጣይፍ 80 ኪሎ ሜትር በሚገኝ ገጠር በቀን ስራ ተሰማርቶ የሚገኝ ወንድም በተቀሰቀሰው አመጽ ውስጥ አልፎ ወደ ሳውዲ ያሰደደው እስር ግርፋቱን ሸሽቶ መሆኑን አልደበቀኝም ። ይህን ወንድም በቅርብ ስለሚያውቀው አመጻና እምቢተኝነት ጠይቄው ” ሰው በቅቶታል ፣ ማንም ሳይለው ችግሩ ነው ለአመጽ ያነሳሳው ፣ ጭቆናው በዛበት ” ነበር ያለኝ ! እናም ወጣቱም ከመሳደድ መታሰር መገደሉ ስደት ተሽሎታል ! ሲናገረው ያማል … በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው አመጽ ከ400 በላይ የሰው ክቡር ህይወት ተቃጥፏል ፣ በሽዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል ፣ በሽዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል ፣ ተሰደዋልም ፣ እውነቱ ይህ ነው ! የኦሮሞው ተቃውሞና አመጽ ” በመልካም አስተዳደር ” ምክንያት ነው ብሎ የማስተንፈሻ ተደጋጋሚ መግለጫ የሰጠው መንግሥት ” ጥቂት ጸረ ሰላሞች ” የፈጠሩት ነውጥ እንደሆነ በመግለጽ ግድያ እስራትና ማሳደዱን ህጋዊ ለማድረግ ዳድቷል …

ሀገሬው ከላዩ ላይ ያሽቀነጠረው ፍትሐት …

ለአመታት የተካሔደው የሙስሊማን መብታችን ይከበር ጥያቄ ስልቱን እየቀያየረ ቀጥሎ ላንድ አፍታ ተቃውሞው ጋብ ሲል የኦሮሚያ አመጻ በእጅጉ አገረሸ ። ቀጠለና የአማራው ተጋድሎ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ታጅቦ ብቅ አለ ። የማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ተወንጅለው ለመያዝ በተደረገው ሙከራ ተጋድሎው አጠያያቂና የንጹሃንን ሕይወት ቀጥፎ አመጽ እንቢተኝነቱ በመላ አማራ እየተሰራጨ ይገኛል ። ይህም አሜሪካ ሜሪላንድ አለያም ፊንላንድ ያለው መረጃ አቀባይ በወዳጃችን ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው የሚዘወር አይደለም ። ሰውን በግል ለማግኘትና ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ በኢህአዴግ / ህወሓት ወገንተኛ አገዛዝ ተማሯል ። በቃ እውነቱ ይህ ነው !

ዛሬ በመላ ሃገሪቷ በሚባል ደረጃ በኦሮሚያና በአማራው ተጋድሎ ገፋኤነት የህዝቡ ፍላጎት በአደባባይ እየተሰማ ፣ እየታየ ነው ! የታመቀው ብሶት የወለደው አመጻ ፍርሃትን አሽቀንጥሮ ጥሎታል ። በተለይም ወጣቱ በአማራ ተጋድሎ ባሳየው ቁርጠኝነት የታየበት ሰላማዊ ሰልፍና ተጋድሎ ከሚወዳት አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዴራው ጀምሮ የተለያየ ጥያቄዎችን እና ፍላጎቱን በአደባባይ ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ በድፍረት እያሳየ ነው ። ከዚህ ቀደም በሚወዳት ሐገሪቱ ጉዳይ ደፍሮ እንዳይናገር እስር ፣ ግርፋት፣ ግድያን ይፈራ የነበረው ወጣት ትኩስ ሐይል ዛሬ ፍርሃቻን በድፍረት ሰብሮ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን እያሰማ ነው! ብቻውንና ጓዳ ለጓዳ ሲያንሾከሽከው የባጀውን ፍላጎት፣ የመብትና የማንነት ጥያቄ ይከበርለት ዘንድ ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ በሰላማዊ ሰልፍ በአደባባይ ተቃውሞውን እያሳየ ነው !

ጥያቄው የሚቀርብላቸው የመንግሰት ባለሥልጣናት ግን የአይፈሬውን ወጣት ቁርጠኝነት በጠመንጃ ለማንበርከክ አልሰለቻቸውም ። የህዝቡን አመጽ እንዳሻቸው ከአሸባሪና ነውጠኛ ጋር እያላከኩ ብዝሁን የሀገሬ ጥያቄ የ “ጥቂት ነውጠኛና አሸባሪዎች! ” እያሉ ማለገጥ ይዘዋል ። መሪዎቻችን ዛሬም ከቀደመው አልተማሩም ፣ መብቱን ለማስከበር ክቡር ህይዎቱን እየከፈለ ባለው ሰማዕት ደም እየተከፈለ ያለውን መራራ መስዋዕትነት በማጣጣል ከእውነት ጋር ተጣልተው የህሊና ቢስ ሙግት ይዘዋል !

ኢትዮጵያን ልቀቋት …

yemaleda weg...by Nebiyu Sirak1jpgዛሬ ማለዳ ከህወሓት መንደር ስለሚሆነው ብርቱ መረጃዎችን የሚያገኘው በጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሃኔ የሚዘጋጀው HornAffairs ገጽ ላይ አንድ መጣጠፍ አነበንኩ ። ርዕሱ ” ኢትዮጵያ የማን ናት ? የወጣቱ ወይስ የባለሥልጣናት? ” ይላል ። በቀረበው መጣጥፍ በርካታ ቁምነገሮች ታጭቀዋል ። ከቁምነገሮች ከፍ ሲል ያስደሰተኝ ለወቅቱ መሪዎች የተላለፈው መልዕክት ሲሆን ይህም ከመደምደሚያው ላይ ይገኛል ! እንዲህ ይላል …

” በአጠቃላይ፣ ከዚህ በኋላ ሀገሪቷንና ህዝቧን በበቂ ሁኔታ ለማስተዳደር የሚያስፈልገው ብቃት እና አመለካከት የላችሁም። ምክንቱም፣ እናንተ በስልጣን ላይ ያላችሁ አብዛኞቹ የቀድሞ ትውልድ አባላት፤ ብዙ ነገር አታውቁም፣ አለማወቃችሁንም አታውቁም፣ ያላወቃችሁትን ነገርም ማወቅም አትፈልጉም። ለምሳሌ ዴሞክራሲን በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ እንጂ በተግባር አታውቁትም። በንድፈ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተው እውቀትና ግንዛቤ ሕገ-መንግስትን ከማፅደቅ ያለፈ አልሄደም። በዚህ ምክንያት፣ አዲሱ ትውልድ ስርዓቱን በኃይል መናድ ይቅርና እናንተ ያወጣችሁትን ሕገ-መንግስት ለማክበርና ለማስከበር እንኳን እድል አልሰጣችሁትም። “ሕገ-መንግስቱ ይከበር” ብሎ የወጣ ወጣትን “ፀረ-ሰላም እና ፀረ-ልማት” እያላችሁ ለሞትና እስር እየዳረጋችሁ የሀገሪቷንና የትውልዱን ተስፋ አያጨለማችሁ ነው። እስካሁን ላበረከታችሁት አስተዋፅዖ እናመሰግናለን። በዚህ አያያዛችሁ ከ25 ዓመት በፊት የተረከባችኋትን ሀገር እንደነበረች መልሳችሁ እንደምታስረክቡን ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ፣ ኢትዮጲያ የወጣቱ ናትና እባካችሁ ልቀቋት! ” የሚል ሁነኛ ምክር ይዛለች ! ወድጃታለሁ ! ይህችው ” ኢትዮጵያ የኛን ናት ? ” በሚል ርዕስ ስር በዳንኤል ብርሃነ በምትመራው Horn Affairs ገጽ ላይ የተላለፈች መጣጥፍ ” ጌቶች ሆይ ማስተዳደር አልቻላችሁም ቦታውን ለሚያስተዳድረው ልቀቁ !” ብርቱ ወቅታዊ ምክርን ውሃ ታነሳለችና ጀሮ ያለው ይስማ !

ኢትዮጵያን ታደጓት …

እኔም ስለሀገሩ እንደሚያገባው ዜጋ እንዲህ አላችኋለሁ ፣ ትልቅ ሐገርን እና ትልቅ ህዝብን በጫካ ህግ ማስተዳደር ይብቃ ! ህዝብ ደጋግሞ የጠየቃቸው ጥያቄዎችን በማናናቅ በነቂስ የወጣው ብዝሁን ህዘብ ” የጥቂት አሸባሪ ነውጠኞች ሴራ ነው! ” እያሉ ማላገጥ ለሃገራችን አይበጅም ! እንኳንስ የአንድ ሐገር ህዝብ በገሃድና በአደባባይ በቃኝ ብሎ የአንድ ቀበሌ ነዋሪ ሲከፋውና ሲያምጽ ጥያቄውና ጉዳዩ በመንግሥት በኩል በውል ሊጤንና መልስ ሊሰጠው ግድ ይላል ! ይህ ባለመሆኑ በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደቀደመቀው ሁሉ ለማንም ግልጽ የሆነ ሰብአዊ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየታየ ነው ፣ ግፍ በዝቶና ገኖ ስለ ልማትና ዲሞክራሲ መደስኮር ማደናቆር ብቻ ነው ፣ ሰልፍ የወጣ ሰላማዊ ሰልፈኛን በባሩድ መቁላት ፣ መደብደብ ማሰርና ማሳደድ አመጻውን ይበልጥ ያጋግለዋል እንጅ አያበርደውም ፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም ሐገር ናት ፣ አድልኦ ይቁም ፣ ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ ብሎ መጮሁ ድካም ሆኗል ! መፍትሔው በገዥው መንግሥት ቀራቢና ውስጥ አዋቂቀረ በጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሃነ ድረ ገጽ ላይ የቀረበውን እውነት መቀበል ብቻ ነው ! አዎ እኔም እደግመዋለሁ … ሐገር ማስተዳደር አልቻላችሁምና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሽግግር መንግሥት በማቆም በትረ ሰለሞኑን በህዝብ ለሚመረጥ መንግሥት በማስረከብ ኢትዮጵያን ታደጓት እላለሁ !

ኢትዮጲያ የወጣቱ ናትና እባካችሁ ልቀቋት!
.
ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓም

Filed in: Amharic