>

የት ናችሁ የትግራይ ልሂቃን? [ከአንተነህ መርዕድ]

Deadly Protests Grip Ethiopia as UN Calls for an Independent Investigation photo - care2በስማችሁ የተደራጀው ዘረኛና ዘራፊ ቡድን የንፁህ ኢትዮጵያን ልጆች ደም እንደጎርፍ ሲያፈስስ ምነው ድምፃችሁ ጠፋ?
የኦጋዴኖች መጨፍጨፍና ሬሳቸው በሜዳ ላይ መጎተት፣ የጋምቤላዎች በጅምላ መታረድ፣ የኦሮሞዎችና የአማራዎች በጠራራ ፀሃይ በአነጣጥሮ ተኳሽ ትግርኛ ተናጋሪ አጋዚ በየሜዳው መደፋት እንዴት ህሊናችሁን አልኮሰኮሳችሁም?
በጣት የሚቆጠሩ ዘራፊዎች ነገን አጨልመውባችሁ ሊሄዱ ሲዘጋጁ እንዴት አልታያችሁ አለ?
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ህልውናውን እንዲያጣና የግፍ ፅዋ እንዲጨልጥ የተገደደው መላው ኢትዮጵያዊ፤ “ከዚህ በኋላ በቃኝ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነፃነቴን ማግኘት አለብኝ” ብሎ መንቀሳቀስ መጀመሩን ዓለም ሲመሰክር እንዴት አልከሰትላችሁ አለ?
እስከአሁኗ ደቂቃ የኢትዮጵያ ህዝብ እባካችሁ በፍቅርና በእኩልነት እንኑር እያለ የሚያሰማው ልመናና ጩኸት ላለማስማት ምን አገዳችሁ?
ይህ ዘራፊና ዘረኛ ቡድን በስልጣን ለመቆየት ከሁሉም በላይ በትግራይ ህዝብ ዘላቂ ህልውና ላይ እንደዘመተበትና የእሱን ሃጢያት እዳ ከፋይ ሆኖ እንዲኖር እንደፈረደበት አይታታችሁም?
ከሚሞት ጥቂት የአምባገነን ቡድን ጋር በማበራችሁና ዝምታን በመምረጣችሁ እንዴት የዋህና ድሃ የትግራይ ህዝብ ሲጎዳ አልታያችሁ አለ? ህወሃት የትግራይን ህዝብ ጥቅም በዘላቂው እንደጎዳ ለመናገር አንደበታችሁን ምን ዘጋው?
አዎ! ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለየ የሥራ መስክ ተከፍቶላችኋል። ሁሉንም የአገሪቱን ሃብት፣ መከላከያውን፣ ደህንነቱን ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረው ቡድን ተጠቃሚ ሆናችኋል። ለመማርና ሳትማሩም ለትልልቅ የጥቅም ቦታዎች ያለገደብ ተሳታፊ እንድትሆኑ ተመቻችቶላችኋል። ሌላው ሲገደል፣ ሲታሰር፣ ሲዘረፍና አገሩን ጥሎ ሲሰደድ ሁሉም በር በሞኖፖል ተከፍቶላችኋል። ነገር ግን ምስኪኑ በሚሊዮን የሚቆጠረው የትግራይ ህዝብ በድህነት እያለ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር የሚኖረውን ዘላቂ ጥቅሙን በጊዜያዊ ድሎታችሁ ነግዳችሁበታል።
በአጋዚ አልሞ ተኳሽ ህፃናት ኢትዮጵያውን ሲደፉ፣ ህዝቡ ሃዘን ውስጥ ተቀምጦና ዓለም ያየውን ዘግናኝ ነገር ለማመን እስኪቸገር ሲያዝን ውስኪ እየተራጫችሁ ስትጨፍሩ በምትደልቁት አተሞ ስትደነቁሩ፣ ወይም እንዳላያችሁ ፀጥታን ስትመርጡ፤ እንኳንስ የትግራይን ህዝብ የራሳችሁንም ቀጣይ ጥቅም በሚያስዘነጋ የቅዠት ዓለም ውስጥ መሆናችሁ እየታየ ነው።

በህወሃት የቅዠት ዓለም ውስጥ ሳይሆን እውነተኛዋን ትግራይን ተመልከቱ፡

• በብዙ ሺህ ኪሎሜትር ከሚዋሰነው፣ ለዘመናት አብሮት ከኖረው፣ ከተዋለደው ከተዛመደው ከወንድሙ ከኤርትራ ህዝብ አቆራርጠውታል።
• ከላይ ከጎንደር፣ ወሎና አፋር ድረስ በዘረኝነት በተሞላው ስግብግብነትና ትዕቢት ከአማራው፣ ከአገው፣ ከአፋሩ ደም አቃብተውታል።
• ከሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ንብረቱንና የልጆቹን ህይወት በመንጠቅ ለያይተውታል።
• ጋምቤላዎችን በማጨፋጨፍና በመጨፍጨፍ፣ መሬቱን በመዝረፍና ለውጭ ባለሃብቶች በመሽጥ አስሰድደውታል።
• ኦጋዴንን ህዝብ በጅምላ ገድለውታል፤ በርሃብ ዓለም እንዳይደርስለት ቀጥተውታል።
• መሃል አዲስ አበባና ዳር ለዳር የሚኖረውን ድሃ ህዝብ አፈናቅለው ሜዳ ላይ በመጣል እነአቦይ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ገንብተውበታል።
• በዓለም ዙርያ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የህወሃት የግል ቢሮና የአንድ ዘር ተጠቃሚነትን በግልፅ በማወጅ ቀሪውን ኢትዮጵያዊ አግልለውበታል።
ይህ ሁሉ ግፍና ያልተዘረዘረው ወንጀል ምን ያህል ጊዜ ይዘልቃል ብላችሁ ብታስቡ ነው ማዕበሉን ላለማየት አሸዋ ውስጥ እራሷን እንደቀበረችው ሰጎን በጊዜያው ጥቅም ውስጥ ራሳችሁን ደብቃችሁ በማስገምገም ላይ ያለው ህዝባዊ ማዕበል አልታያችሁ ያለው? ከሁሉም የተነጠለች ትግራይ ዕድሏ ከሱዳን ጋር ብቻ እንዲሆን ወሰናችሁ ማለት ነው? የሚቻል አይደለም።
ከሃያ ዓመት በፊት ጥቂት ትዕቢት በወጠራቸው የሻዕብያ ሰዎች ኢትዮጵያውያንን የመናቅ፣ በሃብት በንብረቷ አዛዥና ናዛዥ መሆናቸው እንዴት እንዳሳወራቸው ትምህርት የሚሆነን ይመስለኛል። የኤርትራ ኤምባሲ እንደማዕከላዊ ይፈራ ነበር።የራሱ እስር ቤትና ማሰቃያ ነበረውና። “አፍሪካዊት ሲንጋፖር” የምትሆነውን ኤርትራን ለመገንባት ያለሙት ግን በኢትዮጵያ ጥሬ ሃብትና ገበያ ላይ ነበር። ቅዠት እውነት አይደለምና ከእንቅልፋቸው ሲባንኑ ወንድሞቻችን ኤርትራውያንም እኛም አሁን ካለንበት እንገኛለን። የዘሩትን ማጨድ ይሏል ይህ ነው።
የመከላከያው ተቋም ተነቃቅሎ ትግራይ ተገንብቷል። ብዙ ትልልቅ ነገሮች ከመሃል አገር እየተነቀሉ ወደትግራይ የመሄዳቸው ጉዳይ “በጠላት” የሚነገር ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን የአለፉት ሃያ ዓምስት ዓመታት እውነታ ሲሆን በትናንቱ ዜና ደግሞ የቴሌኮሙኒኬሽን የመረጃ ቋት (ዳታ ሲስተም) ከአዲስ አበባ ተነቅሎ መቀሌ መተከሉ ስንሰማ የህወሃትን የዕብደት መጠን ከመግለፅ ባሻገር እንግዳ ባህሪ አያደርገውም። አፍ የሚችለውን እጅ ይመጥናል ይባላልና ህወሃት ግን መዋጥ የሚችለውን አይደለም እያነሳ ያለው። ይልቅስ የስስታም መጨረሻው በጎረሰው ታንቆ መሞት ነውና እናየዋለን። ለመሆኑ ለይስሙላ የተቀመጡት የፌደራል ባለስልጣናት እነኃይለማርያም ዋና ከተማቸውንም መቀሌ እስኪሆን ነው የሚጠብቁት?
እዚህ ላይ ህዝቡ በትዝብት የገጠማትን ላካፍላችሁ።
የሚጓጓዝ ቢሆን ሁሉም በመኪና
ትግራይ ውስጥ ነበሩ አባይና ጣና። ብለዋል።
ግድ የለም ፋብሪካውም ይሂድ፣ ሁሉንም የቻሉትን ይውሰዱ። በቅዠት ዓለም ውስጥ የሚያልሟት ትግራይ አየር ላይ ነው የምትገነባው? ጥሬ እቃው፣ የሃይል አቅርቦቱ፣ ገበያው ከየት ነው? በስልጣን ጥም የተመረዙ ህወሃቶች ይህ ሁሉ እንደማይሳካ ቢያውቁትም የትግራይን ህዝብ እንደሰባዊ ጋሻ መያዣነት ለመጠቀም ነው። ለእውነተኛ የትግራይ ዘላቂ ልማት ቢያስቡት ከኢትዮጵያ ህዝብ ተለይቶ ከቶም የትግራይ ህዝብ ሊያድግ አይችልም። ከገፉበትና ድጋፍ ካገኙ ለታሪክ የሚተው ፀፀት የሚያስይዝ ህንፃ ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው። ለመሆኑ የትግራይ ልሂቃን ይህ እንዴት ይጠፋችኋል? ብቸኛ ተጠቃሚነታችሁ ምን ያህል ይዘልቃል ብላችሁ ታስባላችሁ? ለአፈራችሁት ሃብትና ቤተሰብ ዋስትና የሚሰጣችሁ የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ የሚሞት ስርዓት አይደለም።
የስብሃት ነጋ፣ የአባይ ወልዱ፣ የስዩም መስፍን፣ የአባይ ፀሃዬ፣ የአዜብ መስፍን፣ የብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ የቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ምን አለፋችሁ የትልልቆቹ ህወሃት ባለስልጣናት በቢልዮን የሚቆጠር የዘረፉት ንብረትና ቤተሰባቸው ውጭ ነው ያለው? ለምን ትግራይ ውስጥ ያንን ሃብት አላፈሰሱትም? እንደመንግስቱ ኃይለማርያም የዘረፋና የወንጀሉ ተባባሪ ጓዶቻቸውን ጥለው እብስ ለማለት ዝግጁ ናቸው። ውሃ ሃጅ ደንጋይ ቀሪ እንደሚባለው የስርዓቱ ተባባሪ ሆናችሁ ያስገደላችሁና ያስዘረፋችሁ እንደነለገሰ አስፋው ጎርፉን መጠበቅ ሊኖርባችሁ ነው። የዚች አገር ታሪክ እንደሆነ ራሱን የሚደጋግም ነው። ህወሃቶች ለአፈሰሱት የንፁሃን ደም፣ ለዘረፉት ንብረት፣ ለአደረሱት ሰቆቃ እዳ ከፋዩ እዚያው ይቀራል። የትግራይ ልሂቃንና የትግራይ ህዝብ በፍጥነት ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ካልቆመ የሚመጣውን ጉዳት ማሰቡ ያስፈራል።
ኦሮሞው፣ አማራው፣ ሶማሌው፣ ደቡቡ፣ ጋምቤላው፣ መሃል አዲስ አበባ፣ በአጠቃላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዘረኛውና ዘራፊው ህወሃት ላለመገዛት መቁረጡና መንቀሳቀሱ ካልተሰማችሁ መልካም እንቅልፍ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ የከፋ ምንም አይደርስብኝም ብሎ ተነስቷል። ኳሷ እጃችሁ ላይ ናት። ውጤቱም እንደምርጫችሁ ይወሰናል። ፈጥናችሁ የትግራይንና የኢትዮጵያ ህዝብ ካንጃበበት መከራ ለመታደግ የትግሉ አካል ሁኑ። ህዝቡ እያለቀሰና እየጮኸ በዝምታችሁ ከቀጠላችሁ እናንተ ስታለቅሱ ሌላው በዝምታ የሚታዘባችሁ ቀን ተቃርቧል። ልቦና ይስጣችሁ።
ኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጆቿ ይታደጓታል!
መከራው በትግላችን ያበቃል!

Filed in: Amharic