>
2:41 am - Monday July 4, 2022

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማሪያም ደሳለኝ [ፓስተር ያሬድ ጥላሁን]

 
Yared Tilahunይህን ደብዳቤ የምጽፍሎት ሰው ያሬድ ጥላሁን እባላለሁ። የወንጌል አገልጋይ ነኝ። ከጌታ ምሕረትን ተቀብዬ ላለፉት 27 ዓመታት ዘር፣ ጎሣ፣ ቀለም፣ ጾታ፣ እምነትና የፖለቲካ አመለካከት ሳልለይ ለትንሽ ለትልቁ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስሰብክ የኖርኩ ነኝ። ዛሬ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍሎት በልብ ጭንቀትና በብዙ ዕንባ ነው። ከሰሞኑ በእርሶ አንደበት የተነገረውንና የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ የሚፈቅደውን ንግግር አድምጫለሁ። ከተቀመጡበት ወንበር ግዝፈትና በዙሪያዎ ከከበቦት ውጥረት አንጻር የገቡበትን አስጨናቂ ሁኔታ ለመረዳት እሞክራለሁ። የሚወስኑትም ውሳኔ በግል የእርሶ ብቻ እንዳልሆነና አንዳንድ ጉዳዮች ከዐቅሞት በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምታለሁ።
ሆኖም በአንደበትዎ የተነገረውና በታሪክ መዝገብ ተቀርጾ የሚኖረው ይህ ውሳኔዎ በእግዚአብሔር፣ በሰውና በኅሊናዎ ዘንድ ከፍተኛ ተጠያቂነት እንደሚያመጣብዎ ሳስብ ከልብ አዝናለሁ። እርሶ በእግዚአብሔር ምህረት የተፈጠሩ፣ በምሕረቱ ያደጉና አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ የኃላፊነት ሥፍራ የበቁ መሆንዎን በሚገባ ያውቃሉ። ይህን ለእርስዎ የተሰጥዎትን የመኖር መብት ለሌሎች ይነፍጋሉ ብዬ አላስብም። ሆኖም አሁን በእርሶ መሪነት በገዛ አንደበትዎ የተሰጠው ይህ ውሳኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምትክ የማይኖራቸው ኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ሞት የሚያጠላ ነው።
ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ብሎ አደባባይ ሲወጣ፣ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘሁም፣ እንዳልናገር ታፍኛለሁ ብሎ እምቢተኝነት ሲያሳይ የተለያዩ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን በማፈላለግ ሕዝብን ማረጋጋት የመንግሥት ባሕሪ ነው። ይህ ዛሬ ድምጹን ለማሰማት በየሥፍራው እንደ አሸን የፈላው ሕዝብ ላለፉት 25 ዓመታት ለኢሕአዴግ አመራር ጸጥ ለጥ ብሎ የተገዛ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ባረፉ ጊዜ ዕንባውን የረጨ፣ ደረቱን የደቃ ሕዝብ ነው። የፍትሕ ዕጦትና የመድልዎ ብሶት አንገሽግሾት የሚሰማኝ መንግሥት አለ በሚል አደባባይ ቢወጣ እንደ እባብ ተቀጥቅጧል፣ ተዋክቧል፣ ታስሯል፣ ተሰዷል፣ ተገድሏል። ለዚህ እውነታ ማስረጃ ማቅረብ የሚገባኝ አይመስለኝም፤ እርሶም አጥርተው እንደሚያውቁት አልጠራጠርም።
“በቁስል ላይ ዕፀጽ” እንዲሉ አሁን በኢሕአዴግ ጉባዔ የተወሰነውና በእርስዎ ትዕዛዝ የተንቀሳቀሰው ኃይል ጉዳዩን ወደ ከፋ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውና በብሔሮች መካከል የማይሽር ጠባሳ እንደሚያሳድር እርሶዎንም በእግዚአብሔርና በሰው፣ በታሪክና በሕሊናዎ ተወቃሽ እንደሚያደርግዎ በብዙ ትህትና መግለጽ እወዳለሁ።
አሁንም ጊዜው ሳይመሽ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ላይ እንዲተኮር፣ የኃይል እርምጃው እንዲቆም፣ ተዓማኒ እርምጃዎች እንዲወሰዱና ሌሎችንም ያሳተፈ አገራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ አቅምዎ እሰከሚፈቅድ የበኩሎትን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ፤ ይህንንም ማድረግ ካልቻሉ ከሚፈሰው የንጹሐን ደም እጅዎን እንዲያነጹ ሰውን በመልኩና በምሳሌው በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ስም እማጸኖታለሁ።
 
የጌታ ጸጋ ከእርስዎ ጋር ይሁን! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic