>
4:53 pm - Saturday May 25, 7833

አንዷለም አራጌና እስክንድር ነጋ እንዲሁም አበበ ቀስቶ የርሃብ አድማ ጀመሩ

ከያሬድ አማረ

Andualem-Eskindir-300x165Abebe Kestoኢትዮጵያውያን ከምንኮራባቸው ታሪኮቻችን አንዱ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር አለመውደቃችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ የነበሩ አያሌ የአፍሪካ ሀገሮች እንኳ የቅኝ ገዥዎችን ቀንበር ብቻ ሳይሆን የየሀገሮቻቸው አምባገነኖች የጫኑባቸውን የአገዛዝ ቀንበር ጭምር ሰብረው ዴሞክራሲያዊ አገር ለመፍጠር ችለዋል፡፡ በአንፃሩ ግን ኢትዮጵያችን በዓለማችን ከሚገኙ ጥቂት የአፈና ደሴቶች አንዷ በመሆን ትታወቃለች፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በበለጠ የተጫነባቸውን የአገዛዝ ቀንበር ለመስበር በኦሮሚያ፣ በጎንደርና ጎጃም እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁንእንጂ ኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው መጠየቃቸው ስርየት እንደሌለው ሃጢያት ተቆጥሮባቸው በየቀኑ በስርዓቱ አልሞ ተኳሾች እንደ አውሬ እየታደኑ መገደላቸውን ስንሰማ ጥልቅ ሀዘንና ከፍተኛ ቁጭት አድሮብናል፡፡

እስከዛሬ ድረስ ከጨፍጫፊው ደርግ በመራራ ትግል ነፃ እንዳወጡን ሳይታክቱ የሚደሰኩሩት ገዥዎች ንፁሃን ዜጎችን በመጨፍጨፍ ተመሳሳይ ወንጀል እየሰሩ ነው፡፡ የአገዛዙ የእስካሁን ታሪክም ሆነ እስካሁን የሄደበት ያለው መንገድ የሚነግረን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት የሚገነባው በኢህአዴግ መቃብር ላይ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን እየተጋፈጠ ያለው ችግር ከ50 ዓመት በላይ ያለመፍትሄ የዘለቀው የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አለመከበር የወለደው ችግር ነው፡፡

በመሆኑም፡-

1. አገዛዙ በሕዝባችን ላይ መተኮሱን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲያቆም እናሳስባለን፤

2. ‹‹አስተማማኝ ዴሞክራሲ ገንብቻለሁ›› የሚለውን ቧልት እና አለባብሶ የማረስ መፍትሄ ተብየዎችን አቁሞ አሁን እየተተረተሩ ያሉ ችግሮች ዋና ምንጭ ሀገራችን ዴሞክራሲ ምድረ በዳ መሆኗን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ለመፍትሄ እንዲሰራ እንጠይቃለን፤

3. በተለይም ከ97 ዓም በኋላ ያወጣቸውን አፋኝ ህጎች ፓርላማውን በአስቸኳይ ጠርቶ እንዲያሰርዝ እንጠይቃለን፤

4. የሀገር መከላከያና የተለያዩ የፖሊስ ሰራዊት አባላት የወጣችሁበት ሕዝብ ተቃውሞውን በሚያሰማበት ጊዜ በሰለጠነ መንገድ ልታስተናግዱትና ልትጠብቁት ይገባል እንጂ ሕዝቡ ላይ ልትተኩሱ እንደማይገባ እንዲሁም ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ ልዕልና ዘብ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፤

5. እኛ ኢትዮጵያውያን ህልውናችንም ሆነ ተስፋችን አንድ ላይ የተገመደ በመሆኑ ለአፍታ እንኳ ልንዘነጋው አይገባም፡፡ በመሆኑም ተከፋፍለን የአገዛዝ መሳሪያዎች ከመሆን ተላቀን ለልጆቻችን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመፍጠር ልናወርስ ይገባል፡፡ ስለዚህ ለጋራ ግባችን በጋራ እንድንታገል ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፤

6. የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገዛዙ ላይ ያለውን ተቃውሞ በወንድማማችነትና በሰላማዊ ትግል እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፤

7. የአለማቀፉ ማህበረሰብም ለሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች መከበር ክቡር ሕይወቱን እየከፈለ ካለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን፤

በመጨረሻም በሰላማዊ ትግሉ ህይወታቸውን በግፍ የተነጠቁ ወገኖቻችንን በማሰብ እና ሕዝቡ እያደረገ ላለው ሰላማዊ ትግል ያለንን ድጋፍ ለመግለፅ፣ እንዲሁም በቅጥፈት በደለበ ዶሴ በግፍ መታሰራችን አልበቃ ብሎ በእስር ቤት ውስጥ ለዓመታት እየተፈፀመብን ያለውን ኢሰብዓዊ አያያዝ አስመልክቶ ተቃውሟችንን ለማሰማት ከጳጉሜ 2 እስከ ጳጉሜ 5 ለ3 ቀናት የሚቆይ የርሃብ አድማ ላይ መሆናችንን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

የህሊና እስረኞች

– እስክንድር ነጋ

– አንዷለም አራጌ

– ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)

Filed in: Amharic