የወያኔ ሎሌዎች እኔ ስለትግራይ ያለኝን አመለካከት እያጠናገሩ ማውራት ከጀመሩ ዓመታት አለፉ፤ ፋይዳ የላቸውም ብዬ ንቄ ትቻቸው ቆይቻለሁ፤ አሁን ግን የወያኔ ሎሌዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረሱትንና የቃጡበትን ከባድ አደጋ በጥልቅ ስለተገነዘብሁ፣ የምችለውን ያህል ለማስተካከል ቆርጫለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ከክንፈ ወልደ ሚካኤል ጋር ብቻ ተነጋገሬበት ነበር፤ ዛሬ እንደክንፈ የሚያምነኝና የማምነው ወያኔ የለም፤ ችግሩም እየተባባሰ በመሄዱ ጊዜን የሚሰጥ አልመሰለኝም፤ ስለዚህ አደባባይ ላውጣውና የሌሎች ሰዎች ሀሳብ ተጨምሮበት በጊዜ መፍትሔ ብንፈልግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
በአጼ ዮሐንስ ዘመን የትግራዩ ራስ አሉላ መረብ-ምላሽን ይገዙ ነበር፤ ኢጣልያኖች ለመረብ-ምላሽ ኤርትራ የሚል ስም ካወጡለት እአአ ከ1900 በኋላ፡
- ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣልያ በተወረረችበት ዘመናት እአአ ከ1935 አስከ1941 ኤርትራ ከትግራይ ጋር ተቀላቅሎ እንደአጼ ዮሐንስ ዘመን በአንድ ላይ ይተዳደር ነበር፤
- እአአ ከ1961 እስከ1993 ኤርትራ አንድ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ሆኖ ነበር፤
- እአአ በ1991 ሻቢያና ወያኔ በተቀናጀ ጦር የደርግን የጦር ኃይል ጥሰው ኢትዮጵያን በሙሉ ኤርትራንም ጭምር ተቆጣጠሩ፤
- ኤርትራን በሚመለከት ወያኔ የመጀመሪያውን ብሔራዊ ስሕተት ፈጸመ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ራሱን የቻለ ሉዓላዊ አገር እንዲሆን አደረገ፤
- ገና አሥር ዓመታት እንኳን ሳይሞላ እአአ በ1998 ሻቢያና ወያኔ በድንበር ጦርነት ተፋልመው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አልቀዋል፤ ጦሱ አሁንም አልበረደም፤
- በዚህ ጦርነት ኤርትራ ልዩና ከኢትዮጵያ ጋር የታሪክም ሆነ ሌላ ግንኙነት ካልነበራቸው አገሮች ጋር ተፈረጀ፤
- የኤርትራ ሕዝብ አንኳን ለቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ለትግራይ ሕዘብም ባዕድ እንደሆነ ታወጀ፤
- የኤርትራ ሕዝብ ባዕድ ብቻ ሳይሆን ጠላትም ሆነ፤
ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ
ዛሬ ኢትዮጵያ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ኢጣልያ ዙሪያዋን ከብበው አፍነዋት እንደነበረው ዘመን አሁንም ምንም የባሕር መፈናፈኛ ሳይኖራት የተቆለፈባት አገር ሆናለች፤ ከትግራይ ጋር የኢትዮጵያ ታሪክ መካነ ልደት የሚሆነው ኤርትራ ዛሬ በባዕድነትና በጠላትነት ተፈርጇል፤ ለብዙ ሺህ ዓመታት አብሮ በመኖርና በመጋባት የተዛመደውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በፋሺስት ኢጣልያ የወረራ ዘመናት (ከ1928-1933 ዓ.ም.) እንደነበረው በጎሣና በቋንቋ ተከፋፍሎ እርስበርሱ ለመተላለቅ እየተዘጋጀ ነው፤ ኢጣልያ በአምስት ዓመት የግዛት ዘመኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመበታተን ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም ነበር፤ ወያኔ ያንኑ ኢትዮጵያን በጎሣና ቋንቋ የመበታተኑን ሙከራ ለአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ሞከረ፡፡
እውቀትም፣ እምነትም አብሮ ሲከዳ ሰው የሚንቀሳቀሰው እንደእንስሳ በእውር-ድንብሩ ነው፤ ያለፉት አርባ ዓመትት፣ በተለይም ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በእውር-ድንበር ስተመራ ቆይታለች፤ ቆይታለች ከማለት እዚህ ደርሳለች ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፤ የቁልቁለቱ ተዳፋት እየጨመረ ሲሄድ የት እንደሚያደርሳት ገና በውል አናውቅም፤ መቼም ተለይቷት የማያውቀው የእግዚአብሔር ድጋፍ የአባቶቻችንን ወኔ በዛሬ ወጣቶች ውስጥ አስርጾ፣ በያለበት የሚታየውን የጸብ ዝንባሌ ወደፍቅርና ስምምነት ለውጦ፣ የፈይሳ ለሊሳን በጎ ማኅበረሰባዊ ግንዛቤ አስጨብጦ ተአምር እናይ ይሆናል፤ ለዚያ ብቁ ያድርገን!
የትግራይ ሕዝብ ያለበት ሁኔታ
ዛሬ የትግራይ ክልል የሚባለው ከመጀመሪያ አስከመጨረሻ ከባድ የአስተሳሰብ ስሕተት የተጠናወተው አመራር ያለው ነው፤ የሚከተሉትን የማያስፈልጉ እክሎች ለትግራይ ሕዝብ ፈጥሮአል፡–
- የጎንደርንና የወሎንም፣ የአፋርንም መሬት ወደትግራይ ማካተቱ ኤርትራ ደጀን ይሆናል በሚል እሳቤ የተፈጸመ ሳይሆን አይቀርም፤
- ከኤርትራ ጋር ግጭት፣ ከዚያም ጦርነት የተካሄደው የኢትዮጵያን ኃይል በመተማመን ነበር፤
- ሁሉም እንደሚያውቀው ውጤቱ ኤርትራን ባዕድና ጠላት አድርጎ በጦርነት ማዋረድና ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ኤርትራን ሽብርተኛ በማድረግ ማዕቀብ እንዲጣልበት አድርጎ በማደህየት የበላይነትን ለማረጋገጥ ነበር፤
- የወያኔ አገዛዝ ኃላፊነት የጎደለው (ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች) በሚዘገንን ጭካኔ የታጀበ ሆኖ በሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ በመሻሻል ፋንታ እየተባባሰና እየከፋ በመሄዱ ዛሬ ሰላማዊ ዓመጽ ወደእርስበርስ ጦርነት ለመሸጋገር ተቃርቧል፤
- በዚህም የተነሣ ትግራይ በሁለት ሆን ተብሎ ወያኔ ጠላት ባደረጋቸው ሕዝቦች መሀከል ተጥዶ እንደገና ዳቦ እሳት እስኪቀጣጠልበት እየጠበቀ ነው፤
ትግራይ በሰሜን በኩል ‹በባዕድ ጠላት› ታጠረ፤ ለትግራይ ሕዝብ በማናቸውም መመዘኛ የተፈጥሮ ዝምድና ያላቸው የኤርትራ ተወላጆች ባዕድና ጠላት በመደረጋቸው የኤርትራንም ሆነ የትግራይን ሕዝብ የሚጎዳ ነበረ፤ በዚህ ባበቃ!
የትግራይ ሕዝብ በችግርም ይሁን በደስታ በስተደቡብ በጎንደርና በወሎ፣ በአፋርም ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በጣም የቀረበ ግንኑነት ነበረው፤ የወያኔ አመራር ግን ልባቸው ያረፈው በጎንደሬዎቹ፣ በወሎዬዎቹና በአፋሮቹ ላይ ሳይሆን በመሬታቸው ላይ ነበር፤ ስለዚህም ከጎንደርም፣ ከወሎም፣ ከአፋርም መሬት እየቆራረሱ ወደትግራይ ግዛት ጨመሩ፤ በዚህ የወራሪነት ተግባር ወያኔ በትግራይ በስተሰሜን የፈጠረውን ጠላት ረስቶ በስተደቡብ ደግሞ ከጎንደር፣ ከወሎና ከአፋር ጋር ለትግራይ ሌላ የጠላት ቀጣና ፈጠረ፤
እንግዲህ አሁን የትግራይ ሕዝብ የሚገኘው በሰሜን በኤርትራ ‹‹የጠላት አጥር፣›› በደቡብ ደግሞ በጎንደር፣ በወሎና በአፋር ‹‹የጠላት አጥር›› ተከቦ መውጫ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው፤ ይህንን ሁኔታ የፈጠረው ወያኔ ነው፤ የትግራይን ሕዝብ መውጫ ቀዳዳ በማሳጣት በአጥሩ ውስጥ ጠርንፎ በመያዝ የማይነጥፍ የታዛዥ አገልጋዮች ምንጭ ለማድረግ ነው፤ ወያኔ የራሱን የሥልጣን ጥም ለማርካት ሲል ብቻ በኢጣልያ አገዛዝም ጊዜ ቢሆን ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የነበረውን ዝምድና ጠብቆ የኖረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ (የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ) አጣልቶና ለያይቶ ጠላት አድርጎ ኢትዮጵያን የባሕር ወደብ የሌላት አገር አደረጋት፤ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የተንቤኑ ራስ አሉላ ከኢጣልያ ጋር ያለማቋረጥ እየተፋለሙ በትግራይና በኤርትራ ሕዝብ ጀግንነትና መስዋእት ተከብሮ የቆየውን ኢትዮጵያዊነት የባንዳ ልጆች ለወጡት፤ የትግራይ ሕዝብ የአባቶቹን መስዋእትነት ረስቶ የባንዳዎች ተልእኮ አስፈጻሚ ተደረገ፡፡
ወያኔ ትግራይን ከተቆጣጠረ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የትግራይ ሕዝብ በአጠቃላይ ያገኘውን ጥቅምና የኑሮ መሻሻል — እያንዳንዱ አባወራ ራሱንና ቤተሰቡን በየዕለቱ በተሻለ ሁኔታ መመገብ፣ ማልበስ፣ የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ የተሻለ የጤና አጠባበቅና ትምህርት … አግኝቷል ወይ? ወያኔ ያለማቋረጥ ስሐተትን መፈጸም እንጂ ስሕተትን ማረም የባሕርዩ አይደለም፤ ስለዚህም መጀመሪያ በትግራይ ዙሪያ የፈጠረውን ‹‹የጠላት አጥር›› (ካርታ አንድ) ያሻሻለ መስሎት ትልቁ ትግራይ የሚል ሌላ የበለጠ ሰሕተት ለመሥራት እየተንደረደረ ነበር (ካርታ ሁለት)፤ እንደዚህ ያሉ የእብጠት ሕመሞች ሁሉ ለሞት የሚዳርጉ መሆናቸውን የሂትለርም የዚያድ ባሬም ታሪኮች ያስተምሩናል፤ የሂትለር ጀርመን ለሁለት ተከፍሎ ከብዙ ዓመታት በኋላ ጀርመን እንደገና አንድ ሆኗል፤ የዚያድ ባሬ ሶማልያ ክፉኛ ተከፋፈሎ እስከዛሬ በትርምስ ውስጥ ይገኛል፤ የወያኔ የማሰብ ችግር መገለጫው የሚሆነው መጀመሪያውንና ትንሹን ስሕተት በሁለተኛና በባሰ ስሕተት ‹ለማረም› መሰናዳቱ ነው፤ ስለዚህም ለትግራይ ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም እንደተባለው ሆኖበታል፡፡
መፍትሔው ምንድን ነው?
ችግሩን በትክክል ከተረዳነው መፍትሔው አይጠፋም፤ ችግሮቹ ሁለት ናቸው፤ ሁለት ቢመስሉም አንድ ናቸው፤ የተወሳሰቡና የተቆላለፉ ናቸው፤ ገነጣጥለን ስናያቸው አንዱ ችግር የትግራይ ነው፤ አንደኛው ደሞ የኢትዮጵያ ነው፤ ሁሌም የትግራይ ችግር የአትዮጵያ ችግር ነው፤ የኢትዮጵያ ችግር የትግራይ ችግር ነው፤ በበጎም ሆነ በክፉ ትግራይን ነክቶ ኢትዮጵያን ሳይነካ የቀረ ነገር የለም፤ አሁን በአለንበት ዘመን ትግራይን ወጥሮ ይዞ ኢትዮጵያን የጎሣዎች መንደሮች ስብስብ ያደረገ ወያኔ ነው፤ ወያኔ ትግራይን በጎሣ ተብትቦ ከኢትዮጵያ ጋር በቅራኔ ጠምዶ ትግራይን በኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን በትግራይ ቀፍድዶ እየተቆጣጠረ ሁለቱንም አስማምቶ ሳይሆን ለያይቶ ለመግዛት እየሞከረ ነው፤ ዛሬም እንደበፊቱ ኢትዮጵያን ለውርደት ያበቃት ትግራይን ለውርደት ያበቃው ሕመም ነው፤ ትግራይ ሳይፈወስ ኢትዮጵያ ትፈወሳለች ብዬ አላስብም፤ አስቸጋሪው ጥያቄ ኢትዮጵያን በትግራይ ገመድ፣ ትግራይን በኢትዮጵያ ሰንሰለት አስሮ የያዘው ወያኔ ገመድና ሰንሰለቱን እንዲበጥስና ሁለቱም ነጻ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ወይም ትግራይንም ሆነ ኢትዮጵያን ሳይጎዳ ገመዱንና ሰንሰለቱን መበጠስ የሚችል ሌላ ማን ነው?የሚል ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር የተወሳሰበና የተቆላለፈ መሆኑን የተረዱ አይመስለኝም፤ ይህንን ካልተረዱ ወደመፍትሔው ለመሄድ የሚቻል አይመስለኝም፤ የዋናው መፍትሔ ቁልፍ በትግራይ ተወላጆች እጅ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ተወላጆች ግምባር-ቀደም ተነሣሽነት ያልተጀመረ የኢትዮጵያ ትግል ውጤቱ እንኳን ኢትዮጵያንና ትግራይንም አያድንም፤ የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ላይ ወያኔን ቢቃወም ወያኔ በቀላሉ የጎሣ ጦርነት ያደርገዋል፤ ለነገሩ አሁንም ጀምሮታል፤ ትግራይ በግንባር-ቀደምነት ከገባበት ግን ዓመጹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሆናል፤ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ (ትግራይን ጨምሮ) ትግል መግጠም አለበት፤ ይህንን ማድረግ አይችልምና ይሸነፋል፤ ይህ አባባል በብዙ ጎሣዎች ኩራት ላይ ቀዝቃዛ ውሀ መቸለስ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ በአንጻሩም የትግራይን ጎሠኞች ልባቸውን የሚያሳብጥ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ጎሣዎቻቸውን በጤናማ ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት የማይችሉ ሰዎች በትርምስ ውስጥ ባለች ኢትዮጵያ ውስጥ የጎሣዎች ሰላም ሊኖር እንደማይችል ራሳቸውን ቢያሳምኑ ከብዙ የአስተሳሰብ ውደቀት ይድናሉ፤ አሁን ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር ይህ ነው፤ ዋናው ጥያቄ ይህንን ችግር እንዴት ልንፈታውና የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውንም ሕዝብ ከእልቂት ማዳን እንዴት ይቻላል? የሚል ነው፡፡
ወያኔ የጀመረው ለትግራይ ሕዝብ ጠላትን የማራባት ዘመቻ የትግራይን ሕዝብ ያጠፋዋል፤ ይህንን ሳንጠራጠር ልንቀበለው ይገባናል፤ ብንደብቀው አይጠቅመንም፤ ስለዚህ የመጀመሪያው ደረጃ መፍትሔ የጠላትነት እሳት እንዳይቀጣጠልና ትግራይን እንዳይበላ መከላከል ነው፤ ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ መፍትሔ ለመጀመር የትግራይ ሕዝብ ግምባር ቀዳሚ መሆን ያለበት ይመስለኛል፤ የገጠመውን የተቆላለፈ ችግር የትግራይ ሕዝብ በትግሬነት እፈታዋለሁ ብሎ ከተነሣ ያባብሰዋል እንጂ በጭራሽ ሊፈታው እንደማይችል መቀበል የትግሉ መነሻ ይሆናል፤ ከዚህም ጋር ወያኔ ትግራይን ድሪቶ በማድረግ ከዚያም ከዚህም መሬት እየቀነጫጨበ በማስገባት ትግራይን አሳብጦ ከጎረቤቶች ሁሉ ጋር ለማጣላት የሚያደርገውን አጉል ቂልነት መቃወም ግዴታቸው እንዲሆን በበጎ ፈቃድ ቢወስኑ ከብዙ ችግሮች የሚድኑ ያመስለኛል፤ ወደትግራይ እሳቱ ሳይቀጣጠል የትግራይ ሕዝብ ነቅቶ እሳቱን ለማዳፈን መዘጋጀት ያስፈልገዋል፤ ለዚህ ሁለት ምክንያቶች አሉ፤ አንደኛ የችግሩ ፈጣሪ የሆነው ወያኔ ቤቱና ምሽጉ ያደረገው ትግራይን ስለሆነ ለወያኔ የተቃጣው ሁሉ ትግራይ ላይ የሚያርፍ ነው፤ ስለዚህም የሚቀጣጠለው እሳት በቅድሚያ የሚበላው የትግራይን ሕዝብን መሆኑ ሁለተኛው ምክንያት ይሆናል፤ ወያኔ ሆነ ብሎ በትግሬነትና በወያኔነት መሀከል ያለውን ልዩነት አፍርሶ ትግሬንና ወያኔን አንድ አድርጎ በማቅረብ የችግሩን ፈጣሪና የችግሩን ገፈት ቀማሽ አንድ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ ነው፤ ይህንን ሀሳብ የትግራይን ሕዝብ ለመከፋፈል የታቀደ የፖሊቲካ ስልት አድርጎ ለመውሰድ ይቻላል፤ ግን የትግራይን ሕዝብ መከፋፈል ለኢትዮጵያ ምን የፖሊቲካ ትርፍ ያስገኛል?
ችግር ፈጣሪውን ወያኔንና የችግሩን ዋና ሰለባ የሚሆነውን የትግራይ ሕዝብ አንድ ማድረጉ የሚያስከትለውን ለትውልድ የሚተላለፍ ችግር አስቀድሞ አለማየት በጣም አደገኛ ይሆናል፤ ይህ መንገድ ለትግራይ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጉዳት እንደሚያመጣ መረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም፤ መመለስ የማይቻልበት የጥፋት መንገድ ነው፤ ኢትዮጵያ ያለትግራይ ከሲታ ሆና መኖር ትችል ይሆናል፤ ትግራይ ያለኢትዮጵያ ከሲታ ሆኖ መኖር ይችላል? ችግር የሚፈታው ችግሩን አውቀው ሲጋፈጡት ብቻ ነው፡፡
የችግሩ ሰንኮፍ
ወያኔ ያለልፋት በኢትዮጵያዊነት ሊያገኝ የሚችለውን ሁሉ በብቸኛነት ባለቤት ለመሆን ተመኘ፤
- የአገሩን ሥልጣን የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- የአገሩን ሀብት (መሬትና ማዕድን፣ ገንዘብ) የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- የጦር ኃይሉንና ፌዴራል ፖሊስን የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- የአግዓዚን ጦር የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- ፍርድ ቤቶችን የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- ትግራይን የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- ወልቃይት-ጸገዴን የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- ከወሎ የቀማውን መሬት የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
- ከአፋር የቀማውን መሬት የራሱ፣ የግሉ አደረገ፤
… ወዘተ.
በእርግጥ ወያኔ ይህን ሁሉ ያደረገው ብቻውን አይደለም፤ በግድም ይሁን በውድ ተባባሪ የሆኑለት ወያኔ ራሱ የፈጠራቸው ድርጅቶች ነበሩ፤ በሕግ ባይሆንም በተግባር በሕወሀት ስር የተዋቀሩትና ኢሕአዴግ በሚል መጠሪያ የተጠቃለሉት የጎሣ ቡድኖች የሚከተሉት ናቸው፤ አምስት ክልሎች (የአፋር፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ የቤኒ ሻንጉል-ጉሙዝና የሀረሪ) በገዢው ቡድን አልታቀፉም፤ ማን እንዳቀፋቸው የታወቀ ነገር የለም፤
- ብአዴን፣ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፤
- ኦሕዴድ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣
- ደሕዴድ፣ የደቡብ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣
አሁን እንደሚታየው በአማራና በኦሮምያ ክልሎች ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ያለመተባበር አድማ ስላነሣ በጦርና በፌዴራል ፖሊስ ኃይል ስር ወድቀው የክልሉ አስተዳደር አቅመ-ቢስ ሆኗል፤ በደቡብም ቢሆን በኮንሶ ያለው ተመሳሳይ የሕዝብ ንቅናቄ ብዙ ችግሮችን እየፈጠረ በመሆኑ ወሬው ዓለምን አዳርሷል፤ ከነዚህ ሁሉ ተለይቶ ደልቶትም ይሁን ከፍቶት ሳይታወቅ ጸጥ በማለቱ ሰላም የሰፈነበት የሚመስለው ትግራይ ነው፤ እንዲህ በመሆኑም ትግራይን በአጠቃላይ ከወያኔ ጋር የተሰለፈ አስመስሎ ያሳየዋል፤ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ተሰንጎ በጉልበት ተይዞ ነው እንዳይባል ብዙ ትግሬዎች በነጻነት ሀሳባቸውንና ለወያኔ አገዛዝ ያላቸውን ተቃውሞ የሚገልጹ አሉ፤ ወይም ደግሞ ብዙዎቹ በጉልበት ሳይሆን በባህላዊ ጫና (የፈረንጅ ፈላስፋዎች the tyranny of custom በሚሉት) እየተገደዱ ይሆናል፤ ለማናቸውም ትክክለኛ ምክንያቱን ባናውቅም ወያኔ አብዛኛውን የትግራይ ሕዝብ በጫማው ስር አድርጎ እንደሚቆጣጠረው የማይካድ ነው፡፡
በኦሮምያና በአማራ ክልሎች ብቻ ከስድሳ አምስት አስከሰባ ከመቶ የሚሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበት ነው፤ ደቡብ ከአሥር ከመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖርበት ነው፤ እንግዲህ በሦስቱ ክልሎች ብቻ በትንሹ ሰባ አምስት ከመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኖራል ማለት ነው፤ ይህ ሦስት ሩብ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖርበት መሬት የቆዳ ስፋትም በጣም ሰፊ ነው፤ እንግዲህ የትግራይ ሕዝብ ይህንን ያህሉን የኢትዮጵያ ሕዝብ አስቀይሞ ከወያኔ ጋር መሰለፉ ይጠቅመዋል ማለት በጣም ይከብዳል፤ በካርታ አንድ የሚታየውን ሁኔታ ሁሌም በዓይነ-አእምሮአችን ልናየው ይገባል፤ ለአሁኑም ይሁን ለወደፊት፣ በጦርነትም ሆነ በሰላም፣ በደሀነትም ሆነ በብልጽግና የትግራይን ሕዝብ የሚያዋጣው ከሰባ አምስት ከመቶ ከሚሆነው ከወገኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መቆም ነው፤ ለእኔ ይህ ክርክር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡
የትግራይ ሕዝብ አስቸጋሪ ምርጫ
- ምርጫ አንድ፡ የትግራይ ሕዝብ እንደጥንቱ እንደጠዋቱ ታሪኩን ይዞ በኢትዮጵያዊነቱ ይቀጥላል፤ በኢትዮጵያዊነት ታሪኩ በግምባር-ቀደም ተሰልፎ በፖሊቲካም ሆነ በመንፈሳዊ ጸጋው የኢትዮጵያዊነት ግዴታውን ይወጣል፤ ይህ ምርጫ የኢትዮጵያዊነት ግዴታ ነው፤ ይህ ምርጫ ታሪካዊ ግዴታ ነው፤ ይህ ምርጫ የዜግነት ግዴታን ከጎሣ ግዴታ ማስቀደም ነው፤ ይህ ምርጫ ከጨለማው ዘመን ወጥቶ ወደሃያ አንደኛው ምዕተ-ዓመት መሸጋገር ነው፤ ከሁሉም በላይ ይህ ምርጫ የሰፊ ሀብት ባለቤትና የመቶ ሚልዮን ዜጎች ማኅበረሰብ አባል ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ የትግራይ ነች፤ ስለዚህም ትግራይ ኢትዮጵያን ነች፤ ሁለቱ አይለያዩም፤ ይህንን ወያኔም በሚገባ የተረዳው ይመስላል፤ አለዚያ ከጎንደር፣ ከላስታም፣ ከራያም፣ ከጎንደርም … የሚለቃቅመው ለምንድን ነው!
- ምርጫ ሁለት፡ የትግራይ ሕዝብ የወያኔ መሣሪያ እንደሆነ ይቀጥላል፤ ይህ ሲሆን ትግራይ በመሠረቱ ከኢትዮጵያ ይገነጠላል ማለት ነው፤ በትግራይ ዙሪያ ኤርትራ በሰሜን፣ በደቡብ ደግሞ ጎንደር፣ ወሎና አፋር ይገኛሉ፤ ወያኔ ሆን ብሎ ትግራይን ከኤርትራ፣ ከጎንደር፣ ከወሎና ከአፋር ጋር አጋጭቶ ደም እንዲቃቡ አድርጓል፤ (በትግራይ ዙሪያ ያሉትን ብቻ ለማንሳት ነው እንጂ ከጂጂጋ እስከጋምቤላ፣ ከወሎ እሰከሲዳሞ ቦረና የግፍ ጠባሳዎች አሉ፤) ስለዚህም ትግራይ በወያኔ ስር ሆኖ ከአነዚህ ከከበቡትና በጠላትነት ከተፋጠጡት ሕዝቦች ጋር ዘለዓለም ሲቆራቆዝ ሊኖር ነው፤ ዙሪያውን ካሉት ሕዝቦች ሁሉ ጋር መቆራቆዝ የትግራይን ሕዝብ ያደኸያል፤ የትግራይ ሕዝብ መሸሻ ስለሌለው በአጥንቱ እየሄደ የወያኔ አገልጋይ ይሆናል፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ በምሥራቅ በአሰብ በኩል፣ በምዕራብ በጎንደር በኩል የልማትና የጋራ ደኅንነታቸውን ይመራሉ፤
የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ በሚካሄደው ልማት ተሳታፊ አይሆንም፤ (ካርታ አንድ) የሩቅም ሆኑ የቅርብ ወዳጆች ካሉ በመሬትም ሆነ በዓየር ግንኙነት ማድረግ ከባድና አስቸጋሪ ይሆናል፤ ትግራይ በወያኔ ጫና ከኢትዮጵያ ሲለይ ኢትዮጵያ ታንሳለች፤ ትግራይ ደግሞ ይበልጥ አንሶ ኢምንት ይሆናል፤ በሌላ በኩል ሲታይ የትግራይ መለየት ኢትዮጵያዊነትን ሬሳ ሲያደርገው ትግሬነትን የሬሳ ተሸካሚ ያደርገዋል፤ ኢትዮጵያዊነት ያለነፍስ፣ ትግሬነት ያለአካል ጎረቤቶች ይሆናሉ! ነፍስና ሥጋ እየተፈላለጉ ምጽአትን ይጠብቃሉ፡፡
የወያኔ አስቸጋሪ ምርጫ
ወያኔ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ብዙ ሀብት እንዳለው የታወቀ ነው፤ ዶላርና ወርቅ በሻንጣ ሲጓዝ ዓለም በሙሉ አይቷል፤ አንድ የእንግሊዝ አገር ዳኛ ምነው በአገራችሁ ባንክ የለም እንዴ! ብሎ ተገርሟል፤ ይህ የወያኔ ሀብት ምንጩ ሲደርቅ እየመነመነ ይደርቃል፤ በውጭ አገር ባንኮች የተቀመጠውም በግለሰቦች ስም ስለሆነ የድርጅቱ ድርሻ ትንሽ ይሆናል፤ የወያኔ አመራር ያከማቸው ገንዘብ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው በውጭ አገሮች የተመቸ ኑሮ እንዲኖሩበት የታለመ እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለማበልጸግ አይደለም፤ አመራሩ ሁሉ ያከማቸው ገንዘብ አንድ ላይ ቢሆንም ለማያቋርጥ ጦርነት፣ ለትግራይ ልማትና ለአመራሩ ቤተሰብ መኖሪያ እየተከፋፈለ ብዙ አይቆይም፤ ከዚያ በኋላ እያፈጠጠ የሚመጣውን ችግር የትግራይ ሕዝብ ማየት ያለበት ዛሬ ነው፡፡
ወያኔ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ብዙ ጥፋቶችን መፈጸሙ አይካድም፤ ምናልባት ፈረንጆች እንደሚሉት (The road to hell is paved with good intentions.) ወደገሀነመ እሳት የሚወስደው መንገድ (በአስፋልት ፋንታ) በጎ አስተያየቶች የተነጠፉበት ነው ማለት ነው፤ በሌላ አነጋገር ሰዎች ወደገሀነመ እሳት የሚገቡት ጥሩ እንሠራለን እያሉ በፈጸሙት ጥፋት ነው ማለት ነው፤ ወይም ደግሞ ወያኔ በጎረምሳነት ስሜት የአክሱም ጽዮንን ኪዳን በአጉል ማርክሳዊ ፍልስፍና በመለወጣቸው ለወያኔም፣ ለትግራይ ሕዝብም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም በአጠቃላይ የሚጠቅም መስሏቸው የፈጸሙት የጉርምስና ጥፋት ነው፤ ወይም ደግሞ ደርግን ለማውረድ በፈለጉ ኃይሎች እኩይ ምክር ተጠምደው ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ሁሉ ምክንያት የወያኔን ጥፋት መከርከም ይቻል ይሆናል፤ ይህ የሚሆነው በሥልጣን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን በወያኔ በኩል ሆነን ስናየው ከሥልጣንም ሌላ በጣም አስቸጋሪ ምርጫ ይገጥመዋል፤ ብዙዎቹ ባለሚልዮን ወይም ባለቢልዮን ዶላር ሀብታሞች ሆነዋል ይባላል፤ ይህንን ከኢትዮጵያ የተዘረፈ ሀብት መመለስ ሥልጣንን ለሕዝብ የማስረከቡን ያህል ቀላል አይመስለኝም፤ ቢሆንም በሁለት በኩል በጎ ፈቃድ ከአለ መፍትሔ የማይገኝለት ችግር አይኖርም፤ የደቡብ አፍሪካ ግፈኞች ነጮች ልክ እንደወያኔ በሥልጣንም በሀብትም ያበጡ ነበሩ፤ መፍትሔ አግኝተውለታል፤ በጎ ፈቃዱ ከአለን እኛም አያቅተንም፡፡
ፍትሐዊ የሆነ መፍትሔ ላይ ለመድረስ ለወያኔ መንፈሳዊ ወኔ ያስፈልገዋል፤ ይህ እስካሁን ያልታየባቸው ቢሆንም ከየትም ፈልገው ማግኘት አለባቸው፤ የደቡብ አፍሪካ መፍትሔ የተገኘው ብዙ ጊዜ ስሙ ከማይነሣው ከደ ክላርክ ነው፤ ያለደ ክላርክ የመንፈሳዊ ወኔ የደቡብ አፍሪካ ችግር አይፈታም ነበር፤ የደ ክላርክ ዓይነት ሰው በወያኔ ድርጅት ውስጥ መገኘቱ አጠራጣሪ ነው፤ ሆኖም የወያኔ መሪዎች የጉልበተኛነትን ጠባይ አውልቀው ጥለው ለእርቀ-ሰላም የሚያዘጋጃቸውን መንገድ ቢመርጡ ለራሳቸውም፣ ለትግራይ ሕዝብም፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝብም ትልቅ የሰላምና የልማት በርን ይከፍታሉ፤ በጉልበተኛነት ያላገኙትን ክብር በሰላም ያገኙታል፤ ኢትዮጵያ በፖሊቲካም ሆነ በመንፈሳዊ ታሪክዋ የነበራትን የሽምግልና የበላይነት የአፍሪካ ቀንድን ሕዝቦች ለመምራት ትችላለች፡፡
ወደዚህ ዓላማ ለመድረስ ወያኔ የሚከተሉትን መነሻ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲያደርግ ይጠበቅበታል፡—
- ነጻ የተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሞ ሙሉ ሥልጣን ይረከባል፤
- በስሩና በእሱ ተቆጣጣሪነት ከሁለት ዓመታት በላይ የማይቆይ የባለአደራ መንግሥት ያቆማል፤
- የባለአደራው መንግሥት የሚቋቋምበትንና የሚሠራበትን ሕጎች ያወጣል፤
- የወያኔ ባለሥልጣኖች ከሂሳብ አዋቂዎችና ከሕግ አዋቂዎች ጋር ሆነው የንብረታቸውን ጉዳይ ያጣራሉ፤ በዚህ ተግባር ላይ ከዓለም ባንክና ከተባበሩት መንግሥታት አግባብ ያላቸው ድርጅቶች፣ ከአሜሪካ፣ ከብሪታንያ፣ ከጀርመን፣ ከጃፓንና ከህንድ የተውጣጡ ባለሙያዎች እንዲማክሩ መጠየቅ ይቻላል፤
- ተጣርቶ የተገኘው ሀብት (የማይንቀሳቀስ ንብረትን ጨምሮ) እንደሚከተለው ሊደለደል ይቻላል፡– ይህ መነጋገሪያ ሀሳብ ብቻ ነው፡–
- ለትግራይ ልማት፤
- ለሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ልማት፤
- ለትግራይ የጦር ጉዳተኞች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለትግራይ የሟች ቤተሰቦች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለሌሎች ኢት. የሟች ቤተሰቦች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለሌሎች ኢትዮጵያውያን የጦር ጉዳተኞች፤ ለእያንዳንዳቸው መጠነኛ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት፣
- ለወያኔ መሪዎች፤ ለመኖሪያ የሚያስፈልጋቸውን ጡረታ መስጠት፤
- የወያኔ መሪዎችና ካድሬዎች (የቅርብ አገልጋዮች) ለመጀመሪያው የክልልም ሆነ አገር-አቀፍ ምርጫ እንዳይሳተፉ በሕግ ገደብ ይጣልባቸዋል፤
መደምደሚያ
ይህ የሰላማዊ ለውጥ ወያኔን ከትግራይ ሕዝብ ጋር፣ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር፣ ከዓለም ማኅበረሰብ ጋር ያስታርቀዋል፤ በተጨማሪም ሰላማዊ እርቁ የወያኔ መሪዎች በውጭ አገሮች እንደልባቸው እንዲዘዋወሩ የዜግነት መብቶቻቸው ሁሉ የሚከበሩበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ዓላማችን ያለፈውን ስሕተት በማረም የሚቀጥለውን ጉዞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ አብሮ በአንድነት ለመተለምና ከሁሉም በላይ ትግራይ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ምልክት ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው፤ ደብረ ቢዘንን በማጣት ደህይተናል፤ አሁን ደግሞ አክሱም ጽዮንንና ደብረ ዳሞን በማጣት አንደኸይም፤ የያሬድን ዜማ በምን እንለውጠዋለን? ትግራይ የኢትዮጵያ መካነ ልደት ነው፤ ትግራይ የኢትዮጵያ ክብርና ሞገስ ነው፤ ስለዚህም ትግራይን በወያኔ ክህደትና ሸር አናረክሰውም፤ ወያኔን ከርክሰቱ ልንመልሰው እንሞክራለን እንጂ ወያኔ ርክሰቱን በትግራይ ላይ እንዲያጋባ ልንፈቅድለት አንችልም፡፡
በአለንበት የታሪክ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ሁለት ከባድ ምርጫዎች ገጥመውታል፤ አንዱ ምርጫ በኢትዮጵያዊነትና በትግሬነት መሀከል ነው፤ በመሠረቱ ኢትዮጵያዊነትና ትግሬነት አንድ ስለሆኑ አንዱን መርጦ ሌላውን መተው አይቻልም፤ ነገር ግን በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ወያኔነት ትግራይነትን ስለሸፈነው ወይም ስለበከለው፣ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊነትንና ትግሬነትን እያራራቃቸው ነው፤ በዚህም ምክንያት የትግራይ ኢትዮጵያዊነትን የበከለውን የወያኔነት አረመኔነት በአክሱም ጽዮን፣ በደብረ ዳሞና በሌሎችም ቅዱሳን ገዳማትና አድባራት ማጽዳት ያስፈልገዋል፤ ለትግራይ ሕዝብ ከባድ ምርጫ የሚሆነው ወያኔን አቅፎ ኢትዮጵያዊነቱን መጠበቅና ማደስ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ትግሬነትን ከወያኔ ነጻ ማውጣትና ኢትዮጵያዊነትን ቀዳሚ ስፍራ የማስያዝ ግዴታ አለበት፤ በሌላ አነጋገር የትግራይ ሕዝብ ወይ ወያኔን አርሞና ገርቶ ወይም ወያኔን አውግዞ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መቆም ያስፈልገዋል ማለት ነው፤ ወያኔ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ታሪኩንና አቅዋሙን ይዞ በትግሬነት ተሸፋፍኖ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መቆም አይችልም፤ የትግራይ ሕዝብም ከወያኔ ጋር ቆሞና የወያኔ ምሽግ ሆኖ ወያኔ በዙሪያው ያጠረለትን የጠላትነት አጥር አልፎ ኑሮውን ለማሻሻል አይችልም፤ እንዲያውም የጦርነት ሜዳ ይሆናል፤ የወያኔ መሪዎች ዛሬም የሚያስቡት ወያኔን በሥልጣን ላይ ለማቆየት የትግራይ ሕዝብ ገና ወደፊት የሚከፍለውን መስዋእትነት ነው፤ ሥዩም መስፍን የሚከተለውን ይላል፡
ከ60 ሺ በላይ ሕይወት ከፍለን ፣ ከዚህ በላይ ሕዝብ ተጎድቶብን ነው ስልጣን ላይ የወጣነው፡፡ ዛሬ ትግራይ ላይ የሚነጣጠረው ነገር ለማንም አይተርፍም ሁላችን በዜሮ ነው የምንወጣው፡፡ ማንም አያተርፍም፡፡ ኢህአድግ መተኪያ የለውም፡፡
‹‹ሁላችንም በዜሮ እንወጣለን፤›› ፉከራ አይደለም፤ የእኩይ መንፈስ የመጠፋፋት ቃል ኪዳን ነው፤ የኢትዮጵያን መሬትና የተፈጥሮ ሀብቱን ለሌሎች ማስረከብ ማለት ነው፤ ይህንን ጤናማ አእምሮ ያስበዋል ለማለት አይቻልም፤ የወያኔ መሪዎች ዛሬም የሚያስቡት የትግራይ ሕዝብን መሣሪያቸው አድርገው ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ነጻ ሆኖ የራሱን ውሳኔ መወሰን እንደሚችል አያስቡም፤ የትግራይ ሕዝብ መሪዎቹ በአሜሪካና በአውሮፓ ያካበቱትን ሀብትና ያጠራቀሙትን ገንዘብ የማያውቅ ይመስላቸዋል፤ በመቀሌ ለተሠሩት የባለሥልጣኖች መኖሪያ ሰፈሮች የትግራይ ሕዝብ የሰጣቸውን ስሞች — የሙስና ሰፈር፣ የአፓርቴይድ ሰፈር — አልሰሙም ይሆናል፤ ወይም ቢሰሙም አልገባቸውም ይሆናል፤ ዛሬም ሆነ ነገ የትግራይ ሕዝብ ለወያኔ መሪዎች ግዑዝ መሣሪያ ሆኖ የሚቀጥል አድርገው ይገምቱታል፡፡
ሥዩም መስፍን በሥልጣን ኮርቻው ላይ እንዲቀመጥ የተከፈለው ዋጋ ስድሳ ሺህ የትግራይ ተወላጆች ሕይወት መሆኑንና ከዚያም የበለጠ የትግራይ ሕዝብ ተጎድቶ እንደሆነ ይነግረናል፤ በዚህ አያበቃም፤ በሚቀጥለው ዙር ትግል ‹‹ሁላችንም በዜሮ ነው የምንወጣው›› ሲል ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ የደገሰለትን የጥፋት ማዕበል እየነገረን ነው፤ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ በ1997 ምርጫ ላይም የሩዋንዳውን ‹‹ኢንተርሀምዌይ›› አንሥቶ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ አግዓዚ የሚባለውን የወያኔ ‹‹ኢንተርሀምዌይ››ን አሳየን፤ ዛሬም ለትግራይ ሕዝብ የተደገሰው የጥፋት ማዕበል የወያኔን መሪዎች በሩቁም እንደማይነካቸው ያውቃሉ፤ የትግራይን ሕዝብ በጥፋት ማዕበል ‹‹በዜሮ አስወጥቶ›› እሱ አሜሪካ ወይም አውሮፓ አንዱ ዘንድ ገብቶ የሙጢኝ ይላል፤ ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ራሱን ከዚህ ከተደገሰለት የጥፋት ማዕበል ለማውጣት ወያኔን እምቢ ብሎ ኢትዮጵያዊነቱን ማጠንከሩ ይጠቅመዋል፡፡
የወያኔ መሪዎች የትግራይን ሕዝብ ይዘው የትግራይንም የኢትዮጵያንም ሕዝብ ለማጠፋፋት ታጥቀው የተነሡ ይመስላል፤ ሌላው የወያኔ መሪ ዓባይ ጸሐዬ የሚከተለውን ይነግረናል፡–
<<እርስ በርስ ጦርነት ከጀመርን እንደ ሩዋንዳ እንኩዋ ተመልሰን አንድ ሀገር የመሆን ዕድል የለንም ፣ ደቡብ ሱዳን እስከ አሁን እየተጫፋጨፉ ነው፡፡ እጎዝላቭያ የደረሰው ይህ ነው ማንም ሊያስቆመው አልቻልም፡፡ በቅርባችን የመን ምን እየሆነች ነው? አንዴ እርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ አለቀ፤ ተመልሶ ሀገር መሆን አይቻልም፡፡ አሁን አንድ ብሔር ላይ ትግራይ ላይ ጦርነት ቢጀመር አለቀ … የትግራይ ሕዝብ እና አማራው እርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ የት ነው የሚቆመው ምንም ማቆሚያ የለውም፤
ዓባይ ጸሐዬ የታየው የኢትዮጵያ መበታተን ብቻ እንጂ የትግራይን ዕጣ አልተገነዘበም፤ ‹‹እንደሩዋንዳ እንኩዋ ተመልሰን አንድ ሀገር የመሆን ዕድል የለንም፣›› ይላል፤ የሚታየውና እንደማስፈራሪያ ሊጠቀምበት የፈለገው የኢትዮጵያን መበታተን ነው፤ እሱ ምሽጉ ያደረገውን ትግራይን አያነሣም! ትግራይን ሲያነሣ እንደሚከተለው ነው፡- ‹‹ትግራይ ላይ ጦርነት ቢጀመር አለቀ … የትግራይ ሕዝብ እና አማራው እርስ በርስ ጦርነት ከጀመረ የት ነው የሚቆመው? ምንም ማቆሚያ የለውም፤›› ሌሎች ጎሣዎችን በተለይ አማራ የሚለውን ለማስፈራራት በትግራይ ሕዝብና በአማራ በተባለው መሀከል ጦርነት ሲደረግ ሌሎች ጎሣዎችስ ውጤቱን የሚጠብቁት ምን እየሠሩ ይሆን? ኢትዮጵያ የምትባል አገር በሌለችበት ወያኔ ራሱን የጎሣዎች ንጉሥ አድርጎ ሰይሟል፤ ትግሬና አማራ ሲጨራረሱ ወያኔ ሌሎች ጎሣዎችን በጣቶቹ ጨፍልቆ መያዝ የሚችል መስሎታል፡፡
የተጠቀሱትን የወያኔ ባለሥልጣኖች አስተሳሰብ (?) ስንመረምረው የዛሬ ሃያ አምስት ዓመታትና ከዚያ በፊት የነበራቸውንና ኢትዮጵያን ለውርደት አዘቅት ያደረሳትን አስተሳሰብ እንዳልለወጡ ያሳያል፤ የሚያስፈራውም ለዚህ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ወያኔን ‹‹ልጆቻችን›› እያለ የሚመክትላቸው እነሱ ለሞቱት ቤተሰቦችና አካል ጉዳተኞች ለሆኑት ወያኔዎች የሚያደርጉትን የይስሙላ እርዳታ መሪዎች ነን የሚሉት ከሚኖሩት ኑሮና ከሚያገላብጡት ዶላር ጋር ስናስተያየው በሰውነት ደረጃም ሆነ በጎሣ አባልነት ደረጃ፣ በዜግነትም ደረጃ ሆነ በጦርነት ተሳታፊነት ደረጃ ምንም ዓይነት እኩልነት የማይታይበት መሆኑን በየቀኑ በየሰፈራችን ከሚኖሩ ወያኔዎች ኑሮ እያየን ነው፤ የወያኔ መሪዎች እነሱ የጥይት ባሩድ ሳይሸታቸው የትግራይን ወጣቶች ለጥይት እየማገዱ የደለበ ኑሮ ይኖራሉ፤ በኢትዮጵያውያን ሕይወት፣ ደምና አጥንት የሰላም ጠባቂ ኃይል እያሉ ለተባበሩት መንግሥታትና ለአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያውያንን እያከራዩ የገቢ ምንጭ አግኝተዋል፡፡
ትግሬዎች በወያኔ አገዛዝ ተጠቅመዋል የሚባለውን ወሬ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፣ በኢትዮጵያም ስቃወም ብዙ ዓመታት ሆኖኛል፤አሁንም እቃወመዋለሁ፤ በየቀኑ የሚያጋጥሙኝ ያፈጠጡ እውነቶች ከጅምላ ወሬው ጋር አይሄዱልኝም፤ አንድ ጓደኛዬ ጫማውን ሲያስጠርግ አጠገቡ ቆሜ እያወራን ሳለ አንድ ቄስ የዕለት ምግባቸውን ለመኑ፤ የችጋርን ምንጭና መንገድ ለማወቅ ሁልጊዜ ለማኞችን ከየት እንደመጡ እጠይቃለሁ፤ ቄሱን ስጠይቃቸው ከአሩሲ ነኝ አሉኝ፤ ተቆጣሁና ለምን ይዋሻሉ! ብዬ ሳፈጥባቸው፣ ምን ላድርግ ትግሬ መሆኔን ስናገር ከስድብ ሌላ ሰላይ ነህ እባላለሁ፤ አሉኝ፤ አራት ልጆቿን ይዛ የምትለምን፣ ከኔ ጋር ተዛምደን ‹እጓል መቀሌ› የምላት ሴት አለች፤ ሌሎች ብዙዎችን መጨመር እችላለሁ፤ እንዲያውም በችግር የሚኖሩ ተጋዳላይ ወያኔዎችንም አውቃለሁ፤ እነዚህ በወያኔ አገዛዝ የተጎዱ እንጂ የተጠቀሙ አይደሉም፤የተጠቀሙ አሉ፤ ግን ለአንድ የተጠቀመ ትግሬ ቢያንስ አንድ ሺህ ያልተጠቀሙ ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡
ለማናቸውም አሁን በቅን ልቡና ተነሣስተን ማሰብ ያለብን ያለፈውን ሳይሆን የሚመጣውን ነው፤ አሁን ማተኮር ያለብን በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ወያኔ ብቻውን በጉልበተኛነት የሠራውን ሳይሆን ለወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በአንድ ላይ ሆኖ በመመካከርና በመተባበር የሚሠራውን ነው፤ አሁን የምንንጠራራው ከወደቅንበት ተነሥተን፣ ዳገቱን ወጥተን፣ የአምላክን በር አንኳኩተን ይቅር ለእግዚአብሔር በማለት ምርቃትንና በረከትን ተቀብለን ለመታደስ ነው፤ እሱ ይርዳን!