>
9:23 am - Tuesday July 5, 2022

የጁነይዲን ሳዶ 4 ውሸቶች [ኤርሚያስ ቶኩማ]

Juneyd Sadoአንድ ወዳጀ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲን ሳዶ ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ከሲሳይ አጌና ጋር ቆይታ እንዳለው ነገሮኝ ቃለመጠየቁን ተከታተልኩት። ከሞላ ጎደል ኦቦ ጁነይዲን ያው ከዚህ ቀደም ወያኔነት በቅቶናል ብለው አሜሪካ ሀገር እንደከተሙ የቀድሞ የወያኔ ካድሬዎች ምንም የተለየ ነገር ሳይነግረን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ስደተኛ ወያኔዎች እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ ጲላጦስ ነኝ ብሎናል። ቃለመጠይቁ የፖለቲከኛ ሳይሆን መኮንን ላእከ ወይም ክበበው ገዳ ኢሳት ላይ ኢንተርቪው የሚደረግላቸው ይመስላል። አይን ያወጣ ውሸት እና ቅጥፈት የሞላበት ኢንተርቪው ነበረ። እኔ በዋነኝነት ሰውዬው በቃለመጠይቁ ከገለፃቸው የሚከተሉት አብይ ጉዳዮችን ላይ የበኩሌን ማለት እፈልጋለሁ።

1, የኦህዴድ አባል አልነበርኩም

ይህንን ያለው ጁነይዲን ነው። ነገሩ ሳቅ የሚጭር ከመሆኑም በላይ ሰውዬው እውነቱን ከሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሀይምና የማያውቅ አድርጎ የሚያስብ ይመስለኛል። ሰውዬው ኦህዴድ ከመሆንም አልፎ ኦህዴድ ኢህአዴግን ወክሎ ምርጫ የተወዳደረ ከዛም አልፎ በወያኔ አጠራር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበረ ግለሰብ ነው። ሆኖም ሰውዬው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሆንኩት የኦህዴድ አባል ሳልሆን ነው ብሎ የተለመደ ቅጥፈቱን አሳይቶናል። መቼም የወያኔን ባህሪይ የሚያውቅ በሙሉ ወያኔ ኦሮሚያን ለገለልተኛ ሰው አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ከዚህ ቀደም የወያኔ አመራሮች በመንግሥት ስልጣን ላይ የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ እንደመኮንን ማንያዘዋል ያሉ ግለሰቦች ይገኛሉ ብለው ፈገግ እንዳደረጉን ልብ ይሏል። ታድያ ኦቦ ጁነይዲን ኢህአዴግ አባል ያልሆኑ ባለስልጣናት ያሉት ጥሩ ድርጅት ነው ማለት ፈልጎ ይሆን?

2, ስኮላርሽፕ ተልኬ ገንዘብ አጥቼ ነው የተመለስኩት

ይሄ ነው ሌላኛው የኦቦ ጁነይዲን ሳታየር ኮሜዲ። ኦቦ ጁነይዲን ከተሰደደ በዃላ ወይ ጨዋታ ጨምሯል ወይ ነገሮች ተምታተውበታል። ስኮላርሽፕ ትምህርቴን ያልጨረስኩት በገንዘብ ምክንያት ነው ቢልም አሁንም ድረስ በለገጣፎ እና በቦሌ ቡልቡላ የሚገኙ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት ነው። ሆኖም ሰውዬው ትምህርቱን በገንዘብ ምክንያት ነው ያቋረጠው ሲባል ከመሳቅ ውጭ ምን ማድረግ እንችላለን።

3, ሳልፈልግ ነው የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆንኩት፤ እኔ ሳላውቅ ምርጫ አወዳደሩኝ

እነዚህ ሦስተኛ ቅጥፈቶቹ ናቸው ሆኖም እውነታው ይህ ነው። ህወሀት በተገነጣጠለበት ወቅት ከእነስዬ ቡድን የነበሩት እነኩማ ደመቅሣ ሲቀጡ ብልጣብልጡ ጁነይዲን ግብ ከአሸናፊው የመለስ ዜናዊ ቡድን ጋር በመሆኑ ምክንያት ከስዬ ጋር ሲሰሩ የነበሩትን የኦህዴድ አባላት አጋልጦ ነው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሆነው ነገር ግን ሳላውቅ ነው ይላል። ታድያ እነኩማን ያስመታው ፕሬዚዳንት ለመሆን ካልሆነ ምቀኝነት ይዞት ነውን?

4, የኦህዴድ አባላት ክልሉን አናውቀውም በማለት ከሥልጣን ይሸሹ ነበረ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ስብስባ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በሙሉ ተነስቷል የሚለው ቅጥፈት ተጨማሪ ውሸቱ ነው።

በዚህ አባባሉ ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ የቆመ ድርጅት ነውና ለማለት ነው ይዳዳዋል። በዚህ ጉዳይ ላይም ምንም ማለት አልፈልግም። ድፍን የኦሮሚያ ህዝብ እውነታውን ያውቀዋል። ይልቁስ በጣም ያሳቀኝን ነገር ላጫውታቹህ ኦህዴድ በወቅቱ ጠንካራ ነበረ ብሎ ከብሔራዊ ባንክ ዘርፈው ህወሀቶች ኤፈርትን ስላቋቋሙበት ሲጠየቅ ከ77 ረሀብ እህል ሳይሆን ጆንያ ነው የሰረቁት እናም ያንን ጆንያ ሸጠው ባጠራቀሙት ገንዘብ ኤፈርትን እንዳቋቋሙ መለስ እንደነገሯቸው ገልጿል ወዳጆቼ ጆንያው ግን ከምን ቢሰራ ነው እንዲህ በውድ የተሸጠው?
ኦቦ ጁነይዲን እንደዚህ እንደሚል በመገመት ከሳምንት በፊት ፌስቡክ ላይ ያሰፈርኩትን ከዚህ በታች አንብቡት
ኦቦ ጁነዲን ከስድስት ወራት ቆይታ በዃላ ሠሞኑን በየሚዲያው እየቀረበ እንደጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ወያኔን ለማውረድ እኔን ስሙኝ እያለ ነው። በአንድ ወቅት ተወዳጁ የኦሮሚኛ ዘፋኝ ሲዮ ደንደና ለጁነዲን እና ጓደኞቹ እንዲህ ሲል ዘፍኖ ነበረ።
“Budden Oromoo Furdaan ituu jiru
maal barbaacha dhaqxe mana wade gabru” ወደአማርኛ ስንመልሰው
“ወፍራም እንጀራ እያለ ከኦሮሞ ማጀት
ምን ፍለጋ አስኬደህ ወዲ ገብሩ ቤት”
ይህ ግጥም በትክክል የኦሕዴድ አባላትን የሚገልጽ ነው። እንደውሻ ከወያኔ መሪዎች ስር ሲልከሰከሱ ከርመው ዛሬ እንደመልካም ሰው እንደህዝብ ተቆርቋሪ እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ ይላሉ። እኔ ከብዙ ወዳጆቼ ጋር የማያስማማኝ ነገር ቢኖር የወያኔ አባላት የነበሩ ሰዎች እራሳቸውን ሲያገሉ ይቅርታ ይደረግላቸው የሚለው ጉዳይ ነው። እኔ በወያኔ ሰዎች ዙሪያ የይቅርታ ሰው አይደለሁም ላጠፉት ጥፋት መቀጣት አለባቸው ባይ ነኝ። ሆኖም አንዳአንዶቻችን ፃድቅ ለመምሰል ወይም በየዋህነት ሕዝብን ሲበድሉ የነበሩ ሰዎች ከወያኔ ሲጣሉ ላይጣሉም ይችላሉ ይቅርታ ይደረግላቸው ማለት እንወዳለን አሁን ከሰሞኑ እንኳን የሕወሐት 40ኛ አመት ሲከበር አብሮ ሲንጎማለል የነበረ ፣ ህፃናትን በማባለግ የሚታማ አንድ አርቲስት ነኝ ባይ ወያኔ ፀረ ኢትዮጵያ ነውና ሲባል የኢትዮጵያን ባንዲራ አልብሰን በአደባባይ ጀግና ስንለው ነበረ። በግሌ እንኳን ከወያኔ ጋር አይደለም አብሮ ህግ ያረቀቀ ቀርቶ በወያኔ ሰርግ የጨፈረ ለደቂቃም ቢሆን አባል የነበረ ግለሰብ ባለፉት 25 አመታት ሕይወታቸው ላለፉ ንፁሃን ዜጎች ህልፈት እጅ አለበት። ለእኔ የወያኔ አባል የነበረም ሆነ አሁንም በአባልነት ላይ የሚገኝ ሰው በሙሉ ጸረ ኢትዮጵያ ነው። በምንም አይነት አመክንዮ ሕዝቤን ልጥቀም ብሎ ሰው የወያኔ አባል አይሆንም። የጁነዲንም እንደዛው ነው። በየሚዲያው እየቀረበ አስተያየት እየሰጠ ነው። የሚዲያ ሰዎች ስለኢህአዴግ ብዙ ስለሚያውቅ ነው እንግዳ ያደረግነው ይሉናል ግን እኛ ከምናውቀው ውጭ ምን አዲስ ነገር ነገረን? የሕወሐት የበላይነት አለ ይላል ይሄ ምስጢር አይደለም ሊወራ የማይገባው ሁሉም የሚያውቀው ነው። ጁነዲን ሳዶ አማራውንና ኦሮሞውን ለማጫረስ ከሕወሐት ተቀብሎ ስለፈፀመው እልቂት አይነግረንም፤ ለገጣፎ አካባቢ ገበሬዎችን አፈናቅሎ ለሕወሐት ሰዎች ስለሰጠው መሬት፤ ታይላንድ አሁንም ድረስ በስሙ ስለሚገኘው ገንዘብ ምንም ሊነግረን አልቻለም ደግሞም አይነግረንም።

ምክንያቱም ሰውዬው ፀረ ህዝብ ፀረ ኢትዮጵያ ነው። የቀድሞ የወያኔ ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳቢ ናቸው የሚለው ቀልድ ከዘመኑ ጋር አይሄድም ለእኔ ይቅርታ ጠይቀናል አሁን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ነን ብለው በሁለተኛ ቢላ የኢትዮጵያን ህዝብ እየበሉ ከሚገኙ ፀረ ህዝቦች ይልቅ ስራው አሳፍሮት ተሸማቆ ለሚኖረው ታምራት ላይኔ የተሻለ አመለካከት አለኝ። ማንም የቀድሞ የወያኔ አባል የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃ በማውጣቱ ረገድ ጥሩ ድጋፍ ይሰጠናል ብዬ አላስብም ምክንያቱም አእምሯቸው በጥቅም ወይኗል (ወያኔ ሆኗል) እናም እባካችሁ አንድ የወያኔ ባለሥልጣን በጥቅም እየተጣላ በወጣ ቁጥር የጀግና አቀባበል እያደረጋችሁ መሳቂያ አታድርጉን።

Filed in: Amharic