>
8:17 pm - Tuesday January 31, 2023

ዓለምአቀፍ ማስጠንቀቂያ፤ ለምዕራባውያን ፖሊስ አውጪዎች፤ ለጋሽ አገራትና ባለጉዳዮች! [ኦባንግ ሜቶ የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር]

በህወሃት/ኢህአዴግ ላይ የከረረ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል!!

14729084_1361222397251379_4462207546209365267_nዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት የሚያራምደው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብን ድምጽ ለማፈንና ጨቋኝ አገዛዙን ለማስፈን እንደመሆኑ በራሱ ላይ ያወጀው የመጥፊያ አዋጅ መሆኑና ይህም ያለጥርጥር ለመጥፊያው ያዘጋጀው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

አዋጁን በተመለከተ በተሰጠው ዝርዝር መረጃ መሠረት ጨቋኙን ድንጋጌ የጣሱ ከ3-5 ዓመታት በሚደርስ እስራት የሚቀጡ ሲሆን ዜጎች ከተከለከሉት በርካታ ነገሮች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፤
• በዳያስፖራ የሚገኙ ሁለት የቲቪ ጣቢያዎች ማለትም ኢሣትና ኦሚማ (የኦሮሞ ሚዲያ መስተጋብር OMN) መመልከት በጥብቅ የተከለከለ ነው፤
• እንደ ጀርመን ድምጽ እና አሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ያሉትን የውጪ ጣቢያዎችን መስማት የተከለከለ ነው፤
• ማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክና የመሳሰሉት) ላይ መጻፍና አስተያየት መግለጽ እስከ 5ኣመት በእስራት ያስቀጣል፤
• ቫይበርና ኋትስኧፕ የተሰኙ የመነጋገሪ መንገዶች በጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፤
• ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ምልክት ማሳየት፤ የፖለቲካ ሃሳብ መስጠት፤ እጅን አጣምሮ ወደላይ በማድረግም ሆነ በሌላ መንገድ የሚደረጉ የተቃውሞ ምልክቶች በሙሉ የተከለከሉ ናቸው፤
• ዲፕሎማቶች ያለፈቃድ ከአዲስ አበባ ዙሪያ 40ኪሜ (25 ማይልስ) ርቀው እንዳይሄዱ ታግደዋል፤
• ዋና ዋና በተባሉ መሰረተልማቶች ፕሮጀክቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ እርሻዎች፣ ወዘተ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ድረስ የሚቆይ የሰዓት ዕላፊ ተደንግጓል፤
በትላንትና እና በዛሬ መካከል ከገዢው ህወሃት/ኢህአዴግ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 2700 ዜጎች በኦሮሞ እና በአማራ ሥፍራዎች ታስረዋል፡፡ ይህ በአገዛዙ ያመነው ሲሆን ቁጥሩ ከዚህ እንደሚበልጥ የብዙዎች ግምት ነው፡፡

በየቦታው የሚደረገው አፈና፣ እንግልት፣ ሰቆቃ እንዳለ ሆኖ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽሙ የታዘዙት የሠራዊት አካላት በዜጎች ላይ የፈለጉትን እንዲፈጽሙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፈለጉት ቤት እየገቡ ይበረብራሉ፤ የፈለጉትን ዕቃ ይወስዳሉ፤ ሥልኮችን፣ ቴሌቪዥኖችን፣ ሳተላት ዲሾችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ ሌሎችንም ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ይዘርፋሉ፡፡ ጠያቂም ሆነ ከልካይ የላቸውም!

የእኛ የአሁኑ ስጋት ህወሃት/ኢህአዴግ ለራሱ መውጫ በማሳጣት እየፈጠረ ያለው አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ራሳቸውን (ህወሃት/ኢህዴግን) ጥግ በማድረግ እና መውጫ በማሳጣት ለመኖር በሚያደርጉት መፍጨርጨር ብዙ ዓመጽን እየፈጠሩና ብዙ ሕይወትንም እያጠፉ ነው፡፡ ሕዝብን እያጠቁ እድናለሁ፣ ሥልጣኔን እቀጥላለሁ ብሎ ማሰብ የሞኝ ሙከራ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የማያስተማምን ሁኔታ ራሳቸው እየካዱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የራሳቸውን የመውጫ በር እየደፈኑ ነው፡፡

እንዲህ ያለው ኃይልን የመጠቀም፣ የጭከና፣ ሕዝብን የማሰር፣ የመርገጥ አካሄድ የራሳቸውን ሕዝብ፣ ራሳቸውን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ የአፍሪካ ቀንድን፣ ምዕራባዊ መንግሥታትን፣ ለጋሾችን እና ሌሎች ባለድርሻዎችን በአደገኛ ሁኔታ እንዲገቡና አደገኛ ውጤት የሚያመጣ ነው፡፡ እንዲህ ያለው መብት የሚረግጥ ሕግ የሚያመጣው ነገር የበለጠ ቁጣ፣ የበለጠ ዓመጽ ነው፡፡ ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያን ከሰሜን ኮሪያ ጋር እያነጻጸራት ያለ ብቻ ሳይሆን እንደ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሶሪያና ሊቢያ የከሸፈች አገር ሊያደርጋት የሚችልም ነው፡፡

ስህተቱ ያለው ህወሃት/ኢህአዴግ ዘንድ ቢሆንም ሌሎች አሁን ያለውን የአገሪቱን ሁኔታ መቀየር እና በአገሪቱ ላይ ልዩነት ማምጣት ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ የአሜሪካ ፖሊሲ፣ ዕርዳታ እና ሕግጋት የህወሃት/ኢህአዴግ ሹማምንትን ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይችላል ብለን እናምናለን፡፡

ሌሎች ለጋሽ አገራትና ባለጉዳዮች ማለትም የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮጳ ማኅበር፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ አውስትራሊያ፣ እና ሌሎችም በተለይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የተባበረ ጥረት ቢያደርጉ ሊከሰት የሚችለውን በዘር ላይ የተነጣጠረ ጥቃት እና ውድመት ከወዲሁ መቀልበስ ይቻላል፡፡ ውድመት ከጀመረ ቆይቷል፤ መነጋገርና መደማመጥ ስለሌለ የሰላም ድምጾች ቁጣን ማብረድ የሚችሉበት ሁኔታ ሁሉ እያከተመ ነው ያለው፡፡

በአብዛኛዎቹ ለጋሽ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሁለትዮሽ መመሪያ እያወጡና እየተከተሉ በሌሎች “ችግር ፈጣሪ” አገራት በሚሏቸው ላይ የሚያሳዩትን ዓይነት የከረረ አደራረግ በተመሳሳይ አለማድረጋቸው፤ በኢትዮጵያ እየደረሰ ላለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዝምታን መምረጣቸው ወይም ለስለስ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ተግሳጽ ብቻ መስጠታቸው፤ እንደሌሎቹ በተመሳሳይ ዓይን አለማየታቸው ለችግሩ መባባስ ብዙ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ይህ አሠራር ህወሃት/ኢህአዴግን የልብ ልብ የሰጠው ብቻ ሳይሆን ራሱን በማጥፋት ተግባር እንዲሠማራ በማድረግ ማቆም ይቻል የነበረውን ውድመት ያለተጠያቂነት እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

በተለይ በአሁኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳር የሚባለው እንዳይኖር ያደረገ ሲሆን በተለይ የመያዶች ህግ የሲቪል ማኅበረሰቦች እንዳይኖሩ ያደረገ፤ የጸረ ሽብር ሕጉ ደግሞ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ሁሉ በአሸባሪነት ተመድበው ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ የዴሞክራሲ ድምጾች፣ ወዘተ ለእስር፣ ለሞትና ለስደት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ህወሃት/ኢህአዴግ መቶ በመቶ የፓርላማ ወንበር መቆጣጠሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ በዘር ፖለቲካ፣ በሃብት ዘረፋ፣ በሙስና ተዘፍቆና ይህንኑ ዓላማውን ለማስፈጸም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን እየገደለ፣ እያሰረ፣ እያሰቃየ … እንዳለ በግልጽ እየተመሰከረ እያለ ለጋሽ አገራት ትርጉም የሚሰጥ እርምጃ አለመወሰዱ የሚያስደነግጥ ነው፡፡ በተለይ ይህ ከአገሪቱ ህዝብ ስድስት በመቶ የሚሆኑት አናሳዎች የተቆጣጠሩት አፓርታዳዊ የዘር ፖለቲካ በሥርዓቱ ላይ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ባለጉዳዮች መላ ካላሉት ወደከፋ የዘር ዓመጽ እንደሚመራ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ህወሃት የኔ ነው ያለው ሕዝብ ባብዛኛው እንደሚባለው የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ናቸው ቢባልም አሁን ባለው አደገኛ አካሄድ የመጀመሪያ ተጠቂ የመሆናቸው ጉዳይ ከደኅንነታቸው ጋር ተያይዞ ያሳስበናል፡፡

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የተዛባ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን እንደ ተረጋጋች፣ ልማታዊ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት አገር አደርጎ በመውሰድ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን የሰላም አስጠባቂ ሠራዊት እንድትልክ እስከመፍቀድ የተደረሰው በምን ስሌት ይሆን? ይህ የሚላከው የዕርዳታ ገንዘብ ሁሉ እየሰራ እንዳልሆነ ይታወቅ ዘንድ ያሻል፡፡ ዜጎች ተስፋ በመቁረጥ የዓመጽ እርምጃ በመውሰድ እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ ውድመትን ማስከተላቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህ የጭከና አካሄድ መልሶ ራስን እንደሚጎዳ ወዳጅ ሆነው እየቀጠሉ ባሉት አንዳንዶች ላይ የረጅም ጊዜ በሌሎች ላይ ደግሞ የአጭር ጊዜ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ወሳኝ ጣልቃገብነት ካልተደረገ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በየመን፣ በሶሪያ እና በሊቢያ መንገድ ጅማሬ ላይ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ስለዚህ ከአሜሪካ መንግሥት የምንሰማው ተመሳሳይ “ጉዳዩ አሳስቦናል” የሚል የቃላት ሽንገላ በላይ ህወሃት/ኢህአዴግ ላይ ተጽዕኖ የሚመጣ ለውጥ መደረግ አለበት፤ ይህም ህወሃት/ኢህአዴግን ቢያንስ የሚከተሉትን እርምጃዎች እንዲወስድ የሚያሳስብ እርምጃ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እነዚህም፤
1. ሕዝብን ማሰር፣ መግደል እንዲቆም
2. የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ፤
3. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲሰርዝ፤
4. ኢንተርኔትን፣ ሚዲያን እና ሌሎች የመገናኛ መንገዶችን እንዲከፍት፣
5. የመያዶችንና የጸረ ሽብር ሕጎቹን እንዲሽር፤
6. ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጸሙትን ወንጀሎች እንዲመረምሩ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎችን እንዲፈቅድ፤
7. የሽግግር ባለአደራ መንግሥት እንዲመሠረት የሚያስችል ውይት እንዲጀመር እንዲፈቅድ፤
መደረግ አለበት፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ የሚከተሉት የከረሩ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፤ እነዚህም የህወሃት/ኢህአዴግ ንብረትን ማገድ፣ ወደ አሜሪካ እንዳይበሩ የጉዞ ዕገዳ ማድረግ እና ሌሎች እርምጃዎች ሊጨምር ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ ህወሃት/ኢህአዴግ የማይሰማ ከሆነ የሚሰጠው ዕርዳታ በሥልጣን እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው ስለሆነ ዕርዳታ መቆም ይገባዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኦባማ አስተዳደርና ሌሎች ለጋሽ አገራት በጋራ አቋም በመውሰድ በከፍተኛ ሁኔታ ሊመጣ ያለውን አደጋ ሊታደጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ይህንን በዘር ላይ የተመሠረተ አፓርታይዳዊ አገዛዝ እንዲቀጥል መደገፍ የአፍሪካ ቀንድን ወደ አለመረጋጋት በመውሰድ ከዚያም አልፎ ለዓለም ሰላምና መረጋጋት አደጋ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህ ዕድል እያለና ጊዜው ከማለፉ በፊት ለጋሽ አገራት እርምጃ እንዲወስዱ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም፤ የህወሃት/ኢህአዴግ ተግባር ከመጠን በማለፍ ገደቡን ለቅቆ በመሄዱ በሥልጣን ለመቆየት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ስለዚህ ለእነርሱም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ለትግራይ ተወላጆች የሚጠቅመው ነገር በሰላም ከሥልጣን ቢለቅቁ ነው፤ ምናልባት ያመጡትን ጥቂት ውጤት ከነጥፋታቸው ኢትዮጵያውያን ተቀብሎላቸው ይህንን ጊዜ የመጨረሻቸው ቢያደርጉት በጣም የሚጠቅም ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላምን፣ ትርጉም ያለው ለውጥ፣ ፍትህና ዕርቅ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲሰፍን ተባብረን ለመሥራት ዝግጁዎች ነን፡፡

ይህን መልዕክት ተቀብለው ምላሽዎን እንደሚሰጡን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

አክባሪዎ፤
ኦባንግ ሜቶ
የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር
አድራሻ፤
910- 17th St. NW, Suite 419
Washington, DC 20006 USA
Email: Obang@solidaritymovement.org
Website: www.solidaritymovement.org

ይህ ደብዳቤ ለሚከተሉት ግልባጭ ተደርጓል፤
ለአሜሪካው ፕሬዚዳንትን ኦባማ፤ ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጆን ኬሪ፤ የብሔራዊ ጸጥታ ጉዳይ አማካሪ ሱዛን ራይስ፤ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር፤ በብሔራዊ ጸጥታ ጉባዔ የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ ግራንት ሃሪስ፤ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአፍሪካ ጉዳዮች ጸሃፊ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፤ የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊ/መ ቦብ ኮከር፤ በአሜሪካ የህዝብ ምክርቤት የውጭ ጉዳዮች ሊ/መ ኤድዋርድ ሮይስ፤ በምክርቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊ/መ ክሪስ ስሚዝ፡፡

ለጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ መርከል፤ ለካናዳ ጠ/ሚ/ር ጀስቲን ትሬዱ፤ ለታላቋ ብሪታኒያ ጠ/ሚ/ር ቴሬሳ ሜይ፤ ለስዊድን ጠ/ሚ/ር ስቴፋን ሎፍቨን፤ ለኖርዌይ ጠ/ሚ/ር ኤርና ሶልበርግ፤ ለፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንዴ፤ ለኔዘርላንድስ ጠ/ሚ/ር ማርክ ሩት፤ ለዴንማርክ ጠ/ሚ/ር ላርስ ሎክ ራስመሰን፤ ለእስራኤል ጠ/ሚ/ር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፤ ለአውስትራሊያ ጠ/ሚ/ር ማልኮም ተርንቡል፤ ኒውዚላንድ ጠ/ሚ/ር ጆን ኪይ፤ ለህንድ ጠ/ሚ/ር ናሬንድራ ሞዲ፤ ለጃፓን ጠ/ሚ/ር ሺንዞ አቤ፤ ለኮሪ ፕሬዚዳንት ፓርክ ግዩንሄ፤ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፤ የዘርማጥፋት መከላከያ ልዩ አማካሪ አዳማ ዲዬንግ፤ ለጄኖሳይድ ዎች ኃላፊ ግሬጎሪ ስታንተን፤ ለሮም ካቶሊካዊት ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ፤ ለእንግሊዝ የካንተርበሪ ሊቀጳጳስ እና ከዚህ በታች ለተጠቀሱት የዓለምአቀፍ ድርጅቶችና የሚዲያ ተቋማት በግልባጭ ተልኳል፡፡

President of Enough Project; International Crisis Group; Council on Foreign Relations; Jews against Genocide; High Commissioner of the United Nations Human Rights; International Federation for Human Rights (FIDH); International Commission of Jurists�International; Service for Human Rights�Protection International; World Organization Against Torture (OMCT); President of Human Rights Watch; President of Amnesty International; Permanent Member of the UN Security Council; President of the African Union; Head of State Member of the European Union; President of the European Union Commission; Member of the European Union Parliament; Africa Confidential; Al Jazeera; BBC; The Guardian; New York Times; Washington Post; Wall Street Journal; Bloomberg News; MSNBC; CNN; REUTERS AFRICA; The East Africa; Deutsche Welle Radio; VOA Amharic; VOA-English; ESAT; OMN

Filed in: Amharic