>

የማለዳ ወግ ... ደፍሮ ስለሀገር መሞትና ፈርቶ ስደትን መምረጥ! [ነቢዩ ሲራክ]

* ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተገኝቷል !
* ተሜ ኢትዮጵያ አስቀደመ ፣ እኔ ፈሪው እናቴን
* የኢትዮጵያ ፍቅር ፣ የወላጅ እናት ፍቅር … !!!

ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተገኝቷል …
==============================
nebiyu-sirak-yealeda-wrg-17122016የህግ ታሳሪ ፍርደኛ ሆኖ ለአስር ቀናት ከነበረበት ወህኒ ” የለም ” ተብሎ የብዙዎቻችን ልብ ተሰብሮ መረጃውን ስንከታተል የቆየነው ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን መገኘቱን ሰማሁ። በማለዳው መረጃውን ያደረሰን ሌላው ደፋርና ቆፍጣና ወንድሙ Tariku Desalegn ሲያደርሰን የተሜ የጤና ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ግልጿል ።

” እርግጥ ነው ተመስገንን አግኝተነዋል ግን…ቢሆንም ግን ለ10 ቀናት ያህል በምን ምክኒያትና እና በማን ትእዛዝ የዝዋይ እስር ቤት ሀላፊዎች ተመስገን ደሳለኝ የሚባል ሰው አናውቅም ያሉበትን ምክኒያት ማወቅ እንፈልጋልን፡፡ ዛሬ ተመስገንን ስናገኝው ለብቻው በተለየ ቦታ በተለምዶ የመንግስት ታሳሪና ቤተሰብ በማይገናኝበት ቦታ በ 7 ወታደሮች ተከቦ መልስም ጥያቄም በሌለበት ሁኔታ እንድናገኝው ለምን ተደረገ? እንዲሁም ተመሰገን ሲረመድ እግሩ እንደሚያስቸገረው አይተናል በተጨማሪም በሀይለኛ ጨጓራ ህመም አንደታመመ ነግሮናል እነዚህ ሁለት ህመሞች በጨራሽ ተመስገን ከዚህ ቀድሞ ታሞቸው የማያቁ ናቸው አንዴት አንዲህ ሊሆን አንደቻለ አንዲነገረን አንፈልጋልን፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታ በለማቀፍ ተቋማትና በሚዴያዎች ተፅኖ Facebook ጨምሮ በተፈጠረው ጫና ምክኒያት ዛሬ ተመስገንን እንዳሳዩን ግልፅ ነው፡፡ ነገ እና ከነገ ወዲያ ምን ሊሉ ወይም ሊፈጥሩ አንደሚችሉ አይታወቀወም፣፣ በአጠቃለይ በተመሰገን ላይ ስለተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ አሁንም ከመንግስት መልሽ አንፈልጋለን
ታህሳስ 8/2009ዓ.ም ”

የማይከበር ህግ አለንና …

ይህም ከበደል ላይ በደል ተፈጽሞበት የተገኘው መረጃ ድንዛው ጠፍቶ ሲከላተሙ ለ10 ቀን ለሰነበቱ እናት ትልቅ የምስራች ነው ! እንኳን ደስ ያለዎ እማማ ! የተመስገን መታሰር ሲያመን በእስር ላይ ደጋግሞ የሚፈጸምበት በደል ለእኔና ለቀረነው ግን ህግ በህግ አስፈጻሚና አስከባሪ እንዳሻው ከሚደጥበት ሀገር እንዳለን ማሳያ መረጃ ነው ወይ በግኖ 🙁 ህግ የሚከበር ቢሆን ኑሮ መታሰር ባለከፋ ነበር ፣ ከታሰሩ በኋላ እንኳንስ ተከራክሮ መብትን ማስከበር ፣ የታሳሪ ህግ ደግግሞ ሲዳጥ ነዋሪው በአገዛዙ እንዴት እምነት ይኑረው ? ቂም በቀል ትይዞ በህግ ከለላ በወህኒ ባለ ሰው ህግ በሚጣስበት ሀገርስ እንዴት ከወህኒ ውጭ ያለው ሰው በህጉ ላይ አመኔታ ይኖረዋል ? ይህ ሁሌም በውስጤ የሚጉላላ ጥያቄ ነው ፣ መልስ የሌለው !

የኢትዮጵያ ፍቅር ፣ የወላጅ እናት ፍቅር … !!!

ተሜን ሳስብ ከእናቱ አስበልጦ የሚወዳት ኢትዮጵያና የተሜ እናት ይታዩኛል ፣ ልጃቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቱን ተጠቅሞ ጻፈ ብለው አስረው ፈረዱበት ። ከዚያም ልጃቸውን ፣ ደጋፊያቸውን አስረው አቅም አልባ ፣ ስንቅ ቋጣሪ ያደረጓቸውን የእድሜ ባለጸጋ እናቱን ሁሌ አስባቸውና እታመማለሁ ፣ … አንዴ ተደበደበ ፣ በጨለማ ታሰረ ፣ አንዴ ህክምና ተነፈገው ፣ ጠያቄ ተከለከለ ፣ አሁን ደግሞ ጠፋ ሲባል የእናት ክልትማቸውን በራሳችሁ ውስጥ ተመልከቱትና ስቃይ መከራቸውን እሰቡት … እኔ ሰቆቃው ሁሌም ይታየኛልና እናቴ ይሆኑና ልቤብ በሀዘን ይሰብሩታል 🙁

ጋዜጠኛ ተመስግን ከእናቱ ኢትዮጵያን አስቀድሞ መከራን እስከቀራንዮ ለመቀበል የቆረጠ ደፋር የዘመኔ ጀግና ነው ! እኔ ከእናቴ ኢትዮጵያን ያላስቀደምኩ ደካማ ፍጡር ነኝ ፣ ሀገሬን ኢትዮጵያን ከእናቴ አስበልጨ ያለመውደዴን የማውቀው ስለ እስር ፣ ስለ እናቴ እንግልት ሳስብ ነው ፣ በውስጤ የታመቀውን ፍርሃት አለ ! እናቴን እየናፈቅኩ ርቄየታለሁ … ምንም እንኳን በአረቡ አለም ስደት ከወገኖቸ መረጃ ስላቀበልኩ በሚደርስብኝ ዛቻ ቂም ቋጥረው ” ያስሩ ያንገላቱኛል !” ብዬ ስለሰጋሁ ከእናቴ ጋር ከተለያየሁ አመታት ነጉደዋል ። መረጃ ማቀበሉን ፣ መታሰር ፣ መገረፍ ፣ መገደሉን በፍጹም አልፈራውም ! የምፈራው የ88 ዓመት እናቴን እንዳያንገላቷት ነው ፣ እናቴ ለአንድ ቀን አንገቷን ሰብራ ማየት አልሻም ! … ከምንም በላይ የተገላቢጦሽ በመጦሪያዋ ሰዓት የጠዋሪ ልጇን ስንቅ አቀባይ ለማድረግ አልሻም ! ይህን ከማድረግ ከእናቴ ጋር ሳንገናኝ ብንለያይ እመርጣለሁ 🙁 ይህ የፈሪው አቅመ ደካማ ፍላጎት ነው ፣ !

ሁሌም ጋዜጠኛ ተመስገንንና የቀሩትን የህሊና እስረኛ ወገኖቸን ሳስብ አምርሬ የማስበው ይህንኑ ነው ! እነሱ ከተራው የእናት ፍቅር ሀገርንና የወገንን ፍቅር አስቀድመው በመሰዊያው ላይ ናቸውና እጅጉን አከብራቸዋለሁ ! በተለይ የትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን የልብ ጽናትና ስለ ኢትዮጵያ ፍቅር ለመሞት መቁረጥን ከጎኑ ተቀምጭ አጫውቶኝ ያውቃለሁ ፣ ሁሌም በመንፈስ ጥንካሬው ተሜን እኮራበታለሁ ፣ የእኔና የተሜ ልዩነት እሱ ከእናቱ ኢትዮጵያ አስቀድሞ ግፍ ማስተናገዱ ፣ ተመስገን ስለሚሞትላት ሀገረ ኢትዮጵያ እኔ ከኢትዮጵያ አስቀድሜ ስለ አንዲት እናትና ስለልጆቸ ፍቅር መሰደድ መምረጤን ነው 🙁 ሁሉም ያማል 🙁

የቸር ያድርገው !

ነቢዩ ሲራክ
ታህሣሥ 8 ቀን 2009 ዓም

Filed in: Amharic