>
5:14 pm - Friday April 20, 6660

''....ቢያንስ ለራሳችን መዋሸትን እናቁም።'' (ፈቃደ ሸዋቀና)

Feqade Shewaqenaአንዳንድ ጊዜ ቀላልና ግልጽ ነገር ለምን እንደሚሰወርብን አይገባኝም። በኢትዮጵያ የቱንም ያህል ቢጎለብት አንድ ጎሳ ወይም ብሔር ብሔረሰብ ወይም ጠበብ ባለ በተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል (Region) የተደራጀ ሀይል የወያኔን ስርዓት ማስወገድ አይችልም። አራት ነጥብ። በዚህ መንገድ ለማሸነፍ የመነመነች እድል አለች ቢባልም እንኳን በጣም ከባድና ብዙ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ትግል ነው የሚሆነው። በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ በየጎሳው (ብሔር ብሔረሰቡ) የተደራጁት የተቃውሞ ሀይሎች ህብረ ብሄር የፖለቲካ ሀይሎችን ጨምሮ ሁሉም መተባበርና የጋራ ስትራቴጂ መንደፍ ብቻ ሳይሆን ትግላቸውንም ማስተባበር ይኖርባቸዋል። ከዚያ በፊት ደግሞ የጋራ የሆነ ራዕይ ሊኖራቸውና ርስበርስ እንደባላንጣ መተያየታቸው ሊቆም ይገባል ማለት ነው። ልዩነት ቢኖራቸውም ልዩነታቸውን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ማውረድ ይኖርባቸዋል። በቅርቡ አርበኞች ግንቦት7 ያደረገው አይነት ትብብር በኔ አመለካከት ብልህ አካሄድ የመስለኛል።

እስካሁን በተለያየ መንገድ የማይግባቡና የተራራቁ ሁሉ የሚያቀራርብ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል። በጠብ የሚተያዩም ድርጅቶችና የየብሔረሰቡ ልሂቃን ይቅር መባባል ይኖርባቸዋል። ወያኔ በግሉ አንድ ጎሳ የሚያደርገውን የነጻነት ትግል ለማስጨንገፍ የሚያስችል የዳበረ ስልት አለው። አንድ ጎሳ በግል ጎልብቶ ሲወጣ ሌሎች የባሰ እንዳይመጣ ይፈራሉ። ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ፍርሐት ስለሆነ ማሰቀረት አይቻልም። ለገዥዎች ማኒፑሌሺንም ይመቻል። ጎልብቶ የሚነሳው ብሔረሰብ ምን ያመጣ ይሆን የሚል ፍርሐትና ጥርጣሬ በሌሎቹ ዘንድ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ይህ ደግሞ ለገዥዎች በጣም ይመቻል።

እኔ አሁን ኦነግን ከመሳሰሉ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ከሆኑና ከነበሩ ጋር ቀደም ሲል በነበሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ላይ ተነስቶ ሂሳብ ካላወራረድን የሚሉ ፎካሪዎች ይገርሙኛል። እነዚህ ሂሳቡንም አያወራርዱም ድል የሚገኝበት ስፍራም አይደርሱም። የኦሮሞ ልሂቃንን ጨምሮ አንዳንድ ብሔርተኞች ደግሞ መጭው ጊዜ ላይ ከማተኮር ይልቅ ገና በግልጽ ባልተጻፈና ብዙ ክርክር ባልተካሄደበት ታሪካችን ላይ አንዳንዱም ፈጽሞ ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ በተጻፈ የውሸት ታሪክ ላይ ያላቸውን ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ማንሳት ይኖርባቸዋል። ከሁሉ በላይ ዋናው ነገር መጭውን ዘመን የተሻለ ማድረግ ላይ መስማማትና መወሰን ነው የሚሻለው።

ለምሳሌ እኔ በግሌ በኦሮሞ ድርጅቶችና ትልቅም ይሁኑ ትንሽ መሪዎቻቸው ላይ እሽኮለሌ የማልወርደው አለመግባባት ሲኖርም ቀስ ብዬ የምመለከተው አንዳንዴም ጫማቸው ውስጥ የምቆመውና እንደነሱ ለማሰብ የምሞክረው በዚህ እምነቴ ምክንያት ነው። አንዳንዶች በፈሪነትና ባድርባይነት ሲያዩት ያሳዝኑኛል። የውሸትም የውነትም ቂም እየኮተኮቱና አግድም እየተናቆሩ ነጻነት አመጣለሁ ማለት የህልም እንጀራ መጋገር ነው። ቢያንስ ለራሳችን መዋሸትን እናቁም። አስተሳሰባችን በዚህ አቅጣጫ ካልተቃኘ የመከራ ዘመናችን ረጅም መሆኑን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

Filed in: Amharic