>
9:29 pm - Wednesday February 1, 2023

ስክነት ያድነናል ! [መስፍን ማሞ ተሰማ]

እኛ እኔን አቅፎ ደግፎ
እኔ በኛ ውስጥ እፎይ ብሎ አርፎ
እንዳይኖር የሚጠናወት ታሪክ መጣ
የእኛና የእኔ አንድነታቸው ላንዳፍታም ቢሆን ቅጡን ሊያጣ።

እኔ እኛን ሰምቶ ሲኖሩ
እኛም እኔን ሹሞ ሲኖሩ፤ አንድነት ሰፍኖ በምድሩ፤
ህሊና ድንገት አቀንቅኖ፤ አእምሮ ድንገት ቢፈነድቅ
እኔ በዚህ ሁል መከሰት
ከኛ ፈጠረ ልዩነት።

ዮሐንስ አድማሱ “ታሪክ” መጋቢት 1965 ዓ/ም

************************************
አንድ ፤

እርግጥ ነው ዛሬ ዘመን (በስደት ዓለም) ኢትዮጵያዊነት ጠልሟል። ሀቅ ነው ኢትዮጵያዊነት በፅኑ ታሟል። ዕውነት ነው ዛሬ – “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለት ‘ባዶ’ነት ፤ ‘ቅል’ነት፤ ‘ፅናፅል’ነት . . . ነው ይባል ጀምሯል። እርግጥ ነው ዛሬ ላይ “በቅድሚያ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለት ‘ያስፈራን?’ ጀምሯል። ዛሬ ላይ ‘ጀዋር’አዊነት ተንሰራፍቷል – በቅድሚያ “ዘሬን” ነኝ ማለት። ሀቅ ነው ዛሬ ጊዜ ‘ፀአራርሳ’ዊ(*) ፕሮፓጋንዳ ፋሽን ሆኗል – የዘር ማንዘር ማንነት እንጂ ኢትዮጵያዊነት ብሎ ማንነት አልነበረም ፤ የለም፤ አይኖርም – ማለት።

ቢጎመዝዝም ሀቅ ነውና ዛሬ ጊዜ “መለስ አዊ” ከ’ወርቅ’ ዘር መገኘትን – ሁሉም በየዘሩ ያዜመው ጀምሯል – ቢለያይም ቋንቋው ፤ ቢለያይም ዜማው። ዕውነት ነው በዚህ ዘመን ‘ዘሩን’ ያላስቀደመ ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ የሚል – ካድባር አውጋሩ ከሰፈር ከጓደኛ፤ ከጀማው ከማህበር – ይገለል ጀምሯል። ምስጢር ይነፈጋል ፤ ይጠረጠራል ፤ ይብጠለጠላል . . . “የኛ ደም የለውም” ይላሉ። ስለ ‘እኛ’ ለመታገልም ሆነ ለመቆርቆር ለመቆምም ሆነ ለመሞት በቅድሚያ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ሳይሆን “የኛ ደም” ንጥር ሊሆን ይገባል ይላሉ።

ዛሬ ዘመን ‘ኢትዮጵያዊ ነኝ’ ማለት ‘የኢምፓየሯ ቃፊር’ ፤ ‘የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ‘ አፋኝ የጉልበተኞች መታወቂያ ነው ይሉናል – የ’ቅኝ ገዢዎች’ መጠሪያ። ቅድሚያ ‘ኢትዮጵያዊ’ ነኝ ማለትና ‘ኢትዮጵያን ማስቀደም’ ዘመኑ ያፈጀበት ፤ የሁዋላ ቀር ሥርዐት ናፋቂ ፤ የ’አንድነት’ አዝማሪዎች ዜማ ነው ይባል ጀምሯል። ‘ኢትዮጵያዊነት’ ማለት የጦረኞቹ የነቴዎድሮስ ፤ የነዮሐንስ ፤ የነምኒልክ ፤ የነጎበና… ጋሻጃግሬዎች መለያቸው ነው ይላሉ። እናም ‘ወንጀለኞችም’ ያደርጉናል።

‘ኢትዮጵያዊነት’ – ዜግነት ብቻ እንጂ ደም የለውም ይሉ ጀምሯል። ኦሮሞነት፤ አማራነት ፤ ትግሬነት . . . እንጂ መለያ ደሙ – ‘ኢትዮጵያዊ ‘ ደም ብሎ ታሪክ የለም ባዮች ተፈጥረዋል በዝተዋል። በዚህ ዘመን ‘ኢትዮጵያዊ’ ነኝ ማለት ፍዳው በዝቷል። የየዘሩ አክራሪ ተከራካሪ ተቆርቋሪ (በዘመኑ አጠራር አክቲቪስት) ሆኖ መታወቅ መታየት መናገርና መፃፍ ‘ክብር’ ሆኗል። ኦሮሞ ነኝ ፤ አማራ ነኝ ፤ ትግሬ ነኝ፡ . . . የኩራትና የክብር መለያ መሆናቸው ባልከፋ . . . ኢትዮጵያዊነትን ባያጠፋፋ ፤ ባያዳፋ ፤ ባያበሻቅጥ ፤ ባይረጋግጥ። ‘ኢትዮጵያዊ’ ነኝ ማለትም ኩራትና ክብር ቢሆን !! ኢትዮጵያን ማስቀደም ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን – ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነት የሰውነት መብቱን ለማስከበር መቆም – የማይሰራና ጊዜው ያለፈበት ነው – እሚል መዝሙር የዘመኑ የዘር መንፈስ ማቀንቀኛ ባይሆን ! አማራነት ኦሮሞነት ትግራዊነት ጉራጌነት ሲዳማነት . . . ኢትዮጵያዊ የመሆን ድርና ማግ መሆናቸውን ብናምንና ብንኮራበት ብናስከብር ብንቆምለት ብንሰራበት !

(*) ፀአራርሳ ፤ በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ወደር በማይገኝለት ጥላቻ ከዘመቱት ፅንፈኛና በቀለኛ ኦነጋውያን ፕሮፓጋንዲስት ‘ምሁራን’ መካከል አንደኛው ቁንጮ ለሆነውና መኖሪያውን በአውስትራሊያ ሜልበርን ላደረገው ፀጋዬ ረጋሳ አራርሳ (ዶ/ር) መጠሪያ የምጠቀምበት ምህፃር ነው።

ሁለት ፤

እነሆ በዚህ ዘመን (በተለይ በውጪው የስደት ዓለም) ስለ ኢትዮጵያ የሚፃፉትን የሚያነቡ ዐይኖች ፤ ስለ ኢትዮጵያ የሚነገሩትን የሚሰሙ ጆሮዎች መንምነዋል። ኢትዮጵያን ለመበቀልና ኢትዮጵያዊነትም “ጥንቅር” ይበል የሚሉ ልቦች በዝተዋል – ለዘሬ ያልሆነች ኢትዮጵያ ‘ገደል ትግባ’ የሚሉ።

ሲጀመር ኢትዮጵያ የትግሬ ብቻ አልነበረችም። የኦሮሞ ብቻ አልነበረችም። የአማራ ብቻ አልነበረችም – እንደ ድርና ማግ የተቆላለፉ የተመሳሰሉ የተጠላለፉ አንዱ ያለሌላው ምንም የሆኑ (ድር ብቻውን ፤ ማግ ብቻውን ምንም ነውና) የአያሌ ነገዶችና ዘሮች ውሁድ ጭምር እንጂ። የአኝዋኩ የጉርጂው የኮንሶው የአፋሩ የጉራጌው የቆቱው . . . እና ይህንን አበክረን እንላለን ፤ ጆሮ ያለው ይስማ ልብ ያለው ልብ ይበል – “ለዘሬ ያልሆነች ኢትዮጵያ ገደል ትግባ” ስትሉ – ኢትዮጵያ ገደል ስትገባ አፋፍ ላይ ቆሞ የሚተርፍ ዘር የለም – ሁላችንም ተያይዘን ገደል እንገባለን እንጂ ! !

ኢትዮጵያ ዛሬ (በ2ሺዎቹ ዓመታት መጀመሪያዎች) ላይ ለምትገኝበት ህልውናዋን ፈታኝ አጣበብቂኝ የዳረጓት ውለታዋን የገፉ፤ የወለደ ያስተማረና ያሳደገ ማህፀኗን የካዱ በዋናነት በጣሊያናዊ / ግብፃዊ አስተምህሮና ዓላማ የታነፁ ሶስት ነውጠኞች ተጠያቂዎች ናቸው። ሻዕቢያ ኦነግ ህወሃት ። እኒህ ሶስቱ በጋራና በተናጥል በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ መጠነ ሰፊ ወንጀል ፈፅመዋል። በአኝዋኩ በኮንሶው በጉራጌው በአማራው. . . የዘር ማጥፋትና እጅግ አስከፊም ሰቆቃ ፈፅመዋል። ይህ ትውልድ ለተላበሰው ፅልመት እኒህ ሶስቱ ነውጠኞች ተጠያቂዎች ናቸው። ዛሬ ዘመን ኦነግ ከህወሃት ማዕድ ባይገኝም በቦታው ኦህዴድ በባንዳነት አድሮ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ልጆችን በፋሽስት የአጋዚ ጦርና በራሱ የኦህዴድ ታጣቂዎች ለህወሃት ዘመነ ሥልጣን መስዋዕት እያቀረበ ነው። በተቀረው ኢትዮጵያውያን ላይም በተለይም “አማርኛ ተናጋሪው” በሚሉት የአማራ ተወላጅ ላይ ከህወሃት ፋሽስቶችና ናዚስት አጋዚ ጋር ሆነው የሚፈፅሙት “ኦነጋዊ” እና “ህወሃታዊ” ግፍ የትየለሌ ነው።

የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ከቀሪው ኢትዮጵያዊ አካላቸው ጋር መግባባት እንዳይችሉና በባዕዳዊ ቋንቋ ሥነ መንፈስ እንዲያድጉ በግዕዝ ወይ በአማርኛ ፊደላት ኦሮምኛን እንዳይፅፉም ሆነ እንዳያነቡ (ለኢትዮጵያ እሴቶች ካለው በቀለኝነት ጥላቻና ክፋት) የላቲን ቋንቋን ፊደል መጠቀምን በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የደነገገው በ1983 ዓ/ም ከሁለቱ ነውጠኞች ጋር ሥልጣን ላይ የመጣውና የትምህርት ሚኒስትርነቱን ቦታ የያዘው ህወሃት ሳይሆን ኦነግ ነው። ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥም የኦሮሞን ህዝብ በዋናነት ደግሞ የኦሮሞን ወጣት ትውልድ ኢትዮጵያዊነት ለመሸርሸር ይህ የኦነግ ሴራ (በላቲን ቋንቋ ትውልዱን የማነፅ – በቁቤ መፃፍና ማንበብ) የተጫወተው ሥነ ልቡናዊ ተፅዕኖ እንዲህ በዋዛ የሚቀረፍ አይደለም።

(ኦሮምኛ ሀገርኛ በሆነው ፊደል ትምህርት ቢሰጥበትና ቢሰራበት ኦሮምኛ የማያውቅ በቀላሉ እንዲማረው ፤ አማርኛን የማያውቅ ኦሮሞ ደግሞ አማርኛን በቀላሉ እንዲረዳው ይችል ነበር – የኦነጋውያን እርኩስ ክፋት ካልሆነ በቀር ቋንቋ እንዴት ሆኖ ነው ጨቋኝ የሚሆነው? ስለምን እንግሊዝኛ በደቡብ አፍሪካ ወይም በጎረቤት ኬንያ ከዋናው ቋንቋ እኩል ቦታ አለው? ስለምን በኢትዮጵያ ፓርላማና ቤተ መንግሥት ሁሉም በየዘሩ ቋንቋ እንዲናገር አልሆነም?)

ሻዕቢያ ኦነግ ህወሃት በፖለቲካ ዓላማና ግብ ኢትዮጵያን ለማንበርከክና በእግራቸው ሥር ለመርገጥ በቅድሚያ ማንኛውንም በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንን ዜጋ አስተሳሰቡን ማምከን እና ማጥፋት ሲሆን ለዚህም በቀንደኛነት ዐቢይ ኢላማቸው ያደረጉት “ነፍጠኛ የሚሉትን አማራን” ነው። አማራን በጠላትነት መፈረጅ።

እንቆቅልሹ ህወሃት የፈጠረውና “የአማራ ክልል” ብሎ የሰጠው “ብአዴን” እንደ ኦህዴድ ሁሉ በዚህ ወቅት የአማራን ህዝብ የቁም ስቅል የሚያሳዩ ከአማራው አብራክ የወጡ የህወሃት ታዛዦች “ሺህ ባንዳ” ብአዴኖች መኖራቸው ነው። ብአዴን በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት ሲኖሩት በጣም ጥቂት ከሆኑት የትግራይ ተወላጅ ባለሥልጣናቱ በስተቀር ያው ከአማራው አብራክ የተገኙ ናቸው። ሶስቱ ነውጠኞች ሲጀመር ጀምሮ በግንባር ቀደምትነት ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ለዚህም አማራውን ለማንበርከክ እንቢም ካለ ለመጨፍለቅ የተፈጠሩና የሚሰሩ መሆናቸውን አያውቁም ማለት ትርጉም ያለው ሙገት አይሆንም – ቢያንስ በሃያ አምስት ዓመት የህወሃት የሥልጣን ዘመን በ አማራው ክልል በአማራው ላይ ከተፈፀሙ ኢኮኖሚያዊ ሰብዐዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘግኛኝ ተግባራት አንፃር ብአዴናውያን ከህወሃት ባልተናነሰ ሃላፊነትንም አድራጊነትንም ይጋራሉና።

እነሆ ከላይ ባስቀመጥነው አንደምታ ተነስተን እንደ ቆላ ሙቀት የሚለበልብ ዕውነት እንፅፋለን – አዲስ ባይሆንም ቅሉ። ኢትዮጵያን መታደግ የሚቻለው በአዲስ መንፈስና ቆራጥነት “ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ” ባልሆኑ፤ የጠራና የነጠረ ሀገራዊና ህዝብ ተኮር ፖለቲካዊ ግብ ባላቸው ፤ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ራዕይ ባነገቡ ፤ ኢትዮጵያዊነታቸውን ባስቀደሙ ትንታግ የዘመኑ ወጣት ኢትዮጵያውያን ትውልዶች እንጂ “ደምና / ዘርን” መነሻና መድረሻ ባደረጉ ሃይሎች አይደለም። “ደም እና ዘር” የነፃነታችንና የኢትዮጵያዊነታችን መነሻና መድረሻ ቢሆን ኖሮ በኦህዴድ ውስጥ ባሉ ኦሮሞዎች በብአዴን ውስጥ ባሉ አማሮች ወይም በደኢህዴግ ውስጥ ባሉ የህወሃት ቃፊሮች ኦሮሞው ፤ አማራው ኮንሶው . . . ባልተጋዘ ፤ ባልተሰቃየ ፤ ባልተፈናቀለ ፤ የጥይት ራት ባልሆነ ነበር። እንደውም ብአዴንና ኦህዴድ ኢትዮጵያን አስቀድመው ከአብራካቸው የወጣውን ህዝብ በተለይም ወጣቱን መፍጀታቸውን አቁመው ባሳዳሪያቸው ህወሃት ላይ ቢነሱ የኢህአዴግ ኢፌዲሪ የአንድ ቀን ዕድሜ አይኖረውም ነበር ።

የደምና የዘር መስፈርት አንፆና ቀይሶ የተነሳ ድርጅት በየትኛውም ዓለም የዴሞክራሲና የነፃነት፤ የፍትህና የእኩልነት መሥራች ሆኖ አያውቅም። እንዲያ ያለ አደረጃጀት የዘር መድልዖና ፍጅት ያሰፈነን አምባ ገነን ዘረኛ ሥርዐት ገርስሶ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን መገንባት የሚችል ቢሆን ኖሮ የደቡብ አፍሪካዋ እነ ኔልሰን ማንዴላ ከ”ኤኤንሲ” ይልቅ የዙሉ ወይም የኢንካታ የዘር ፓርቲ ታጋዮች በሆኑና ደቡብ አፍሪካን ነፃ ባወጡ ነበር ። ነገር ግን እነ ማንዴላ ከሶስት ዐስርታት በላይ የታገሉት መከራን ግፍ እስርና ስደት የተቀበሉት በመላዋ ደቡብ አፍሪካ በዘር መድልዖ (አፓርታይድ አገዛዝ – እንደ ዛሬይቷ ኢትዮጵያ) ለሚማቅቁትና ለሚገፉት የደቡብ አፍሪካ ህዝብ / ዜጎች ሁሉ ነበር።

( እዚህ ላይ ሜንጨኛው ጃዋርና እርሱ በተገኘበት ወይ በግራው ወይ በቀኙ ወይም በግራና ቀኙ የማይጠፉት መንፈሶቹ ፕሮፌሰሩ ሕዝቅኤል ጋቢሳና ዶ/ሩ ፀአራርሳ የነማንዴላን “ፍሪደም ቻርተር” ማገታቸውን (ሃይጃክ ማድረጋቸውን) ያስታውሷል። እንደውም በቀለኛው ፀአራርሳ በ “ኤስ ቢ አሴ” ሜልበርን አውስትራሊያ በሚገኝ ሬዲዮ ላይ ሲናገር በአትላንታው ጉባኤ ላይ እስከ ሶስት ሺህ የኦሮሞ ታዳሚዎች ሊገኙ ይችላሉ ብሎ ነበር። እዚህ ላይ ይህ ሶስት ሺህ የተባለው ቁጥር እነ ማንዴላ ‘ፍሪደም ቻርተራቸውን’ ሲያቀርቡ የተገኘው ህዝብ ቁጥር ሲሆን እነ ፀአራርሳ የደቡብ አፍሪካን ህዝብ ትግልና የፍሪደም ቻርተሩን ዓላማ ብቻ ሳይሆን ‘ሃይጃክ’ ያደረጉት በደቡብ አፍሪካ ከመላው የህብረተሰቡ ክፍል ተውጣጥተው ‘ፍሪደም ቻርተራቸውን” ለማፅደቅ የተገኘውንም ህዝብ ታሪክና ቁጥር ጭምር ነው – የኢትዮጵያን ታሪክ መጠምዘዛቸው ሳያንስ የደቡብ አፍሪካንም ትግልና ድል ታሪክ ለኦነግ ታሪክና ግብ መጠምዘዛቸው ይባስ ! ! )

ሶስት ፤

እነሆ ላለፉት አርባና ሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን ለማምከንና ዘረኝነትን ለማስፈን የደከሙት ኦነግና ህወሃት ሠምሮላቸዋል ፤ ቢያንስ በውጪው ዓለም በሚኖሩ የአማራ ተወላጅ ወጣቶች። የኢትዮጵያ መከላከያ የመጨረሻው ኬላ ተሰብሯል። ኬላው በመሰበሩ ህወሃትና ኦነግ ለየራሳቸው ዒላማ በየራሳቸው ቅኔና ዜማ እየጨፈሩ ይገኛሉ – ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል – እንዲሉ አብናቶች ፤ ይጨፍሩ ግዴለም። ኬላውን መስበር ቢችሉም ኢትዮጵያን ለመስበር ግን ከቶም አይችሉም ፤ አዳዲስ ኬላዎች በተሰበሩት ኬላዎች ሥፍራ ኢትዮጵያን በሚሉና የኢትዮጵያን ሠንደቅ ባነገቡ “ኢትዮጵያዊነት መለያዬ” ነው በሚሉ ወጣት ትውልዶች ይገነባሉና ! !

እነሆ (ለጊዜው ግን) የየዘሩ “ሀዋርያት’ (አክቲቪስቶች) እና ደቀመዛሙርቶቻቸው ተበራክተዋል። እንደ ማለዳ ጤዛም በዝተዋል። ዕውነት ነው በዚህ ዘመን የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፍዳው እንደ ራስ ዳሽን ተራራ ሰማይ ጥግ ደርሷል – ‘ጃዋር ውስጤ ነው’ የሚሉ የአማራ ወጣቶች ተነስተዋልና ! የአንድነት ሃይሎች ኢትዮጵያን ይዛችሁ ገደል ግቡ የሚሉ የአማራ ወጣቶችን መስማት ጀምረናልና ! ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ “ነፃ የአማራ መንግሥት” መመሥረቱ በእቅድ ሁለት ወይም (ፕላን ቢ) የተያዘ አጀንዳችን ነው የሚሉ አክቲቪስቶችና ድርጅቶቻቸው በይፋ ወጥተዋልና ! “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” የሚሉት አብናቶቻችን ለእንዲህ ያለው ወቅት ይሆን?

ሸበቶዎቹ ኦነጋውያን እነ ጃዋርን የመሳሰሉ ፅንፈኛና አይሲሳዊ ቫይረስ ተሸካሚ ዘረኞችን ለማፍራት ለመኮትኮትና ለማሳደግ የአንድ ትውልድ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። እንዲህ ያለውን ፅንፈኛ ፀረ ኢትዮጵያዊና ፀረ ኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝን – “ጃዋር ውስጤ ነው ፤ አንድነት የምትሉ የኢትዮጵያ አቀንቃኞች ገደል ግቡ” የሚሉ የአማራ ወጣቶችን ለመፍጠር እጅግ በሚገርም የብርሃን ፍጥነት የአማራው አክቲቪስቶች ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ ነው የወሰደባቸው ! ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

እነሆ ዛሬ ዘመን መቼስ ጆሮ አይሰማው ዐይንም አያየው የለምና እነ ጃዋር “ኢትዮጵያውያን ቤት አልባዎች” ‘ሆም ለስ’ ወይም ‘ሀገር አልባዎች’ ናቸው ሲሉ አውጀዋል ፤ አዲሱን የአማራውን ተራማጅ ብሄረተኝነት ለማዳነቅ ባደረጉት ዲስኩር። “ቤት አልባ” ያደረገን ዘርን ያላስቀደመ ኢትዮጵያዊነታችንን መግለፃችን ነው። በእነርሱ ስሌት ወይም አንቀፅ 39 ሲተገበር ኢትዮጵያውያን ነን የምንለውን መቀመጫ ሀገር አይሰጡንምና ወይ በሜንጫ ሊጨርሱን ወይ በሻዕቢያ በኩል ቀይ ባህር ሊከቱን እንደሁ እናያለን ፤ እነርሱን የዚያ ሰው ካላቸው ። ያም ተባለ ይህ ግን ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ተምሯል የተባለው ሃይል “ምሁር” በአመዛኙ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ እንደዘመተ እንደገዘገዘ ነገር እንደጎነጎነ ነገር እንደተረተረ በነገር እንደተናቆረ ሀገርና ህዝብን በከንቱ ርዕዮት እንዳመሰ አለ። እነ ጃዋር የእኒህ ‘ምሁራን’ ፍጡራን ናቸው።

አሁን ደግሞ ልክፍቱ ሰፍቷል። ጃዋር ውስጤ ነው፤ ከኢትዮጵያ የተገነጠለ ነፃ የአማራ መንግሥት ይመሰረታል – የሚሉ ወጣት አማሮችን “በአንድ ጀንበር” ማፍራት ተችሏል። (እዚህ ላይ እንዲህ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ጉዳይ ለሙግት የሚቀርብ ከቶም አይደለም። የዛሬዎቹ ፋሽስት ህወሃታውያንም ሆኑ ሜንጨኞቹ ኦነጋውያን ወይም ወደባችንን አሰብን ጠቅልሎ የተገነጠለው ተንኮለኛው ሻዕቢያ – እዚህ የደረሱት በጣት በሚቆጠሩ ፅንፈኞች ጅማሮ መሆኑን ማስረገጥ እንወዳለን)።

“ኢትዮጵያውያን ከኦሮምያ ውጡ፤ ኦሮምያ ለኦሮሞዎች፤ ክርስትና ተከታዮችን በሜንጫ፤ አማራ የኦሮሞ ደመኛ ነው . . .” በማለት በየአደባባዩ በመንፈስ አባቶቹ (ፕሮፌሰሩና ደ/ሩ) እየታጀበና እየተመራ ደርዝ የሌለውን ጥላቻ የሚገልፅን ዘረኛ በምን ሂሳብ ነው የአማራ አክቲቪስቶችና ወጣቶች “ጃዋር እኛ አማሮች ስለ እኛ በደልና ሰቆቃ ከእኛ በላይ ባማረና በረቀቀ ትንተና አውጆልናል” እያሉ ጮቤ የሚረግጡት? የዚህን አይሲሳዊ ሁለት ስለት ካራ ወዘዋዥ ፅንፈኛ “ሰሞነኛ የምርቃና ንግግር” “የአማራው ህልውና ተሟጋችና ታጋይ ነን” የሚሉ አካላትና ደጋፊዎቻቸው አማሮች በምን ተአምራዊ ስሌት ነው ‘ጃዋርና የመንፈስ አባቶቹ ኦነጋውያን” ለአማራ አዛኛና ተቆርቋሪ ናቸው በማለት የሚያሞግሷቸው?

ጃዋር አንደኛውን የመንፈስ አባቱን (ፀአራርሳን) ከወዲያ ማዶ በሚታይ ‘ስክሪን’ ላይ አድርጎ አዲስ ስለተፈጠረው ተራማጁ የአማራ ብሄረተኝነት ታላቅነት በኦኤምኤን ሲደሰኩርና አድሃሪያን የኢትዮጵያ ብሄረተኞችን (ኢትዮጵያውያንን) ሲያወግዝ ፀአራርሳ (የመንፈስ አባቱ) ፊቱን ትኩስ የአርሲ ቅቤ እንዳወረዛው ሁሉ እያብረቀረቀ አናቱን ከፍና ዝቅ በማድረግ ሲያበረታታው – እንዴት ቢሆን ነው ስለ አማራው ህልውና፤ ሰቆቃ እና ስለ ተፈፀመበት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተቆርቋሪም ጠያቂም ተፋራጅም ነን ባዮች – ለነጃዋር መሰሪና ርካሽ ግብ የሚያጨበጭቡት? በየማህበራዊ ገፆቻቸው በየፌስ ቡካቸው ላይም ንግግሩን የሚለጥፉና የሚያስተጋቡት?

ይህ አመክኗዊ ያልሆነ ድርጊት ደም / ዘር ባስቀደመ ‘ርዕዮት” እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ መንገድ መሸምጠጥ ለኢትዮጵያ ብቸኛው መስመር ነው ከሚል እሳቤ የፈለቀ ለመሆኑና ለአደገኛነቱም ከዚህ በላይ ምን ማረጋገጫ ሊመጣ ይችላል? ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ይህን ያህል ወደ ፅንፍ የተወነጨፉ የአማራ ወጣቶችን መፍጠር ከተቻላ ጊዜው እየገፋ ሲሄድ እስከ የትኛው ጥግ ሊደርስ እንደሚችል ማንኛውንም ጤነኛ አስተሳሰብና ሀገራዊ ጭንቀት ያለበትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በእጅጉ ሊያሳስብ ግድ ይላል።

አራት ፤

በታሪክ የትኛውም ሀገር እጅ በማውጣትና ተሰብስቦ በማጨብጨብ አልተመሰረተም። ነገር ግን በትውልድና በሂደት የሁዋላ ጎርባጭ ታሪካቸው ምክንያቶችን እያስወገዱና እየተማሩበትም ተቀጣጣዩ ተተኪ ትውልድ ከቀድሞው ትውልድ የተሻለና የበለፀገ ሀገር እየገነባ ያድጋል ይለወጣል። ቀደምት አባቶቹን ያከብራል ፤ ታሪካቸውን ይዘክራል ፤ ከህፀፃቸው ይማርበታል እንጂ ሙታንን እየቀሰቀሰ አያወግዝም።

ታሪኩን በማውገዝና ዘር ማንዘሩን ከሀገራዊ ማንነቱ በማስቀደም አባዜ የተበከለ ትውልድ ደግሞ ሀገሩንም ሠላሙንም ማንነቱንም አጥቶ በቀቢፀ ተስፋ ከመቃብር ድንጋይ ላይ ተቀምጦ መፈጠሩን እያማረረ ይኖራል። ከቅርብ ጎረቤቶቻችን ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያን ያስተውሏል። ኢራቅን ሊቢያንና ሶሪያንም ልብ ይሏል። ታሪክን መካድና ሀገርን መናድ ቀላል ነው ፤ የተናደውን መገንባትና ታሪክን ማደስ ግን ከባድ። አባቶቻችን እንደ ዘመናቸው እንደ ዕውቀታቸው እንደ ማህበራዊ ቁሳዊና ፖለቲካዊ ግንዛቤያቸው ኖረውና ሀገርን ገንብተው በአጥንታቸው ክስካሽ በደማቸውም ፍሳሽ ዳር ድንበር አበጅተውም ጠብቀውም አልፈዋል። ሀገር አስረክበው በማለፋቸው ልናመሰግናቸውና ልንዘክራቸው የደምና የአጥንት ቃል ኪዳን አለብን ፤ ባንሰማውም እግራችን ሥር ካለ መቃብር የሚጣራ የቀደምት ትውልድ ድምፅ ! !

ነገር ግን ባልነበርንበት ባልኖርንበት ዘመን ስለተፈፀመው የታሪክ ወይም የመንግሥት ግድፈትና ጥፋት ዛሬ ያንን ማስታወሻ ሀውልት በመገንባት መጠመድና፤ ያንን የሩቅ ዘመን ታሪክ እየጎተቱ በዛሬ ውስጥ ትላንትን መፍጠር፤ ትውልድን እንደ ትውልድ ዘመኑ እንዲኖር ሳይሆን በጋርዮሽ ዘመን አስተሳሰብ በዋሻ ውስጥ ህልውና መጥመድ በጭለማ ማደናበርና ሀገርንና ትውልድን ምርኮኛ ማድረግ በይቅርታ የማይታለፍ ወንጀል ነው። ኦነግ ህወሃትና ሻዕብያ ያደረጉት ይህንን ነው። አማራው በነርሱ ቦይ ውስጥ ማለፍ አይኖርበትም ፤ ለሃያ አምስት ዓመት የወረደበትን ወጀብ አልፎ እዚህ ደርሷልና ! ! ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን ፤ ሁላችንም አማሮች ነን ፤ ሁላችንም ኦሮሞዎች ፤ ጉራጌዎች ፤ ጉርጂዎች ፤ አኝዋኮች ፤ ኮንሶዎች ፤ አፋሮች… ነን ! ! የአማራ ደም ደማችን ነው ፤ የኦሮሞው ደም ደማችን ነው ፤ የአኝዋኩ ደም ደማችን ነው ፤ የኮንሶው ደም ደማችን ነው ። የጎንደር ወጣቶች ያስተማሩን ያበሩልንም መሪ ኮከብ ይህንን ፈለግ እንድንከተልና ቅዱስ መስዋዕትነትንም እንድንቀበል እንጂ በኦነግ በህወሃትና በሻዕቢያ መስተዋት ራሳችንን እንድናይ አይደለም። የመሥዋዕትነትና የትግል ምህዳራችንን አታጥቡት። እንተቃቀፍና እንታገል ፤ ስለ ነፃነታችንና ስለ ሰውነታችን እንዳባቶቻችን አብረን እንሰዋ ! በዚህች ደቂቃም እንኳ በአጋዚና በባንዶች ጥይት ስለሚወድቁት ሰማዕታትና በብር ሸለቆና በመሰል ናዚስት ካምፖች ስለሚሰቃዩት የነፃነታችን ጀግኖቻችን ስንል ለኦነግ ለህወሃትና ለሻዕቢያ ተንኮል አንፈታ !!

ደም / ዘር የኢትዮጵያዊነት ማንነታችንን አያደብዝዘው። ጠላቶቻችን እነሆ ዛሬ በየጎራው ቤት ዘግተው የሚፈነድቁት ህልማቸው የተሳካ ስለመሰላቸው ነው። አማራውን በጎጥ ፓለቲካ አዙሪት መክተት ኢትዮጵያን የማሸነፊያው የመጨረሻው የፍልሚያ ጎራ አድርገው ስለወሰዱት ነው። ግርግር ለሌባ ያመቻል ነውና በዚህ ሆያሆዬ ውስጥ ሀገራችንንና እናመጣዋለን የምንለውንም ማንነታችንን ጠቅልለን እንዳናጣ ስክነት እናድርግ ! ! በፉክክር ወደ ገደል የምናደርገው ጉዞም አፋፍ ላይ እየደረሰ ስለሚመስል ሰከን ብለን አደብ ገዝተን የሚንተከተክ ደማችንን አብርደን ብናስብበት ብንመክርበት ብንደማመጥና ብንቻቻል ይበጀናል ፤ ተያይዞ ከመጥፋት ያድነናልና። የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዳንሆን እንጠንቀቅ ! !

ታላቁ ደራሲና መምህራችን አቤ ጎበኛ “ተስፋ አንቁረጥ ፤ አንዴ ኢትዮጵያዊ ሆነን ተፈጥረናልና” በማለት እንዳስተማረን ስለ ኢትዮጵያዊነታችንና ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ህልውና ስንል፤ ሰው ስለመሆናችንና ስለ ነፃነታችንም ስንል፤ከማንም ከምንም የማትወግን የሠላም የዕድገትና የመሥዋዕትነት ምልክታችንና የሁላችንም የኢትዮጵያዊነት መለያ የሆነችውን ቅዱሷን ህብረ ቀለም ሠንደቃችንን ይዘን – ስለ ኢትዮጵያ እየዘመርን ስለ ኢትዮጵያ እየተዋጋን እስከ ቀራንዮ እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተደጋግፈን እንዘልቃለን !! ከመሥዋዕትነታችን ማዶ አዲስ ቀን ይወጣ ዘንድ እናምናለንና ! !

ኢትዮጵያ በወጣት ትንታግ ልጆቿ ከታሰረችበት የፍዳ ሠንሰለት ነፃ ትወጣለች !

ኢትዮጵያዊነት ደማችን ነው !

ተፃፈ ታህሳስ 2009 ዓ/ም (ዲሴምበር 2016)

ሲድኒ አውስትራሊያ

mmtessema@gmail.com

Filed in: Amharic