>
8:25 am - Tuesday August 9, 2022

ራስን ፍለጋና ትዝብት [አሰፋ ጫቦ]

Assefa_chabo_yetizeta_feleg_large“የአቶ አስፋ ጫቦ የተባ ብዕር ስለነገም ቢናገር!” በሚል ይገረም አለሙ የጻፈው በየድሕራተ ገጾች ወጥቶ ነበር። እኔ መውጣቱን የሰማሁት በስልክ ከእመቤት አሰፋ ነበር። “በላይ መጀመሪያ ሥራ ቦታ አንብቦት ነገረኝና አንብቤ አሁን ልጆቹ እያነበቡት ነው…” አለች። በላይ ባለቤትዋ ነው። ”ምንድነው የሚለው?” አልኳት። ”ብቻ አንብበው ጥሩ ነው የጻፈው። ሥነስርዓት ያለው ሰው ነው” አለች። ሥነስርዓት የምትለው የአያቷ የማቱኬ አጆ መለኪያ (ሰው መመዘኛ) መሆኑ ነው። ማቱኬ ነች ያሰደገቻቸው። በማቱኬ ቤት፣ ልጆቿን፣ ዘመድ አዘማድም ጨምሮ፣ ሰው ሁሉ በሁለት ይመደባል። ሥነስርዓት ያለውና ሥነስርዓት የሌለው!

ከስልኩ መልስ እኔም አነበብኩት። ከዚህ ሌላ ብዙ ወዳጆቼና ጓደኞቼም ደውለው አስተያየት ሰጡ። እዚህ ከአሜሪካ፣ ከኒውዚላንድ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከካናዳም ደውለው ተነጋገርንበት።በመጠኑ ይለያይ እንጅ ተቀራራቢ አስተያየት ነበር የሰጡት።የተለመደው“ጠርጥር ገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር!” የሚለው ለስለስ ባለ መልኩ ነበረበት። “ለመሆኑ ይገረም አለሙ ማነው? ምን ፈልጎ ነው?” የሚለው አይነት መሆኑ ነው።

እኔ ይህንን አይነቱን “ማነው? ምን ፈልጎ ነው?” የሚለው አይነት ውስጥ ገፍቶ ካልመጣ በስተቀረ አልገባበትም። እዚያው ተጽፎ ወይም ተቀርጾ የተቀመጠውን ለበጎ ነው (Posetive Outlook) በሚል አይቼ ተገቢ የመሰለኝን ተመን እሰጣለህ።”ማነው?” ለሚለው ሰው መሆኑ በቂ ነው። “ምን ፈልጎ ነው (Motive)?” የሚለውን አላጠያይቅም።

ሁላችንም አንድ አይነት ነገር ላንፈልግ እንችላለን። የምንፈልገው አንድ አይነት ነገር ቢሆንም ግላዊ ቅላጼና ቃና ሲጨመርበት የተለየ ሊመስል ይችላል እንጅ አንድ ነው። አባይ፣ አዋሻ የብዙ ተፋሰስ ወንዞች (Tributaries) ውጤት ናቸው። አደፍራሽ ጎርፍና ናዳ የሚፈጥር ጉዳንጉድ ይዘው የተቀላቀሉ ጅረቶችም ይኖራሉ። በትግስት ከተያዘ፣ ማለትም ረባዳው መሬት ላይ ሲደረስ ያ ላይዘልቅ የተሳፈረው ግሳንግስ በየእዳሪው ይጣልና ይዘቅጣል። ዘላቂው አባይ ሱዳንንም ግብጽንም እያለማ ወደ ባሕር ይገባል።

ለጠጥከው እንዳልባል እንጅ ዲሞክራሲ ወይም ዲሞክራሲያዊ ውይይት የሚሉት የሐሳብ መንሸራሸርና ማንሸራሸር ከዚህ ጋር የሚሔድ ይመስለኛል። የጠራው ይዘልቃል! ግብስብሱ ይሰምጣል ወይም ይዘቅጣል! ብቻ ለማለት የፈለኩት ይገረም አለሙንም ሆነ ማንንም፣”እንዲህ ያሰኘው የውስጥ ምክንያቱ (Motive) ምንድነው?” ብዬ አላጠያይቅም። ግለስቦችን የሚገፋቸውን ምክንያት ለነሱ እተዋለሁ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከፍተን እንድናየው የምንገደድ ይመስለኛል። ሰው ምክንያታዊነትና (Reasonable and Rational) የውስጥ ግፊት(Motive) ካሌለውማ ”ጉድ ፈላ!” ወደማለት ሳይወስደን የሚቀር አይመስለኝም። ሰው ሊያሰኘው ከሚገባው ውስጥ መሠረታዊና ዋንኛ ቅመማት ተነፍጓል እንደማለት የሚሆን ይመስለኛል።

ይገረም አለሙ ስለ እኔ ጽሁፎች ብዙ ነገር አንስቷል። ሁሉንም ባይሆነ ዋናና (በኔግምት) መልስም፣ ማብራሪያያና ከመጋረጃው ጀርባ የነበር ምክንያት የሚመስሉኝን ለመመለስ እሞክራለሁ።

****

ይገረም አለሙ “የእገሌ ጽሁፍ ኮርኩሮኝ ነው ብቅ የምለው… በቅርቡ ደግሞ ልጽፍ ብዬ አስቤ ሳይሆን ብልጭ ሲልብኝ ወይም ሲልልኝ ነው የምጽፈው ብለው እቅጩን ስለነገሩን…” ከሚለው ልጀምር።ይገረም የጠቀሰው ያልኩትን ነው። እውነትም ነው! ይህ “ብልጭ ሲልብኝ!” የሚለው ነው የዚህን ጽሁፍ ርዕስ ራስን ፍለጋ ያሰኘው።

አሁን ወደ ሁለት ዓመት ሊሆነው ነው። በአንድ ወዳጄ ምክር አንድ ኮሌጅ ውስጥ የሥነልቡና ሳይንስ (Psychology) ትምህርት ተከታተልኩ። የወዳጄ ምክር የሚለው “አስተማሪው (ፕሮፌሰሩ) የሥስነልቦና ሐኪም (Psychiatrist) ሆኖ ለ25 አመት የሰራ ነውና ይጠቅምሐል!” የሚል ነው። ለጠቅላላ እወቀት (General Knowledge) እንደማለት ነው። ተመዘገብኩና ተካፈልኩ። ከሁለተኛው ሳምንት በኋላ ጥያቄ አበዛሁ መሰለኝ። ወደሶስተኛ ሳምንት ገዳማ “ሚስተር ጫቦ ሁለተኛ እንዳትጠይቅ!” አለኝ። ደንግጬ “ምን አጠፋሁ?” ብለው “ያጠፋኸው ነገር የለም። ጥፋቱ ያለው እምነትህ ላይ ነው። መልሱ እዚህ መመሪያው መጽሐፍ (TextBook) ውስጥ ያለ መስሎህ ነው። ወይም እኔን ያውቃል ብለህ ነው። አናውቅም! የሰው ልጅ አእምሮ፣ ጭንቅላት (Brain)፣ ብትፈልግ አንጎል (Mind) እንዴት ነው የሚሰራው? ለመሆኑ አንጎል (Mind) ጭንቅላት (Brain) የሚባለውስ ምንድነው? ለመሆኑ የምናስበውና የምናመዛዝነው በአንጎላችን ነው? በልባችን? ወይ በስሜታችን? ወይ በኩላሊታችን? ወይም በአንጀታችን? ይህንን ለመለየት ጥናቱ ቀጥሏል! ይህ መጽሐፍ ከአንድ አመት በኋላ በሌላ ይተካ (Obsolite or Revised) ይሆናል። እኔ የማውቀውም እንደዚያው! አሁን ጥናቱ ያተኮረው ድሮ በትእቢት (Supriority)፣እኛው ብቻ እናውቃለን ተሞልተን፣ ንቀንና ኋላ ቀር ብለን በተውናቸው ሥልጣኔዎችና ሕዝቦች ታሪክ፣ተረት፣ እምነት ላይ ነው። “ያንን ያሉትን ለምን አሉ?” ያንን ያመነቱን እንደዚያ ለምን አመኑ?” የሚል።ለጊዜው የምናውቀው፣ ሰው የሚያስበው በጭንቅላቱ ወይም በአንጎሉ ሳይሆን፤ ወይም ብቻ ሳይሆን የሰራ አካላቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ብልቶች በጋራ መሆኑን ነው። እንዴት ነው የተቀናጀው? ለዚህ ገና “ከማወቁ በር” (The Tip of the Iceberg) ላይ ነን!” አለ። ወይም ያለውን ሳሳጥረው ይህንን ይመስላል።

“ያንን ያሉትን ለምን አሉ፧” ”ያንን ያመኑትን እንደዚያ ለምን አመኑ?” የሚለውን የኛ ሰው በየቀኑ የሚለው ነው። “ዛሬ ሆዴን ባር ባር አለው! ከአንጀቴ ነው የምናገረው! ልብ ያለው ልብ ያድረገው! ልቤ ጠረጠረ! ዛሬ ቀፈፈኝ! እና የመሳሰለውን ሲል ይህንኑ ማለቱ ነው። አንዳንዴ “ነገሩ ራስ ያዞራል!” ሲል ወደአንጎል፤ ወይ ወደጭንቅላት ወይም ራስ (የፈለገው ስም ይኑረው) መሔድ መሆኑ ነው። ሁለንተናችን ለምንለው፣ ለምናደርገው፣ ለማናደርገው ሁሉ ተባባሪና ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው።

እንግዲህ “ብልጭ ሲልብኝ እጽፋለሁ!” ማለቴ “ከአንጀቴ ነው!” ማለቴ መሆኑ ይመስለኛል።ከሆነ ደግሞ ሳይንሱም ባሕሉም ይደገፈኛል ማለት ነው። ፈርንጅ ሁሉ ማለት አለማለቱን አላውቅም እንጅ አሜሪካኖቹ “ሰውነትን አዳምጠው አይዋሽም እውነቱንም ይነግርሐል (Listen to Your Body! It will Tell You the Truth!)” የሚሉት አላቸው። እኔ ስጽፍ ሰውነቴን አዳምጬ ያንን የነገረኝን “የኔን እውነት!” መፃፌ ነው ማለት ነው። “የኔ እውነት!” የኔ ቢሆንም ያንን እውነት ከሌሎችም ጋር እጋራለሁ ማለት ነው። እንዳልኩት ማንም ሰው ብቸኛና አንድ ደሴት አይደለም። ከልዩነታችን ይልቅ አብረን የምንጋራው ያመዝናልና።
****

ሌላው ይገረም አለሙ ጽሁፍ ላይ ያስተዋልኩት “ነካ ነካ አድርጎ እመልስበታለህ ብሎ ሳይመለስበትም ይቀራል“ የሚለው ነው። ይህም እውነት ነው! ለማስረዳት ልሞክር።

አስተማሪ ለመሆን ነበር ብቸኛ ምኞቴ። ሻሽመኔ ስምንተኛ ክፍል ስንፈተን “ሰከንደሪ ማዶ!” (ያኔ ሰከንደሪ ማዶ፣ ይጥላል በርዶ የሚል ዘፈን ብጤ የነበር ይመስለኛል)። ምን ለመማር እንደምትፈልግ ሶስት ይሁን አራት ትምህርት ቤትና አይነት ምረጥ የሚሉት ነበራቸው። እኔ ሁሉንም “መምህራን ማሰልጠኛ” ብዬ ሞላሁ። እግረመንገዴንም ሐረርንም ለማየት። በስምም ቢሆን የማውቀው መምሕራን ማስልጠኛ የነበረው ሐረር ነበርና! ከዚህም ሌላ ስምንተኛ ክፍል እያለሁ አስተማሪ በጎደለ ጋሽ ሚካኤል፣ዳይሬክተሩ ይልከኝ ነበር። ሐረር አይሆን እንጅ መምሕራን ማሰልጠኛ አዲስ አበባ ኮከበ ጽባሕ ደረሰኝ። የዚያን አመት መከፈቱ ነበር። ሁለተኛ ድረጃ ትምህርቴም ከአስረኛ ክፍል አላለፈም። የመምህርነት ትምህርቱም ያሰብኩትን አይነት አልሆነም። Education የሚል የሚያስተምር የዞረበት የሚመስል ሲድኒይ የሚባል ሕንድ ነበርና አንዱ ምክንያትም ያ ሊሆን ይችላል። ባሕር ዳር በሌላ ሙያ ሥራ ሔጄ እዚያም በትርፍ ጊዜ 7ኛ፣ 8ኛ አስተምር ነበር። ዲሬክተሩ ሐረገወይን የካርምቦላም የቢራም ጓደኛዬ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። ዩኒቨርሲትም ስገባ የገባሁት ልክ እንደኮከበ ጽባሁ Faculty of Education ነበር። አልጥም አለኝና ወደሕግ ቀየርኩት። ይህንን ማምጣቴ እዚያም እዚያም መረጃ ለማምጣት መሔዴና የመሳሰለው አስተማሪ ሊሆን ፈልጎ የተቀጨው ፍላጎቴ እየገባበት ሳይሆን አይቀርም እላለሁ። ከሰው ጋር ሳወራም ሆነ ብዙ በተሌቪዥንና ራዲዮ የሰጠሁትን ቃለ መጠይቅ ያዳመጠ ይህንን አንዳንዴ ሀራምባና ቆቦ የመርገጥ ነገር የሚያይ ይመስለኛል።

አንድ ሌላ ለዚህ ሀራምባና ቆቦ (እኔ ነኝ ያልኩት) የመርገጥ ነገር ምናልባትም ከአንባቢዎቹ ጋር ተሰባስበን የምናወጋ ስለሚመስለኝም ይሆናል። የሚያነቡኝ ሳይሆን የሚያዳምጡኝ ሳይመስለኝ አይቀርም። “ብልጭ ሲልብኝ!” ወረቀት አነሳና ወይም ወደኮምፒውተር እሔድና የሆነውን እናገራለሁ። ወይም እላይ “ከአንጄተ ነው!” ያልኩት መሆኑ ነው። በምጽፍበት ጊዜ እኔ እዚያ ያለሁ አይመስለኝም። ያለው አስፋ ቃል ተቀባይ (Trnscriber) ወይም ጸሐፊ ነው። የተነገረውን እንዳለ ያስፍራል። ልክ ጽፌ ስጨርስ አለቀ ማለት ነው። የቃል ተቀባይነቱ ሥራ አለቀ ማለት ነው። ተመልሽ ፊደልም ሆነ ሌላ ግድፈት ካለ ማስተካከሉ ወይ ይደክመኛል፤ ወይም ያስጠላኛል፤ ወይም “እኔ ቅድም ሥራዬን ጨርሻለሁ!” የማለት ነገር የሚመጣብኝ ይመስለኛል። ከዚህ የተነሳ በጻፍኳቸው ውስጥ ብዙ የፊደል ግድፈት ይገኛል።

የሀራምባና ቆቦው ሌላው ምክንያት አንድ ሰው ከሌላ ወይም ከሌሎች ጋር ሲያወራ እየተናጠቀ ወይም እየተቀባበለ ብልጭ የሚለውን እየጨመረ እየቀነሰ እንደአመጣጡ ስለሆነ በጽሁፌ ውስጥ የሚታየው “ነካክቶ ማለፍ፣ ያንንም ያንንም መነካካት” እዚያው ቁጭ ብሎ ከማውጋት ጋር የሚገናኝ ይመስለኛል። ይህ መልስ መላምትነት የሚያጣው አይመስለኝም።

ይህ “እመለስበታለህ!” ብሎ አለመመለስ ሳይንሳዊ መሠረት፣ የተፈጥሮ ህግ የሚገዛው ይመስለኛል። የምናውቀውን የምናስቀምጥበት ጊዚያዊና (Short Memory) ዘላቂ (Long Term Memory) ሳጥን አለ። ዘላቂ የምንለው ዘለዓለማዊ ባይሆንም እንደጉዳዩ ክብደት ከዘመናት በኋላም፣ አንዳንዴ በልጅነታችን የሆነውን እናስታውሳለን። ጊዚያዊው ሳጥን ውስጥ የሚቀመጠው ከደቂቃ ወይም አንዳንዴድ ከስኮንዶች በኋላ ሊተን ይችላል። “አሁንኮ ምላሴ ላይ ነበር!” ስንል ያንን ማለታችን ነው። ይህ የተፈጥሮ ህግ ዛሬ እዚህ ከገባሁበትም ለመውጣት አገለገለኝ ማለት ነው!

****

ጥያቄዎቹና መልሶቻቸው

ይገረም አለሙ ስምንት ጥያቄዎች ሰንዝሮልኛል። ከአንድ እስከ አራት ያለው ጥያቄ ተቀራራቢነት ያለው ስለመስለኝ አንድ መልስ ልስጥ ፈለግሁ። ተቀራራቢነቱ “በጽሕሁፎችህ ውስጥ “ያም ሆነ፤ ይህም ሆነ እያልክ ነካክተህ ተውካቸው እንጅ እንዲህ ቢሆን፤ እንዲያ ቢሆን የሚል ቁልጭና ጥርት ያለ ምስል ጠልቀህ አልሳልክም“ የሚል ነው። ቃል በቃል ባይሆንም መንፈሱ ይኸው ይመስለኛል። አባባሉ በከፊል ልክ ነው። በከፊል ልክ አይደለም። ለማስርዳት ልሞክር።

አሁን ወደሁለት አመት ይጠጋዋል። ዋሺንግቶን ዲሲ ሔጀ ነበርና ያሬድ ጥበቡ “መወያየት መልካም“ በሚለው ፕሮግራሙ ለረዥም ሰአታተ ጠይቆኝ ነበር። ከውልደቴ፣ እደገቴ ጀምሮ እስከአሁን ዝቅጠት ድረስ። እኔ ተከታትዬ አላዳመጥኩትም። የራሴው ስለሆነ የምማረበት አዲስ ነገር የለውም በሚል ይመስለኛል። በዚህ ሰሞን በሆነ ምክንያት youtube ስገባ ያ ከያሬድ ጥበቡ ጋር ያደረግነው ”መወያየት መልካም“ እዚያ ተለጥፎ አብዛኛውን ቦታ ይዞ አገኘሁት። ከዚህም በላይ ከ35,000 በላይ እስካሁን አዳምጦታል የሚልም አነበብኩና እስቲ እኔም ላድምጠው ብዬ አንድ ሶስቱን ያክል አዳመጥኩ። በስድስት ክፍል ተከፋፍሎ ነበር የቀረበው።

እኔ ሳዳምጠው ወደድኩት። እንደዚያ በዝርዝርና በጥልቀት መሔዳችን ትዝ አይለኝም ነበር። የነበረውን የኦሮሞ እንቅስቃሴ ይዳስሳል። ይህ የሆነው የአሁኑ ሕዝባዊ አመጽ ከመጀመሩ ከአመት በፊት ነበር።

ይሕ ሕዝባዊ አመጽ እንደሚነሳ በግልጽና በማያሻማ ተናግሬአለሁ። በሁለት ምሳሌ ነበር ያስረዳሁት። በደርግ ዘመን “ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ የካቲት 1966 አብሮት ፈነዳ” የሚለውንና “መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፤ ሲገስግስ አድሮ ከተፍ ይላላል እንጅ!” የሚለውን። በነዚህ ምሳሌዎች ወያኔን “የመጥፊያህ ቀን ተቃርቧልና መጀመሪያ ራስክን አድን። ለራስህ መዳን የምታደርገው ከተነጋገርነበት ዘልቆም ለጋራ ቤታችን መዳንም ይረዳል” የሚል ነው። ለማጋነን ብፈልግ “ትንቢት ተናገረ” ተብሎ ሊውሰድ የሚችል ይመስለኛል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይም ያተኮረ ረዥምና ሰፋ ያለ ትንተናና ምክርም ሰጥቻለህ።

ይህ “የመወያየት መልካም” ፕሮግራም የተላለፈው በድሕረገጾች ላይ ነው። ከዚህም የተነሳ ምንም እስከዛሬ ከ35,000 በላይ ሕዝብ ያዳምጠው እንጅ ይገረም አለሙን ጨምሮ ብዙዎች ያዳመጡት አልመስለኝም። በዚህ ጉዳይ ላይ የምሰጠው ምክር ወይም ማሳሰቢያ ቢኖር እባካችህ “መወያየት መልካም” ቃለ መጠይቅ አዳምጡት የሚል ነው። እኔ በዚህ ድሕራተ ገጾችን በመኮርኮር ይህንንም ያክል የላቀ እውቀት የሌለኝ youtube ላይ ያለችግር ማግኘት ከቻልኩ ለአብዛኛው ሰው ቀሎ የሚታይ ይመስለኛል።

*****

ሌላው የይገረም አለሙ ጥያቄ “አሁን ባለው ሕዝባዊ አመጽ ጉዳይ በቀጥታ ለምን አትጽፍም?” የሚል አንድምታም አለው። በነሐሴ ወር 2008 አንድ “ግልጽ ደብዳቤ” ለኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች የተዘጋጀ ረቂቅ ለመነጋገሪያ ርእስ ይሆናል በሚል፤ ከዚያም ተነስቶ የአማራጭ መንገድ አዘጋጆች ማደራጀት የሚችል የሽምግልናና የሁከት አስወጋጅ አካል (Conflict/Dispute Resolution) ለማቋቋም በማሰብ ለዚህ ይመጥናሉ ለምላቸው ወደ አስራ አምስት ለሚሆኑ በቅርብም፣ በሩቁም፣ በስምም ለማውቃቸው በEmail ላኩኝ። ከአንድ ሰው በስተቀር ደርሶኛል የሚል ተራ መልስ የሰጠኝም አልነበረም። የዚህ የአንዱ ሰውዬ መልስም የለበጣ ነበር። ይህንን “ግልጽ ደብዳቤ” አደባባይ ላይ እንዲነበብ ሰሞኑን ከትንሽ ማብራሪያ ጋር ድሕረገጻት ላይ እለጥፋለሁ። ለአዲስ አድማስም እልካለሁ።

ከዚያ በኋላ ይህ “የሕዝብ አመጽ” የ”አማራ”ና “የኦሮሞ” “ምሁራንና ብሔርተኞች ነን” የሚሉ ፈለፈለ። ሁሉም የዚህ “የሕዝቡ አመጽ ጠንሳሽ አነቃናቂ፣ መሪ እኔ ነኝ!” የሚል ሆነ። ከዚህም ሌላ ይህ ግልጽ ደብዳቤውን ከላኩላቸው ወዳጆቼ ሌላ በግል የማውቃቸው፣ ቢያንስ በሳምንት አንዴ ስልክ የሚደውሉልኝና የምደውልላቸውም ሰዎች ሸሹኝ። እንኳንስ ስልክ ሊደውሉ ስደውልም አላነሳም አሉ። አንዳንድ የሕዝብ መገናኛዎች (Massmedia) እኔንም ስልኬንም አናውቅም ያሉ መሰለኝ። በዚህ ላይ የሚጽፉትንና የሚናገሩትን ሳነበው ሳዳምጠው “ይህ የመጨረሻው እውነት ነውና ወይ ተከተለኝ ወይም አርፈህ ተቀመጥ! ያለበለዚያ…!” የሚል አንድምታም ያለው ሁኖ አገኘሁት። በዚህ ላይ “የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል!” አይነት ዘለፋ መዘላለፍ በአደባባይ ላይ አየሁ። “የውሻን ጥርስ ማየት አጥንት ሲግጥ ነው!” የሚባለውንም አስታወስኩት። የሾለ ጥርሱንም አየሁት!

ይህ ጅምላ ጩኸት ደርግ “የታሪክ ሽሚያ” ያለው አይነቱ ጋብ እስኪል እስቲ ጋብ ልብል ብዬ መለስተኛ ሱባዔ (Introspection) ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል። ወዳጄ የነበረው ጸጋዬ ገብረመድኅን “የከረሞ ሰው” ውስጥ አብዬ ዘርፉን ያናገራቸውንም ያስታውሰኛል። ”ምኞቴ እንደጉም ፈንጥቆ፤ ተስፋዬ እንደጉዱፍ ወድቆ…” ይላሉ አብዬ ዘርፉ። እነኝህም “ቅዠቴ እንደጉም መንጥቆ፤ እውነቱ ግን እዚሁ ፊታችን ተደብቆ…” የሚሉ ወይም ማለት ያለባቸው ይመስለኛል።

ያም ሆኖ መሀል ለመሀል ሰንጥቄ አልሂድ እንጅ ዙሪያውን ማንዣበቤ አልቀረም። ይገረም አለሙ የሚጠቅሳቸው ጽሁፎቼ የዚህ ተአቅቦ (Introspection) ውጤቶችም ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ አስባለሁ።

አሁን እኒህ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ አመጽ ባለቤትና መቆራመት የፈለገው መጯጯህ ጋብ ወደማለት የመጣ ይመስለኛል። “ሽል ከሆነ ይገፋል፤ ቦርጭ ከሆነ ይጠፋል!” የሚባለው አይነት መሆኑ መሰለኝ። ቦርጭ ነውና የሚግበሰበስ ሲጠፋ ወይም ሲያልቅ መሟሸሹ ያለ ነው። ለመጠባባቂያ ብለው መጋዘን ውስጥ ያስቀመጡት፤ ይህም ማለት ታሪክ፣ ትምህርት፣ ተመክሮ፣ የፖለቲካ ንድፈሐሳብ (Theory)፣ እምነት፣ እና የኢትዮጵያ ፍቅር በአብዛኛው የሚጎለው ስለነበረ መሟሸሹ ባይገርመኝም “እስኪያልፍ ያለፋል!” ማለቴም አልቀረም።

የ”አማራ” ንቅናቄ፣ “የኦሮሞ” እንቅስቃሴ “ያ ይህ” እያሉ መድረኩን አጣበው በነበሩት ላይ የጻፍኩት ”የጋራ ቤታችን፤ ሳይደፍርስ አይጠራም!” የሚል ሰሞኑን አወጣለሁ። በመጠኑ “ከፈት አድርጎ ለማየት!” ነው። በአውራ ጎዳናው መጓዝ ለምንፈልገው መነጋገሪያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

****

አሁን ደግሞ ወደይገረም አለሙ ስድስተኛ ጥያቄ ልሂድ። ”ወያኔ አዲስ አበባ እንደገባ፣ ለፖለቲካው ጫወታ በየጎሳችህ ተደራጁና ኑ ሲል በአንድ ጀንበር ሊባል በሚችል መልኩ ከደቡብ ወደአስራ አምስት ድርጅቶች ተመሠረቱ። ከነዚህ አንዱ የርሶ ነበር” ይላል።

ይህ ጥያቄ ከፊል እውነት ከፊል እውነትም ያልሆነ አለው።

በ”አንድ ጀንበር” ላለው አንድ የማውቀውን ብናገር ጥሩ ይመስለኛናል። ምክር ቤት እንደተገባ ሕዝብ ደሕንነት ውስጥ የሚሰሩ ይመስሉኛል ሁለት ወላይታዎች የወላይታን ህዝብ እንወክላለን ብለው መቀመጫ ያዙ። በኋላ በወያኔ መለኪያ መሠረት “ንክኪ” ናቸሁ ተባለ። ንክኪ ማለት የደርግ ጠረን ኢሰፓ የሚሉት መሆኑ ነበር። ቢል ቢደርግ የተንዛዛ ክርክር ፈጥረው አንወጣም አሉ። በነጋታው ይሁን እንዲያ ኢትዮጵያ ሆቴል ፊትለፊት አቶ ሙሉ ማጃን አገኘሁት። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ አርባምንጭ በመጠኑ አውቀዋለሁ። ወላይታ ነው። ይህንኑ ችግር ነገርኩት። በነጋታው ሶስት ሰዓት አራት ኪሎ ምክር ቤት በራፍ ላይ አገኘሁትና “ምን ታደርጋልህ?” ስለው “የወላይታን ሕዝብ ወክለን መጣን!” አለ። አብሮት በኋላ ስሙን ያወኩት አቶ ሉለሥላሴ ቴማሞ ነበር። ሉለሥላሴ ባለቤቱ የትግራይ ሰው ነች ያሉኝ መሰለኝ። በኋላ የባህል ሚኒስቴር ሆነ። ከስንት አመት በኋላ ሙሉ ማጃ ከዶክተር በየነ ጴጥሮስ ጋር ስለደቡብ ሊያስርዳ አሜሪካን መጥቶ ነበር። አላገኘሁትም። ሙሉ በዚያ ሽፋን ዘመድ ለመጠየቅ ነው የመጣውና ካናዳ ሔደ ብሎ በየነ ነገረኝ። ፊታውራሪ መኮንን ዶሪም አብሮ መጥቶ ነበር። ለደቡብ ጉዳይ! ፊታውራሪ መኮንን ከኦሞቲክ “ውሐ ቀጠነ!” ብሎ ለቆ ኢሕአደግ ሁኖ የማስታውቂያ ምክትል ሚኒስቴር ሁኖ ተሹሞ ነበር። ይህ ነገርን ነገር ያነሳዋል ነው። እገረ መንገዱን በየነ ጴጥሮስ የደቡብ ሕብረትን እንዴት እንደቀበረው የሚጠቁምም ይመስለኛል።

እኔ ምክር ቤት የገባሁት በጎሳ አይደለም። “ጎሳ”ቃሉንም ሲባል ከመስማቴ በስተቀር ተጠቅሜበት አላውቅም። በተፈጥሮ ሕግ መሠረት “ቆሞ- ቀር” ነገር የለም። ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይተካል፤ ይሞታልም።ይህ ለሰውም ለሕበረተሰብም ለፍጡራን ሁሉ የሚያገለግል ነው። እኔም፣ ወደድኩም ጠላሁም፣ በዚሁ ሕግ መሠረት እጓዛለሁ። ይህንን ሕግ አንቀበልም የሚሉ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ በአደባባይ ላይ ይታያሉ። ወደ”ዘመነ መሣፍንት” ለመጓዝ መፈለጋቸውን በተለያያ መንገድና ቃላትም ይገልጹታል። ”የጎበዝ አለቃ” የሚለው ከነዚህ ውስጥ አንዱ ይመስለኛል። ጉድ የሚያክል መጽሐፍም የጻፉም አሉ። ለክፉም ለደጉም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አካል ነበርኩ። አምሳልም ባልሆን። ግራ ዘመም የፓለቲካ እምነት አለኝ። ገና ለገና ሶቭየት ሕብረት ወደቀ ብለው “ቅሌን ጨርቄን!” ሳይሉ ፈርጥጠው ዕምነት አልባ የሆኑት ውስጥ አይደለሁም። የምኖረውም በ21ኛው ምዕተአመት ውስጥ ነው። ”ብሔረሰብ” ነው የምለው። “ጎሳ” ማለት ዘመናይ አባባል አይመስለኝም። የሕብረተሰብን እድገት አያንጸባርቅማና! ይህንን ጥያቄ፣ እላይ ባነሳሁት “መወያየት መልካም” ውይይት ውስጥ ያሬድ ጥበቡም አንስቶብኝ ስመልስ በሳቅ የፈነዳ ይመስለኛል። ያንን መመልከቱ ጥሩ ነው። ከጅምላ መደመር (Generalization) የመጣ ጥያቄ ይመስለኛል። ”ከነእንትና ጋር ነበርና … ስለዚህም…” (by Association) እንደማለት።

****

እኔ፣ አፍሪቃ አዳራሽ ስበሰባውም ሆነ በኋላም የሽግግር ምክር ቤቱ አባል የሆንኩት “ኦሞቲክ” የሚል ድርጅት ሊቀመንበርና አባል ሆኜ ነበር።

ለመሆኑ ኦሞቲክ ምንድነው?

የኦሞን ወንዝ ሥም ተከትሎ የወጣ ስም ይመስለኛል። የኦማቴ ሕዝቦች ዝርያ ማለት ነው። ከሲዳማ ይጀምርና ዛሬ አሶሳ አካባቢ ያለው ባምባሲ ድረስ የሚደርስ ህዝብ ነበር። ማእከሉ የከፋ ንጉሥ ነበር። የከፋው ንጉስ ጋኪ ሸረቾ በራስ ወለደጊዮርጊስ፣ ደጃዝማች ደምሰው ነሲቡና ደጃዝማች ተሰማ ናደው በሚመራ የምንሊክ ጦር ተሸንፈው በግዞት በ1911 አመት ሞቱ። የጅማው አባጅፋር የራሱን 30,0000 ጦር ይዞ የዚህ ዘመቻ አካል ነበር። ለአባጅፋር ሁለተኛ ዙር መሆኑ ነው!

ጂማ ጅማ የሆነው፣ ማለትም የተፈጠረው፣ የኦሮሞን የ16 ምእተ አመት ወረራ ተከትሎ ነው። በዚያ ወረራ የአካባቢውን ሕዝብ ደምሰሰዋል ማለት ነው። አሁን የምንሊክ አካልና አምሳል ሆነው ከፋን ሲወር ሁለተኛ ዙር መሆኑ ነው። አባጅፋር ምናልባትም በመላው አለም ተዋዳዳሪ የማይገኝለት የባሪያ ፈንጋይና ነጋዴ ሆነ። የተለያዩ ጸሐፊዎች በዚህ የባሪያ ንግድ ላይ ጽፈዋል። ከተዋቁት ውስጥ ታዋቂው ሪቻርድ ፓንክራስት ይገኙበታል። የበለጠ በጥልቀት ለመረዳት Ethiopian Slave Export at Matama, Massawa and Tajura c1850-1885 by Abdussamad H. Ahmed የሚል ጥናት ማንበብ ሙሉ ምስሉን ይስጣል ብዬ አምናለሁ።

በዚያን ዘመን ከኢትዮጵያ ውደ 500,000 ባርያ ወደመካከለኛው ምስራቅ እንደተሸጠ ተመዝግቧል። ባሪያዎቹ የተፈነገሉት በአብዛኛው ከዚህ የከፋ ግዛት ወይም ተባባሪ ግዛት ከነበሩት ሁሉ ነው። ይህም ማለት ከጋሞም የተፈነገሉ እንዳሉ የተፈነገሉበት አገርና ስም ጭምር ተመዝግቧል። የጋሞ ባሪያዎቹ ብርቱ ሠራተኛ ስለሆኑ ጥሩ ዋጋ ያወጣሉ ይላል። ከሁሉም የሚደንቀው አባጆብር ለጥርስ ሀኪማቸው የከፈሉት አምስት ባሪያ ነው። አንድ ውሻ በሁለት ባሪያ ለውጧል። የሰውን ልጅ በውሻ ሲለውጥ ነበር። ከዚህም ሌላ አባጆቢር ምንሊክ ወላሞ (በወቅቱ አጠራር) ሲመቱ 10,00 ወታደር አሰልፎ የዘመተና ወላይታ ለመሸጥ መለወጡ አባልና አካል ነበረ።

ጅማ የአባጆቢር ቤተመንግስት ያለበት፣ ሔርማታ፣ ምንልባትም በዓለምም ደርጃ ትልቁ የባሪያ መሸጫ ገበያ ነበር። ከዚህ ገበያ የተገዙ ባሪያዎች በመተማ፣ በታጁራ፣ በምጽዋ በኩል ለመካከለኛው ምስራቅ ገበያ ይቀርባሉ። የጉዞው መንገድ ከሔርማታ ወደ ጂረን ወደሰቃ፣ ወለጋ ሌቃ-ነቀምቴ ውስጥ ቢሎ በሆሮ ጉድሩ ውስጥ አሳንዳቦ፣ ጎጃም ውስጥ ባሶ ትግራይ ውስጥ አድዋ ነበር። ጥቂቶችን ለመጥቀስ!

ከነዚህ አጥኒዎችና ጸሐፊዎች መረዳት የሚቻለው በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸመው ባሪያ ፍንገላ፣ ማጓጓዝ፣ መሸጥና መለዋወጥ ትልቁ ድርሻ የሚወደቀው ዛሬ ከፋ፣ ኢሊባቦርና ወለጋ በሚለው አካባቢ በሚገኙ ኦሮሞዎች ላይ መሆኑ ነው። ምንሊክም፣ ጎጃም፣ ጎንደርና ትግሬም የዚያው ንግድ ሰንስለት አካልና አባል ነበሩ። የሚገርመው ለክርስቲያኖቹ እምነታቸውም፤ ሕጋቸውም ባሪያ መሸጥ መለወጥን ይፈቅድላቸዋል። ፍተሕነገሥቱ የሚለው ይህንኑ ነው። ፍትሐነገሥቱ የተቀዳው ደግሞ ከኦሪት (Old Testament) ነው።

****

እናም እነዚህ ኦሞቲክ ወይም ኦማቴ ተበለው ይጠሩና፣ ከሲዳማ አስከ አሶሳ ባምባሲ ይደርሱ የነበሩት ሕዝቦች ዛሬ የት ደረሱ?

የዚህ Afroasiatic Languages ብለው የሚያጠኑትን የቋንቋ ሊቃውንት የጥናት ወጤት ማንበብ የሚጠቅም ይመስለኛል። ከነዚህ አንዱ M. Lionel Bender ብዙ መጽሐፍ ጽፏልና Comparative Merphology of the Omotic Languages የሚለውን ማነበቡ ያግዛል። ከነዚህ ሕዝብ ዛሬ መላው ኢሉባቦርና ወለጋ የተረፉትን በቁጥር ይመዘግባል። አንፊሎ፣ ወለጋ፣ ደምቢዶሎ፣ ውስኪ በመለኪያ ሳይሆን በጠርሙስ በሚቀርብበት ከተማ (1967 ክረምት አይቻለሁና) የኦሞቲክ ተናጋሪ 50 ያህል ቀርተዋል። ዶክተር ግርማ ደመቀ፣ የቋንቋ ምሁር፣ አንዴ ለጥናት ሔዶ አንፊሎ ቋንቋን በመጠኑ የሚናገሩ ሁለት ሽማግሌ እንደአገኘ ነግሮኛል። ባምባሲ ወደ 500 ተርፈዋል ይላል ቤንደር። አንዴ፣ በ1967 ወዳጄ ከነበረው የደርግ አባል፣ በኋላም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነ ከነበረው ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ጋር ወለጋ፣ ነጆ ከተማ በተደረገ፣ ወደ100,000 ሕዝብ በተካፈለበት ስብሰባ ላይ አንድ የዚህ የኦማቴ ሕዝብ ተራፊ ሽማግሌ ተነስተው “ዛሬ ለማመን የሚያዳግት ነገር ሰማሁ! ኦሮሞ ተጨቆንኩ ሲል ሰማሁ! እኛ በአለም ላይ የምናውቀው አንድ ጨቋኝ ቢኖር ኦሮሞ ብቻ ነው!” ብለው ነበር።

ሁሉም የሚያየው ከራሱ አንጻር መሆኑ ነው። ግና ለእኩልነት እንታገላለን የምንል፤ በተለይም ተማርን ተመራመርን የምንል በአንጻራዊ መልኩ (In Context) ሙሉውን ስዕል ብናይና ብናሳይ ቢያሳዩን ለሁላችንም የሚበጅ ይመስለኛል።

በነገራችን ላይ ዛሬ ይህ የኦሞቲክ ሕዝብ አናኗር ልክ በአፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍርቃ ውስጥ Homeland እንደሚሉት ወይም እዚህ አሜሪካ ቀይ ሕንዶች ብለው የሰየሟቸውን የጥንት ባለርስቶችን Reservetion ብለው በሰየሙት ውስጥ እንደሚያኖሩት ነው! የሞትና እልቂት ፈፋ ላይ ማለት ነው!

አጥኝዎቹ ይህንን የኦሞቲክ ሕዝብ የአፍሪቃ ቀንድ (Horn of Africa) የመጀመሪያው ሕዝብ ይሉታል። ዝሪያዎቻቸው ጥቂትም ቢሆን ታንዛኒያ ውስጥ እንደሚገኙ ጽፈዋል።

ጅማ፣ ሔርማታ ሴነጋል ወስጥ ያለ ደሴት ላይ ያለ አንድ በባርነት እየተፈንገሉ ለተሸጡ አፍርቃውያን የቆመ ሐውልት አስታውሰኝ ። Gore Island! Home of “The Door Of Never Return!” ይላል። ጅማ ከተማ በሙሉ ባይሆንም ሔርማታ ላይ “ተፈንግለው ወጥተው ለቀሩ!” መታሰቢያ ሐውልት ማቆም ተገቢ ይመስለኛል። ቢያንስ ከአንድ ታሪካዊ እድፋችን የሚያነጻን ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እገረመንገዱን ለጅማም የቱሪስት ትኩርት የሚፈጥር ይመስለኛል። የዚህ የሴነጋሉን “የማይመለሱበት በር”ን The Door Of No Return ሐውልት የአለም ቱሪስቲ ይጎበኘዋል። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማም ጎብኘቶታል።

ይህ ሁሉ እኔ ተካፋይነቴ “በጎሳ” ሳይሆን ኦሞቲክ በሚል ነበር ለማለት ነው። ወዳጄ የነበረው ጸጋዬ ገብረመድኅን “ማነው ምንትስ?” በሚለው ግጥሙ ውስጥ ዝም ብንል፤ ብናደባ ዘመን ስንቱን አሸክሞን፤ ተርስተንኮ አይደለም እንድናንቻቻል ብለን ነው…” የሚለው አለው። እውነቱ ታውቆ ለዚህ አይናችን ስረ ቁጭ ብሎ በመውደም ላይ ላለ ሕዝብ “ለመሆኑ ማድረግና መደረግ የሚቻል ምን አለ” ብሎ ለማጠያየቅ አስቤ ነበር ኦሞቲክ ያልኩት።

*****

አምስተኛውን ጥያቄ ልሞክረው። ”ኦነግ የተመሠረተው እርስዎ ቢሮ.. ነው” የሚለውን። የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት) ሀሳቡ የፈለቀው በኔና በእሸቱ አራርሶ ሐይቆችና ቡታ ጅራ አውራጃ፣ ሻሸመኔ፣ ኢሕአፓ ፈጥሮ የነበረውን ብጥብጥ ለማጥናት የአንድ ወደ አስር የሚሆኑ የመንግስት መሥሪያ ቤቶችና የወታደር አለቆች የነበረው ቡድን መሪ ሆኜ በሔድንበት ጊዜ ነበር። ጭብጡ ቀላል ነበር። “በአንድ በኩል መኢሶን በሌላው ኢሕአፓ የያዙት መንገድ የፖለቲካውን መድረክ አበለሻው ብቻ ሳይሆን አማራጭም አሳጣ” በሚል ነው። አማራጭ ፍለጋ! አዲስ አበባ እንደተመለስን ኢጭአት ተመሠረተ።

ያማከርኩት በአብዛኛው ኦሮሞ ለነበሩ ጓደኞቼ ነበር። እሸቱ አራርሶን ሜኢሶን አስከዳው። እኔ ሊቀ መንበር ተስፋዬ ሐቢሶ ዋና ጸሐፊ ሆነን ተመረጥን። በአደባባይ የሚታውቁትን ብጠቅስ፣ አቶ ዘገየ አስፋው፣ ባሮ ቱምሳ፣ ኢብሳ ጉተማ፣ አቢዩ ገለታ የማእከላዊ ወይም የፖለቲካ ቢሮ አባል ሆኑ።

ከዘገዬ አስፋው በስተቀር የቀሩት ኦነግ ሆኑ። ሚስኪን ዘገየንም አሳሰሩት። ዘገዬ፣ ደግነቱና የመሬት ይዞታ ሚንስቴር ነበርና ቢሮውን አምኖ ከፍቶ ማሳየቱ(Accomodating) ለእስራት አበቃው። ሌሎችን ያን ጊዜ ኦነግ ነበሩ ማለት አይቻልም። የዚያኑን ሰሞን እዚያው ሆነው መሠረቱ። መሪያቸው ባሮ ቱምሳ ነበር። አሁን ሌንጮ የሆነው ዮሐንስ ለታም ነበረበት። ባሮ ቱምሳና ዘገየ አስፋው ኢማሌድህ ተብሎ ለተመሠረተው ኢጭአትን ወክለው የሚሳተፉ ነበሩ።ኢማሌድሕ ማለት በወቅቱ ተመሥርቶ የነበር የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌነኒስት ድርጅቶች ሕበረት ማለት ነው። የሚጎድለው ነገር ቢኖር አለመተባብራቸውና ተቆላልፈው አጥፊና ጠፊ መሆናቸው ነበር።

ባሮና የተቀረቱ፣ ያኔም እንደምጠረጠረው፣ በኋላም ማስረጃው እንደሚያሳየው አምስተኛ ረድፎች (Fifth Column) ነበሩ። አምስተኛ ረድፍነታቸው በኢጭአት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በደርግም ውስጥ አምስተኛ ረድፍ ነበሩ። አምስተኛ ረድፍ ምንድነው ለሚለው በስፔይን የርስ በርስ ጦርነት (Spanish Civil War) ጊዜ የተፈጠረ አሁን ከሐዲ፣ የውስጥ ቦርቧሪና ሰርሳሪ የሚገልጽ ገላጭ (Code) ቃል ነውና ማንበቡ ጥሩ ነው።

ባሮ ቱምሳ ሲያቀርባቸው በነበሩት፣ ከኢጭአት ግብ ውጭ በሆኑ አስተያየቶች ምክንያት ኢጭአት ከኢማሌድሕ ታገደ። ከሁሉ በላይ እኔን በግልና ቤተሰቤንም ጭምር ለማጥፋት ኦነግ ወይም ከአንድ አካባቢ የሆኑ የኦነግ አባላት ሌት ተቀን መሥራት ጀመሩ። ለማስረጃ ያክል በኔ አሳሳቢነት የጋሞ ጎፋ ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ የነበረው መኮንን ገላን፣ (ኢጭአት)፣ ከደርግ አባሉ ደምሴ ዴሬሳ ጋር ሆኖ ትንሹ ወንድሜን እሸቱ ጫቦን አደገኛ ጸረ አብዮተኛ ብለው፣ ወአዲስ አበባ አስልከው፣ ወህኒ ወርዶ 7 አመት ታስሮ ተፋታ። እኔ ታስሬ የልጆቼ አሳዳጊ የሆነውን፣ አዛውንት ወላጆቻችንን የሚጦረውን የራሱ ብዛት ያላቸው ልጆች ያለውን ትልቁ ወንድሜን ሻምባል ሐብተገብርኤል ጫቦን “የአሰፋ ወንድም ስለሆነ ነው ያልዘመተው!” ብለው መኮንን ገላንና ደምሴ ዴሬሳ ጦር ሜዳ ላኩት። ሀብቴ ያልዘመተው ከተቀጠረ ጀምሮ የፖሊስ ክበብ ሐላፊና በዚያ ሙያ የተካነና ተፈላጊም ስለነበር ነው እንጅ ከአስፋ ወንድምነት ጋር የሚያገናኘው ነገር አልነበረውም።

ባሮ “የጦር ሜዳ!” ብሎ ሐረርጌ የወረደ ለታ ባለቤቱ ወርቅነሽ ቡልቱ ገና ቢሮ ስገባ “ባሮ ታፍኗል” ብላ ደውላልኝ ይህንኑ ለኮሎኔል ተካ ቱሉ ነገርኩት። ተካ የደርግ የደሕንነት ሹም ነበር። በኋላ በአበሻ ደንብ ሲተሮጎም ተጨምሮ “አስፋ ደርግ ባሮን አፍኖ ወስዶታል!” ብሏል ተባለ።

ኢጭአት የሆነ ኦሮሞ በታሰረ ቁጥር የማስፈታው እኔ ነበርኩ። ቁጥሩን አላውቀውም። አሁን የኦነግ መሪ ነኝ የሚለውን ወይም ያኔ ከወያኔ ጋር መሪ ሆኖ ተፈሪ ባንቲ ቤት የሰፈረው ዮሐንስ በንቲ (የአሁኑ የጦር ሜዳ ስሙን ማስታወስ አልችልም) ከሰባት ይሁን ስምንት ተከታዮቹ ጋር ከክላሽንኮቭ ጠበንጃ ጋር እጅ ከፍንጅ ተይዞ ያስፋታሁት እኔ ነበርኩ። የመጨረሻው መቆራረጥ ከኮለኔል መንግስቱ ጋር የተፈጠረው አብዩ ገለታ፣ የወለጋ አስተዳዳር የነበረው፣ “የደርግ አባሉ ንጉሤ ፋንታ ዶክተር ታደስ ቀንአን አስሯልና አስፋታው!” ብሎን ነው። ኮሎኔል መንግሥስቱ በማያሻማ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ እነደ አለቃ፤እንደመሪ እንደወታደር ሆኖ “አስፋ ብታርፍ ይሻልሀል! ታደስ ቀንአ ኦነገ ነው! አንተን መሳሪያ አድርገዋል!” የሚል ነበር። ይህ ተደማማሮ እኔን ለእስር ዳረገኝ።

አሁን ወደኋላ ተመልሼ ያኔ የነበሩት የኦነግ መሪዎች ሥልጣን ከመፈለግ፣ ሰው ለማጥፋት ከመፈለግና ማሴር ሌላ ለራሳቸውም ለኦሮምም የማይሆኑ፣ የሚፈልጉትንና የሚፈለገውን የማያውቁ አድርጌ ነው የማየው። የሚያሳዝነው እስከ አሁን አንዳቸውም ተጸጽተው ሲናዘዙ አልሰማሁም። ወጥተው እንዲናዘዙ ወይ እኔ የምለውን እንዲያስተባብሎ በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን በኢሳት ቴሌቪዥን ባደርኩት ቃለ ምልልስ ተማጽኜ ነበር። ከፖለቲካ ድርጀት ይልቅ ግራ የተጋቡ ትንንሽ የሰፈር አድመኞች መስለው ይታዩኛል። አሁን ተለውጦ ተለዋውጦ እንደሆነ አላውቅም። ለማወቅም ጉጉት የለኝም! የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቅል እንዲሉ።

ጋሞ ጎፋ ከዚያ በፊት የተማረም ይሁን በመጠኑ የተማረ በማንኛቸውም የመንግሥት ሥራ ያልነበረበት ጠቅላይ ግዛት ነበር። ለአንድ አመት ተኩል ወይም ሩብ እዚያ አካባቢ በነበርኩበት ጊዜ በታቻለ መጠን መምህራን የነበሩና ዩኒቨርስቲ አካባቢ የነበሩ የጋሞ ጎፋ ተወላጆችን ቦታ እንዲያገኙ አደረግኩ። የደርግ መመሪያውም ይኸው ነበርና! እኔ ከዚያ ስለቅ ደምሴ ዴሬሳና መኮንን ገላን በቤተሰባችን ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ የጋሞ ጎፋ ሰው ላይ ምንጠራ ጀመሩ። መኮንን ገላንና ደምሴ ዴረሳ የጋሞ ጎፋ ሰው የሆነ ነቅለው በኦሮሞ ተኩት። ለምሳሌ የአውራጃ አስተዳዳሪ ሁኖ የነበረውን አያሌው ምትኩን፣የነፍጠኛ ልጅ፣ አስነስተው በኦሮሞ፣ የክፍለ አገሩ አስተዳዳሪ ጸሐፊ የነበረውን ሰው ነቅለው በመርጊያ በኦሮሞ ተኩ። ብዙዎቹም ወህኒ ቤት ወረዱ። ከተፈቱም አገር ጥለው ተሰደዱ። የማስታውሰው የኮንሶው ልጅ፣ ገለቦ ሰንጎጎ፣ የጋሞው ወንድሞ ቱንኮላ፣ የኩሎው ልጅ ዘለቀ ጀበሮ እስከዛሬ ስደት ላይ ናቸው። በተዘዋዋሪ መንገድ የመንግስት ሥልጣን መከታ አድርገው የ16ኛውን ምእተ አመት የኦሮሞ ወረራ የጀመሩ የሚያስመስለው ቃና ነበረው። ይበልጥ የሚገርመው መኮንን ገላንን አስተዳዳሪ ያስደረኩት እኔ እንዳልሆንኩና ሌላም የሚመጥን የጋሞ ጎፋ ሰው ስለአልነበረ፣ ያልዘሩት አይታጨድምና፣ ነበር።

አንድ ሌላ የሚያሳዝን አጋጣሚ ተፈጠረ። የተፈጥሮ ቧልታ ወይም ፈተና ሊመስልም ይችላል። “ኢትአግብአነውስተ መንሱት!” እንዲሉ። እኔ ግን ፈተናውን ያለፍኩ ይመስለኛል። ማእከላዊ ታስረው የነበሩ ብዙዎች ኦነግ የነበሩ ሲፈቱ መኮንን ገላን ሳይፈታ ቀረ። የቀረበት ምክንያት ማእከላዊ ባሳየው መጥፎ ምግባርና እስረኛውን ሲያጋጨው ስለነበር ነበር። በተፈታሁ ማግስት ይሁን ሰልስት እስረኛ ለመጠየቅ ማእከላዊ ስሔድ ከሌሎች ጠያቂዎች መካካል አንድ ሴት ልጅ ጋር የቆመችና የምታለቅስ ሴት አየሁ። “ምን አስለቀሰሽ?” ብል ባሌ ሳይፈታት ቀረ አለች። “ባልሽ ማነው?” “መኮንን ገላን” ብላ “አሰፋ አንተንኮ አውቃለህ” አለችኝ። በነጋታው የማእከላዊ ሹሙ ኮሎኔል አርጋው እሼቴ ቢሮ ሔድኩኝ። ጓደኛዬ ነበር። የመጣሁበት ምክንያት ስነግረው ገረመው። ”ብለህ ብለህ መጥፎ ምግባርና እስረኛውን እርስበርሱ ሲያጋጭ ለነበረ ሰው አማላጅነት አማላጅነት ትመጣ ጀመር? እዚህ ይሰራ የነበረውን አታውቅምና ነው?”ሲለኝ የሚስቱንና የልጅቷን ለቅሶ ነግሬው “እስቲ ለአለቃዬ እነግራለሁ” ብሎ ነበርና መኮንን ገላን በማግስቱ ተፈታ። የሚስቱ ስም የሽእመቤት መሰለኝ። ጥያቄው ከተነሳ አይቀር ብዬ ብዙ ዝርዝር ውስጥ የገባሁ መሰለኝ።

****

ስለኦነግ ከተነሳ አይቀር አንዳንድ በግል የማውቀውንና፣ ተመዝግቦ በአደባባይ የሚታየውን እንደግርጌ ማስታወሻ ብጨምር ሙሉ ስእሉን ለማየት የሚጠቅም መሰለኝ።

ኦነግ የተጸነሰውም ሆነ አሁን ድረስ ያለ የሚመስለው ጅምሩ በአንድ አካካባቢ የኦሮሞ ተወላጆች ነበር። ይህ አካባቢ ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ስለሚገኙት ሌሉች ኦሮሞዎችም ሆነ ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት ነገር ቢኖር ከመጤፍ የማይቆጠር ነው። በብዙ ምክንያቶች!

አንደኛ፣ ይህ አካባቢ ሌላውን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ወደገባርነት ያሽጋገርውን፤ በየካቲት 25, 1967 በመሬት ለአራሹ አዋጅ የተገረሰሰውን፤ የምንሊክ ውርስ የነበረውን ገባርነት አያውቅም። ማለትም፣ ነፍጠኛ የሚባል አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ቃሉንም በቅጡ አይውቁም። ይህንን መሥራች ከነበሩት አቢዮ ገለታና ሌንጮ ለታ ጋር ባደርኩት ውይይት “ነፍጠኛ ማለት ምን ማለት?” ብለው እንደጠየቁኝ “በትዝታ ፈለግ” መጽሐፌ ውስጥ አንስቻለሁ።

ሁለተኛም፣ ከምንሊክ ጀምሮ ልጅ እያሱን ጨምሮ አስከ ኃይለሥላሴ ድረስ ከቤተመንግስቱ ጋር አምቻና ጋብቻ መሆን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛውን ደረጃ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የበቁ ናቸው። የአሁኑ የኃይለሥላሴ አልጋ ወራሽና “የዘውዱ ተስፈኛ” ከዚሁ አካባቢ ነው።

በደርግ ዘመን ከፍተኛውን የመንግስት ስልጣን የያዙ ከዚሁ አካባቢ የወጡ ነበሩ። ላለፈው 120 ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በመንግስት ቁልፍ ቦታ በመያዝ የኢትዮጵያን መንግስት ያሽከረከረ ብቸኛ አካባቢ ቢኖር ብቸኛው ይህ አካባቢ ነበር። የቀረው ኦሮሞ ገባርና “የበይ ተመልካች” ነበር።መነሻ ምክንያት ነበረው/አለው። ለመጀመሪያ ምንሊክን “ወርቁን እዚያው እንጦጦ ድረስ እናመጣሎታለንና እዚህ ድረስ አይልፉ!” በሚል ከገባርነት ዳኑ። ሁለተኛው የመጀመሪያው የፕሮቴስታንት እመነት መሠረት እዚያው ጣለ/ሆነ። ለዚህ አንድ ስውዲናዊ የጻፈውን Evangelical pioneers in Ethiopia: Origins of the Evangelical church Mekane Yesus 1978 by Gustav Arén የሚል መጽሐፍ ማንበቡ ገለጫ ይሆናል።

ኤርትራ ውስጥ በተፈጠረው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የውስጥ ሹኩቻ የተባረሩና የፈረንጅም እጅ የነካካቸው ተሰደው ለማረፊያ የተሰጣቸው ያ አካባቢ ነበር። መካነ የሱስ ቤተክርስቲያን የዚያ ውጤት ነው። በዚህ ምክንያት፣ አንደኛም ከላይ ተጽእኖ የሚያደርግ የበላይ ነፍጠኛ ባለመኖሩ በትምህርት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደርጃ የተስፋፋበት አካባቢ ሆነ። ከፍተኛ ባለስልጣናትን ለማፍራትም ምንጩ ይኸው ነው። ገዥው የሚባለው አማራ እንዲህ ሥራ ፍለጋ የመጣው ካልሆነ የለበትም። አማርኛም አይነገርበትም። ኦሮምኛ ካልተናገሩ (Lingua Franca) በስተቀር በዘመን ደርግ እንኳን በየሆቴሉ ምግብም ለማዘዝና መኝታ ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ይህንን ብዙዎች የጻፉበትም ቢሆንም እኔ በግሌም የደረሰብኝ ነው።

ተሰሚነት፣ ተጽእኖ፣ ስፋትና ጥልቀት ያለው አካል በኢትዮጵያ ቢኖር የመካነ የሱስ ቤተ ክርስቲያን ነው። በመላው ደቡብና ምእራብ ኢትዮጵያ ይህ ኃይሉ በአደባባይ ይታያል። ዩኒቨርስቲ እያለህ አምስት ኪሎ መካነ የሱስ ህንጻ ለሁለት አመት አመት ያክል ኖሪያለሁ። ከዘበኛው ጀምሮ የመነጋጋሪያው ቋንቋ ኦርምኛ ነበር። አለቃው ወዳጄ የነበሩት ቄስ ጉዲና ቱምሳ ነበሩ። ባሮ የቄስ ጉዲና ቱምሳ ወንድም ነበር።

አንዴ፣ በ1970 በጋ ይመስለኛል በባሮ ቱምሳ ቮክስዋገን መኪና ጉለሌ ዮሐንስ ለታ ቤት አመሸን።በኔ አነሳሽነት ነበር ውይይቱ የተጀመረው። ይህንን በኦሮሞ ሥም የሚያደርጉትን እርግጠኛ ባልሆንም እጠረጥር ስለነበር የሚያስቡት “አንደኛ ታሪካዊ መሠረት እንደሌለው፣ ሁለተኛም ቢኖርም እነሱ በኦሮሞ ሕዝብ ሥም ለመናገር መሰረታዊ ታሪካዊ ብቃት እንደሌላቸው” ለመግለጽ ነበር። በክስና ውቅስ መንገድ ሳይሆን ወዳጅ ወዳጁን እንደሚመክረው ማለት ነው። አልሰሙኝም! ማስረጃው ከዚያ ቀን ጥቂት ቆይቶ ዮሐንስ ለታ ሌንጮ ተሰኝቶ ሸፈተ። ቆየት ሲል ደግሞ ባሮ ቱምሳ ተከተለ።

ይህ ከላይ የገልጽኩት ማለትም የምንሊክ ተጽእኖ አለመኖር፣ ትምህርት፣ ከነገሥታቱ ጋር መጋባት እና የፕሮተስታንት እምነት ተደማምሮ ከሌላው የማግለልና ራስን የማግለል/ የመገለል (Insulated)፣ በውስጠ ታውቂነት እበለጣለሁ የማለት ስሜት (Supriority Syndrom) የፈጠረ ይመስለኛል።

ከእስር እንደተፈታሁ በአምስት ኪሎ በኩል ሳልፍ መካነ የሱስ ህንጻ ገባሁ።ኖሬበታለሁና የማውቀው ሰው ባገኝ ብዬ ነበር። ቤቱ ጭር ያለና የተወረረ መሰለኝ። በወቅቱ አለቃ ወደነበረው ወደ ቄስ ፍራንሲስ እስጢፋኖስ ቢሮ ገባሁና ተዋወቅን። “ምነው ቤቱ የተወረረ መሰለ?” አልኩት ሳቀና “የለም! ሥራውን ሁሉ ለየአካባቢውና ለአካባቢው ቤተክርስቲያን አከፋፈልኩ” አለኝ። “ነጻ አውጭ ሆንክ እንዴ!?” ስለው “እሱን እንኳን አላውቅም!” ብሎ የነበረውን የሚያሳዝን ታሪክ ተወያየን። ቄስ ፍራንሲስ የቡርጂ ልጅ መሰለኝ። አሁን አሜሪካን ነው ያለው ብለውኝ ፈልጌ አጣሁት። ቡርጂ ማለት እንደሲዳማና ጌዴኦ በኦሮሞ የተከበብች ደሴት ነች።

ይህ የኋላ ታሪክ ፈረንጅ background History የሚለው የተነሱትንና የሚነሱትን ነጥቦች የበለጠ ለመረዳት ትንሽ ብርሐን ይፈነጥቃል በሚል ነው።ኦነግ መሥራቾች ኦሮሞ ከመሆናቸው ሌላ/በስተቀር (ያንንም የሚያስጠይቅ አንዳንድ ነጥብ አይጠፋም) ስለኦሮሞ ሕዝብ ሕመም፣ ቁስል የስሚ-ሰሚ ካልሆነ በስተቀረ እምብዛም ናቸው ለማለት ነው። ሥልጣንን ግን ጥቁሙንና ጣእሙን ማወቃቸውና የበለጠ ሥልጣን ፈላጊ መሆናቸው ብዙ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

****

አሁን ወደይገረም አለሙ ሰባተኛው ጥያቄ ልግባ። ”በዛ ጉባዔ ተቃውሞ ያሰሙና ድምጸ ታአቅቦ ያደርጉት ፕ/ር አሥራት ወልደየስ ብቻ እንደነበሩ ይታውቅል” ይላል።

ዓሥራት ብቸኛ ተቃውሞ እንዳደርጉ አይታወቅም! እኔ እዚያው ነበርኩና ተቃውሞ በማድርግ ብቸኛው መሆናቸውን አላውቅም! አልለሰማሁም! አላየሁም!

መቃወም ብቻ ሳይሆን እንዳለ ወያኔ ቻርተር ብሎ ያመጣውን ብጣሽ ወረቀት እንዲወድቅ በማድርግ በሌላ አዲስ ሰነድ እንዲተካ ያደርግንም እዚያ ውስጥ ነበርን። እኔ በምንም ለምንም ድምጽ አለመስጠት ብቻ ሳይሆን ድምጽ እንዲሰጥበት የመጣውን ቻርተር ይሉት የነበረውን ወረቀት ከሽፎ በሌላ እኔ ባመጣሁት ሐሳብ እንዲተካ አድርጊያለሁ።

ይህ እኔ የምለው እውነት ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ በድምጽም በቪዲዮም የተመዘገበ፤ በተሌቪዥን ይተላላፍ የነበር፤ ተሌቪዥን የነበረው የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ የተከታተለው፤ ከዓለም የተሰባሰቡ ጋዜጤኞች የመዘገቡትና ያስተላለፉት ነው። ይህ የተሰነዘረው አስተያየት ከዚህ ከታወቀው፤ ከተመዘገበው፤ ከተረጋገጠው ጋር የማይሔድ ነው። ይህንን የመስለ ተረት አዘል ነገር ስለፕሮፌሰር አስራት ላለፈው 20 ምናምን አመታት ሳነብ ነበር። ለዚህ ያልነበር ታሪክ ፈጠራ ምክንያት የሚመስለኝን ትንሽ ቆየት ብዬ ለማሳየት እሞክራለህ። በዚህም ላይ የዛሬ 20 አመት ገደማ ስለፕሮፌሰር አስራትና ስለመላው አማራ ድርጅታቸው ጽፌ ራዕይ በሚባል ጀርመን ይታተም በነበር መጽሔት ላይ ወጥቶ ስለነበር አሁን የለኝምና ፈልጌ አንድ ቀን በድሕረገጻት ላይ መለጠፌ አይቀርም።

እዚህ ጥያቄው ላይ ሁለት ቁልፍ ቃላት አሉ።”ተቃውሞ ያሰሙና ድምጸ ተአቅቦ ያደርጉት” ይላል። ታቃውሞ ስለምን እንዳደርጉ ስለአልተገለጸ እዚያ ውስጥ አልገባበትም። በኤርትራ ጉዳይ ላይ ተአቅቦ አድርገዋል። ለመሆኑ ተአቅቦ ማለት ምን ማለት ነው? የታወቀውና ተቀባይነት ያለው (official) ትርጉሙ ይኸውና።

An abstention may be used to indicate the voting individual’s ambivalence about the measure, or mild disapproval that does not rise to the level of active opposition. Abstention can also be used when someone has a certain position about an issue, but since the popular sentiment supports the opposite, it might not be politically expedient to vote according to his or her conscience. A person may also abstain when they do not feel adequately informed about the issue at hand, or has not participated in relevant discussion.

ፕሮፌሰር አስራት ታአቅቦ ያደረጉት በዚህ ትርጉም ውስጥ A person may also abstain when they do not feel adequately informed about the issue at hand, or has not participated in relevant discussion በሚለው መሠረት ነው። ያሉትን ቃል በቃል የማስታውሰውን ያክልላና ራሴን ተጠራጥሬ ሌላ እዚያው ስብሰባ ላይ የነበር ሰው ጠይቄ እንዳረጋገጥኩትም አስራት ያሉት “የላከኝ የከፍተኛ ትተምህርት ተቋም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ድምጽ እንድሰጥ መመሪያ ስለአልሰጠኝ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጽ ለመስጠት አልችልም” ነበር።

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በዚህ ስብሰባ መዝጊያ ላይ አስተያየት ሰጥተው ነበር። አስተያየታቸውም “እስከዛሬ በብዙ አለም አቀፍም ሆነ የአገር ውስጥ ስብሰባዎች ተካፋይ ሆኜ አውቃለሁ። እንደ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አይነት ሊቀ መንበር እስከዛሬ አላየሁም። ብቁና የተዋጣላቸው ሊቀ መንበር ስለሆኑ ተከፋዮች ተነስተን ይህንን በጭብጨባ እንገልጥ” የሚልነበር። ከዚያ ተስፋዬ ሐቢሶ ተነስቶ መናገራያውን ማይክራፎን ከፊቱ ዘንጥሎ ለማውጣትና በቁጣ ወደዚያ ለመሔድ እየዳዳው “እስከዛሬ ይህ ሁሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሲያልቅ ድምጽህን ሰምተን የማናውቅ ሰውዬ ዛሬ ደጎሞ አጨብጭቡ ትለናለህ!” ብሎ የሚናገረውን ሳይጨርስ ተሰብሳቢዎቹ አዳራሹን ለቀን ወጣን። ይህ የአስራት የመጨረሻ ንግግርና አስተያየት ተነስቶም ተጠቅሶም አያውቅም። እዚያ ደግሞ ተመዝግቦ የተቀመጠና ለዘለዓለም የሚኖር ነው።

ከዚህ ስብሰባ አንድ ሌላ ትዝ የሚለኝ፤ስብሰባው በተጀመረ በ15ኛው ደቂቃ ወይም እንዲያ “ገለልተኛ ሊቀ መንበር ካልተመረጠ አንተ ይህንን ሁሉ ሥልጣንና ተከታይ ይዘህ ሊቅ መንበር ሆነህ በገለልተኝነት መምራት አትችልም!” አልኩኝ መለስ ዜናዊ አበደ! ትርፍ ቃላትም ተለዋወጥን! ይህንን ሐሳቤን የደገፈ አንድ ሰው ብቻ ነበር። እሱም አቶ መሸሻ ብሩ ነበር። ከዚያ መለስ ዜናዊ በንዴት ለአንድ ሰዓት ይመስለኛል እረፍት ሰጠ። ከእረፍት መልስ፣ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆነው፣ ታምራት ላይኔ፣ ሁለት ገጽ የሚሆን ዘለፋ ጽፎ መጥቶ ዘለፈኝ። ፍሬ ነገር አልነበረውምና አላስታውሰውም! “በደንብ ሳትደራጁ መጥታችህ ደሙን አፍስሶ የተዳረጀውን ኢሕአደግን ማፍረስ ትፈልጋላችሁ!’ የሚል እንደነበረበት አስታውሳለሁ። ኢሕአደግ ዛሬ፣ እኔ እንኳን ባልሆን፣ የዘረፋ ነቀዝ ውስጡን ቦርቡሮ ጨርሶ ኮፈኑ ብቻ ያለ ይመስለኛል።

ፕሮፌሰር አስራት በዚያው ሰሞንም ቢሆንም ወዳጄና የቅርብ አማካሪያቸውም አይነት የነበርኩ ይመስለኛል።ከዩኒቨርስቲ ተውክለው የመጡት እሳቸውና ዶክተር መኮንን ቢሻው ነበር። መኮንን ቢሻው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማሕበር ሊቀ መንበር ከመሆኑም ሌላ የማሕበራዊ ሳይንስ (Social Science) ፕሮፌሰር ነበር። አንድ መቀመጫ ብቻ ሲመደብላቸው መኮንን ተመልካች ሆነና አስራት ተሳታፊ ሆኑ።ምጸቱ የጀመረው እዚያ ላይ ይመስለኛል። ፖለቲካ የሚያውቀው ተመልካች ሆኖ ፖለቲካ የማያውቀው ተሳታፊ መሆኑ ላይ።

የዚያን ሰሞን ተሳታፊዎች ሁሉ አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ታጉረን ስለነበር ፕሮፌሰር አስራት በየማታው”አስፋ እነዚህ ልጆች ምን አድርግ ነው የሚሉኝ? ይስድቡኛል ያዋርዱኛል!” ይላሉ። በተቻለ መጠን አስረዳለሁ፣ “መቶ ሃምሳ ያክል ሰው በየቀኑ እኔን እየሰደብኝ ችያለሁና መቻል ነው” እላለሁ። ሳስበው ነገር አለሙና የሚደረገውም ሆነ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በቅጡ የተረዱት አይመስለኝም።

“መላው አማራ” የሚል ድርጅት ሊያቋቁም ላይ ታች ሲሉ አገኘኋቸው። በአገር አቀፍ፣ ማለትም በኢትዮጵያ ደርጃ የተደራጁትን ጨምሮ እሱን ትታችህ መላው አማራ ውስጥ ግቡ ማለት ጀመሩ። አንድ ቀን በጥሞና መከርኳቸው። “አንደኛ ይህን ያደርጉ እንደሆነ ለወያኔ እጅ ሰጡ ማለት ነው። ይኸውና አማራ ተደራጅቶብህ መጣብህ! ለማለት ያገለግለዋል። ሌላው ደግሞ እውነትም ሆነ አልሆነ ያለፉት መንግስታት የአማራ መንግስታትና ነገስታት ስለሚባሉ ዘውዱን ሊመልስብን ለሚል መሳሪያ ሊሆን ይችላልና…” የመሳስለውን ነበር። አልሆነምና መላው አማራ የሚል ድርጀት መሰረቱ።

ላሳጥረውና፣ ብዙ ሌላ የማውቀው ስለሌለ ነው ላስጥረው ያልኩት፣ በ1984 አሜሪካ መጡና የሞራል ግዴታ ስለመስለኝ ለመካፍልም እሳቸውንም ሰላምታ ለመስጠት ስብሰባው አዳራሽ፣ ዋሺንግተን ዲሲ ሔድኩ። አዳራሹ ከጢም እስከገደፉ ሞልቷል። አብዛኛው የወያኔ ተቃዋሚ ነኝ ይል የነበርና ትላንትና ኮምኒስት ነኝ የሚል አሁን ደግሞ እዚሁ ኢድሐቅ ተብሎ የተሰየመው ድርጀት አባላትና ተባባሪዎች ነበሩ። ለብሔረሰብ ድርጀት እንዲህ ግልብጥ ብለው መምጣታቸው ገረመኝ። ከዚያ አስራት መጡና ገና ከመግቢያው ጀምሮ የማይቋርጥ፣የሚያደነቁር ጭብጨባ አዳራሹን ሞለው። አስራታ ገቡ። ካባ ለብሰው ነበር የመጡት። ደነገጥኩ! ካባ የምን ምልክት ነው። የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ካባ ለብሰው ምን መልእከት እያስተላለፉ ነው? የቤተ መንግስት፣ ማለትም የንግሥናና የቤተክህነቱ አጣምሮ ነው? ካባ የነዚህ አርማ ነውና።

ከዚያ አስራት በተነፈሱ ቁጥር አደንቋሪ ጭብጨባ ስለቀጠለ አንድ ከጎኔ ተቀምጠው የነበሩ የፍርድ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴር የነበሩ የሕግ ባለሙያ “በል አስፋ አንተ ክቻልክ ቀጥልብት እኔ እንዲህ አይነቱን አልችልም!” ብለው ወጡ። እኔ ጨርሼ ወጣሁ። ፕሮፌሰር አስራትን ላገኛቸው አልፈልኩም። የምንነጋገረው ነገር የለማ!

ከዚያ ይኸው ያቀጣጠሉት ችቦ በርቶ ዛሬ አማራ የሚባል ድርጀት ይፈለፈላል። አንደኛው ሌላውን “እኔ የበለጠ፣ የጠራሁ አማራ ነኝ!“ ይላል። በዚህ ሰሞን ”ከአማራ የሐኪሞች ማሕበር የተሰጠ መግለጫ!” የሚልም አየሁ። ዘውድና ንጉስ እንድሚያስፈልግ የሚናገር በአማራ ስም የተጻፈ ምን የሚያክል መጽሕም ገበያ ላይ ውሏል። ምኑ ቅጡ!

ብቻ ለኢትዮጵያዊነት ሁለተኛን ቦታ ያሰጡት ይመስለኛል!

Filed in: Amharic